በቅዱስነታቸው ዘመነ ፕትርክና የተከናወኑና በታሪክ የሚዘከሩ ዐበይት ተግባራት፤

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ወደ ፓትርያርክነት ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በርካታ ዘመን ተሸጋሪ የሆኑ ሥራዎች በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰኑ እንዲሠሩ አድርገዋል፡፡ ከዚህ አኳያ እጅግ የጎሉና በትውልዱ ሊታወሱ ከሚገባቸው ታሪካውያን ሥራዎቻቸው መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

1. የመገናኛ ብዙኃን መቋቋምን በተመለከተ፣

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1966 ዓ.ም በፊት በሀገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንደዚሁም ብሥራተ ወንጌል በሚል ይሰራጭ በነበረው፣ የሬዲዮ ድምፅ ጣቢያ በነበራት የአየር ሰዓት የሰላም፣የእምነትና የማኅበራዊ ተልእኮ ትምህርቶቿን፣ ዓመታዊ በዓላቷንና ሥርዐተ አምልኮቷን በቀጥታ ሥርጭት ታስተላልፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይኽ እንቅስቃሴ በወታደራዊው የደርግ ሥርዐተ መንግሥት ከተቋረጠ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ መልእክት በጥቂት የኅትመት ሚዲያ ሥርጭቶች ብቻ ተወስኖ ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜም ምንም እንኳ የመናገርና ሃይማኖትን ጨምሮ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሕገ መንግሥቱ የታወጀ ቢሆንም በኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖት ተቋማት ስም የብዙኀን መገናኛ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የተመቻቸ ነገር ባለመኖሩ ችግሩ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይሁንና በሀገራችን ካሉ የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ከኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቀር አብዛኛዎቹ በውጭ የሚኖሩ አጋሮቻቸውንና በሀገር ውስጥ ያሉ ተከታዮቻቸውን በማስተባበር ቅርብና አመች ከሆኑ ጎረቤት ሀገሮች የሥርጭት መሥመሮችን በመጠቀም በብዙ የሀገራችን ቋንቋዎች ሃይማኖዊ ትምህርቶቻቸውን በልዩ ልዩ የሳተላይት ቴሌቪዥን የሃያ አራት ሰዓት ሥርጭትን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ዕድል በመጠቀም ከነገረ መለኮቱ አስተምህሮ በተጨማሪ ሀገራዊ ሰላምን፣ መከባበርን፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ እድገትን፣ የሕዝብን በፍቅር ተባብሮ መኖርን፣ የሰው ልጅ ደኅንነትንና የሀገርን በጎ ገጽታ ማሳየትን መሠረት ያደረጉ ልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኅንን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባት ታምኖበት ማእከላዊና ተጠያቂነት ያለው የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት እንዲቋቋም በቅዱስነታቸው ርእሰ መንበርነት ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ወር 2006 ዓ/ም ወስኗል፡፡

በውሳኔው መሠረትም የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥራ ይጀመር ዘንድ በቋሚ ሲኖዶስ በተሰየመ ቦርድ እና ቦርዱ በሾመው ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ልዩ ልዩ ጥናቶች ተጠንተዋል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በድርጅታዊ መዋቅር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙኀን ሥርጭት አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤቱ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ነው፡፡ ድርጅቱ ለሥርጭት የሚሆኑት ማናቸውንም ዝግጅቶች በሀገር ውስጥ የሚያዘጋጅ ሲሆን በወቅቱ በተገባው ውል መሠረት ሥርጭቱ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት አማካኝነት ኢየሩሳሌም ከሚገኘው የሳተላይት ድርጅት ጋር በተደረገው ስምምነት ሥርጭቱ ሊጀመር ችሎአል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በገዳሙ ተገኝተው በመሩት ስብሰባና ውይይት ገዳማቱ ለዚህ አገልግሎት ያላቸውን ሙሉ ስምምነትና ፍላጎት በሙሉ ድምፅ በማረጋገጣቸው ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሳተላይት ውልን በተመለከተ የውሉን ይዘት በሕግ ባለሙያዎች እንዲታይ ቦርዱ በሰጠው ውሳኔ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ መሠረት የተላከውን የውሉ ረቂቅ ዓለም ዐቀፍ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ እንዲመረመሩትና እንዲያስተካከሉት ተደርጎአል አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴም (በወቅቱ የመንበረ ፓትርያርክ ሕግ አገልግሎት መምሪያ ኀላፊ) በቦርድ ስብሰባ ተገኝተው አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ በሕግ ባለሙያዎች የታረመው ውል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ቦርድ አባላት በተገኙበት በወቅቱ የድርጅቱ ሥራ አስኪጅ በነበሩት በመምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልና በሳተላይት ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ኤራን አማካኝነት ከተፈረመ በኋላ የቴሌቪዥኑን ሎጎና አጫጫር ክሊፖችን በማሠራጨት የሙከራ ሥርጭቱን ጀመረ፡፡ አጠቃላይ ይዘቱን በተመለከተ አንድ አጠቃላይ የመርሐ ግብር አዘጋጅ ኮሚቴ፣ የኤዲቶሪያል ኮሚቴ፣ የሌሎች ሠራተኞች ቅጥርም ተፈጸመ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነውን ይህ የቴሌቭዥን ሥርጭት ማስተላለፍን በተመለከተ ለዓመታት ጥናትና ቅድመ ዝግጅት ሲከናወንለት የቆየው የሙከራ ሥርጭት መርሐ ግብር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የድርጅቱ የቦርድ አባላትና የሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኀላፊዎች በተገኙበት ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓ/ም ባርከው ከፍተውታል፡፡
በወቅቱ ብፁዕ ወቅዱስነታቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ባስተላለፉት ቃለ በረከት፡- “በቅድሚያ የመልካም ስጦታ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በእርሱ ቅዱስ ፈቃድ ቃሉን በዚህ መገናኛ ብዙኃን /ሚዲያ/ በምልአት ለመስማት ስላበቃን ክብርና ምስጋና፣ አምልኮትና ስግደት ለእርሱ ይሁን ካሉ በኋላ ለረጅም ጊዜ በጒጉት ስትጠባበቁት የነበረው የታላቋ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ እግዚአብሔር ለፍጡራን በሰጠው አእምሮ በተሠራ በዚህ መገናኛ ብዙኀን ለመስማት በመብቃታችን እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡
ታላቋና ገናናዋ ቤተ ክርስቲያናችን ከብዙ ተጋድሎ ጋር ለረጅም ዘመናት ጠብቃ ያቆየችውን ነገረ ሃይማኖት ዛሬም ባለበት ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ለማስፋፋት የዘመኑ መሣሪያ መጠቀም ተገቢ እንደሆነ ጥርጥር የለውም@ በአሁኑ ጊዜም ቤተ ክርስቲያናችን ያልደረሰችበት ክፍለ ዓለም የለምና በየትኛውም ክፍለ ዓለም የሚገኙ ልጆችዋ ሁሉ በእርስዋ በኩል በቀጥታ የሚተላለፈውን የእግዚአብሔር ቃል በምልአት ያዳምጡና ይሰሙ ዘንድ እነሆ በአፍሪቃ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በሰሜን አሜሪካና በላቲን አሜሪካ ያሉትን ምእመናን ሁሉ ሊያዳርስ የሚችል ”የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት እውን አድርጋለች” በማለት በወቅቱ ለተገኙትና በሚድያው ለሚከታተሉት ሁሉ የቴሌቪዥን ሥርጭቱ በይፋ መጀመሩን አብሥረዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በመጨረሻ ባስተላለፉት መልእክታቸው ‹‹ይህ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሀብትና ንብረት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንዋ ልዕልና መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ምእመናን ሁሉ ድጋፋቸውን በመስጠት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድጉት፣ ሊንከባከቡትና እንደ ዐይን ብሌናቸው ሊጠብቁት ይገባል፣ ጣቢያው የምእመናን ድጋፍ ከታከለበት ሃያ አራት ሰዓት በሙሉ መጠቀም የሚያስችል ቻናል እንደሆነ ገልጸው በዚህ መገናኛ ብዙኃን ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን፣ ሥርዐተ አምልኮን፣ ደማቁ የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክን ስትማሩ ኢትዮጵያንም እዚያው ታገኟታላችሁ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታ ናቸውና፡፡ “በአንድ ወንጭፍ…” እንደሚባለው ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስትማሩ ስለ ኢትዮጵያም የግድ ትማራላችሁ ማለት ነው” በማለት ቃለ በረከታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ወቅት ያስተላፉት ቃለ በረከት ሙሉ ቃል የቅዱስነታቸው የሀገር ውስጥ የሥራ ክንውን በተዘገበበት በገጽ … ያገኙታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚድያ ከሰኔ 16 ቀን 2008ዓ/ም ጀምሮ ሲያከናውነው የቆየውን የሙከራ ጊዜ ስርጭት አብቅቶ ከታኅሣሥ 29 ቀን 2009 ዓ/ም ጀምሮ መደበኛ የስርጭት መርሐ ግብርን ማስተላለፍ ጀመረ፡፡
ይኸው መደበኛውን የቴሌቭዥን ስርጭት መርሐ ግብር ታኅሣሥ 27 ቀን 2009 ዓ/ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሄደው ሥነ ሥርዐት ባርከው የከፈቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሲሆኑ፤ በወቅቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የድርጅቱ የቦርድ አባላትና መላ ሠራተኞች የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኀላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አመራሮች፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና አበ ምኔቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቴሌቭዥኑ በበዓለ ልደት ዕለት መደበኛ ፕሮግራሙን በይፋ መጀመሩን አስመልክተው ባሰሙት አባታዊ ቃለ በረከት “በቅድሚያ ለቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ ላለው ለመደበኛ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ማስጀመሪያ ቀን ቸሩ ፈጣሪ እግዚአብሔር እንኳን በሰላም አደረሰን፡፡ ይህንን ፕሮግራም ለማስጀመር ካሰብን የቆየን ቢሆንም ከሥራው ውሰብስብ ባሕርይ አኳያ እስከ አሁን ጠብቀናል፡፡ ሥራው አሁን ለደረሰበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ የቦርድ አባላትና ባለሞያዎች ብዙ ደክመውበታል፣ በዚህም ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል “ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም መልክ ሙሉ ናት፡፡ ሊቃውንቶቿ፣ ካህናቶቿ፣ ምእመናኖቿ እጅግ በርካታ ናቸው፣ በዚያው ላይ ዕውቀቱ፣ ሀብቱ፣ ምሥጢሩ፣ ሥልጣኑ ሰፊ ነው፤ ገንዘቡና ሀብቱ የኛ ሆኖ ሳለ በሩ ክፍት ሆኖ ስላገኙት እስከ አሁን ግለሰቦች ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ቤተ ክርስቲያን በራስዋ ሀብት መጠቀም መቻል አለባት፣ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሑሩ ወመሐሩ እያለች ቆይታለች፡፡ ይህን ስታደርግ የቆየችው ግን አባቶቻችን በባዶ እግራቸው ጋራው ሸንተረሩን፣ ዐቀበት ቊልቊለቱን በበጋ በሐሩር እየተጠበሱ፣ በክረምት በዝናብ እየበሰበሱ በከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡ አሁን ግን ጊዜው ተቀያይሯል ጒዞው ሁሉ በምድር መሆኑ ቀርቶ በአየር ሆኗል፡፡
አሁን የጀመርነው የቴሌቭዥን መርሐ ግብርም የሚተላለፈው በአየር ስለሆነ ሙሉ ዓለምን በአንዴ ማዳረስ ይችላል፡፡ በመሆኑም በዚህ መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ትውፊትን፣ ታሪክን ወዘተ በመላ ዓለም ላሉ ምእመናኖቻችን ማስተማር፣ ማሳወቅ እንችላለን፡፡ ይህ እንዲሆን ከተፈለገ ግን የዚህች ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆንን ሁሉ የገንዘብና የዕውቀት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይ ባለሀብት ልጆቻችን የጐላ ተሳትፎ ያደርጋሉ የሚል እምነት አለን ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ጊዜው በእድገት ለውጥ እየሮጠ መሆኑን ቅዱስነታቸው አውስተው በዚህ ፈጣን የጊዜ ሩጫ ሁላችንም ለልማትና ለሰላም መፋጠን ይኖርብናል፡፡ በዚህ የቴሌቭዥን ሥራ የተሰለፋችሁ ባለሞያዎችም ሥራው ጥንቃቄና ጽናት የሚጠይቅ መሆኑን ዐውቃችሁ ሥራችሁን በትጋት፣ በሥነ ሥርዐትና በሕጉ መሠረት ማከናወን አለባችሁ በማለት አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
ከቅዱስነታቸው ቃለ በረከት ቀደም ሲል ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በወቅቱ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ፣ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኀላፊና የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አጭር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በዚህ ጊዜ ባሰሙት ቃል በቅድሚያ እንኳን ለዚህ መደበኛ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር መጀመር አደረሳችሁ ካሉ በኋላ” ተነግሮ፣ ተጽፎ፣ የማያልቅ ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሐዋርያዊትና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለም የሌሉ በርካታ ሀብቶችና ቅርሶች ባለቤት ናት፣ ያሬዳዊ ዜማ ከእነዚህ ሀብቶቻችን አንዱ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም አሁን የደረስንበት ደረጃ ለማየት የተመኙ ብዙ ነበሩ ነገር ግን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብዙ ነቢያት፣ ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኙ አላዩም@ እናንተ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኙ አልሰሙም እንዳለው አልቻሉም፡፡ እኛ ግን በቅዱስነትዎ ዘመን ይህን ለማየት በመቻላችን ዕድለኞች ነን፣ የዘንድሮን የልደት በዓል የምናከብረው የሚዲያ ልደትንም ጨምረን ነው” ብለዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በመጨረሻም ሥራው እዚህ የደረሰው ከብዙ ውጣ ውረድና ሌት ተቀን ልፋት በኋላ መሆኑን አውስተው ከአሁን በኋላ ላለው ሥራ ኀላፊነቱ በሁሉም የቤተ ክርስቲያንዋ አገልጋዮች ጫንቃ ላይ ያረፈ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ የቴሌቭዥን ስርጭት መደበኛ መርሐ ግብር መክፈቻ ሥነ ሥርዐት በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቭዥን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበሩት መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ድርጅቱ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት የሚገልጽ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
በዚህ መልክ የተጀመረው የቤተ ክርስቲያናችን ታሪካዊ ሚድያ በቅዱስነታቸው ጸሎትና ልዩ ክትትል እስካሁን ድረስ የአገልግሎት ዘርፉን በማስፋት ቤተ ክርስቲያናችንን በዓለም ሁሉ እንድትሰበክ እያደረገ ይገኛል፡፡

