• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ

፩. ሃይማኖተ ኦሪት

በአንድ እግዚአብሔር ማመን ሃይማኖተ ኦሪት ወይም ሃይማኖተ አይሁድ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ነገ ደካም፣ ነገደ ሴም፣ ነገደ እስራኤል[1] የተባሉ ሕዝቦች ከሰፈሩባት ጊዜ ጀምሮ ሃይማኖተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማመን) የታወቀባት ሀገር መሆንዋን ብዙዎች የታሪክ ምንጮች ያስረዳሉ[2] እነዚህ ነገዶች የመምለኬ እግዚአብሔር የኖህ ልጆች ናቸው፡፡ ከአባታቸው የወረሱትን ሃይማኖተ እግዚአብሔር ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡  በተለይም ክብረ ነገሥት የተባለውን ታሪክ መጽሐፍ መሠረት አድርገው የተጻፉ ታሪክ መዛግብት ቀጥተኛ ጊዜውን በመግለጽ በአንድ እግዚአብሔር ማመን በኢትዮጵያ የተጀመረው በአንድ ሺሕ ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ መጀመሪያ በንግሥተ ሳባ እና በልጅዋ በቀዳማዊ ንጉሥ ምኒልክ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡[3] መጽሐፍ ቅዱስ ንግሥተ ሳባ ንጉሥ ሰሎሞንን ለመጐብኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ እንደ ነበረች ያስረዳል፡፡[4] ክብረ ነገሥት የተባለው የታሪክ መጽሐፍ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አጕልቶ በመግለጽ ንግሥተ ሳባ ከንጉሥ ሰሎሞንን ፀንሳ ወደ ኢትዮጵያ መመለስዋን፣ በኋላም ልጅዋ ምንልክ ተወልዶ ለአካለ መጠን ሲደርሥ ወደ ኢየሩሳሌም  በመሄድ ከአባቱ ጋር ተገናኝቶ በሚመለስበት ጊዜ በአባቱ መልካም ፍቃድ ከሕዝበ እስራኤል የተወጣጡ የበኲር ልጆች የሰዶቅ ልጅ አዛሪያስን፣ ሌዋውያን መምህራነ ኦሪትን፣ ካህናትንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ እንደተመለሰና በአክሱም እንደተቀመጠ ዘርዝሮ ያስረዳል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖተ ኦሪትን (ሃይማኖተ አይሁድን) አምኖ ካህናተ ኦሪት፣ ሌዋውያን በአክሱም ታቦተ ጽዮንን ያገለግሉ፣ ሕገ ኦሪትን ያስተምሩ ነበር[5] ይህ ይታወቅ ዘንድ ከሕገ ኦሪት፣ ሥርዐተ አይሁድ፣ ባህለ አይሁድና ልማደ አይሁድ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሠርጸው ይገኛሉ፡፡[6] ይህ ሃይማኖተ ኦሪት፣ ሥርዐተ አይሁድና አይሁዳዊ ባህል ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብና ሕዝበ እስራኤል የረዥም ታሪክ ትስስር እንዲኖራቸው አድርጎአቸዋል፡፡ ከዚህም ጋር የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት ሃይማኖተ ኦሪትን (ሃይማኖተ አይሁድን) አምኖ መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅድመ ሃይማኖተ ክርስትና በሃይማኖተ ኦሪት (ሃይማኖተ አይሁድ) ለረዥም ዘመናት መኖሩን በሁለት ዐበይት የታሪክ ነጥቦች መረጋገጥ ይቻላል፡፡

 

  1. ከዚህ በላይ የተገለጹት ሕገ ኦሪት፣ ሥርዐተ አይሁድና ባህለ አይሁድ በኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና (አኗኗር) ሠርጸው መገኘታቸው ነው፡፡
  2. ኅጽዋ ለንግሥት ሕንደኬ (የንግሥት ሕንደኬ ጃንደረባ) ለአምልኮተ እግዚአብሔር (ለእግዚአብሔር ለመስገድ ) ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱና ከብሉይ ኪዳን ክፍል መጽሐፈ ኢሳይያስን ሲያነብብ መገኘቱ ነው ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሕዝቦች ቀድሞ በሃይማኖተ እግዚአብሔር የተመሠረተ ስለነበረ ሃይማኖተ ክርስትናን ለመቀበል ያዳገተው አንድም ነገር አልነበረም፡፡

