• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም.የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በአጠቃላይ በዚህ የመስቀል አደባባይ የተገኛችሁና በየአካባቢው ሆናችሁ በዓለ መስቀሉን እያከበራችሁ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤

በኀይለ መስቀሉ ሕዝቡንና አሕዛቡን አንድ አድርጎ በወንጌለ ሰላሙ ወደ እርሱ ያቀረበን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለበዓለ መስቀሉ አደረሳችሁ።!
‹‹መስቀል በሉ፤ ኪያሁ ተወከሉ፤
መስቀል እያላችሁ ተናገሩ፤ እሱንም ተማመኑ።››
(ቅዱስ ያሬድ)
መስቀል እንደየፅንሰ ሐሳቡ ወይም እንደየዐውደ ንባቡ የተለያየ ትርጒም አለው፤ ይሁን እንጂ ሲጠቃለል ትእምርት፤ ተጋድሎና መሥዋዕትነት በሚሉ ሦስት መሠረተ ሓሳቦች ሊጠቃለል ይችላል፡፡ ሦስቱ መሠረተ ሓሳቦች ሲገናዘቡ ደግሞ ወደ አንድ ነገረ አመሥጥሮ ይመጣሉ ፡፡ ትእምርተ መስቀል እያልን የምንገልጽው አገላለጽ በዐይናችን የምናየውን፣ በአንገታችን የምናስረውን፣ በልብሳችንና በአካላችን የምንቀርፀውን፣ በእጃችን የምንጨብጠውን፣ በአፋችን የምንሳለመውና ከቊስ የተሠራውን መስቀልን ማመልከታችን ነው፤ ይህን ትእምርተ መስቀል ባየን ቊጥር ክርስቶስ የኀጢአታችንን ዕዳ ለመክፈል የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ እናስባለን፤ ድኅነታችንም ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ባደረገው መሥዋዕታዊ ቤዛነት እንደተፈጸመ እናስታውሳለን፤ በዚህም እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንገነዘባለን ፡፡
እኛ ክርስቲያኖች በትእምርተ መስቀሉ አማካኝነት ድኅነተ ዓለምን እንሰብካለን፤ ትእምርተ መስቀሉ በሃይማኖት እንባረክበታለን፤ እንባርክበታለንም፤ ትእምርተ መስቀሉ የክርስቶስን መከራና አዳኝነት የወከለ መንፈሳዊ ትእምርት በመሆኑ እናከብረዋለን፤ በቤተ ክርስቲያን ጕልላትም ሆነ በአካላችን ሁሉ ትእምርቱን በማሳየት ነገረ ድኅነትን ለዓለም እናስተምርበታለን፡፡
ሁለተኛው የመስቀል ትርጒም ተጋድሎ ነው፤ ዓለም የዳነበት ነገረ መስቀሉን በማመን፣ አዳኙን ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተልና በማምለክ ወደ እግዚአብሔር በሚቀርቡ ክርስቲያኖች ላይ ክፉው መንፈስ ምን ጊዜም መከራ ማምጣቱን አያቆምም፤ ታድያ በክፉው መንፈስ አዝማችነት በክርስቲያኖች ላይ የሚዘንበውን መከራ ሳይፈሩ፣ ሳይሰቀቁና ከእምነታቸው ዝንፍ ሳይሉ በጽንዐ ሃይማኖት የሚቀበሉት መከራና ተጋድሎ መስቀል ይባላል፤ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መስቀሌን ተሸክሞ ሊከተለኝ የማይወድ የኔ ሊሆን አይችልም›› ያለው ይህ ዐይነቱን ተጋድሎ ሲያመለክት እንደሆነ ግልጽ ነው ፡፡ ይህንን ክርስቶሳዊ አስተምህሮ ተከትለው በዓለማችን ስፍር ቊጥር የሌላቸው ሰማዕታት መስቀላዊ ተጋድሎን በመሸከምና ሕይወታቸውን ገብረዋል፤ አሁንም እየገበሩ ነው፡፡