2. መጽሐፈ ቅዳሴ በኦሮምኛ ቋንቋ መተርጐምን በተመለከተ፣

በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የትርጒም ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲተረጐም የቆየው የኦሮምኛ መጽሐፈ ቅዳሴ የትርጒም ሥራው ተጠናቅቆ መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መጽሐፉን መርቀው አገልግሎት እንዲጀምር አድርገዋል፡፡
በምርቃት መርሐ ግብሩም ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያናችን ለሥርዐተ አምልኮት የምትገለገልባቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን በተቻለ መጠን በሁሉም የሀገራችን ብሎም የዓለማችን ቋንቋዎች ተተርጒሞ ለሕዝባችን እንዲዳረስና ሁሉም በሚሰማው ቋንቋ እንዲገለገል ማድረግ ሐዋርያዊ ግዴታ መሆኑን አስረድተው ይህ የኦሮምኛ መጽሐፈ ቅዳሴም በሊቃውንት በጥንቃቄ ተተርጒሞ ለዚህ በመብቃቱ እንኳን ደስ አለን ካሉ በኋላ መጽሐፉ ለሁሉም እንዲዳረስና አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ረገድም ካህናት የበኩላቸው እንዲወጡ ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ለዓመታት የደከመችበትን የአፋን ኦሮሞ መጽሐፈ ቅዳሴ ትርጒምና ኅትመት በዛሬው ዕለት እውን ሆኖ ለመመረቅ በመብቃታችን ከሁሉ አስቀድመን ሥራን አስጀምሮ የሚያስፈጽም እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው ‹‹ወተመልኡ ኵሎሙ መንፈሰ ኀይል ወአኀዙ ይንብቡ ዘዘ ዚኣሆሙ በነገረ ኲሉ በሓውርት በከመ ወሀቦሙ መንፈስ ቅዱስ ይንብቡ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስ ቀዱስ እንዲናገሩ በሰጣቸው ችሎታ መጠንም በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ›› (የሐ.ሥራ 2÷4)
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በኃምሳኛው ዕለት ባረገ በዐሥረኛው ቀን፤
• በሃይማኖት ፍጹማን፤
• በማስተማር ጥቡዓን፤
• በዕውቀት ማእምራን የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ ለሐዋርያት ወረደላቸው፣ የዓለምን ቋንቋ ሁሉ እንዲናገሩም ዕውቀት ሰጣቸው ብለዋል፡፡

ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት መሠረት የሆነው ቅዱስ መጽሐፍ በአሁኑ ዘመን ኅብረተሰቡ በቀላሉ ሊረዳው በሚያስችል አኳኋን በተብራራ መልኩ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጒሞና ተባዝቶ በሁሉም የዓለም አቅጣጫ ለሰው ልጅ ሁሉ እንዲዳረስ ተደርጓል ፡፡
የክርስትናው ሃይማኖት መገልገያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስትናው እምነት መስፋፋትና እድገት ያለው አስተዋፅኦ መተኪያ የለውም፤
ቅድመ ልደተ ክርስቶስም ሆነ ድኅረ ልደተ ክርስቶስ የተነሡት መንፈሳውያን አባቶቻችን በየጊዜው ዘመኑ የፈቀደላቸውን ያህል ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበትን ተግባር እየፈጸሙ አልፈዋል፤ እኛም ቀደምት አባቶታችን ባቆዩልን አሠራር መሠረት የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑትን ምእመናን ለመጠበቅና ለማስተማር በአባቶቻችን ቦታ ተተክተናል ፡፡
በዚህ በተሰየምንበት ኀላፊነት የቤተ ክርስቲያን ዓላማን ከግብ ለማድረስና ሕዝባችንም የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሽ እንዲሆን ለማድረግ፣ በቅዱስ መጽሐፍ እንደታዘዘው ምእመናንን በለመለመው የሃይማኖት መስክ ላይ ለማሠማራት፣ ከእግዚአብሔርም ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ፣ ትልቁ ተልእኮአችንን ለመወጣት፣ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን ፡፡ ካሉ በኋላ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩና የተለያየ ባህል ያላቸው ልጆች አሏት፤ እነዚህ ልጆቻችን በቋንቋቸው አምላካቸውን ማመስገን ይችሉ ዘንድ ማስተማርና ለእግዚአብሔር መንግሥት ማዘጋጀት ተቀዳሚ የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው ፡፡
በመሆኑም የኦሮሞ ብሔረሰብ ምእመናን ልጆቻችን በአሁኑ ወቅት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አምልኮአቸውን መፈጸም እንዲችሉ፣ በቋንቋቸውም እንዲያስቀድሱና እግዚአብሔርንም እንዲያመሰግኑ ታስቦ በሦስት ዐምድ ተከፋፍሎ የተተረጐመውና በዛሬው ዕለት ለምረቃ የቀረበው ዐሥራ አራቱ የአፋን ኦሮሞ መጽሐፈ ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉን ዐቀፍና ሁሉን በእኩል የምታገለግል መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው፤ ብለዋል፡፡
ለብዙ ጊዜ ሲደከምበት ቆይቶ አሁን በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ታትሞ በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው መጽሐፈ ቅዳሴ የክልሉን ምእመናን መንፈሳዊ ፍላጎት ያሟላ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስኬት ስለሆነ መላው የኦሮሞ ክልል ምእመናን ልጆቻችን እንኳን ደስ አላችሁ እንላቸዋለን፤ ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በዚሁ የመጽሐፈ ቅዳሴ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ያስተላለፉት ታሪካዊ እና አባታዊ መልዕክት ሙሉ ቃል በገጽ … ላይ ይመልከቱ፡፡

3. የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ መመዝገብን በተመለከተ፣

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 ቀን የሚከበረው የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ፓትርያርክነት በተባበሩት መንግሥታት የማይዳሰስ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ኅዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ ለመሆን በቅቷል፡፡
በዓለ መስቀልን በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ ብዙ ጥረትና ጥረት ድካም ያደረጉት አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤቴ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትም ይህንኑ ጥረት አጠናክረው በማስቀጠል አስቀድሞ የተጀመረው በዓለ መስቀልን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በቅርስነት የማስመዝገብ ጥረት ፍጻሜ አግኝቶ የመስቀል ደመራ በዓል ኅዳር ወር 2006 ዓ.ም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በቅርስነት ተመዝግቦ ዕውቅና እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡
የመስቀል ክብረ በዓል ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ ተዳሳሽ ዓለም ዐቀፍ ቅርሶች (ታንጀብል) በተጨማሪ ዐሥረኛውና የመጀመሪያው የማይዳሰስና የማይጨበጥ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርስ በመሆን ሊመዘገብ ችሏል፡፡
የመስቀል ክብረ በዓል በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መመዝገብ የመንግሥት አካላትና ሌሎች ተቋማት ለቅርሱ የሚሰጡት ትኵረት ከቀድሞው የተሻለ እንዲሆን ከማስቻሉም በተጨማሪ ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና ጥበቃና እንክብካቤ ከማግኘቱ ጋር በተያያዘ የቱሪስቶች ቊጥርንም ለመጨመር ይረዳል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ዕውቅና በማግኘቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ አጥኚዎችና ተመራማሪዎች አገሪቷን እንዲጎበኙ በማድረግ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሀገራችንንና ሕዝባችንን በመጥቀም ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ቅርሱ መንፈሳዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆና የማንነት መገለጫ ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚረዳ እሙን ነው፡፡

4. የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገብን በተመለከተ፣

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መመሪያ ሰጭነት እና የቅርብ ክትትል ቤተ ክርስቲያናችን፣በዓለም ሁሉ የሚገኙ ምሁራን፣ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ባደረጉት የጋራ እንቅስቃሴ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና የባህል ድርጅት አስፈላጊውን ጥናት ካደረገ በኋላ የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል አከባበራችን የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ሆኖአል፡፡
በመሆኑም ምዝገባው መከናወኑን በተሰማበት ታኅሣሥ 2 ቀን 2012 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ካህናት፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና ምእመናን የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ የማያቋርጥ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው በዓለ ጥምቀት በዩኒስኮ መመዝገቡ የቤተ ክርስቲያናችን፣ የሀገራችንና የሕዝባችን ስም በዓለም ደምቆና ጎልቶ እንዲታወቅ ያደርጋል፣ከዚህም ጋር ሀገራችን በቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን ያግዛል በማለት አብራርተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በሚመለከታቸው ሕጋዊ አካላት የቀረበለትን ጥያቄ በአዎንታ በመቀበል በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ስም በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲመዘገብ የወሰነውን የዩኔስኮ ጉባኤም በቤተ ክርስቲያናችን ስም አመስግነዋል፡፡
በመጨረሻም በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ፍጹም የሆነ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመከባበር በዓል ሆኖ ሕዝባችንን አንድ አድርጎና አስተሳስሮ የቆየ የአንድነታችን ማኅተም ስለሆነ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ዕሴቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጥብቅ አደራችንን በአጽንዖት እናስተላልፋለን፡፡ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያስተላፉትን አባታዊ የደስታ መግለጫ መልእክት ሙሉ ቃል በገጽ … ይመልከቱ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዓለ ጥምቀት ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና አግኝቶ በዩኔስኮ በመመዝገቡ ምክንያት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ራብዓይ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ሳድሳይ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እንጂነር ታከለ ኡማ፣ ልዩ ልዩ የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አምባሳደሮችና ታዳሚዎች በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ ሕዝበ ክርስቲያን በተገኙበት ታኅሣሥ 12 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በዝማሬና በቅኔ በታላቅ ሥነ ሥርዐት ተከብሮአል፡፡
በዚሁ ወቅት ቅዱስነታቸው ከፍተኛ ተጋባዥ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የልዩ ልዩ ሃይማኖት መሪዎች በተገኙበት በዚሁ መርሐ ግብር ላይ የደስታ መግለጫ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው፦
ሁሉም እንደሚያውቀው በዓለ ጥምቀትም ሆነ ሌሎች ክርስቲያናዊ በዓላት በሌላው ክፍለ ዓለም መከበራቸው አልቀረም፤ ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን አከባበር ከሌሎች ተለይቶ የዓለምን ሕዝብ ትኵረት ለመሳብ የቻለው ከላይ በተገለጸው የአበው ጽንዐ ሃይማኖትና ጥልቅ የሆነ ፍቅረ እግዚአብሔር የተነሣ በተሠራው ሥራ የሥነ በዓሉ ውበትና ድምቀት ከሌላው ልቆና በልጦ ስለተገኘ ነው፡፡ ብለዋል፡፡ አያይዘውም በየጊዜው የተነሣ ትውልድ የአባቶቹን ሃይማኖትና ባህል ለመጠበቅ የሚያደርገው ጠንካራ እንቅስቃሴ ድምር ውጤት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር “የኢትዮጵያ ሰዎች በፊቴ ይሰግዳሉ” ብሎ የገባልን ቃል ኪዳን በምንም በምን የማይታጠፍ በመሆኑ በእነዚህ ምክንያቶች የተገኘ ልዩ ዕድል ነው፤ በዚህም እግዚአብሔር አምላካችንን ሳናቋርጥ ዘወትር እናመሰግነዋለን፣ እናከብረዋለን፣ እንታዘዘውማለን፤ ብለዋል፡፡

ታላቁ የዓለም ድርጅት ዩኔስኮ፣ በዋናነት ደግሞ እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ዕድል ሲያቀዳጀን በዓለ ጥምቀቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ባህሉን፣ ማኅበራዊ መስተጋብሩንና ተወዳጅነቱን ጠብቀን በታማኝነት እንድናስቀጥል ነው፡፡ ያሉት ቅዱስ ፓትረያርኩ ይህን የመሰለ ግዙፍና መላ ሀገርን ያካለለ፣ እንደዚሁም ሁሉንም የማኅበረ ሰብ ክፍል ያቀፈ፣ ለሕዝቦች አንድነትና መከባበር መጐልበት የላቀ ሚና ያለው መንፈሳዊ ትዕይንት ከነ ሙሉ ዕሴቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል ከሁሉም በላይ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላምን ለማስፈን ደግሞ የሕዝቦች አንድነትና እኩልነት ዋስትና እንዲኖረው ማድረግ ከሁላችን ኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፤ ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ከፍተኛ ጥረት ያደረጋችሁ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስና ባለ ድርሻ አካላት፣ የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ደማቅና ውብ፣ ሳቢና ማራኪ ሆኖ እንዲከበር እየጣራችሁ ያላችሁ ወጣት ልጆቻችንና መላው ሕዝበ ክርስቲያን በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤ በማለት መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡ የቅዱነታቸው መልእክት ሙሉ ቃል በገጽ … መመልከት ይቻላል፡፡

5. ለ18 ዓመታት ተሰርቆ የነበረው የቅዱስ ያሬድ መስቀል መመለስን በተመለከተ፣

ከታሪካዊው ገዳም ከጣና ቂርቆስ ተሰርቆ ለ18 ዓመታት በስደት የቆየውና በ2001 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመንበረ ፓትርያርክ ሙዚየም በጊዜያዊነት ተቀምጦ የነበረው ታሪካዊው የቅዱስ ያሬድ መጾር መስቀል ኅዳር 14 ቀን 2006 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በክብር ወደ ቦታው እንዲመለሰ አድርገዋል፡፡
በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ በተደረገበት ወቅት የተፈጠረውን አለመረጋጋት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ሰርጎ ገብ ታጣቂዎች መነኮሳቱን አፍነው የወሰዱትን የመጾር መስቀል ከ18 ዓመታት በኋላ ኅዳር 14 ቀን 2006 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሺሕ በሚቈጠሩ የባሕር ዳርና የአከባቢዋ ምእመናን በተገኙበት በክብር ወደ ጣና ቂርቆስ ገዳም ተመልሷል፡፡
ቅዱስነታቸው ታሪካዊ መስቀሉን ለገዳሙ አበምኔት ካስረከቡ በኋላ እንደገለጹት ገዳሙ በርካታ መጻሕፍትና ልዩ ልዩ ቅርሶችን የያዘ ስለሆነ ብርቱ ጥበቃና እንክብካቤ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ ጣና ቂርቆስ በአመሠራረቱ ጥንታዊና ዕድሜ ጠገብ ስለሆነ በጣና ሐይቅ ዙሪያ ላሉት ገዳማት እንደ አባት በመሆኑ በገዳሙ ዙሪያ የምትገኙ ምእመናን ቅርሶቹን እንድትጠብቁና ለትውልድ እንድታስተላልፉ አደራ አለባችሁ ብለዋል፡፡ በልዩ ልዩ ሀገሮች የሚገኙ መንፈሳዊ ቅርሶቻችን ለማስመለስ የተጀመረውን ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥም ቅርሶቻችንን ወደ ነበሩበት ስፍራ ለማስመለስ በምናደርገው ጥረት እግዚአብሔር ይረዳናል ብለዋል፡፡
ይህ የቅዱስ ያሬድ የመፆር መስቀል በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ከሌሎች 14 ቅርሶች ጋር ከገዳሙ ሲወሰድ ለ5 ዓመታት በአሜሪካ፣ ለ13 ዓመታት ደግሞ በፈረንሳይ ከቆየ በኋላ በ5ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከፍተኛ ጥረት በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመንበረ ፓትርያርክ ቅርስ ጥበቃ ሙዚየም ለጊዜው እንዲቆይ ተደርጎ ከቆየ በኋላ በ2006 ዓ.ም በጥቅምቱ የሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ወደ ገዳሙ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በወቅቱ በጣና ቂርቆስ ገዳም ለገዳሙ ቅርስ መጠበቅያ ለሚገነባው ሙዜየም የመሠረት ደንጊያ ያስቀመጡ ሲሆን ለገዳሙ አባቶችም በቤተ ክርስቲያኗ ስም የ30 ሺሕ ብር ርዳታ ሰጥተዋል፡፡