፪. ሃይማኖተ ክርስትና በኢትዮጵያ

፪.፩. ኅጽዋ ለሕንደኬ

በኢትዮጵያ የሃይማኖተ ክርስትና ታሪክ መነሻው በግብረ ሐዋሪያት ምዕራፍ ፰፡፹፮-፵ የተመዘገበው መልእክተ መንፈስ ቅዱስና ሐዋርያዊ ተልእኮ ነው፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሕንደኬ የምትባል ንግሥት በአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ነግሣ እንደነበረ “ኅጽዋ ለሕንደኬ” በሚባል የሚታወቅ አንድ የዕቃ ግምጃ ቤት አዛዥ(ሹም) እንደነበራት ያስረዳል፡፡ ደሀው ኅጽዋ ለንግሥት ሕንደኬ (የንግሥት ሕንደኬ ጃንደረባ) ለእግዚያብሔር ሊሰግድ በ፴፬ ዓ/ም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር[7] የኢትዮጵያ ሕዝብ ከላይ እንደተገለጸው ከአንድ ሺህ ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ሕገ ኦሪትን፣ ሥርዐተ ኦሪትን ማክበርና እግዚአብሔርን የማምለክ ልምድ ነበረው፡፡ ኅጽዋ ለንግሥት ሕንደኬ ለአምልኮተ እግዚያብሔር ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ የሆነው ፊልጶስን “ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ የሚወስደውን መንገድ ሂድ” ብሎት ሲሄድ ይህን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ አገኘው፡፡ ኢትዮጵያዊ የንግሥቲቱ ጃንደረባ ለእግዚአብሔር ሰግዶ ሲመለስ በሠረገላው ተቀምጦ መጽሐፈ ኢሳይያስን ያነብ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ጃንደረባው የተቀመጠበትን ሠረገላ ተከተለው ብሎ አዘዘ፡፡ ፊልጶስም ይህን የመንፈስ ቅዱስን ትዕዛዝ ተቀብሎ ሮጦ ሠረገላውን ደረሰበት፡፡

ፊልጶስ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ከቍ. 7-8 ያለውን ቃለ ትንቢት ሲያነብ ሰምቶ ጃንደረባውን “የምታነብበውን ታውቃለህን” ብሎ ጠየቀው ጃንደረባውም ያስተማረው ሰው እንዳልነበረና የንባቡን ጥልቅ ምሥጢር እንደማያውቅ ገልጾ መለሰለት፡፡ ፊልጶስም እንደማያውቅ  ከገለጸለት መነሻ ሐሳብ ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ አስረዳው፡፡ ጃንደረባው ቀድሞውም በሃይማኖተ እግዚአብሔር የሚኖር ነበር፡፡ በፊልጶስ ትምህርት ረክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ ወዲያውኑ በፍጹም ልቡ አመነ፤ በአፉም መሰከረ፡፡ አያይዞም ፊልጶስ እንዲያጠምቀው ጥያቄ አቀረበ፡፡ ፊልጶስም ጃንደረባው ለመጠመቅ ሙሉ ፍቃደኛ መሆኑንና በመንፈስ ቅዱስ የተላከበት ዐላማ መሆኑን በመገንዘብ ወዲያውኑ ውኃ ካለበት ወንዝ ወስዶ አጠመቀው፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም የተነገረውን የእግዚአብሔር ቃል በመረዳቱ፤ ሃይማኖተ ክርስትናን በማመኑና በመጠመቁ ደስ እያለው ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡[8] ይህ በግብረ ሐዋርያት ምዕራፍ ፰፡፳፮የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ የተለዩ መሠረታውያን ነጥቦች መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡ ከነዚህ አንዱ መሠረታዊ ሐሳብ ፈቃደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከላይ በተገለጸው የግብረ ሐዋሪያት ክፍል (ግብ.ሐዋ ፰፥፹፮) ፊልጶስ ከኢየሩሳሌም ተነሥቶ ወደ ጋዛ እንዲሄድ መልአከ እግዚአብሔር መንገሩና መንፈስ ቅዱስ በዚህ በጋዛ መንገድ ላይ የሚጓዘውን የጃንደረባው ሰረገላ ተከትሎ እንዲሄድ ፊልጶስን ማዘዙ ክርስትና ሃይማኖትና ጥምቀት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሐዋርያት በቀጥታ እንዲተላለፍ የእግዚያብሔር ፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው የዚህ ክፍል መሠረታዊ ሐሳብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትና የልብ ቅንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው የንግሥት ሕንደኬ ጃንደረባ ለእግዚአብሔር ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱና መጽሐፈ ኢሳያስን ሲያነብብ መገኘቱ ከሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት በተጨማሪ ፊልጶስ ጃንደረባውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሥጢረ ሥጋዌ ባስተማረው ጊዜ እንደ አሕዛብ ወይም እንደ አይሁድ ሳይጠራጠር፣ ሳይከራከር በአንድ ጊዜ በፍጹም ልቡ አምኖ፣ በአፉም መስክሮ መጠመቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌላው ዓለም ቀድሞ በሃይማኖተ እግዚያብሔር የተመሠረተ ቅንና ጽኑዕ ልቡና ያለው ሕዝብ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሃይማኖተ ክርስትናን አምኖና ተጠምቆ ወደ አገሩ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ፊልጶስ ያስተማረውን ትምህርተ ክርስትና ያጠመቀውን ጥምቀት ከቤተ መንግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያ አስተምሮአል፡፡[9] ኅጽዋ ለሕንደኬ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ ካስተማረበት ከ፴፬ ዓ/ም ጀምሮ ሃይማኖተ ክርስትና እና ጥምቀት በኢትዮጵያ እንደተመሠረተ የማያጠራጥር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐቅ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ሊቅ መጽሐፈ ምሥጢር በተባለው ድርሠታቸው “ጥምቀትን ያመጣልን የንግሥት ሕንደኬ መጋቢ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ነው” በማለት ጃንደረባው አምኖና ተጠምቆ ወደ አገሩ ከመጣ በኋላ ይህን ሃይማኖተ ክርስትና እና ጥምቀት ማስተማሩን ገልጸዋል፡፡[10] ይህን የአባ ጊዮርጊስ ገለጻ በመከተል የጻፉ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ብዙዎች ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ የተባሉ “መርሐ ልቡና” በተባለ መጽሐፋቸው የሚከተለውን ጽፈዋል፡፡

“ጌታችን ባረገ 3ኛው ዘመን የገርሳሞት ንግሥት (በግብረ ሐዋርያት ሕንደኬ የተባለችው) የእርሷ ባለሟል መኰንን ጃንደረባ ስለጌታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ ነገር ወደ ኢየሩሳሌም ተልኮ ሄዶ አምኖ ተጠምቆ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሃይማኖትንና ጥምቀትን አስተማረ”፡፡(ግብ ሐዋ 8፡26-39)

ነገር ግን በዚያ ጊዜ የተጻፈ ወንጌል ስላላገኘን በቃል ያለ ይረሳል በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል እንደተባለ የወንጌል ትምህርት በቃል ብቻ ሲነገር ነበረ፡፡እያደረ ግን እየጠፋባቸው እምነትንና ጥምቀትን ብቻ ይዘው እስከ 317 ዓ/ም ተቀመጡ፡፡ በ317 ዓ/ም አብርሀና አጽብሐ ሁለት ወንድማማቾች በነገሡ በ11ኛ ዐመት በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሃይማኖትና ጥምቀት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ሠለጠነ እንጂ አባ ሰላማ ቀድሞ ያልነበረውን ጥምቀት ያመጣ አይመስልም››[11]