ሦስተኛውና እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነው የመስቀል ትርጒም ደግሞ መሥዋዕታዊ ቤዛነት ነው፤ በዚህ ዐውደ ምንባብ መሥዋዕት ማለት ለሌላው ወገን ሲባል የሚከፈል ኅልፈተ ሕይወት ነው፤ ቤዛነት ሲባልም በመያዣነት የተያዘን ነገር ለማስለቀቅ የሚከፈል ዋጋ ነው፤ ከዚህ አንጻር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጠቃላይ ለትዝምደ ሰብእ ሲል በመስቀል ላይ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ሠውቶአል፤ በኀጢአትና በፍዳ ምክንያት በዲያብሎስ እጅ ተይዘው የነበሩትን ነፍሳተ ሰብእንም ደሙን ቤዛ አድርጎ ለአባቱ በማቅረብ ከኀጢአትና ኀጢአት ካመጣው ፍዳ ነፃ አድርጎአል፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አኮ በዘይማስን ብሩር ወወርቅ ዘተቤዘወክሙ እምውስተ ዘኢይበቊዕ ምግባሪክሙ ዘተመጠውክሙ እምአበዊክሙ አላ በክቡር ደሙ ለክርስቶስ፣ ካባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከማይጠቅም ሥራችሁ ቤዛ የሆናችሁ በሚጠፋ ብርና ወርቅ አይደለም፤ በከበረ የክርስቶስ ደም እንጂ›› ያለው ይህንን መሥዋዕታዊ ቤዛነት ለማመልከት ነው ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ክቡራንና ክቡራት የበዓሉ ተሳታፊዎች፤

ዲያብሎስ ቀድሞውኑም የሰዎችን ነፍሳት በእጁ ሊያስገባ የቻለው በኀጢአትና ኀጢአት ባስከተለው ፍዳ ምክንያት ነበረ፤ ሰዎች በደመ ክርስቶስ ቤዛነት ከኀጢአትና ከፍዳው ነፃ ሲሆኑ በዲያብሎስ እጅ የሚያዙበት ምክንያት አልነበረምና ከዲያብሎስ የግዞት ከተማ ወጥተው ወደ ክርስቶስ ከተማ ወደ መንግሥተ ሰማያት ገብተዋል፤ ይህም ድርጊት በመስቀል ላይ የተፈጸመና መስቀል ያስገኘው ድል ስለሆነ መስቀል ይባላል፤ በሌላ በኩል መስቀል የሚለው ቃል ምሥጢሩን ተከትሎ ወደ አማርኛ ሲተረጐም ‹‹መሰቀል›› ይባላል፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክት ‹‹ወአንሰ ሐሰ ሊተ ኢይዜኀር ዘእንበለ በመስቀሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እግዚእነ፤ እኔስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ካልሆነ በቀር በሌላ አልመካም›› ሲል የገለጸው መስቀሉን መሥዋዕታዊ ቤዛነት ብሎ በማመሥጠር ነው፤ የሚያድን፣ የሚያስታርቅ፣ ሰላምንና አንድነትን የሚያስገኝ፣ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጸመው መሥዋዕታዊ ቤዛነት ነውና፤ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ቤዛነት ካልሆነ በቀር በሌላ መመካት ጭራሽ የማያስኬድና የማያዋጣ እንደሆነ ነግሮናል፤ እኛም መስቀል ኀይላችን ነው፤ መስቀል ጽናታችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው ስንል መሥዋዕታዊ ቤዛነቱን ማመልከታችን እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ የመስቀል ትርጒም እንደየዐውደ ምንባቡ በሦስት ዋና ዋና ትርጉሞች ቢነገርም የሦስቱም መዳረሻ ምሥጢር መዳንን ማመልከት ነው፤ ትእምርተ መስቀሉን ዐርማችን አድርገን የምንይዘው የምንሳለመውና የምንባረክበት ለመዳን ነው፤ ስለሃይማኖታችን ስንል የምንቀበለው መስቀላዊ ተጋድሎና መከራም