• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ታኅሣሥ 29 ቀን 2011 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤ ወሀቤ ሰላም የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አንድ ዓመት ምሕረት የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!

“ኅሥሣ ለሰላም ወዴግና፤ ሰላምን ሻት ተከተላትም”

ቅዱስ መጽሐፍ ደጋግሞ እንደሚነግረን እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ጸጋዎች አንዱ የሰላም ጸጋ ነው፤ የሰላም ጸጋ ሰው ሲፈጠር አብሮ የተፈጠረ አምላካዊ ሀብት ቢሆንም በአግባቡ ካልተያዘ በሰዎች ድርጊት ሊወሰድ የሚችል እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፤ እኛም በተጨባጭ የምናየው ሐቅ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረታትን በፈጠረ ጊዜ ሁሉም በሰላም በፍቅርና በአንድነት ተሳስረው እንዲኖሩ ፍጹም ሰላሙን አድሎአል፤ የሰላም አለቃቸው ደግሞ በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረው ሰው ነበረ፤ ይሁን እንጂ ፍጥረታትን አንድ አድርጎ በሰላም እንዲያስተዳድር ኀላፊነት የተሰጠው ሰው የበላይ መሪው እግዚአብሔር ባስቀመጠለት መርሕ መመራት ባለመቻሉ ሰላሙ ተነጠቀ፤ ከዚህ አንጻር ሰላም በሰው መታዘዝ ምክንያት በፍጡራን ጸንቶ የሚኖር፣ በአንጻሩ ደግሞ ሰው ለእግዚአብሔር ባልታዘዘበት ጊዜ የሚወሰድ ስጦታ እንደሆነ ታወቀ፤ በመሆኑም የሰው ሰላም ሲደፈርስ የሌሎች ፍጥረታትም አብሮ ደፈረሰ፡፡ ብርሃን ከሌለ ጨለማ እንደሚነግሥ ሁሉ ሰላም ከሌለም ጠብና ፍጅት ይነግሣልና የሰው ሰላም ሲወሰድ ፍጥረታት በሙሉ መለያየትን መጣላትን እርስ በርስ መፋጀትን ገንዘብ አደረጉ፤ በዚህም ምክንያት ሕይወት በጨለማ ተዋጠች፤ ኑሮም መራራ ሆነች፤ ሰላም ድሮም የተሰጠች ኋላም የተወሰደች በእግዚአብሔር መለኮታዊ ውሳኔ ነበርና ለፍጥረቱ አዛኝ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ እንደገና ሰላምን ለሰው ልጆች ለማደል ወሰነ፤ ሰላሙንም የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ሰው በመሆን ገለጸው፤ እግዚአብሔር ሰውን የታረቀው ለመሆኑ ዋናው ማረጋገጫ የሰውን ሥጋና ነፍስ ተዋሕዶ፣ ባሕርየ ሰብእን የራሱ ባሕርይ አድርጎ መወለዱ ነው፤

ዘለዓለማዊው እግዚአብሔር ወልድ በተዋሕዶተ ትስብእት ሰው ሲሆን፣ ሰውም በተዋሕዶተ ቃል ምክንያት አምላክ ሆኖአል፤ በዚህ ምሥጢረ ሥጋዌ ባሕርየ ሰብእ ወይም የሰው ባሕርይ በተዋሕዶተ ቃል የባሕርይ አምላክ ሆኖ እንደገና የፍጥረታት ሁሉ ገዢ ለመሆን በመብቃቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ አስተማማኝና የማይናወጥ ሰላም ማግኘቱን እንገነዘባለን፤ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ሰማያውያን የሆኑ ሠራዊተ መላእክት “ክብር በአርኣያም ለእግዚአብሔር ይሁን” በማለት እግዚአብሔርን ያመሰገኑበት ምክንያት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በተዋሕዶተ ቃል የተገነባ፣ ፈጽሞ የማይፈርስ፣ የማይደፈርስና የማይናወጥ ሰላምን አጎናጽፎት ስላዩ ነው፡፡ በመሆኑም ከልደተ ክርስቶስ ወዲህ ያለው ዘመን