ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ

ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፤ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሓላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን ጨምሮ ሌሎችም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተዋል።

በተጨማሪ የሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የሥራ ሓላፊዎች ፤ አገልጋይ ካህናትና ፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ ዘማሪያንና በርካታ ምእመናን ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር የበረከቱ ተካፋይ ሁነዋል።

በዚሁ መርሐ ግብር ታቦተ ሕጉ ከመንበሩ ወጥቶ ምእመናንን የባረከ ሲሆን በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና በሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ሕንጻ ቤተክርስቲያኑ ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ለምርቃት መብቃቱንና የቅዳሴ ቤቱ መከበሩን የሚያዘክር ያሬዳዊ ጥዑመ ዜማ ቀርቧል።

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን ድርጅት የበላይ ሐላፊ የሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ትምህርት ደግሞ በአዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን “ቅዳሴው በሊቃነ ጳጳሳት ተቀድሶበታል ፣ሕፃናት አረጋዊያንም ቆርበውበታል ፣ከዚህ የበለጠ ደስታ ምንም ነገር የለም ፣ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም ይህ ሕንጻ ቤተክርስቲያን እንዲጠናቀቅ መመሪያ ሰጥተው ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ እንዲከበር ላደረጉት ለብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና ሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉም ተደምጠዋል።

ከዚህ በመቀጠል የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ ለፍፃሜው እንዲበቃ ገንዘባቸውን ፣ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን በበጎ ፈቃደኝነት የሰጡ እንዲሁም በአስተባባሪነት ፣ በልዩ ልዩ የሥራ ድርሻዎችና ሓላፊነቶች የጎላ ድርሻ የነበራቸው ሁሉ ከቅዱስ አባታችን ሽልማት ወስደዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ሕንጻ ቤተክርስቲያን ለማነፅ አነሳስቶ ስላስፈፀማችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል።

ቅዱስ አባታችን ለለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ምእመናን “ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ለብዙ ዘመናት መገልገያ የሚሆናችሁን እግዚአብሔርን የምታመሰግኑበት ፣ የምትቆርቡበትን ሕንፃ ቤተክርስቲያን ነው የገነባችሁትና እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲሉም አክለዋል።

ቅዱስነታቸው “ከዛሬ ጀምሮ ይህንን አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ካቴድራል ብለነዋል” ያሉ ሲሆን ቤተክርስቲያኑ በስያሜው ልክ መሆን ስለሚገባው ትምህርት ቤትና ሌሎችንም ከዚህ የበለጠ ልማት ሊሰራበት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ፈሰስ ተደርጎበት ለምርቃት የበቃው የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ጥር 29 ቀን 2002 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት፣ የዓለም የሰላም አምባሳደር የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት ግንባታው መጀመሩ ይታወቃል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነችው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ በመሆኗ አበው ቅዱሳን በፍትሕ መንፈሳዊና በጉባኤ አድያም ዘአንጾኪያ “ወይኩን ሲኖዶስ ዘጳጳሳት ፪ተ ጊዜያተ በበዓመት – የጳጳሳት ጉባኤም በዓመት ሁለት ጊዜ ይሁን” ብለው በደነገጉት ቀኖና መሠረት፤ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የሐዋርያት መንበር ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤውን በኅብረተ መንፈስ ቅዱስ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም ድረስ አካሄዷል፡፡

ምልዓተ ጉባኤው ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት፤ ስለ ሰው ልጅ ሁሉ ደኅንነትና ክብር፣ በአጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ዘመኑን የዋጁ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል፡-

የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት መጠበቅና ማስጠበቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ተግባር በመሆኑ ጥንታዊትና ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በአንድነቷና በሉዓላዊነቷ እንደተረከብናት ለወደፊቱም ሉዓላዊ ክብሯ ተጠብቆ እንድትቀጥል በምልዓተ ጉባኤው የተሠየመው በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራው “የሀገራዊ ሰላምና የቤተ ክርስቲያን አንድነት” ኮሚቴ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ በተረጋጋ መንገድ እንዲካሄድ፣ ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት በሚጠቅም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትጸልይ ሲሆን ምርጫው በሁሉም ወገን ለኢትዮጵውያን ዘላቂ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያስገኝ ሆኖ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የአርሲ ሀገረ ስብከትን በሊቀ ጵጵስና በቋሚነት እንዲመሩ፣ ሕዝቡን እንዲያጽናኑ እየደረሰ ያለውን ችግር ከቋሚ ሲኖዶስና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከሚመራው የሰላም ኮሚቴ ጋር በመሆን የሚመለከተውን የመንግሥት አካል በማነጋገር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡

ከጥንት ጀምሮ “ቅዱስ ሲኖዶስ” በሚል ርእስ እየተዘጋጀ ይታተም የነበረው ታሪካዊ መጽሔት የቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ ውሳኔዎችን በማካተት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አስፈጻሚነት ሕትመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንን ደንቦች መመሪያዎች መርምሮ ማጽደቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን በመሆኑ፡-

የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስፈጸሚያ ደንብ በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሰብሳቢነት

የአንድነት ገዳማት ኅብረት መተዳደሪያ ደንብ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ባሉበት በድጋሚ እንዲታይና ሌሎቹም ለውሳኔ የቀረቡ ደንቦች በሊቃውንትና በሕግ ባለሙያዎች ታርመው ለጥቅምት 2019 ዓ/ም ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል::

የቀድሞው የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ”ና “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚሉ አርእስት አዘጋጅተው ያሳተሟቸው መጻሕፍትን የማሳተምና የማሰራጨት የባለቤትነት መብት ከሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
ከተለያዩ አህጉረ ስብከት በቀረቡ ጥናቶችና የማጣራት ውጤቶች መሠረት፡-

የደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ጋር ተደርቦ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ፤
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ሊቀ ጳጳስ የጋምቤላንና የቤንሻንጉል ጉምዝ አህጉረ ስብከትን ብቻ እንዲመሩ፤
ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከትን እንደያዙ እንዲቀጥሉ፤
ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከትን ደርበው በአባትነት እንዲመሩ፣
የኮንታ ዞን ሀገረ ስብከት እንዲሆን የቀረበው ጥያቄ የጸደቀ በመሆኑ ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ እንዲደራጅና በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የልማት ተግባራትን ምልዓተ ጉባኤው በከፍተኛ ደረጃ በማድነቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ/ ዋና ሥራ አስኪያጅ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ሲቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በአባታዊ አመራር የፈጸሙት አስደናቂ የሥራ አፈጻጸም በጉልህ የሚታይ ለውጥ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም፣ ሉዓላዊ ክብሯን የሚያስጠበቅ፣ ለሁሉም አበው ምሳሌነት ያለው በመሆኑ ምልዓተ ጉባኤው እጅግ ከፍ ባለ ክብር አመስግኗል፡፡

በዚህም መሠረት በብፁዕ ጠቅላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መሪነት እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ማለትም፡-

የቤተ ክርስቲያንን ቀደምት ሠነዶች በዲጂታል ቴክኖሎጅ እንዲደራጁ የተደረገበት ሥልት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤

ከ1970 ዓ/ም ጀምሮ በመጋዝን ተከማችተው የቆዩ በርካታ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን የማሠራጨት ሂደት በተጀመረው መንገድ እንዲጠናቀቅ፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የኢንፎርሜሽንና ኮምኒኬሽን ተጠቃሚ እንድትሆን የተጀመረው ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር በየደረጃው ተጠናክሮ ተግባራዊ እንዲሆን፤

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር የተጀመሩ የሕንፃ ግንባታዎችና አጠቃላይ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ሁሉም አህጉረ ስብከትና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦና ትብብር እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

በሰሜን አሜሪካ የሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት አርሴማ ገዳም የመንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የአብነት ት/ቤት ሥርዓተ ትምህርት የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ታሪክና ትውፊት በጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ መዋቅራዊ ተጠሪነቱም በአግባቡ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያቀረበውን የ2019 ዓ/ም በጀት በማጽደቅ በተገቢው መንገድ ሥራ ላይ እንዲውል ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተነጋገረባቸው ጉዳዮች በትኩረት የተወያየው የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ዕድገትና ተቋማዊ ሕልውና ስለማስጠበቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሀገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም እየታየ ያለው ግጭትና የሰላም መታጣት በእጅጉ አሳስቦታል፡፡