ለመዳን ነው፤ በጌታችን የተፈጸመልን መሥዋዕታዊ ቤዛነትም እኛን ለማዳን ነው፤ ስለሆነም በሁሉም አቅጣጫ የነገረ መስቀሉ መነሻ መገሥገሻና መድረሻ መዳንና መዳን ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፤ ኢትዮጵያዊው ሐዋርያ ቅዱስ ያሬድም ‹‹መስቀል በሉ፤ እሱንም ተማመኑ›› ብሎ የዘመረው ከፍ ብሎ እንደተገለጸው በቤዛነት ደረጃ በመስቀል ላይ ከሆነው የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ቤዛነት በቀር ሌላ መዳኛ እንደሌለ ለመግለጽ ነው፤ በሥጋም በነፍስም፣ በሰማይም በምድርም የቤዛነትን ተግባር ፈጽሞ ያዳነን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና መስቀል አዳነን ስንል ክርስቶስ አዳነን ማለት እንደሆነ ልብ ይሏል ፡፡ ይህ ቤዛነት ሰማይንና ምድርን አንድ አድርጎ አስታርቆአል፤ ይቅርታም አጎናጽፎአል፤ ሰላምንም አስፍኖአል፤ ትዝምደ ሰብእን በአጠቃላይ ወደ አንድነት አምጥቶአል ፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራንና ክቡራት የበዓሉ ተሳታፊዎች፤

መስከረም 17 ቀን በየዓመቱ የምናከብረው የመስቀል በዓል ትእምርተ መስቀሉ ከተቀበረበት ጕድጓድ በአምላካዊ ተኣምር ስለተገኘ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ባለፈ ለዘለዓለሙ ሲያበራ የሚኖር አምላካዊ የማዳን ኀይልንም ለመመስከር ነው፤ ይህ የማይደበዝዝ ብርሃን በትክክል በሕይወታችን ውስጥ ከበራ ሰላምን እናገኛለን፤ አንድነታችንን እናጸናለን፤ ሁሉንም ነገር በዕርቅና በይቅርታ እናልፈዋለን፤ ዐይናችን ልባችንና ኅሊናችን ወደ ልማትና ሰውን ሊጠቅም ወደሚችል ተግባር እንጂ በሰው ላይ ጥፋትን ወደሚያስከትል ነገር አያተኵርም ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለ ምሥጢረ አምላክ የተሸከመ መስቀልን በግንባርዋ ቀርጻ በትከሻዋ ተሸክማ በሃይማኖቱ ከብራ ባለችበት ሁኔታ ዛሬ የምናየው የመስቀል ተቃራኒ ድርጊት ከምን የመጣ ነው? በመስቀላዊቷ ሀገር በኢትዮጵያ መጨካከንን፣ መገዳደልን፣ መለያየትን፣ መነቃቀፍን፣ ያስተማረና ያስለመደብን ከቶ ማን ይሆን? እውን አሁን የምናየውና የምንመለከተው ሁሉ የኢትጵያውያን ጠባይ ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ይህ እየሆነ ያለው የሀገራችንን አንድነት፣ ልማትና እድገት እንደ እሬት ከሚመራቸው የውጭ ኀይሎች የሚሰነዘር እንጂ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን አይደለም፤ ሰፊው አስተዋይ ሕዝብ ከነባሩ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ዕሴትና ትውፊት፣ ባህልና ማኅበራዊ ኑሮ ያልተለየ አስተዋይ ሕዝብ ነው፤ ኢትዮጵያዊ አብሮ መብላትን፣ አብሮ መኖርን፣ ተደጋግፎና ተጋግዞ የችግር ዘመን ማሳለፍን ያካበተ ቅዱስ ሕዝብ ሆኖ ለሺሕዎች ዘመናት ኖሮአል፤ ለማንነቱ መገለጫ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ የለም፤ ታድያ ይህንን የራሳችን ነባርና ቅዱስ ባህልን ትተን የሌሎቹን ደባል ባህል ለምን አስፈለገን? ደባሉ ባህልስ ከጥፋትና ከውድመት በቀር ምን አስገኘልን?