6. ከአፍሪካ ቀዳሚነት ያላቸውን ግዙፉን መስቀሎችን በተመለከተ፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዘመነ ፓትርያርክናቸው እስካሁን ድረስ በትልቅነታቸው በአፍሪካ ደረጃ የሚጠቀሱትን ትልልቅ መስቀሎች መስከረም 17 ቀን 2009 ዓ.ም እና መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም በዓዲ ግራትና በመቐለ ሀገረ ስብከት ተገኝተው ባርከው መርቀዋል፡፡
• የዓዲ ግራት ሀገረ ስብከት መስቀልን በተመለከለተ፤
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በብሔራዊ ደረጃ የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓል መስከረም 16 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ በከፍተኛ መንፈሳዊ ድምቀት ካከበሩ በኋላ ከምሥራቃዊ ዞን ዓዲ ግራት ሀገረ ስብከትና ከክልል ትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትንና የሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኀላፊዎችን በማስከተል መስከረም 17 ቀን 2009 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በክልል ደረጃ በሚከበርበት በዓዲ ግራት ሀገረ ስብከት ሕዝቡን ለመባረክ በተገኙበት ጊዜ 22 ሜትር በ14 ሜትር የሆነ ትልቅ መስቀል በቃን ዳዕሮ ተራራ ላይ ተገኝተው ባርከዋል፡፡
ዓዲ ግራት ከአዲስ አበባ 898 ኪ.ሜ. የምትርቅ ስትሆን ከመቐለ ደግሞ 120 ኪሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ አከባቢው የክርስትና ሃይማኖት መሠረት እንደመሆኑ መጠን ክርስትና ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ያለ ማቋረጥ መስቀል የሚከበርበት፣ የሚዘከርበትና በየዓመቱም በከፍተኛ መንፈሳዊ ድምቀት የሚከበርበት ቦታ ነው፡፡ ከመንፈሳዊ ይትበሃሉ ጎን ለጎንም በዓሉ በፈጠራቸው ባህላዊና ማኅበራዊ መስተጋብር ደምቆ ከሚከበርበት የሀገራችን ክፍል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
በመሆኑም በአካባቢው በልዩ ሁኔታ ለዘመናት ሲከበር ለኖረው የመስቀል ደመራ በዓል መገለጫ ይሆን ዘንድ የከተማዋ ሕዝብ በአጠቃላይና የሚመለከታቸው አካላት መክረውበት የበዓሉን ጥንታዊነትና በሕዝቡ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር መኖሩን የሚያሳይ ትእምርተ መስቀል በከተማዋ ጫፍ በሚገኘው ተራራ ላይ ቁመቱ 22 ሜትር ወርዱ 14 ሜትር የሆነ በአፍሪካ በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነ መስቀል ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አሠርተው ካቆሙ በኋላ ይህንን በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው መስቀል መባረክ ያለበት በቅዱስ ፓትርያርኩ ነውና ይጠሩልን በማለት ሕዝቡ መጠየቁን ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ ክልል ቢሮዎች ለቅዱስነታቸው የጥሪ ደብዳቤ ማቅረባቸውን ተከትሎ ቅዱስነታቸው የሕዝቡን ጥሪ አክብረው በቦታው ተገኝተዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በዚህ ታሪካዊ ቦታ ሲደርሱ ከፌደራል ሚኒስትሮች እስከ ዞኑ አስተዳዳሪዎች ብዛት ያላቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በብዙ ሽሕ የሚቈጠሩ ምእመናንና ሊቃውንት በተገኙበት መስቀሉን ባርከዋል፤ በበዓሉ ለተገኙት ሕዝበ ክርስቲያንም ትምህርተ ወንጌልን፣ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬን አስተላልፈዋል፡፡
በዚህ በዓል ብፁዕ ወቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው ላይ በዋናነት ካስተላለፉት መልእክት፡- “መስቀል በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት የዕርቅ፣ የምሕረት እና የሰላም አብሣሪ ነው፤ መስቀልን ስናከብር የተደረገልንን ዘለዓለማዊ ይቅርታ፣ አምላካዊ ምሕረት እና ቸርነት በማሰብ መሆን አለበት፤ ስለሆነም መስቀል አከብራለሁ የሚል ክርስቲያን ሁሉ ቅድሚያ የሰላም አምባሳደር መሆን ይኖርበታል፤ መስቀል ሰላም ነውና ሰላማዊ መሆን ይጠበቅበታል፤ ሰላም ለሁሉም የሚጠቅም አምላካዊ ጸጋ ሲሆን ሁከት እና ብጥብጥ ደግሞ ሁሉንም የሚጎዳ የፍጡራን ጠላት ነው፤ ስለሆነም ሁላችንም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሰላማችንን መጠበቅ እንዲሁም ማስጠበቅ ይኖርብናል በማለት በአሀገራችን በአንዳንድ አካባቢ እየታዩ ያሉትን ሁከቶች በአፋጣኝ እንዲታረሙ አባታዊ ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡
በብዙ ድካም እና ወጪ የተገነባው ትልቁ መስቀልም የሃይማኖት እና የሀገር ክብር የሚገልጽ የአማኝነት ምልክት መሆኑን በስፋት ገልጸው አካባቢውን የቱሪስት መስሕብ በማድረግ ከተማዋ የቱሪዝም ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ካስረዱ በኋላ ይህ መስቀል በመሥራታችሁ በመንፈሳዊም ሆነ በማኅበራዊም ተጠቃሚዎች ስለ ሆናችሁ እና በተደጋጋሚ እንደተገለጸውም በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነ ታሪካዊ ሥራ በመሥራታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ሕዝቡን ባርከው በጸሎት በዓሉን ዘግተዋል፡፡
• የመቐለ ሀገረ ስብከት መስቀልን በተመለከተ፤
የዓዲ ግራት መስቀል በተመረቀ በዓመቱ በመቐለ ከተማ 52 ሜትር ቁመት ያለው በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነ መስቀል በጮምዓ ተራራ ተሠርቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያውና የየድርጅቱ ሥራ አስኪያጆች፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የአጐራባች አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆችና የሥራ ኀላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም ባርከው መርቀዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በምረቃው ሥነ ሥርዐት ላይ ለተገኙ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት አባታዊ ንግግር የሰላምና የአንድነት መገኛ የሆነው መስቀል በተለያዩ የዓለማችን ክፍል በተራራዎች ላይ ተተክለው እንደሚገኙ አስታውሰው በኢትዮጵያ ደረጃ ቀደም ሲል በዓዲ ግራት አሁን ደግሞ በመቐለ ተራራዎች ላይ የተተከሉት ሁለቱ መስቀሎች ሕዝባችን በሰላም፣ በስምምነትና በአንድነት ለመኖር ያለውን ቊርጠኛ አቋምና ለእምነቱ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ነው በማለት ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም የሰላም፣ የዕርቅ፣ የስምምነትና የአንድነት አብሣሪ የሆነውን መስቀል በከተማዋ ጫፍ ላይ በመትከል የመስቀሉን አዳኝነት ለመጪው ትውልድ ለማስተዋወቅ ያደረጋችሁት ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው መጪው ዘመን የበረከት፣ የዕርቅ፣ የስምምነት እና የአንድነት ዘመን እንዲሆን በአዲሱ ዓመት በመስቀል በዓል ዋዜማ በጮምዓ ተራራ ላይ በዛሬው ዕለት የመረቅነው ቁመቱ 52 ሜትር የሆነው ይህ መስቀል ትልቅ የበረከት ኀይል ነው፤ በመሆኑም አዲሱ ዘመን የሰላም፣ የጤና፣ የዕርቅና የስምምነት ዘመን እንዲሆንልን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በወቅቱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመቐለ ጮምዓ ተራራ ላይ ለመስቀል ተከላ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ለተሳተፉ ወገኖች ሁሉ የተዘጋጀላቸውን ሽልማትና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