በጽሑፍ የተገለጸው ይህ ሐሳብ ክርስትና ሃይማኖትና ጥምቀት ከአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በፊት በ1ኛመቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ መመሥረቱን ያረጋግጣል፡፡በሌላም በኩል ከተለያየ የዓለም ክፍል የተሰበሰበ ልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ በበዓለ ኃምሳ ቀን በዓሉን ለማክበር በኢየሩሳሌም በተገኘ ጊዜ ኢትዮጵውያንም በዚያ በዓል ተገኝተው እንደነበሩና በሐዋርያው ጴጥሮስ ስብከት እንዳመኑ ወደ ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያም ተመልሰው ሃይማኖተ ክርስትናን እንዳስተማሩ ዮሐንስ አፈወርቅ በስብከቱ መግለጹን ጠቅሰው የጻፉ ጥቂቶች አይደሉም[12] በተመሳሳይ ሁኔታ ሩፊኖስ፣ ሶቅራጥስ፣ ቴኦዶሪቶስና ሶዞሚኖስ የተባሉ የታሪክ ጸሓፊዎች በአንደኛ መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ማቴዎስ ሐዋርያ ወደኢትዮጵያ መጥቶ ወንጌለ ክርስቶስን ማስተማሩን እንደገለጹ ጠቅሰው የጻፉ ምሁራን አሉ፡፡[13] በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ በኅጽዋ ለሕንደኬ ትምህርት፣ በቅዱስ ጴጥሮስ የበዓለ ሐምሳው ስብከት በአመኑ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድሕረ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ሃይማኖተ ክርስትናን አምኖ፣ ጥምቀተ ክርስትናን ተጠምቆ ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን እስከ አራተኛ መቶክፍለ ዘመን ድኅረ ልደተ ክርስቶስ ቍርባን፣ ክህነት፣ ጠቅላላ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም አልነበሩትም፡፡ ይህ ይሟላ ዘንድ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት በአጋጣሚ ሳይሆን በጥበበ እግዚአብሔር የሚከተለው ታሪክ ሊፈጸም ችለዋል፡፡

፪.፪.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ)

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድኅረ ልደተ ክርስቶስ ሜሮጵዮስ የተባለ ፈላስፋ ፍልስፈናን የሚያስተምራቸው ሁለት ዘመዶቹ ወጣቶችን አስከትሎ ከጢሮስ ወደህንድ ለመሄድ በቀይ ባሕር(ብሕረ-ኤርትራ) በመርከብ ጉዞ ጀምሮ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች ኤዶስዮስና ፍሬምናጦስ ይባሉ ነበር፡፡ ሁሉም በቀይ ባሕር በመርከብ ሲጓዙ በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያ የባሕር ወደብ(የባሕር ጠረፍ) በነበረቺው በአዱሊስ አጠገብ ዓርፈው ነበር፡፡ ነገር ግን ሜሮጵዮስ የግድያ አደጋ አጋጥሞት እዚው ሞተ፡፡ የሜሮጵዮስን ገዳዮች በተመለከተ የተለያዩ የታሪክ አባባሎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የታሪክ ጸሓፊዎች ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ቅኚ ግዛትን ትቃወም ስለነበረ በዚህ መርከብ ውስጥ የነበሩ ሜሮጵዮስና የመርከቡ ቀዛፊዎች የሮማ ሰላዮች መስለዋቸው የኢትዮጵያ ጠረፍ ጠባቂዎች እንደ ገደሉዋቸው ይገልጻሉ፡፡[14] ሌሎች የታሪክ ጸሐፊዎች ግን ሜሮጵዮስን የገደሉ ሽፍቶች እንደነበሩ ይተርካሉ[15] ይሁን እንጂ ሁለቱም የታሪክ ምንጮች ሜሮጵዮስን በቀይ ባሕር ወደብ በአዱሊስ መገደሉን ያረጋግጣሉ፡፡