እግዚአብሔር ሰውን የታረቀበትና ሰላምን ያጎናጸፈበት ብቻ ሳይሆን ባሕርየ ሰብእን ከመለኮቱ ጋር አዋሕዶ በመንበሩ ላይ በክብረ አምላክነት ደረጃ ያስቀመጠበት ግሩም ዘመን ነው፤ ከዚህ በኋላ ሰው በመንበረ ጸባኦት ላይ በነገሠው አካሉና ባሕርዩ እየተሳበ በሱታፌ አምላክነት ከብሮ ይኖራል እንጂ እንደገና ሰላምን አጥቶ መንፈሳዊ ሕይወቱ የሚናጋበት ሁኔታ የለም፤ እሱ በተዋሕዶተ አምላክ ወሰብእ ጊዜ አብቅቶአል፤ ለዚህም ነው ከልደተ ክርስቶስ ወዲህ ያለው ዘመን “ዓመተ ምሕረት” ተብሎ የተሰየመው፤ ምክንያቱም ምሕረትና ሰላም ለሰው ልጅ በአስተማማኝ ሁኔታ ተሰጥቶአልና ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የሰላም ዕጦት በተዋሕዶተ ቃል ወሰብእ ተወግዶ በልደቱ ዕለት ፍጹም ሰላም የተበሠረ ቢሆንም በሰውና በሰው መካከል ያለው ሰላም ግን አሁንም እክል እያጋጠመው እንደሆነ የማይካድ ነው፤ ይህ ሁኔታ ከዳግም ምጽአት በኋላ እንደሚያከትም ቢታወቅም እስከዚያው ድረስ በዚህ ዓለም ክፉ መንፈስ ተዋናይነት ፈተናው እንዳልተቋረጠ እያየን ነው፤ እርግጥ ነው እኛ ሰዎች በቃለ ቅዱስ ወንጌል በመመራትና በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በመታገዝ ክፉውን መንፈስ ማሸነፍ እንደምንችል እናውቃለን፤ ሆኖም ዛሬም ሰዎች ለእግዚአብሔር ያለን ታዛዥነትና ታማኝነት ዝቅተኛ በመሆኑ ከክፉው መንፈስ ጫና ነፃ መሆን እንዳልቻልን ገሃድ ሆኖ ይታያል፤ ከዚህም የተነሣ በየትኛውም የዓለም ዙርያ የሰላም መደፍረስ ሁኔታ ሲደርስ እናያለን፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ ዓለም አካል እንደመሆኗ መጠን ከዚህ አላመለጠችም፤ በመሆኑም በዚህ ወቅት በክፉው መንፈስ ምክንያት የሰላም ሀብቷ ርቆ በዜጎችዋ መካከል አለመተማመን፣ ሥጋትና መጠራጠር ከዚያም አልፎ መገዳደል መፈናቀልና መዘራረፍ ወዘተ እየተበራከቱ፣ ሴቶችና ሕፃናት በሚያሳዝን ሁኔታ እየተንገላቱ፣ የሰቆቃ ኑሮ እየገፉ ናቸው፤ በውኑ እግዚአብሔር በሚታወቅባትና በሚመለክባት በኢትዮጵያ ምድር እንደዚህ ያለ ችግር መከሠት ነበረበት ወይ? የሚለውን ጥያቄ ስናነሣ መልሱ ፍጹም መከሠት አልነበረበትም ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር የሆነ ሕዝብ ይህንን ያደርጋል ተብሎ አይታሰብምና ነው፤አስተዋዩና አማኙ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህንን አሳፋሪ ድርጊት እንደሚፀየፈው እንጂ እንደማይቀበለው እናውቃለን፤ ይሁን እንጂ ጥቂቶቹስ ቢሆኑ ከዚህ ለመድረስ በቂ ምክንያት ነበራቸው ወይ? ቢባል አሳማኝ መልስ ይኖረዋል ብለን አናምንም፤ ምክንያቱም ጭካኔ፣ ግድያና መለያየት በምንም መመዘኛ አሳማኝ ሆኖ አይገኝምና ነው፡፡

እስካሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ይህ ነው የሚባል የርስ በርስ ቅራኔ እንደሌለ ነው፤ ሕዝቡ አሁንም አንድነቱን ይወዳል፣ ሕዝቡ በሰላም፣ በወንድማማችነት በእኩልነት፣ በስምምነት፣ ተጋግዞና ተረዳድቶ በአንድነት መኖር ለድርድር የማይቀርብ ምርጫው ነው፤ ሕዝቡ በኢትዮጵያ አንድነት፣ በሰላም መረጋገጥ፣ በዜጎች እኩልነትና ሰብኣዊ መብት መከበር የጸና አቋም እንዳለው ጥርጥር የለውም፤ የሀገራችን ሰላም ፈተና እያጋጠመው ያለ በፖለቲካ ኀይሎች ሽኩቻና አንዱ አንዱን ጥሎ ለማለፍ የሚደረገው ቅድድሞሽ ያስከተለው ችግር እንደሆነ አሌ የማይባል