7. በሊቢያ የተገደሉ ሰማዕታተ ኢትዮጵያን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ያስተላፉት አባታዊ መልእክት፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሊብያ ሀገር በንጹሓን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን የግፍ ጭፍጨፋ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በይፋ አውግዘዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በሰዓቱ ተይዞ የነበረውን የውጭ ሐዋርያዊ ጒዞ በመሠረዝ እና ቅዱስ ሲኖዶስ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ ጥሪ በማስተላለፍ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተገቢውን መግለጫ እንዲያወጣ የመሪነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስም ይህንን አሠቃቂ ግድያ አስመልክቶ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግና መግለጫ በማውጣት ሁሉም መገናኛ ብዙኃን ውግዘቱን እንዲያስተላልፉ አድርጓል፡፡ በዚሁ ጊዜ ቅዱስነታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት የሚከተሉትን ነጥቦች ትኵረት በመስጠት አስተላልፈዋል፡፡
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜዲትራንያን ባሕር ዳርቻ አካባቢ አይኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሓን ወገኖቻችን ላይ አሠቃቂ ግድያ እንደተፈጸመባቸው መዘገቡን ያስታወሱ ቅዱስ ፓትርያርኩ ዘገባው ከምኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሓን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኝ ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብኣዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡
አሠቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሓን ወጣቶች ዜግነትና ማንነት ግልጽና አስተማማኝ የሆነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በበርካታ የዓለም ዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው የዚህ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ እንደሚገኙም አስታውሰዋል፡፡
የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ኀላፊነት በማይሰማቸውና በእነሱ ላይ ሊደረግ በማይፈቅዱ ምንም ዐይነት ሰብኣዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ይህንን አሠቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፣ አጥብቃም ታወግዛለች፤ ብለዋል፡፡
ስለዚህ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ የምናደርግ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ሁኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ መልእክታችንን ልናስተላልፍ እንወዳለን ያሉት ቅዱስነታቸው፤ በንጹሓን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሁሉ እንደቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሣራ እንጂ ምንም ዐይነት ትርፍ የማያገኙ መሆናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን፤ ብለዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ቅዱስነታቸው ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ በግፍ ለተገደሉት 30 ኢትዮጵያውያን የሰማዕትነት ቅድስና እንድትሰጥ የመሪነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ አይኤስ በተባለው አሸባሪ ቡድን በግፍ ስለተገደሉት ኢትዮጵያውያን በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ብፁዕ ወቅዱስነታቸው በመላ ዓለም ለሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያንና በመስቀል አደባባይ ለተገኘው ሕዝብ ባስተላለፉት መልእክት፤ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ራሱን አይ ኤስ በማለት የሚጠራው ሰብኣዊ ርኅራኄ የሌለው አሸባሪ ቡድን በወገኖቻችን ላይ ያደረሰውን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ከሰማንበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ በአምላካችን ዘንድ የወገኖቻችን ደም በከንቱ እንዳይቀር ልብን በሚሰብር ኀዘንና በጸሎት በማሰብ ላይ እንገኛለን፤ ብለዋል፡፡
ይህ በሰብኣዊ ፍጡር ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት አሳሳቢና ፍጹም ጭካኔ የተመላው በመሆኑ ከኀዘናችንና ሰማዕታቱን በጸሎት ከማሰብ በተጨማሪ ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን ስለተረዳን ስለጌታችን ስምና ስለቀናች ሃይማኖት፣ ስለ እግዚአብሔርም ፍቅር ዐላውያን በቅጣት የሚያሠቃዩትን ክርስቲያናዊ ቸል አትበሉ ተብሎ በዲድስቅልያ በተደነገገው ቀኖና መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ ልዩ ልዩ መግለጫዎች በማውጣት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልታደርግ የሚገባትን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ሥርዐት በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የሁሉም ሃይማኖቶች ተልእኮ ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን መግደል እንዳይደለ ይታወቃል ያሉት ቅዱስነታቸው ንጹሓን ዜጎችን በሃይማኖት ምክንያት በአሠቃቂ ግድያ የመግደል ወንጀል በዓለማችን መታየት ከጀመረ ሰነባብቶአል፡፡ ኢትዮያውያን ወገኖቻችንም በተለያየ ጊዜና በተለያየ አካባቢ የዚህ ዐይነቱ ግድያ ሰለባ መሆናቸው እንዳልቀረ ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር በዚህ ሰሙን በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች በሆኑት ልጆቻችን ላይ የተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ከምንም ጊዜ በላይ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ያሳዘነና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቶአል ብለዋል፡፡
የተፈጸመው አሠቃቂ ድርጊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን የገለጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ መላው የሀገራችን ሕዝቦችና የሃይማኖት ተቅዋማት እንደዚሁም መላው የዓለም መንግሥታት ይህን ድርጊት በጽኑ መቃወምና ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ካሉ በኋላ ቤተ ክርስቲያናችንም የተፈጸመውን ድርጊት ፈጽሞ ታወግዛለች ከመንግሥትና ከሕዝብ ጋር ተሰልፋም የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ታረጋግጣለች ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ማኅበረ ሰብና ከየሀገሩ መንግሥታት ጋር በመሆን የሚያካሂደውን የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎቻችን ሕይወት በአሸባሪዎች እንዳይቀጠፍ ከእስከ አሁኑ በበለጠ እንዲንቀሳቀስ አደራ እንላለን ያሉት ቅዱስነታቸው፤ ሕዝቡም ከአሁን በፊት በበጎ ታሪካችን እንደሚታወቀው በሃይማኖትና በሌላው ሁሉ ሳንለያይ ጠብቀን ያቆየነውን በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል የመኖር ዕሴት አሁንም አጥብቀን በመያዝ የጋራ ጠላት የሆነውን ግብረ ሽብር በመመከት ራሱንና ሀገሩን ከአሸባሪዎች ነቅቶ እንዲጠብቅ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት እኛም በዛሬው ዕለት በወገኖቻችን የደረሰውን አሠቃቂ ወንጀል ልባችንን ስለነካው ፈጣሪ አቤል ወዴት አለ? ብሎ የተገደለውን አቤልን እንደፈለገው ወንድሞቻችን ወዴት አሉ ብለን ሁላችንም ከመኖሪያ ቤታችን ከሥራችን ወጥተን ይህንን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ለመቃወምና ለማውገዝ ወደ አደባባይ መውጣታችን ሰውን በሚወድ በፈጣሪ ፊት የሚያስመሰግን ነው ካሉ በኋላ ‹ይህ በወገኖቻችን ላይ ደረሰውን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ከሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ተግባር የወጣ ደረቅ ወንጀል ስለሆነ፣ ልንቃወመውና ልንመክተው የምንችለው በጥልቀትና በተረጋጋ መንፈስ በመሆን በመላው ዓለም ካሉ ከፀረ ሽብረ ግብረ ኀይሎች ጋር በመተባበር ስለሆነ በትዕግሥትና በጥበብ ሆነን የሰው ልጅ ሉዓላዊ ክብር እንዳይጣስ በነጻነት ሊኖርባት በተሰጠችው ምድር የሕይወት ዋስትና እንዲኖረው ለማስቻል ሁሉም ነቅቶና ተግቶ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡ የመልእክቱን ሙሉ ቃል በ……. ገጽ ይመልከቱ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመላ አዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና አበምኔቶች፣ በርካታ ካህናትና የሟች ቤተሰቦች በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ/ም በሊቢያ በአይ ኤስ ፀረ ክርስትና ቡድን በግፍ ለተገደሉት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ጸሎተ ፍትሐት አድርገዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላፉት አባታዊ መልእክት “ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡየ ዘበሰማያት — በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ” (ማቴ. 10፥32) የሚለውን አምላካዊ ኀይለ ቃል መሠረት በማድረግ ባደረጉት አባታዊ ንግግር ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕትነት አብሯት የኖረ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ዘመናት ልጆቿ በግፍ ተገድለው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል ካሉ በኋላ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገረ ናግራን፣ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጒዲት፣ በዐሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ፣ በዐሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክፍለ ዘመን በውጭ ወራሪ ኀይሎች በርካታ የሰማዕትነት ታሪኮች በኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ተፈጽመዋል፤ ብለዋል፡፡
በየዘመናቱ ሁሉ በቤተክርስቲያናችን ላይ የተነሡ አሳዳጆችና ገዳዮች ከነታሪካቸው ሲጠፉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን በአምላኳ ጥበቃና በልጆቿ ጽናት ሰማዕታቷን አክብራ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀብትን እያደለች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች ያሉት ቅዱስነታቸው ዛሬ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጠባቡ በር ተጒዘው በደመ በግዑ በተቀደሰው ደማቸው ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት ምስክሮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእነዚህ ልጆቻችን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት የሚገባውን የሰማዕትነት ቅድስና በመስጠት ለመላው ዓለም እንደምታሳውቅ የገለጹት ፓትርያርኩ የክርስቶስ ቤተ ሰቦች የሆናችሁ ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ሳትደናገጡ አሸባሪነትን በአንድነት ሆናችሁ በማውገዝና በመከላከል የተጀመረውን ተቃውሞ ትርጒም ባለውና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ልንፈጽመው እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ሰማዕታት ማለት እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏቸው ስለ ቊርጥ ሐሳባችሁ ሰማዕትነት ይቈጠርላችኋል፡፡ የተባለላቸው ናቸው በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ “ሰማዕታት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፣ መልካም እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ የሰጡ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡” (1ኛ ጴጥሮስ 4፡19)፤
ሰማዕታት ኀላፊ ጠፊ የሆነውን የዚህን ዓለም ጣዕም ትተው ስለእግዚአብሔር መንግሥት እና ፍቅር ታማኝ ሆነው በስለትና በእሳት ፊት በጽናት የቆሙ የእምነት አርበኞች እና ለሃይማኖታቸው ታማኞች ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደማቅ ምስክሮች ናቸው፤ ስለዚህ የእነዚህ ወጣት ልጆቻችን ቤተሰቦች የሰማዕታት ቤተ ሰቦች በመሆናችሁ ልትጽናኑ ይገባል፤ ካሉ በኋላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በደሙ የመሠረታት ወልደ እግዚአብሔር የልጆቿን ነፍስ በክብር እንዲቀበል ትጸልያለች፡፡ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምንና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተ ሰቦች መጽናናትና ብርታትን ይስጥልን፤ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡ የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት ሙሉ ቃል በገጽ…. ይመልከቱ፡፡

8. ተወርሰው የነበሩ የቤተ ክርስቲያናችን ታላላቅ ሕንጻዎችንና ቤቶችን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት መልእክት፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት አመራር መሠረት በመንግሥት ሥር የነበሩት በርካታ ቤቶችና ሕንጻዎች እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ በተለይም ለብዙ ዘመናት ቤተ ክርስቲያናችን ስትደክምባቸው የቆዩትንና አልሳካ ብለው የነበሩት በመንበረ ፓትርያርኩ አጠገብ የሚገኙትን በተለምዶ ቴዎፍሎስ ሕንጻ ተብለው የሚጠሩት ታላላቆቹ መንታ ሕንጻዎችን በተመለከተ ቅዱስነታቸው የፓትርያርክነቱን ኀላፊነት ከተረከቡ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ በጽሑፍና በአካል፣ እንዲሁም በአስመላሽ ኮሚቴ በኩል ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ከዚህም ጋር የመንግሥት ቅንነት ተጨምሮበት ሁለቱ ታላላቅ ሕንጻዎችና በሥራቸው የሚገኙ ሁለት መለስተኛ ሕንጻዎች በአጠቃላይ ለቤተ ክርስቲያናችን እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡
የሁለቱ ሕንጻዎች መመለስን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ከሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር በተለይም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ጋር ያደረጓቸው በርካታ መጻጻፎችና ውይይቶች ፍሬ አፍርተው በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ልዩ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሕንጻዎቹ ሙሉ በሙሉ ሊመለሱ ችለዋል፡፡ የሕንጻዎቹን መመለስ ምክንያት በማድረግም ቅዱስነታቸው ለኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና ለባለቤታቸው ለወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው የወንጌለ ዘወርቅና የካባ ሽልማት በማበርከት ቤተ ክርስቲያናችን የተሰማትን ደስታ ገልጸዋል፡፡