ሁለቱን ወጣቶች ግን ኢትዮጵያውያን ሰዎች ከሞት አዳኑአቸው፡፡ ወደ አክሱም ወስደውም ለንጉሠ አክሱም አስረከቡአችው፡፡ ንጉሡም በፍቅር ተቀብሎ ኤዶስዮስን የግቢው አዛዥ፣ ፍረምናጦስን የአክሱም የጽሕፈት ክፍል ኀላፊና የልጆች አስተማሪ አድርጎ ሾማቸው፡፡

ለንጉሠ አክሱም ኢዛና እና ሳይዛና የተባሉ ሁለት ሕፃናት ልጆች ነበሩት፡፡ ኤዶስዮስና ፍረሚናጦስ ከነዚህ ሁለት ሕፃናት ጋር ሆነው በአክሱም ቤተ ቀጢን በተባለ ቦታ ላይ በነበረው ትምህርት ቤት ግእዝ ቋንቋንና በዚያ ጊዜ የነበረውን የቤተክርስቲያን ትምህርት ሁለቱ ለሰባት ዓመታት ተምረዋል፡፡ በዚህ መካከል ንጉሡ ብዙ ሳይቆይ ታምሞ ከዚህ ዓለም ተለየ (ሞተ)፡፡ ንግሥቲቱ አሕየዋ (ሶፊያ) ከንጉሡ ሞት በኃላ በልጆቹ በኢዛናና ሳይዛና ስም መንግሥቱን ታስተዳድር ጀመር፡፡ ታላቁ የንጉሥ ልጅ ኢዛና ለአካለ መጠን ደርሶ ዙፋኑን በወረሠ ጊዜ ፍሬሚናጦስና ኤዶስዮስ ወደ አገራቸው ለመመለስ የስንብት ጥያቄ አቀረቡ፡፡[16] በጥያቄው መሠረትም እንዲሄዱ ተፈቀደላቸው፡፡ ኤዶስያስ ወደ ሀገሩ ወደ ጢሮስ ሄደ፡፡ ፍሬሚናጦስ ግን በአክሱም ሃይማኖተ ክርስትና፣ ጥምቀት እንጂ ቍርባን፣ ክህነትና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የሚያከናውኑ (የሚፈጽሙ) ካህናት ወደ አብያተ ክርስትያናት ሄዶ ጳጳስ ማምጣት እንደ ሚያስፈልግ በመገንዘብ ይህን ሐሳቡ ለንገሥታቱ ለአብርሀ፣ ለአጽብሐ አቀረበላቸው፡፡ ንግሥቲቱም ሆነ ወጣቶቹ ነገሥታትም ሐሳቡን ተቀብለው ፍሬሚናጦስ የኢትዮጵያን ቋንቋና ባህል በዚያውም ልክ የውጪውን ቋንቋና ባህል ያውቅ ስለነበረ እሱ ወደ እስክንድሪያ ሄዶ ካህናትን ጳጳስን እንዲያመጣላቸው ላኩት፡፡ፍሬሚናጦስም የነገሥታቱን መልእክት ይዞ በ325 ዓ/ም ወደ እስክንድሪያ ሄደ፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት የላኩትንም መልእክት ለእስክንድርያው ፓትርያርክ ለቅዱስ እለስክንድሮስ አቀረበ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ እለስክንድሮስ በወቅቱ ታምሞ ስለነበረ ብዙ ጊዜ ሳይቆይ በ328 ዓ/ም ዐረፈ፡፡ ጉዳዩ ግን በእርሱ ለተተካው ለቅዱስ አትናቴዎስ ቀርቦለት ፍሬሚናጦስ መንፈሳዊ ሕይወትና ዕውቀት ያለው አባት ስለነበረ በ330 ዓ/ም በቅዱስ አትናቴዎስ አንብሮት እድ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡ ፍሬሚናጦስ የነበረው ስሙም አባ ሰላማ ተብሎ ተሰየመ፡፡[17]