ሐቅ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገራችን አሁን ከገጠማት የሰላም መደፍረስ አጣብቂኝ በአፋጣኝ ለመውጣት ሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች ሰፊ የውይይት መድረክ በመክፈት በሀገር አንድነት፣ በሰላም መጠበቅ፣ በዜጎች እኩልነትና ሰብኣዊ መብት መከበር የጋራ አቋም በመያዝ ሰላምን ሊያረጋግጡ ይገባል፤ ሕዝቡም በተለይም ወጣቱ ትውልድ ተረጋግቶና ሰከን ብሎ በማሰብ ወገንን ከመተናኮል፣ ከማፈናቀል፣ ከማሳደድና መንገዶችን ከመዝጋት ሊቈጠብ ይገባል፡፡ ወጣት ልጆቻችን የነገ ሀገር ተረካቢ ባለአደራዎች ስለሆናችሁ ግሎባላይዜሽን ካመጣው የባህል ወረርሽኝ፣ ከሱስና ከአደንዛዣ ዕፅ ተጠብቃችሁ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሰላሟና ለልማቷ የተጋችሁ እንድትሆኑ በአጽንዖት እንመክራችኋለን፡፡ መንግሥትም የጀመረውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላምን የማስፈን በጎ ተግባር ለማጠናከር ሁሉንም የፖለቲካ ኀይሎች በማሳተፍና በማወያየት የሀገሪቱን ሰላምና አንድነትን እንዲያረጋግጥ፣ የዜጎችን ደኅንነትና ሰላም በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር፣ እንደዚሁም የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ የሚያውኩ ድርጊቶችን እንዲያስተካክል በዚህ አጋጣሚ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም፡ “ሰላም በምድር ሁሉ ይሁን” እያልን የገናን በዓል ማክበር ብቻው በቂ ስላይደለ ለሰላም መስፈን የኛ ተሳትፎም ወሳኝ ሚና አለውና ሕዝቡ በአጠቃላይ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ወገንን ከማፈናቀልና ከማሳደድ ተቈጥባችሁ ለሀገር አንድነት፣ ለሰላም መጠበቅና ለሰው ልጅ መብት መከበር በአንድነት እንድትቆሙ፣ የፖለቲካ ኀይሎችም ችግሮችን ሁሉ በውይይትና በውይይት ብቻ በመፍታት ሀገሪቱንና ሕዝቡን በቅንነት ለማገልገል አጥብቃችሁ እንድትሠሩ በእግዚአብሔር ስም አደራ ጭምር አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የገና በዓል ያድርግልን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32019-01-07 13:44:242025-01-28 13:48:10ታኅሣሥ 29 ቀን 2011 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 21 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ Link to: ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 21 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 21 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደው... Link to: ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጥምቀት በዓል በጃንሜዳ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጥምቀት በዓል በጃንሜዳ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጥምቀት በዓል በጃንሜዳ የተሰጠ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top