9. አዳዲስ የሕንጻ ግንባታዎችን ሥራዎችን በተመለከተ፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለልማት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰኑ ቤተ ክርስቲያንን በኢኮኖሚ ሊደግፉና ሊያጠናክሩ የሚችሉ የሕንጻ ግንባታዎች እንዲካሄዱ መመሪያ ሰጥተዋል፣ የመሠረት ድንጋይም አኑረዋል፣ ግንባታቸውን ለመከታተልም ቦታው ድረስ እየተመላለሱ በቅርብ ጎብኝተዋል፤ የግንባታ ሥራዎቹን አፈጻጸምና፣ የደረሱበትን ደረጃም እየገመገሙ ተጨማሪ መመሪያ በመስጠት ግንባታቸው እንዲፋጠን አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በዋናነት በዘመናዊ መልኩ እየተሠራ ያለውን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዘመናዊና ዋና ሁለገብ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንዲሁም የግንባታ ሥራቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ በአሮጌው ቄራ በመገንባት ላይ የሚገኙት ሁለት ባለ 10 ፎቅ ሕንጻዎች፣ በባሻ ወልዴ ችሎት የሚገኘው ባለ9ፎቅ ሕንጻ፣ በድሬዳዋ የሚገኘው የገበያ ማእከል ሕንጻ ወዘተ. የቅዱስነታቸው ልማታዊ ሥራዎች ቋሚና እውነት ምስክሮች ናቸው፡፡

10. የመጽሐፈ ድጓ ኅትመትን በተመለከተ፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት መመሪያ መሠረት አንጋፋው የቅዱስ ያሬድ የጣዕመ ዜማ መጽሐፍ “መጽሐፈ ድጓ” መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ/ም በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ታትሞ አገልግሎት ላይ መዋል ይችል ዘንድ ባርከው መርቀዋል፡፡
መጽሐፈ ድጓ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት በልዩ ክብር እና ጥንቃቄ ጠብቃ ያቆየችውን እና ቤተ ክርስቲያንዋን ከሚያስከብሯት ጥንታውያን የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች መካከል አንዱና ዋናው ሲሆን በከፍተኛ ጥናት በቤተ ክርስቲያንዋ ሊቃውንት (የድጓ መምህራን ተሰብስበው) ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ ታትሞ እንዲሰራጭ ተደርጓል፤ ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልእክት በተለይም ለዜማ መምህራንና ለአድራሽ ለድጓ የአብነት ተማሪዎች ምንም ዐይነት የዋጋ ጭማሪ ሳይደረግበት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

11. የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ወደ “ዩኒቨርስቲ” ማደግና ከፓርላማ እስከ ወወክማ ተብሎ የተነገረለት ግዙፍ ሕንጻን በተመለከተ፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ መሪነት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ያስገነባውና ከግዝፈቱ የተነሣ ከፓርላማ እስከ ወወክማ ተብሎ የተነገረለትን ግዙፍ ባለ4 ፎቅ ሁለገብ ሕንጻ መርቀው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር አድርገዋል፡፡
ኮሌጁ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ባለውለታ የሆኑ ፍሬዎችን ማበርከቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ጐን ለጐን ቤተ ክርስቲያን የሥራ ክቡርነትንና የራስ አገዝ ልማትን አጠናክራ እንደ ምታስተምር የሚያረጋግጡ እንዲሁም የኮሌጁን የመማር ማስተማር ሂደት ከፍ የሚያደርጉ ሕንጻዎችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ቡራኬ እንዲመረቁ አድርገዋል፡፡
በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፤ የኮሌጁ ቦርድ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን የእንኳን ደኅና መጣችሁ እና የመክፈቻ ንግግር በኮሌጅ የበላይ ኀላፊ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ያሬዳዊ ዝማሬና ቅኔ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ቀርቧል፡፡
በዚሁ ጊዜ ቅዱስ ፓትርያርኩ የኮሌጁ ሕንጻ ለዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት ለኮሌጁ የበላይ ኀላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ በዚህ እርጅና ዘመናቸው ይህን ድንቅ ሕንጻ መሥራታቸው ከምስጋና በላይ ስጦታ ያስፈልጋቸዋል በማለት ከቅዱስ ፓትርያርኩ የእጅ መስቀል በወቅቱ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስም በተመሳሳይ የእጅ መስቀል፣ ከብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) እንዲሁም ከኮሌጁ ማኅበረሰብ እና ከተለያዩ አካላት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ከዚህ በላይ ኮሌጁ ባስገነባው ሕንጻ የተከፈተውን ቤተ መጻሕፍት ‹‹አቡነ ጢሞቴዎስ ቤተ መጻሕፍት›› ተብሎ እንዲሰየም ቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቅደዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ከፓርላማ እስከ ወወክማ ድረስ የተሠራው ሕንጻ እጅግ እንዳስገረማቸውና ይህ ደግሞ የሥራ ክቡርነትን ያመኑ ጠንክሮ መሥራትን የለመዱና የልማትን አስፈላጊነት በቃል ሳይሆን በተግባር ያስመሰከሩትን ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስን እና ለግንባታው ሥራ መሳካት አስተዋፅዖ ያበረከቱ አካላትን ሁሉ የሚያስመሰግን መሆኑን በቅዱስነታቸው ምስጋና ተችሯቸዋል፡፡ አንጋፋው የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅም ወደ ዩኒቨርስቲ ማደጉን በወቅቱ አብሥረዋል፡፡

12. የቤተ ክርስቲያን አንድነትን በተመለከተ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቤተ ክርስቲያናችን ተፈጥሮ የነበረውን መለያየት በዕርቅ ሰላም ወደአንድነት ማምጣት ቅዱስነታቸው ከሠሩአቸው እጅግ ዐበይት ተግባራት በዋናነት የሚጠቀስ በመሆኑ እዚህ ላይ ማንሣቱ አግባብ ነው፡፡ ቅዱስነታቸው ረዘም ላሉት ዓመታት የአሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሁለቱንም አባቶች ለማስታረቅ ረዘም ላሉ ጊዜያት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በመጨረሻም ጸሎታቸውንና ምኞታቸውን እግዚአብሔር አሳክቶላቸው የዕርቀ ሰላሙ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ተጠናቅቆ በዘመናቸው የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እውን እንዲሆን አድርገዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በዕርቀ ሰላሙ ስምምነት ላይ ፍጹም የሥልጣንና መሰል ጉዳዮች ሳያሳሳቸው፡- “እኛ በዘመናችን የፈጠርነውን መለያየት እኛ በዘመናችን ማረምና ወደ አንድነት ማምጣት አለብን፤ አለበለዚያ ግን ትውልዱ እንደልማድ ወይም ባህል አድርጎ ይቈጥረው እና ይህችን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ተከፍላ ትቀራለች” ከሚል ጽኑ አስተሳሰባቸው በመነሣት በአቀባበሉ መርሐ ግብር፡- ላይ ባስተላለፉት አባታዊና ታሪካዊ መልእክት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጋር “በአንድ ቀን ተቀብተን ለዚህ አገልግሎት በቅተናል፣ አሁንም ደግሞ ተጋግዘን ቤተ ክርስቲያናችንን ለማገልገል እግዚአብሔር ፈቅዶልናልና ቅዱስነትዎ እንኳን ደኅና መጡ” በማለት በፍጹም ፍቅርና ትሕትና መቀበላቸው ትውልድ ሲያስታውሰው የሚኖር የቅዱስነታቸው ወርቃማ ታሪክ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር በቅዱስነታቸው መሪነት በቅዱስ ሲኖዶስ አርቆ አሳሳቢነት ቤተ ክርስቲያናችን ከሁለትነት ወደ አንድነት ተመልሳ በመልካም ሁኔታ አገልግሎትዋን እንድታካሂድ በማድረግ ረገድ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመሪነቱን ኀላፊነት በሚገባ ተወጥተዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ ታሪካዊ ዕለት ካስተላፉት መልእክት መካከል የሚከተሉት ዋናዋና ነጥቦች ይጠቀሳሉ፡፡
ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልዉ አኀው ኀቡረ፡፡ (መዝ. 132*1) የሚለውን ኀይለ ቃል መነሻ በማድረግ መልእክታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው፤ ይህንን ታሪካዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብረ በዓል ለማክበር በዚህ ዐውደ ምሕረት የተገኛችሁ እንግዶች በሙሉ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም፤ ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ” “ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ፣ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው” ሲል ማስተማሩን አስታውሰው፥ እኛም የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታችንን የምናስተላልፈው በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ኅብረት ነው፤ ብለዋል ፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከብዙ ሺሕ ዘመናት ጀምራ በፈጣሪዋ ታምና ነቅዕ በሌለው ሁናቴ በሃይማኖቷ ጸንታ፤ በነጻነቷ ኮርታና ታፍራ ለሥራዋም የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት መሆኑን አስተምራ፤ ጸሎቷንና ልመናዋን “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” ሲል ንጉሥ ዳዊት በመሰከረላት መሠረት ዕለት በዕለት እያመሰገነችና ወደ እግዚአብሔር እየጸለየች የምትኖር ስብሐተ እግዚአብሔር በየጊዜው የማይለይባት ሀገረ እግዚአብሔር ናት፤ ብለዋል ፡፡