አቡነ ሰላማ መዓርገ ጵጵስናን ተሾሞ ወደ አክሱም በመጣ ጊዜ ነገሥታቱ ኢዛናና ሳይዛና በክብር በደስታ ተቀበሉት፡፡ አቡነ ሰላማ ጵጵስናን ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ወንጌለ ክርስቶስን የማስተማር ሥራው ተያያዘው፡፡ በመጀመሪያ ነገሥታቱ ኢዛናንና ሳይዛናን ከበፊቱ በበለጠ አስተምሮ አጥምቆአቸዋል፡፡ የክርስትና ስማቸውንም “ኢዛናን አብርሀ እና ሳይዛናን አጽብሐ” ብሎ ሰይሞአቸዋል፡፡ ቤተክርስትያን በዓራቱ የኢትዮጵያ ማዕዘን እንድትሰፋ፣ወንጌለ ክርስቶስ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደርስ ከፍተኛ ሐዋሪያዊ ትጋት አድርጎአል፡፡ የወንጌል የዕውቀት ብርሃን በኢትዮጵያ ስለአበራም የኢትዮጵያ ሕዝብ “ከሣቴ ብርሃን” በሚል ቅጽላዊ ስያሜ ሰይሞታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅና ቅዱስ ያሬድ ይህን የአቡነ ሰላማ ሢመተ ጵጵስናንና ሐዋሪያዊ ተልእኮን ሲገልጽ፦

‹‹አሶተ ሥላሴ ዜነወ
ብዕለ ሐዋርያት ዲቤሁ ተክዕወ፤
ይክሥት ብርሃነ ተፈነወ
አባ ሰላማ ዘድልው ለጵጵስና
ሢመተ ክህነቱ ርቱዕ በሕገ ቀኖና”፡፡

በአማርኛ

‹የሥላሴን ሥልጣን አበሠረ፤
የሐዋርያት ሀብት በላዩ ላይ ፈሰሰ፤
ብርሃንን ሊገልጽ ተላከ
ለጵጵስና የተገባ አባ ሰላማ
የክህነቱ ሹመት በቀኖና ሕግ የተገባ ነው”፡፡

“አባ ሰላማ ለብሔረ አግዓዚ ኮነ ብርሃነ
ወበምጽአቱ ገብረ ሰላመ@ ሐዋርያ ዘተፈነወ ውስተ ምድርነ”

በአማርኛ ሲተረጐም
”አባ ሰላማ ለአግዓዚ ምድር ብርሃን ሆነ
በመምጣቱም ሰላም አደረገ ወደ ምድራችን የተላከ ሐዋርያ ነው፡፡ ”

 

በማለት በሰማያዊ ዜማው መስክሮአል፡፡ አቡነ ሰላማ ካሣቴ ብርሃን ከዚህ በላይ በተገለጸው ትጋቱና በተመሰከረለት ሢመተ ጵጵስናው ወንጌለ ክርስቶስን አስተምሮ ብዙ ሕዝብን ካጠመቀ በኋላ ጠንካራና በሁለመናው የተደራጀ መንበረ ጵጵስናን በአክሱም አቋቋመ፡፡ የክህነት አገልግሎት በስፋት እንዲሰጥ ከዲቁና ክስከ ኤጲስ ቆጶስነት ባሉት መዓርጋተ ክህነት የሐዲስ ኪዳን ካህናትን ሾመ፡፡

ሢመተ ካህናት

አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሊቀ ጳጳስ ወንጌለ ክርስቶስን ከማስተማር ሐዋሪያዊ ተግበሩ ጎን ለጎን በአክሱም የብሉይ ኪዳን ደብተራ (ድንኳን) አገልጋዮች የነበሩትን ካህናተ ኦሪት አስተምህሮ ከሃይማኖተ አይሁድ ወደ ሃይማኖተ ክርስትና ከመለሳቸው በኋላ ካህናተ ሐዲስ ኪዳን አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን አንብሮተ እድ እንደተሾሙ በታሪክ የሚታወቁ የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን የሐዲስ ኪዳን ካህናት የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

 

