ሚያዝያ 12 ቀን የ2006 ዓ.ም በዓለ ትንሣኤ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤
እርሱ ሕያው ሆኖ ሕያዋን መሆናችንን በትንሣኤው ላበሠረን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!! ‹‹ወርኢናሃ ለሕይወት፤ ወተዐውቀት ለነ — ሕይወትን አየናት፣ አወቅናትም›› (1ዮሐ. 1÷2)
የሕይወት መገኛና ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፣ ከእግዚአብሔር የተገኘው ሕይወት የሰው ልጅ የዕውቀት ብርሃን ነው፤ አምላካዊ ሕይወት ካለው ሰው የሚፈልቅ ብርሃናዊ ዕውቀት ጽልመታዊውን ዓለም በብሩህነቱ ያሸንፋል እንጂ በጽልመታዊ ዓለም አይሸነፍም፡፡ (ዮሐ.1÷4-5) የሰው ልጅ ሕያው አምላክ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጡር በመሆኑ ሕያውና ክቡር፣ ዘለዓለማዊና ብርሃናዊ፣ የማሰብ፣ የማመዛዘን፣ የመምረጥና፣ የመወሰን ነፃነት ያለውና ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የላቀ አእምሮ ያለው ልዑል ፍጡር ነው፤ ሰው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ነፃነትና አእምሮ መሠረት ነፃነቱን ተጠቅሞ የመረጠውን የማድረግ ነፃነት ያለው ፍጡር ቢሆንም በነፃ ዕውቀቱና ምርጫው ለሚፈጽመው ሁሉ እርሱ ራሱ ኀላፊነቱን ይወስዳል፤ ይህም ማለት በምርጫው መሠረት የሚሠራው ሥራ ሁሉ በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ሆኖ ከተገኘ ምስጋናን፣ መልካም ሆኖ ካልተገኘ ግን ተጠያቂነትንና ፍርድን ያስከትልበታል ማለት ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የመጀመሪያ ሰው የሆነው አዳም ማድረግ ያለበትንና ማድረግ የሌለበትን ተለይቶ ከእግዚአብሒር ቢነገረውም የተነገረውን ሕግ ወደጎን ገሸሽ በማድረግ የራሱን ነፃ ምርጫ ተጠቅሞ ‹‹አትብላ›› የተባለውን በላ፤ በመሆኑም ይህ ድርጊት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ታላቅ ስሕተትና ድፍረት ነበረና ተጠያቂነትን አስከተለ፣ በመጨረሻም ሕይወትን የሚያሳጣ የሞት ፍርድንና ቅጣትን በራሱና በልጆቹ ሁሉ ላይ አመጣ፡፡ ፍርዱ ሥራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ ሰው ሕይወቱን አጣ ማለትም ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ፤ ሞትና ሲኦልም ሰውን ከእግዚአብሔር ለይተውና የራሳቸው ተገዥ አድርገው እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በቊጥጥራቸው ሥር አዋሉት፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር በባሕርዩ መሓሪና ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን ለፈራጅነቱና ለመሓሪነቱ የሚስማማ መንገድ አመቻችቶ መሓሪነቱንና ፈራጅነቱን በፈጸመበት በክርስቶስ ሞት ቤዛነት የሰው ልጅን ታረቀው፤ ያጣውንም ሕይወት መለሰለት፤ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነትም እንደገና ሕይወቱን እንዲያገኝ አደረገ (ዮሐ. 6÷56-58፤ ማር 16÷16)
ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር‹‹በመጀመሪያው ሰው (አዳም) ሞት መጣ፣ በሁለተኛው ሰው (ክርስቶስ) ግን ትንሣኤ ሙታን ሆነ፤ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ እንደዚሁ ሁሉም በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ›› ብሏል፤ (1ቆሮ. 15÷21-22፤ሮሜ 5፥12-19) ከዚህ የምንረዳው ዐቢይ ቁም ነገር በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ያጣናት ሕይወት፣ በክርስቶስ መታዘዝ ያገኘናት መሆናችንን ነው፤ ጌታችንም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም፣ የሚያምንብኝም፣ ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤እኔም በመጨረሻዪቱ ቀን አስነሣዋለሁ›› ብሎ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን እንደነገረን የሰው ልጅን ለዘለዓለማዊ ሕይወት እንደገና አበቃው (ዮሐ. 6÷54፤ 11÷25-26)። የዚህም እውነታ በትንሣኤው አበሠረን፣ የእርሱ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ዋዜማ ነውና የቀደመችው ሕይወት እንደተመለሰችልን በትንሣኤው አየናት፤ ዐወቅናትም። (ኤፌ. 4÷5-7)
የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የዘለዓለማዊ ሕይወት ማረጋገጫ ነው፤ለበርካታ ዘመናት በተስፋ ይጠበቅ የነበረው የክርስቶስ ነገረ አድኅኖ እና ነገረ ትንሣኤ በጊዜው ጊዜ እውን እንደሆነ ሁሉ፣ እንደዚያው በተስፋና በእምነት እየተጠባበቅነው ያለ የሰው ልጅ ሕይወታዊ ትንሣኤ ጊዜው ሲደርስ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውን ይሆናል (1ቆሮ 15÷20-23፤ 1ተሰ. 4÷13-18)። ይሁን እንጂ ዛሬም ሕይወትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ያለን ስለሆን የሕይወትን ጣዕም አሁንም ማጣጣም እንችላለን፤ ሕይወት ጣዕም የሚኖረው በፍቅር ሲታጀብ ነው፣ ፍጹም ፍቅር የዘለዓለማዊ ሕይወት ኀይል ነው፤ ፍቅር ፍጹም የሚሆነው ሦስቱን አቅጣጫዎች ማእከል አድርጎ ሲገኝ ነው፤ ይኸውም ወደ ላይ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር መከተል ስንችል፣ ወደጎን በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን የሰው ልጅ በአጠቃላይ መውደድ ስንችል፣ ወደ ታች ደግሞ የምንኖርባትን ምድርና በውስጧ ያሉ ፍጥረታትን ስንንከባከብ ነው፣ ይህን ካደረግን ፍጹም ፍቅር ከእኛ አለ ማለት እንችላለን፤ እግዚአብሔር ይህንን ዐይነት ፍቅር እንዲኖረን በሃይማኖት አስተምሮናል፡፡
በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ በመዋዕለ ጾሙ በአምልኮ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋትና በስግደት ስንገልጽ እንደቆየን ሁሉ፣ በፋሲካው በዓላችን እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት ከተቸገሩ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋር በመካፈል ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅር ልንገልጽ ይገባናል፤ በዚህ ዕለት በዓሉን ስናከብር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የአካልና የአእምሮ ጒዳት ደርሶባቸው የበይ ተመልካች የሆኑ ወገኖች ሁሉ ከእኛ ጋር በማዕዳችን ተሳታፊ ሆነው በዓሉን በደስታና በምስጋና እንዲያከብሩ ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡
የትንሣኤ መሠረታዊ ትርጒም ከሞት በኋላ በሕይወት መኖርና መመላለስ ነው፤ ስለሆነም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ባለፉት ዘመናት በድህነትና በኋላ ቀርነት ከሞት አፋፍ ደርሳ የነበረችውን ሀገራችን በልማትና በእድገት ትንሣኤዋን ለማረጋገጥ ቃል በመግባት በዓሉን ማክበር ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ አለብን፤ ምክንያቱም ጠንክረን በመሥራት ምድራችንን እንድናለማና እንድንከባከብ ከሁሉ በፊት ያዘዘ እግዚአብሔር ነውና፤ በተለይም የልማታችን የጀርባ አጥንት ሆኖ እንደ ሚያገለግል ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተያዘው ፍጥነት ሥራው ተሠርቶና ተጠናቅቆ የእድገታችን ተሸካሚ ምሶሶ ሆኖ ማየት እንድንችል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።
የሀገራችን የልማትና የእድገት መርሐ ግብሮች ዘርፈ ብዙ እንደመሆናቸው መጠን ገበሬው በየአካባቢው እያከናወነው የሚገኝ አፈርን የመገደብና አካባቢን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ ያለመቋረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ ቤተ ክርስቲያችን በግንባር ቀደም ተሰልፋ እንደምትሠራ በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያሉም ሆኑ ወደፊት ሊሠሩ በእቅድ የተያዙ የሀገራችን የልማትና የእድገት ሥራዎች በሕዝቡ የተባበረ ድጋፍ ሲከናወኑ የሀገራችን ብልጽግና እውን እንደሚሆን የሁላችንም እምነት ነው፡፡
ስለሆነም ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያውን ሁሉ ጽናት፣ አንድነት፣ ስምምነትና ፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ መኖር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፤ ልማታችን በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰውና የተከበረው ባህላችንና ሰብኣዊ ሥነ ምግባራችንን ጠብቆ በማስጠበቅ ጭምርም መሆን ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሀገረ እግዚአብሔር ነች ተብሎ በተደጋጋሚ የተነገረላት ያለምክንያት አልነበረም ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በማናቸውም ጊዜ ከነውረ ኀጢአትና ከርኵሰት ሁሉ ርቀው፣ ሕገ ተፈጥሮንና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው፣ እግዚአሔር የሚለውን ብቻ አዳምጠውና አክብረው የሚኖሩ ቅዱሳን በመሆናቸው እንጂ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ሊፈጸም ቀርቶ ሊወራ የማይገባውን ሰዶምንና ገሞራን በእሳት ያጋየ ግብረ ኀጢአት በኢትዮጵያ ምድር መሰማቱ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን የሰጠውን የቅድስና ክብር የሚያሳጣ ከመሆኑም ሌላ በሀገራችን ላይ ልማትና እድገት ሳይሆን መቅሠፍትና ውድቀት እንዳያስከትልብን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን የሰዶም ግብረ ኀጢአት በጽናት መመከት አለበት፤ ተፈጥሮን ለማልማት እየተረባረብን እንደሆነ ሁሉ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የሰዶም ግብረ ኀጢአትን በመከላከል በቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር እጅግ የበለጸገና የለማ ትውልድ ማፍራት የልማታችን አካል ማድረግ አለብን፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ግብረ ኀጢአት እስከ መጨረሻው ድረስ አምርራ የምትዋጋው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤ ስለሆነም ሕዝባችን ለሰላምና ለአንድነት፣ ለእኩልነትና ለልማት፣ ለቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር ቅድሚያ ሰጥቶ በሁሉም አቅጣጫ ልማቱን እንዲያፋጥን፣ ሃይማኖቱንም እንዲጠብቅ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፤ አሜን።