በመሆኑም ስለ ዓለምና ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ስለ ሰው ልጆች ደኅንነት፣ በየቦታው በሃማኖታቸው ምክንያት መከራ የሚደርስባቸውን በየቦታው የሚገኙና ግጭት ባለባቸው ቦታዎች ያሉ ኦርቶዶክሳውያንን በማሰብ በመጪው የ2018 ዓ/ም ጾመ ሐዋርያት በመላው ዓለም ባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፣ አድባራትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በመላው ዓለም፣ በደቡብ አፍሪካና በሳውዲ ዐረቢያ የሚኖሩ ዜጎቻችን ሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ የርኅራኄ ምሕረትና ፍትሕ እንዲያገኙ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትል እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ጥሪውን በማቅረብ ለሰባት ቀናት ሲያካሂድ የሰነበተውን ቀኖናዊ ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቋል፡፡

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ”

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
ግንቦት 6 ቀን 2018 ዓ/ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ

ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት እንደሚከተለው ነው

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

‹‹ተዘከሩ መቁሓነ ዘከመ ተሞቃሕክሙ ምስሌሆሙ ወእለ ተሣቀዩ ከመ ዘሀለውክሙ በሥጋክሙ፡-
ከእነርሱ ጋር አብራችኋቸው እንደታሰራችሁ ሆናችሁ እስረኞችን ዐስቡ፤ መከራ የጸናባቸውንም በሥጋችሁ ከእነርሱ ጋር እንዳላችሁ ሆናችሁ ዐስቡ››
(ዕብ. 13፡3)

እውነተኛ እምነትም ሆነ ጤናማ አመለካከት የሚመዘነው መከራ ስለሚቀበሉ ሰዎች ሰምቶና አይቶ በዝምታ ባለማለፍ፤ ይልቁንም በእነርሱ ሕመም ውስጥ ራስን በማስገባት በሚሰማው ጥልቅ ኀዘን እና በሚደረገው ድጋፍ ነው፡፡ ይልቁንም በዚች ዓለም የምንኖር ለችግርና ለመከራ ቅርብ እንደመሆናችን የታሰሩትን መጎብኘት፣ የተገፉትን ማጽናናት፣ በስደት ምድር ላይ ሆነው በሞት ፍርድ የሚጨነቁትን ወገኖች ስቃይም እንደራሳችን ስቃይ በመቁጠር ስለእነርሱ ድምፅ መሆንና ማዘን ስንችል በሰማያዊው መንግሥት የማይጠፋ የጽድቅ ዋጋን እናከማቻለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

እረኛ በበረት ውስጥ ያለችው አንዲት በግ ስትጠፋ ወይም ለአደጋ ስትጋለጥ ዝም ብሎ እንደማያይ ሁሉ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ምድር በሞት ጥላ ሥር ሆነው ‹‹የፍትሕ ያለህ›› እያሉ የሚጮኹ፤ በጭንቀት ቀናትን የሚቆጥሩና ድምፅ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን የተሻለ ኑሮ እናገኛለን ብለው በተሰደዱበት ሀገር ሕይወታቸው በጅምላ ሊቀጠፍ እንደሆነ መረጃውን ከልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን የተገነዘብን በመሆኑ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጠቀሜታው የሰው ልጆችን ሕይወት ለመጠበቅ ነውና የኢትዮጵያ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኙ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር በግፍ የተፈረደባቸው ልጆቻችን የሞት ፍርድ እንዲነሳላቸውና ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት መንገድ ይመቻች ዘንድ የተጀመሩ ሥራዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥባቸው፤ ወገኖቻችንም በቋንቋ እጥረትና በሕግ አማካሪ እጦት ለሞት እንዳይዳረጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ የሰጠው ታላቅ ስጦታ ሕይወት ነው፤ “አትግደል” የሚለው ሕግም በማንኛውም ምድርና ቋንቋ የሚሠራ ሲሆን ፍርድ ያለ ምሕረት ከሆነ አምላካዊ ቁጣን ይጋብዛልና የሳዑዲ ባለሥልጣናት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ታሪክና ወዳጅነት አስበው፣ በሞት ፍርድ ጥላ ሥር ላሉት ወገኖቻችን ምሕረትን እንዲያደርጉ፣ ቅጣቱንም ወደ እስራት እንዲቀይሩ በአባታዊ ርኅራኄ እንጠይቃለን ፡፡

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም በማያውቁት ቋንቋ እንዲሁም ባልተረዱት የሕግ ሂደት ሞት የተፈረደባቸውን ወገኖች ስቃይ ተመልክተው የፍትሕ መዛባትን እንዲቃወሙና የንጹሐንን ነፍስ እንዲታደጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