ዲያቆናት ቀሳውስት ኤጲሶቆጶሳት
የብሉይ ኪዳን ስማቸው የሐዲስ ኪዳን ስማቸው
፩  ፊንሐስ ተንሥአ ክርስቶስ ተክለ ሃይማኖት እንበረም-ሕዝበ ቀድስ
፪  አሮን ስምዖን ገብረ መስቀል
፫  አዛርያስ ማቴዎስ
፬  አቤሜሌክ ዘእግዚእ
፭  ላእከሄኖክ አማኑኤል
፮  መልከጼዴቅ አሐዱ አምላክ
፯  ሳዶቅ ማዕቀበ እግዚእ[18]

 

በሚል ስያሜ የሐዲስ ኪዳን ካህናት አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡ እዚህ ከተገለጹት ካህናት መካከል የሁለቱ ቀሳውስት የብሉይ ኪዳን ስማቸው አልተገኘም፡፡ በኋላ ሁሉንም ዲያቆናት ቀሳውስት አድርጎ ሾሞአቸዋል፡፡ በቅዳሴ በሥርዐተ ቍርባንና ሕዝቡን በማስተማር እንዲረዱት አድርጎአቸዋል፡፡ ብፁዕ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በመንፈስ ቅዱስ አየተመራ ይህን ሐዋርያዊ ተልእኮውን በተሳካ መልኩ በማከናወን ተጋድሎውን ከፈጸመ በኋላ በ፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሐምሌ ፳፮ ቀን ዐረፈ፡፡ ይህ ሐዋርያዊ ሰንሰለት ተያይዞ አሁን እስከ አሉ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች፣ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳት ቀሳውስትና ዲያቆናት ደርሶአል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዚህ ሐዋርያዊ ታሪክ አካል ናቸው፡፡

 

 

 

[1] የካም፣ የሴም፣ የኢስራኤል ወገኖች፣ ዘሮች ማለት ነው፡፡

[2] የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ( ) የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት

[3] W.budg(1922) the qeen of sheba and her only son Menylik, ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል (2005) የእግዚአብሔር መንግስት በምድር ላይ ጠቅላላ የቤተ ክርስትያን ታሪክ)ገጽ .151

[4] የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር (   ) የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት

[5] ኅሩይ ወልደ ሥላሴ(፲፱፻፹፩)(1991) ዋዜማ ገጽ፲፮-፲፯

[6] አባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቅ ጳጳስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ 15

 

[7] ምክረ ሥላሤ ገ/አማኑኤል(ቀ.ዶ.ር(2005) የእግዚያብሔር መንግስት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተክርስትያን ታሪክ) ገጽ.156

[8] ማሕበረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት (፲፱፻፶፫) ወንጌል ቅዱስ ሀእግዚአነ ወአምላክነ ወመድኀኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ገጽ ፻፺፫.

[9] sergew Hable selassie (1997) establishment of the Ethiopian church, in the church of Ethiopia, a panorama of history and spiritual life.P.3.

[10] የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (!)1) መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ.

[11] አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ (  ) መርሐ ልቡና ገጽ 23፣24

[12] Sergew Hable Slassie(1997) The establishment of the Ethiopian church ,A panorama of history and spiritual life.p.3

[13] ምክረ ሥላሤ ገ/አማኑኤል(ቀ.ዶ.ር(2005)የእግዚያብሔር መንግስት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላየቤተክርስትያን ታሪክ) ገጽ.157

 

[14] ዝኒ ከማሁ

[15] ዝኒ ከማሁ

[16]                       ( ) መጽሐፍ ስንክሳር ሐምሌ !6 ቀን

[17] ትንሣኤ አሳታሚ ድርጅት (!)8) መጽሐፈ ድጓ

[18] ዝኒ ከማሁ

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/favicon.png 169 151 tc https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc2025-02-28 21:46:282025-02-28 21:49:58ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት Link to: የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ... Link to: ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወሰብዓቱ ዓመተ ምሕረት Link to: ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወሰብዓቱ ዓመተ ምሕረት ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top