ከላይ ከፍ ብሎ በመግቢያችን “ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ” “ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ መልካም ነው” ሲል በተናገረው አስተምህሮ መሠረት ታማኞቹ ለመሆን ለመረጠን ፈጣሪያችን የምንመልሰው ወሮታ ቢኖር የተቀበልነውን አምላካዊ አደራ ሠርተን ጠብቀን መገኘት ነው፤ ያሉት ቅዱስነታቸው፡፡ ተከታዮቻችንንም በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ በሥርዐታችን፣ በባህላችንና በወጋችን መሠረት እንዲጸኑና እንዲሠሩ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውም በኩል ለቤተ ክርስቲያናችንና ለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህን የመረዳዳትንና በአንድነት የመኖርን መርሕ እናስተምራቸዋለን ብለን ይህንን ታሪካዊ ፍጻሜ በፍጹም ልባችን ዳር እንዲደርስ አድርገነዋል፤ ብለዋል፡፡

ሁሉም እንደሚረዳው እኛም አሜሪካ አገር በነበርንበት ወቅት የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊና ሲኖዶሳዊው አንድነታችንን ወደ ቀደመው መሥመሩ ለመመለስ ብዙ ተጒዘን እንደነበር ቅዱስነትዎ ያውቀዋል በማለት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ያደረጉትን ተደጋጋሚ ጥረት ያስታወሱት ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጠረውን ልዩነትና የአንድነት መታጣት ችግሩ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ በየቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤያት በጸሎት ያልታሰበበትና ያልተወሰነበት ጊዜ የለም፡፡ ከዚህ አኳያ የሀገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን የአንድነት ህልውና በሚፈልጉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ካህናት ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግ መቆየቱ አይዘነጋም ብለዋል፡፡

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የኤ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉት የማቀራረብና የማግባባት ሥራ ከ45 ዓመታት ወዲህ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባልታየ ሁናቴ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት መንግሥታዊ ድጋፍ ታክሎበት ችግሩ በሚፈታበት ሥፍራ በአካል ጭምር ተገኝተው በሠሩት ሥራ የቤተ ክርስቲያናችን የአንድነት ታሪክ ዋና ባለሟል ያደረጋቸው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በሠሩት መልካም ሥራ ስታመሰግናቸውና በጸሎትም ስታስባቸው ትኖራለች፤ ካሉ በኋላ ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ማለትም እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ አለው ተብሎ በመጻሕፍት እንደተጻፈው፤ እግዚአብሔር አምላካችን ቅዱስነትዎና እኔ ዕድሜ ከጤና ሰጥቶን ይህን ቀን ለማየት ስላበቃን ለእግዚአብሔር ልዩ ምስጋና ዘወትር እያቀረብን ወንድማማችነታችንንና መንፈሳዊ አባትነታችንን አጽንተን ከመኖር በስተቀር ሌላ ምን እንከፍለዋለን በማለት በዕርቀ ሰላሙ የተሰማቸውን ወደር የለሽ ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዚህ በዛሬው ቀን የቸርነት ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን በመገኘት የአንድ አባት የእግዚአብሔርና የአንዲት እናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ልጆች የሆን እኛ ዳግመኛ በፍቅር ማሰሪያነት ታስረንና ተጣምረን እግዚአብሔርን ማመስገንና ቤተ ክርስቲያናችንን ማገልገል መጀመራችን በምድር ሠራዊትና በሰማይ መላእክት ጭምር ታላቅ ደስታ እንደሆነ እምነታችን የጸና ነው፤ በዚህም እግዚአብሔርን ዕጹብ ድንቅ ብለን ከማመስገን በላይ ምን እንላለን ብለዋል፡፡

አሁንም ደጋግመን የምንለው ይህ የተቀደሰ ፍጻሜ የእርስ በእርስ መመካከርን፣ መግባባትን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታንና አንድነትን፣ የሚያረጋግጥ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ለምንመራቸውና ለምናገለግላቸው ሕዝበ ክርስቲያን በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ላለችው ለቤተ ክርስቲያናችን የሰላምና የአንድነት አስተዳደር የምንናስቀጥልበት የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላምና የፍቅር ድል የተበሠረበት ዕለት ነው፡፡ የፍቅርና የሰላም የአንድነት ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በአደባባይ የተረታበት ዕለት መሆኑንም የምንናገረው በዚሁ ዕለት ነው፤ ያሉት ቅዱስ ፓትርያርክ ከዚሁ ጋር የማይዘነጋው ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ቅዱስነትዎና እኔ በተለይ በእግዚአብሔር ተመርጠንና ተጠርተን በ3ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ በአንድ ዕለት ተቀብተን በኤጲስ ቆጶስነት መሰየማችን ነባሩ የመነሻ ታሪካችን ነው፡፡ በተቀበልነውም የመስቀል መሸከም አደራ ቤተ ክርስቲያናችንን ስናገለግል ቆይተን ለዚሁ ለታላቁ ክብር ላበቃን አምላክ በአንደበታችን ብቻ ማመስገን አይበቃንም፡፡ ለዘለቄታ ቀዋሚ፣ ለትወልድ ተሻጋሪ፣ ለሰው ሁሉ በፍቅር የሚደርስ እኛ ጀምረን መጨረሱን ለእግዚአብሔር የምንሰጥበት ታላቅ የአደራ መቀበያና መስጫ፤ እንዲሁም ፍቅረ እግዚአብሔር ከፍቅረ ቢጽ ጋር ተዋሕዶ የተከበረበት ዕለት በመሆኑ ነው በማለት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋር ያላቸውን ወንድማዊ አንድነት ከመግለጽ ጋር በአንድነት መፈጠር የተሰማቸውን ደስታ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ለመፈጸም ‹‹ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ›› ለሚለው ዘይቤ ተገዝዎች ሆነን ቤተ ክርስቲያናችንንና ተከታዮቻችንን እየመራን ሐዋርያዊ ተልእኮአችንን እንደምንፈጽም ያለንን እምነት እንገልጻለን፤ በማለት አባታዊ የደስታ መግለጫ መልእክታቸውን አጠቃልለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በወቅቱ ያስተላፉትን ታሪካዊ መልእክት ሙሉ ቃል በገጽ … ይመልከቱ፡፡

ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በተደረገው የአቀባበል መርሐ ግብር ላይ በሚሊኒየም አዳራሽ ያስተላለፉት አባታዊ መልእክት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.መ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የአቀባበል መርሐ ግብር ላይ “እምይእዜሰ ይኩን ሰላም:- ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ይሁን ሰላም ይስፈን፣ በመላይቱ ሀገራችን ሰላምና ፍቅር አንድነት ይስፋፋ” በሚል ርእስ የሚከተሉትን ነጥቦች ያካተተ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

እምይእዜሰ ይኩን ሰላም “ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ይሁን ሰላም ይስፈን“ ተብሎ የተነገረው ቃል ለሁለት ተከፍለን በነበርነው አባቶች መካከል ዕርቅ ወርዶ እውን ሆኖ ስምረት አግኝቶ ለዚህ የአንድነታችንና የደስታችን ዕለት ማብሠሪያ ቀን በመድረሳችን ከሁሉም በላይ የሰላም የአንድነት እና የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ካሉ በኋላ ያለፈው የመለያየት ጊዜ አብቅቶ ሰላም ተገኝቶ ብፁዕ ወቅዱስነትዎ እና ብፁዓን አባቶች ወደምትወዷትና ስትናፍቋት ወደነበረችው ቅድስት ሀገራችሁ በመምጣት በዚህ ሁኔታ አንድ ሁነን በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ፊት ለመቆም ያስቻለንን እግዚአብሔርን ደግመን እናመሰግነዋለን፤ ብለዋል፡፡

በዚሁ ሳምንት ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ረቡዕ ዕለት ቅዱስነታቸውን ከቦሌ ኤርፖርት ተቀብለን በቀጥታ ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሄደን ሰፊ የሆነ የአቀባበል ሥነ ሥርዐት እንደተፈጸመ የሚታወስ ነው፤ ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ዛሬ ደግሞ በክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋባዥነት ተመሳሳይ የአቀባበል በዓል ለማክበር በዚህ በሚሊንየም አዳራሽ ተሰብስበናልና አምላካችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የምትገኙና እንዲሁ በዚህ ዐቢይ ጉባኤ የተገኛችሁ ሁላችሁ ሐዋርያዊት ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ጒዞዋ በሃይማኖት መሪዎቿ መንፈሳዊ ብርታት፣ በሊቃውንቶቿ ትምህርት፣ በካህናቶቿ አገልግሎትና በምእመናን ተከታዮቿ ጽንዐ-ሃይማኖት ህልውናዋና አንድነቷ ተጠብቆ መኖሩ ሁሉም የሚያውቀው ነው፤ ብለዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ታሪኳንና ባህሏን ጠብቃ ለረዥም ዘመን ልትዘልቅ የቻለችበት ዐቢይ ምሥጢር፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በነበራቸው የማይበገር የአንድነት ጽናት አንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ይሁንና ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች አለመግባባት በመፈጠሩ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አመራር ለሁለት ተከፍሎ ቆይቶ እንደነበር የሚታወቅ ነው ካሉ በኋላ የሰላምና የአንድነት መሪና አስተማሪ ሆና ለዘመናት ሕዝቧን ስትመራ የኖረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዘመናችን ሰላምንና አንድነትን ማጣቷ መላውን የቤተ ክርስቲያን ልጆች በእጅጉ ያሳዘነና ያሳሰብ ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ እንደቆየ እንገነዘባለን፡፡
በአሁኑ ጊዜ በሁላችንም የዘወትር ጸሎትና ጥረት በፈቃደ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናችን የተገኘው አንድነትና ሰላም ቤተ ክርስቲያናችን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ለምታበረክተው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ምቹ ሁኔታ የፈጠረላት በመሆኑ ተስፋችንና ራእያችንን ሰፊ ያደርገዋል፤ ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ለዚህ የዕርቀ ሰላም ድርድር አሁን ላለንበት የሰመረ ውጤት እንድንበቃ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መላው ካህናትና ምእመናን ልጆቻችን እንዲሁም ችግራችሁ የእኛም ችግር ነው በማለት ከጐናችን በመቆም በጸሎት ስትረዱን ለነበራችሁ፣ ከዚህ እስከ ሰሜን አሜሪካ በመጓዝ ለሰላሙ ጥረት ላደረጋችሁ የሰላምና አንድነት ጉባኤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ቅድስት አገራችንን ለመምራት ከተሰየሙበት ጊዜ አንሥቶ በአገራችን እያሳዩት ካለው የሰላምና የአንድነት ጥሪና ተልእኮ ውጤት ጋር የቤተ ክርስቲያናችንንም ጉዳይ አንዱ አገራዊ ችግር አድርገው በመመልከት መለያየቱ ተወግዶ አንድነት እንዲመጣ በመምክር በማግባባትና በዕርቀ ሰላሙ ጉባኤ ላይ በመገኘት እንዲሁም ይህን የዕርቅና የአንድነት ማብሠሪያ መርሐ-ግብር እንዲዘጋጅ በመፍቀድና መመሪያ በመስጠት ጭምር ያደረጉትን አስተዋፅኦ ምንጊዜም ታሪክ የማይረሳው ሆኖ የሚኖር ተግባር በመሆኑ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በእናንተ በመላው ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ስም ከልብ በመነጨ ስሜት እናመሰግናቸዋለን በማለት የደስታ መግለጫ መልእክታቸውን አጠቃልለዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በሚሊኒየም አዳራሽ ያስተላፉትን ታሪካዊ የደስታ መግለጫ መልእክት ሙሉ ቃል በገጽ… ይመልከቱ፡፡