በመጨረሻም፣ ማንኛውም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሰው ሕይወቱ ሊጠፋ አይገባምና ኦርቶዶክሳውያን ልጆቻችን የክርስትናችን አንዱ መገለጫ የአንደኛው ወገን ሕመምን በጋራ መካፈል እንደሆነ ተረድታችሁ ወደ ፈጣሪያችን በጸሎት እንድትማጸኑ፤ መላው ኢትዮጵያውያንም ለመፍትሔው የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ስንል አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን!
ብፁዕ ኣቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዕ ኣቡነ ሕርያቆስ
የኣዲስ ኣበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት፣
በኣጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፦
ማሕየዊት በምትሆን ሞቱ ሰማያውያንና ምድራውያንን ያስታረቀ፣ በቅድስት ትንሣኤውም የሙታንን ሕይወት በተስፋ ያለመለመ ጌታችን፣ ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንኳን ለዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“እስመ ተዋለጠ እግዚአብሔር ዓለመ በክርስቶስ ኣናኅስዮ ኃጢኣቶሙ ወኢነጺሮ ጌጋዮሙ፤ ወረሰየ ላዕሌነ ቃለ ሥምረቱ፤ ወወሃበነ መልእክተ ሣህሉ፡- እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን ኣይቈጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል ኣኖረ” (2ቆሮ. 5፥19)።
የእግዚአብሔርም ልጅ፣ የሰውም ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሰብእነት ሲገለጽ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ እንደነበረው ቅዱስ መጽሓፍ ይነግረናል፤ እሱም በሰማይም፣ በምድርም ያሉትን በሙሉ ማስታረቅ፣ ማገናኘትና ኣንድ ማድረግ ነበረ፤
ጌታችን ይህንን ሲያደርግ ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን የለያየው ምክንያት በማስወገድ ነው፤ የመለያየቱ ምክንያት ክፉ ኅሊና ኣምጦ የወለደው በደልና እሱን ተከትሎ የተከሠተው ኃጢኣት ነበረ፤ በኃጢኣት ምክንያት የገባው ሞት ደግሞ የቅጣቱ ማሳያ ፍርድ ነበረ።
የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በፈጸሙት ስሕተት መነሻነት ምድርንና ምድራውያንን ለከባድ ቅጣትና መርገም የዳረገው ይህ መለያየት ለሰማያውያኑም ተርፎኣል፤
ምክንያቱም መለያየቱ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በመላእክትና በሰው፣ በሰውና በሰው፣ በነፍስና በሥጋ ጭምር የጥል ግድግዳን ገንብቶ እስከ ክርስቶስ ዕለተ ስቅለት መዝለቁን በቅዱስ መጽሓፍ የምናውቀው ስለሆነ ማለት ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
ቀዳማዊና ዘላለማዊ የሆነው ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብእናችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም የተገለጸው ሰማያውያንንና ምድራውያንን የለያየው የጥል ግድግዳን ለማፈራረስ ነው፤
ለመለያየት ምክንያት የሆነችውን ኃጢኣት በሰውነቱ በመቅጣት የሕግን ትእዛዝ ከፈጸመ በኋላ የዕርቁን ተግባር በወሳኝ መልኩ ኣከናውኖታል፤
በክርስቶስ ቤዛነት የሆነው ይህ ዕርቅ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደደ ነበረና እሱ ራሱ በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ኣስታረቀ፤
ለዚህም ነው ተበዳይ እሱ፣ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው እሱ፣ ኣስታራቂ እሱ፣ ታራቂ እሱ ሆኖ የምናገኘው፤ ለሱ የሚሳነው ነገር የለምና ለኛ ግር የሚል ቢመስልም ለሱ ቀላል ነበረ።