እውነቱን ለመናገር ኢትዮጵያዊውን ባህል አቃልለን ሀገሪቱን ወደማያስፈልግ አቅጣጫ እየነዳናት ያለን ፊደል ቈጠርን፣ ተራቀቅን፣ የባሕር ማዶውን ጥበብ ቀሰምን፤ ተመራመርን የምንል ልሂቃን ሰዎች ነን፤ ግን እኮ መስቀሉ ‹‹የናንተ ጥበብ ሞኝነት ነው›› ብሎናል፤ ከመስቀሉ በላይ ለመሆን እየተፈለገ ከሆነ አያዋጣም፤ አያዛልቅምም፣ ሰፊውና ቅዱሱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ጠባዩን አልለወጠም፤ አንድነቱን አልጠላም፤ ሰላሙን ሊነኩበት አይፈልግም፤ በማይበጠስ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የፍቅርና የወንድማማችነት ሐብል የታሠረ ነው፤ አሁንም እኛ የምንመክረውና የምናስተምረው ከሁሉ በፊት ሁሉም የፖለቲካ ልኂቃኖቻችን ያለምንም ልዩነት በአንድ አዳራሽ ተገናኝታችሁ በመወያየት ለዚህ ሀገርና ሕዝብ የሚበጅ ነገርን ፍጠሩ፤ ኢትዮጵያ፣ ሰላም፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ የሕይወትና የንብረት ዋስትና ይከበሩ የሚሉትን መሠረታዊ ነገሮች የጋራ አድርጋችሁ ያዙልን፣ ሌላውን ለሕዝቡ ዕድል ስጡትና እሱ ይዳኝ፤ የፈለገውን ርእዮተ ዓለም፣ የፈለገውን መንግሥት ራሱ መርጦ ያስቀምጥ፤ ነገሩ ሁሉ በዚህ አልቆ ወደ ልማትና እድገት እንግባ፤ ወጣት ልጆቻችንም እባካችሁ ሰከን በሉ፤ ጥያቄ አትጠይቁ አንልም፤ ግን የሰውን ሕይወትና ንብረት አታጥፉ፤ የሚጠፋው ንብረት የናንተው ነው፤ በወገናችሁ ላይ አትጨክኑ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ወገናችሁ ነው፤ እየተደረገ ያለው ድርጊት ጥፋትን እንጂ ልማትን አያስገኝም ነው የምንለው ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራንና ክቡራት የበዓሉ ተሳታፊዎች፣ መስቀልን በየዓመቱ የምናከብረው፤ ምሥጢረ ድኅነትን፣ ምሥጢረ ፍቅርን፣ ምሥጢረ ሰላምና አንድነትን፣ ምሥጢረ ዕርቅና ይቅርታን ልናስታውስበትና ልንማማርበት ብሎም የጋራ ጥቅማችንንና ሃይማኖታችንን በአዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ ለመተግበር ቃል ለመግባት እንጂ በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት አሸብርቀንና ተሸላልመን እዩን እዩን ለማለት አይደለም፤ ይህ በሚገባ መታወቅ አለበት፤ ከእንግዲህ ወዲህ ባለፈው ዓመት የተከሠቱ ስሕተቶች በሙሉ በሚገባ ታርመው አዲሱ ዓመት የውይይት የመግባባትና የመስማማት እንዲሆን ሁላችንም መጣር አለብን፤ የቃላት ዘለፋና ነቀፋ ከሚያለያዩን፣ ከሚያራርቁንና ውስጣችንን ከሚያቈስሉን በቀር የሚያመጡት ፋይዳ የላቸውም፡፡
ስለሆነም ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሚድያ ተቅዋማት እባካችሁ ልዩነትን ከሚያሰፉ አባባሎች ተቈጠቡ፤ ይልቁንም ሁሉም ኢትዮጵያውያን የኛው ናቸውና መድረክ ፈጥረው በጋራ ሆነው ለጋራ ሀገር በመወያየት መፍትሔ እንዲያስገኙ በፍቅርና በክብር መጐትጐት ማበረታታትና ማጠናከር ይኖርብናል፤ ይህንን ስናደርግ ሁላችንም ተጠቃሚዎች እንሆናለን ፡፡
በመጨረሻም፤ በሀገራችን እየተከሠቱ የሚገኙ መሰናክሎችን ለማስተካከል መንግሥት፣ የፖለቲካ ኀይሎችና ሕዝቡም በአጠቃላይ ጥበብን፣ መመካከርን፣ ሰላምንና ትዕግሥትን ማእከል ባደረገ መልኩ ታላቋ ኢትዮጵያን ወደ አስተማማኝ ሰላምና ዘላቂ አንድነት ለማሸጋገር ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ ደግመን ደጋግመን በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊና አባታዊ ጥሪያችንን በአጽንዖት እናስተላልፋለን ፡፡
መልካም በዓለ መስቀል ያድርግልን! ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32020-09-26 14:07:542025-01-28 14:08:55መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም.የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የርእሰ ዐውደ ዓመት ቃለ ቡራኬ Link to: መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የርእሰ ዐውደ ዓመት ቃለ ቡራኬ መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የርእሰ ዐውደ ዓመት ቃለ... Link to: ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. 39ኛው ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡ Link to: ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. 39ኛው ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡ ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. 39ኛው ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top