13. የዝዋይ ገዳም መንፈሳዊ ኮሌጅን በተመለከተ፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ኮሌጅ ደረጃ እንዲያድግና በዚያ ደረጃ የሚገባውን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያበረክት አድርገዋል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ሆኖ ለብዙ ዘመናት በካህናት ማሰልጠኛነት ብዙ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከተ ተቋም ነው፡፡ ይሁንና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ወደ ኮሌጅ ደረጃ ከፍ እንዲል ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የጥቅምት 2010 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥያቄውን በመቀበል ወደ ኮሌጅ እንዲያድግና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችም እንዲሟሉለት በማለት ወስኖ ወደ ሥራ እንዲገባ ቅዱስነታቸው የመሪነት ኀላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡

14. የቃለ ዐዋዲ ለ4ኛ ጊዜ መሻሻል፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን የሚመጥን የአስተዳደር ሥርዐት እንዲኖራት ለማድረግ የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መመሪያ የሆነው ቃለ ዐዋዲን ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል ሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩት ኮሚቴ በማቋቋም የማሻሻያ ረቂቁ በሚገባ ተስተካክሎ ከተጠናቀቀ በኋላ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡

15. ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በፓትርያርክነት መንበር ላይ ከተሠየሙበት ጊዜ ጀምሮ ባጣም የሚያሳስባቸው ዐቢይ ጉዳይ ተተኪ አበው ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ መሾምና የቤተ ክርስቲያንዋ አገልግሎት በተሟላ መልኩ እንዲቀጥል ማድረግ ስለነበረ ጉዳዩን ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ አቅርበው ካስወሰኑ በኋላ አረፍተ ዘመን በገታቸው አባቶች ምትክ መልምለው የሚያቀርቡ ሊቃነ ጳጳሳት ተመርጠው እንዲያጠኑ በማድረግ የተለያዩ መስፈርቶችን አውጥተውና አጣርተው በኮሚቴው የቀረቡ ዐሥራ አምስት ቆሞሳትን፡- ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመ/ፓ/ጠ/ ጽ/ቤት የየመምሪያ ኀላፊዎች እና የየድርጅት ሥራ አስኪያጆች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኀላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰ/ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት በተገኙበት ሐምሌ 09 ቀን 2009 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በአንብሮተ እድ ሾመዋል፡፡

16. የሕገ ቤተ ክርስቲያን መሻሻል፣

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከቀዳማውያን አጀንዳዎቻቸው አንዱ የቤተ ክርስቲያናችንን ዋና ሕግ የሆነው ሕገ ቤተ ክርስቲያን እንዲሻሻል የሚል ነበር፡፡ በመሆኑም ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ሕጋዊ የማሻሻያ ሥርዐቱን ተከትሎ በሊቃውንትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ከታየ በኋላ ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም ርክበ ካህናት በርካታ ማሻሻያዎች የተደረጉበትና ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ለአሠራር እንዲያመች ተደርጎ የተዘጋጀው ሕገ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲጸድቅና በሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡

17. የግእዝ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ኅትመት፣

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሊቃውንት ጉባኤ ለብዙ ዘመናት ሲደከምበት የነበረው የግእዝ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይና ሐዲስ ኪዳን) በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ ጥራዝ ታትሞ ለአገልግሎት እንዲበቃ በማድረግ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ታሪካዊ የመምራት ኀላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡
የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ በቻይና ሀገር ዓለም ዐቀፍ ጥራቱን ጠብቆ ከታተመ በኋላ የምርቃቱን መርሐ ግብር በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርና በቤተ ክርስቲያናችን የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ታሪካዊ የምርቃት መርሐ ግብር እንዲከናወንም መመርያ አስተላልፈዋል፡፡
ከምርቃቱ መርሐ ግብር አስቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሓፊ የታተመውን የግእዝ መጽሐፍ ቅዱስ ለቅዱስነታቸው በቢሮአቸው ቀርቦ ያበረከቱላቸው ሲሆን ይህ ታሪካዊ ሥራ ከብዙ የሊቃውንት ድካም በኋላ ለኅትመት በመብቃቱ እጅግ መደሰታቸውን በወቅቱ ገልጸውላቸዋል፡፡

18. ቃለ ዐዋዲ በሦስት ቋንቋዎች፣

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምትመራበትን ቃለ ዐዋዲ በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ አማካኝነት ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዥኛ ቋንቋዎች ተተርጒሞ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተካሄደው መርሐ ግብር መርቀው አገልግሎት ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡
በምረቃው ሥነ ሥርዐት ላይ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የወቅቱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የወቅቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሓፊ ሊቀ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍና፣ የትንሣኤ ማሳተሚያ ሥራ አስኪያጅ ክቡር ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቃለ ዐዋዲው ትርጒም ለምእመናን የሚሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያቀላጥፍ መሆኑን በመግለጽ ሰፊ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት መጽሐፉ አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡

19. የማኅበራዊ ማደራጃ መምሪያ መቋቋምና ደንብን በተመለከተ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዘመነ ሢመታቸው ካከናወኗቸው በርካታ ውጤታማ ተግባራት መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የተደራጁ በርካታ ማኅበራት በሕግና በሥርዐት ተደራጅተው በቤተ ክርስቲያን ደረጃ በሚሰጣቸው ፍቃድ አማካኝነት አገልግሎት መስጠት ይችሉ ዘንድ በሊቀ ጳጳስ የበላይ ኀላፊነት የሚመራ የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ እንዲቋቋምና ሥራውን የሚያከናውንበት ደንብ ተዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲወሰን መደረጉ አንዱና ዋነኛው ሲሆን ይህንን ጉዳይ በተመለከተም የጥቅምት 2015 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ መክሮ ውሳኔ እንዲያስተላፍ ተደርጓል፡፡
ይህ ታሪካዊ ክንዋኔ ማኅበራት የሚያከናውኗቸው ተግባራት የታወቁ፣ በሕግ የሚመሩና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት በእጅጉ ወሳኝ ነው፤ ቅዱስነታቸው ከዚህ ቀደም ብሎ ማኅበራት በሕግና በሥርዐት እንዲመሩ በተደጋጋሚ ያቀረቧቸውን ጥሪዎች በተግባር የሚመልስ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳንን በሚመለከትም የፋይናንስ ሥርዐቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ እንዲታወቅና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦዲተሮች እንዲደረግ ያደረጉ ጥረት ተሳክቶ ማኅበሩ ሒሳቡን በየዓመቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦዲተሮች ኦዲት እንዲደረግ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ማኅበሩ ሒሳቡን በየዓመቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ኦዲተሮች እንዲያስመረምር መደረጉም የቅዱስነታቸውን የሕጋዊ አሠራር በተቋም ደረጃ መተግበርን ፍላጎትና ዓላማ በማሳካት ደረጃ በስኬት የሚገለጽ የቅዱነታቸው ውጤታማ ሥራ ያደርገዋል፡፡

20. የቅርስ ጥበቃን በተመለከተ፣

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ከመሆኗም በላይ አገራችን ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንድታተወቅና ቅርሶቹም በመላው ዓለም የሚጐበኙ ቅርሶች በመሆን ለአገራችን ክፍለ ኢኮኖሚ ማደግ የበኩላቸውን ድርሻ የሚወጡ ቅርሶች እንዲሆኑ ያደረገች አንጋፋ ተቋም መሆኗ ይታወቃል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመላ አገራችን አድባራትና ገዳማት የሚገኙ ጥንታዊያን ቅርሶች በአግባቡ፣ ለእይታና ለጥበቃ በሚያመች መልኩ እንዲጠበቁ ተደጋጋሚ መመሪያዎችን በማስተላለፍ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ ቅርሶችን የሚጠበቁበት ዕቃ ቤት እንዲደራጁ ማድረግ ችለዋል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም በአክሱም ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ዘመናዊ ሙዚየም የግንባታ ሥራው በተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይችል ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጀት እንዲፈቅድ፣ የግንባታ አሠሪ ኮሚቴው እንዲጠናከርና ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን በማድረግ ውጤታማ ሥራ የሠሩ ሲሆን፤ ግንባታውን ከሚያከናውነው ሕንጻ ሥራ ተቋራጭ ጋርም ተደጋጋሚ ውይይቶችን በማድረግ የግንባታ ሥራ በተቀላጠፈ መልኩ እንዲከናወን በማድረግ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተከፈተው ጦርነት ሥራው እንዲጓተት እስከሚያደርገው ድረስ የሠሩት ታሪካዊ ሥራ የቅዱስነታቸው ዘመነ ሢመት ዐቢይ ተግባር በመሆን ታሪክ ሲያስታውሰው ይኖራል፡፡