በዚህ የዕርቅ ተግባር ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሰውና ሰው፣ ነፍስና ሥጋ ታርቀው በይፋ ተገናኙ፤ በኅብረትና በኣንድነትም መኖር ቻሉ፤ በቀኙ ለተሰቀለው ሽፍታ “ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” የሚለው ቃለ ምሕረትና “ኣባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ ኣደራ እሰጣለሁ” የሚለው ቃለ ኣማሕፅኖ የዕርቁ፣ የግንኙነቱና የኣንድነቱ ማሳያ ኣስረጅ ናቸው።
ስቅለተ ክርስቶስ ነፍሶቻችን ወደ ግዞት ቤት ሳይሆን ወደ ገነት እንዲገቡ፣ የሚቀበላቸውም ራሱ እግዚአብሔር እንዲሆን ያስቻለ ታላቅ መለኮታዊ ፍጻሜ ነው፤
እኛ “ክርስቶስ መድኃኒታችን ነው፤ ኣድኖናል” ብለን በልበ ሙሉነት የምንመሰክረው፣ እሱም “ሰላሜን ሰጠኋችሁ” ብሎ የሚያረጋጋን በመሰቀሉ ይህንን ውጤት ስላስገኘልን ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!
የድኅነታችንና የሰላማችን መሠረት የሆኑትን የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለዓለም ማኅበረ ሰብ የማብሰርና የማሥረጽ ተግባር የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቍጥር ኣንድ ተልእኮ ነው፤
ነገረ ሞቱና ነገረ ትንሣኤው በኣስተውሎት፣ በጥልቀትና በተመሥጦ ስናስተምር በውስጡ የምናገኘው የዕርቅ፣ የሰላምና የኣንድነት ምስጢር ነው፤
እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ የክርስቶስ መልእክተኞች እንደ ቃሉ ራሳችንን ክደን በሚጠበቀው መጠን ተልእኮኣችንን መወጣት ብንችል ኖሮ፣ ኣሁን በዓለማችን የተፈጠረው መለያየትና ግጭት ኣይኖርም ነበር፤
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባንችልም በእጅጉ መቀነስና ዓቅሙን ማዳከም እንችል ነበር፤ ነገር ግን ተልእኮኣችንን በኣግባቡ ኣለመወጣት ኣንድ ነገር ሆኖ የዓለሙ መሳሪያ ሆነን መገኘታችን “በዕንቅርት ላይ…” ሆኖ ይስተዋላል።
ይሁንና ኣሁንም ሕዝቡን ወደ ኣንድነት፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ ሰላም፣ ወደ ዘላቂ የጋራ ጥቅምና ወደ ፈሪሐ እግዚአብሔር ማምጣት የጉባኤያችን ዓቢይ ተግባር ሊሆን ይገባል፤ እነዚህ ካሉ የምናጣውም ሆነ የሚያመልጠን የለምና ነው፤
ሃገርን በኃላፊነት ተረክባችሁ በላዕላዊ፣ በማእከላዊና በታሕታዊ መዋቅር የምትገኙ፣ እንደዚሁም ኣማራጭ ሓሳብ ኣለን ብላችሁ የምትንቀሳቀሱ ልኂቃነ ሃገር ፣ ሁላችሁም እግዚአብሔርን ከሚያውቅ፣ ከሚያመልክና ከሚፈራ ሕዝብ የተገኛችሁ ናችሁና በልባችሁ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ድምፁንም ስሙ፤ የሱ ገንዘብ በሆኑ ፍጡራንም ኣትጨክኑ፤ ሰውን መያዝ የሚቻለው ኅሊናን በመርታት እንጂ በሌላ ኣይደለምና፣
የሕዝቡን ፍላጎትና የልብ ትርታ በሚገባ ኣዳምጡ፤ ሕዝቡ የሚፈልገው በኣንድነትና በእኩልነት መኖር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ፍትሕን ማስፈን፣ ለኑሮው የሚበቃ ምጣኔ ሃብትን ማግኘት፣ የእምነት ነጻነትና እኩልነት መረጋገጥ የመሳሰሉት ናቸው።
ሕዝቡ እነዚህ ከተሟሉለት ተደመጠ ማለት ነው፤ ከተደመጠ ደግሞ እሱም በበኩሉ ያደምጣል፤ ይከተላልም፤
ስለሆነም ለሁሉም ልጆቻችንና ወገኖቻችን የምናስተላልፈው ወቅታዊ ጥሪ ሁሉንም ችግሮቻችን በሰላምና በሰላም ብቻ ለመፍታት ተባበሩ የሚል ነው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረገው ኣማራጭ ሁሉ ለዘላቂ ሰላማችን ኣይበጅም እንላለን።
መጨረሻም፦
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ ኣምስተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልኣተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለመላው ኢትዮጵያውያን እናበስራለን!!!
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሓት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘኣኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም
ኣዲስ ኣበባ – ኢትዮጵያ