• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. 39ኛው ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ከልዩ ልዩ የሥራ ዘርፍ ተወክላችሁ በዚህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት በአጠቃላይ፤ሁሉንም ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን መከራውንና ፈተናውን አስችሎ በዚህ ታላቅ ጉባኤ ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን!!
‹‹ወይኩን ቅኑተ ሐቌክሙ ወኅትወ መኃትዊክሙ
ወገባችሁ የታጠቀ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን።››
(ሉቃ. 12፥35)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ኀይለ ቃል የተናገረውና ያስተማረው ለቅዱሳን ሐዋርያት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ትምህርቱ ለጊዜው አጠገቡ ለነበሩት ሐዋርያት የተነገረ ቢሆንም ፍጻሜው እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሡ ደቀ መዛሙርት ሁሉ እንደሆነም እናውቃለን፤ ከእነሱ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በየደረጃው በኀላፊነት የምንገኝ ደቀ መዛሙርትም ቃሉ በቀጥታ እንደሚመለከተን አንዘነጋውም፡፡

በመሆኑም ከዚህ እውነታ ተነሥተን፣ ጌታችን ‹‹ወገባችሁ የታጠቀ፣ መብራታችሁም የበራ ይሁን›› ሲል እኛን ያዘዘበትና ያስተማረበት ምክንያት ምን ይሆን? የሚለውን ጥያቄ አንሥተን ማየት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የትጥቅ ነገር የሚነሣው ተቃራኒ ኀይል ራስን ወይም ወገንን ለማጥቃት እንደተዘጋጀ ሲታወቅ ነው፤ መብራትን ማብራት የሚያስፈልገውም ጨለማ መኖሩ ሲታወቅ ነው፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አፅራር ምንጊዜም የማይተኙ መሆናቸውን በአምላክነቱ ኀይል የሚያውቅ እግዚአብሔር አምላካችን ሁሌ ወገባችንን ታጥቀን መንጋውን እንድንጠብቅ አዞናል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብርሃናዊት፣ ሰማያዊትና ዘለዓለማዊት ብትሆንም ለጊዜው ያለችው ጠላት በብዛት ባለበትና በጨለማው ዓለም ውስጥ ነውና በጠላት እንዳትጠቃ በጨለማውም እንዳትዋጥ ሁልጊዜ መብራት እንድናበራላት ታዘናል፤ ይህ የእኛ የክርስቲያኖች ቀዋሚና መደበኛ ሥራችን ነው፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታሪዎች፤ በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ካለው መከራ አንጻር ከምንም ጊዜ በላይ ታጥቀን ለቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠልና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ ነው፤ለሦስት ሺሕ ዘመናት ሀገርን የገነባችና የጠበቀች ሁሉንም በእኩልነት ያስተናገደች በማንም ላይ ግፍን ያልፈጸመች ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ከገጸ ምድር እናጥፋሽ የሚሉ በምሥራቅም በምዕራብም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆናል፤ ፍትሕም ይገኝ ይሆናል እያልን በተስፋ ብንጠባበቅም ሲሆን አናይም፤ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገሩ እየተባበሰ፣ ክርስቲያን ልጆቻችንም ለተደጋጋሚ ጥቃት እየተዳረጉ በክርስቲያንነታቸው ብቻ የግፍ ግፍ እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ጊዜያት ባደረገችው ጥሪ ከልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎችና ከሕዝበ ክርስቲያኑ ለተጐዱ ምእመናን የተወሰነ ድጋፍ ለማድረግ ቢሞከርም ከችግሩ ስፋት የተነሣ የሚያረካ አልሆነም ፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤አበው ሲናገሩ ‹‹ከራስ በላይ ነፋስ›› እንደሚሉት ቤተ ክርስቲያናችን እየገጠማት ያለውን ችግር ለመቋቋም ልጆችዋን አስተባብራና አደራጅታ ራስዋን በራስዋ ወደመጠበቅ አማራጭ ካልተሸጋገረች ዕጣ ፈንታዋ እጅግ አስጊ እየሆነ መጥቶአል፤ ክርስቲያን ልጆቻችን ተሸማቅቀው፣ ነጻነታቸው ተገፎ፣ በሀገራቸውና በወገናቸው መካከል የመኖርና ሃይማኖታቸውን የመከተል መብት አጥተው ባሉበት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቅን ነው ማለት አይቻልም፡፡ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያንን የመጠበቅና የማጽናናት ኀላፊነት ከሁሉ በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ጫንቃ ላይ ያረፈ እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚዘንበውን መከራ ለመግታት ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉባኤ ተገቢውን መፍትሔ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው አባላት፤“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ሁከት፣ ለዘመናት ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የአንበጣ መንጋና ልዩ ልዩ መቅሠፍት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ አንድ ላይ ሆነን በመቆም ሕዝበ ክርስቲያኑን በመጠበቅ ፈንታ ሌላ ተቀጥላና የቤተ ክርስቲያንን ዐቅም በመከፋፈል ለማዳከም በውስጣችን የሚደረጉ ሤራዎችም ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ጥንካሬ ከባድ ዕንቅፋቶች እየሆኑ መምጣታቸው ሌላ የጥፋት ገጽታ ሆኖ እየታየ ነው ፡፡እንደ እውነቱ ከሆነ እንደዚህ ያለው ድርጊት ለዘመናት ቤተ ክርስቲያናችንን ሲፈታተኑ የነበሩ የውጭ ኀይሎች በረቀቀ ስልትና በእጅ አዙር ቤተ ክርስቲያናችንን ሊያፈራርሱ የጠነሰሱት ተልእኮ እንጂ ላይ ላዩ አጥባቂ የኦርቶዶክስ ተከታይ መሳይ ውስጡ ግን ኦርቶዶክስን በመከፋፈል ማዳከምና ማፍረስ የሆነ ድርጊት የንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ተግባር ይሆናል ብለን አናምንም፤ ይህንን ደባ ሁላችንም ልናጤነው ይገባል ፡፡ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የተፈጸመው ሕገ ወጥና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ይገኝበታል፤ እንደዚህ ያለ ድርጊት የሁለት ሺሕ ዘመን ሐዋርያዊ ቀኖና እና ሥርዐት ባላት ቤተ ክርስቲያናችን ቀርቶ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ተደርጎ የማያውቅ ድፍረትና ስሕተት ነው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ድርጊት መነሻ የሆኑ ምክንያቶችና የምክንያቱ ሰለባ የሆኑ፣ እንደዚሁም ሳይላኩና ሥልጣኑ ሳይኖራቸው ዳግም ጥምቀትን ዳግም ክህነትን በማወጅ ለዚህ አደጋ መከሠት ምክንያት የሆኑ ሁሉ በማያዳግም ሁኔታ ይህ ጉባኤ የማስቆሚያ መፍትሔ እንዲያበጅላቸው በዚህ አጋጣሚ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ዛሬ በብዙ መልኩ እንግልት ላይ ወድቀው ማየት የተለመደ ሆኗል፤ ብዙ ወጣት ልጆቻችን ለእንጀራ ፍለጋ ሲሉ ሃይማኖታቸው ወደማይወደድበት ሰብኣዊ መብታቸው ወደማይከበርበት፣ የንብረትም ሆነ የሕይወት ዋስትና ወደሌለበት ሀገር በመሰደድ የምድር ሲኦል እየለበለባቸው እንደሆነ እያየን ነው፤ ይህንን እየተመለከትን ተኝተን የምናድር ኢትዮጵያውያን ካለን ክርስቲያንነቱንም ሰብኣዊነቱንም ዘንግተነዋል የሚያሰኝ ነው፤ ስለሆነም ልጆቻችን በባዕድ ሀገር ራቁታቸው እንደቅጠል እየረገፉ ከማየት የበለጠ (የከፋ) አንገትን የሚያስደፋ ውርደት ስለሌለ ሀገር ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ተቅዋማት፣ የኢፌዲሪ መንግሥትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገባውን ሁሉ በማድረግ ልጆቻችን ወደሀገራቸውና ወደቤተሰቦቻቸው በአስቸኳይ እንዲመለሱ ያደርጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ማሰማት አለባት የበኩሏን ድጋፍ ለማድረግም መዘጋጀት አለባት፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤የሰው ልጅ በተፈጥሮው ምግብና መጠጥ ልብስና መጠለያ እንደሚሻ ሁሉ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የእኩልነት፣ የመብትና የፍትሕ ፍላጎቱም የላቀ ነው፤ እነዚህ ፍለጎቶቹን ባጣ ጊዜ ያላስፈላጊ ሁከትና ግጭት ይፈጠራሉ፤ በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን የሚታዩ አለመግባባቶች ይብዛም ይነስ ከዚህ የሚመነጩ ከመሆን አያልፉም፤ እነዚህ ነገሮች በተቻለ መጠን ካልተከበሩ ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆን እያየን ነው፤ በመሆኑም በሀገራችን ያለው ያልተረጋጋ ሁኔታ ያልሆነ መልክ እንዳይዝ መንግሥታችንና የሀገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወንድማማቾች እንደመሆናቸው መጠን ምንም ልዩነት ሳይኖር በክብ ጠረጴዛ ሆነው በመመካከር ችግሮችን ሁሉ እንዲፈቱ እንጂ ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ እንዳይገቡ ቤተ ክርስቲያናችን በገለልተኝነትና በእናትነት መንፈስ ማገዝ አለባት፤ ማስታረቅም ማስተማርም አለባት፤ ሁሉም ነገር በሰላምና በውይይት ብቻ እንጂ ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ የሚደረግ አማራጭ ከጒዳት በቀር ውጤት አናገኝበትም፤ ከዚህ ጎን ለጎንም ፍትሕና ርትዕ እንዲሰፍን፣ ፍትሕ የተነፈጋቸው ወገኖች ካሉ ፍትሕ እንዲያገኙ ቤተ ክርስቲያን በማእከል ሆና የመምከር ሥራ መሥራት አለባት፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤ከዚህ በላይ የጠቃቀስናቸው ችግሮች በሀገራችን ሥር እየሰደዱ የመጡበት ምክንያት በርከት ያለ ቢሆንም የድህነት ጉዳይ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ አያጠራጥርም፤ ወጣት ልጆቻችን ሥራና ዳቦ ባጡ ቊጥር ሌላውን አማራጭ በመከተል ሲታክቱ እነሆ በጣም በርካታ የሆኑ ዓመታት ተቈጠሩ፤ ስያሜውና አቀራረቡ ቢለያይም ከሕገ ንጉሣዊ ሥርዐት ማክተም ማግሥት ጀምሮ የተደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ፀረ ድህነት የሚል አንድምታ ይዘው የተደረጉ ናቸው፣ ሆኖም ይቀረፋል የተባለው ድህነት ባለመቀረፉ፣ በዚያም ላይ ሌሎች ነገሮች በመካከሉ እየተሰነቀሩ ጒዞአችንን የኋልዮሽ አድርገውታል፡፡ ስለሆነም ድህነትን በእዕድገት በመቀየር ረገድ ቤተ ክርስቲያን በልማቱ፣ በድህነት ማጥፋቱና በሰላም ማረጋገጡ ዙሪያ በርትታ መሥራት ይጠበቅባታል፤ ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመውም ሕዝቡ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በአንድ ወጥ አደረጃጀት ተሰባስቦ አረጋውያንን በመጦር፣ ሕፃናትን በማስተማርና በመንከባከብ፣ የራስ አገዝ ልማትን በማስፋፋት፣ ለወጣቱ ትውልድ ሥራ በመፍጠርና የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነ ይታወቃል፤ ከዚህ አንጻር ሰበካ ጉባኤ ከተቋቋመበት ዘመን አንሥቶ የተገኘው እድገት የማይናቅ ቢሆንም መጓዝ የሚገባውን ያህል እንዳልተጓዘ፣ ያለውም ሀብት በአግባቡ እንዳልተያዘ የአደባባይ ምሥጢር ነው፤ ከዚህም ሌላ ሌሎች ደባል ቡድኖች በየአካባቢው ሲፈጠሩ ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ለምጣኔ ሀብት መባከን ያለው አደጋ ሳይጤን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ፈቃድ እየሰጠን በየፊናው ያሰማራናቸው ሁሉ በስመ ቤተ ክርስቲያን እየተሰበሰቡና ገንዘብ እየሰበሰቡ በርከት ያለ የምእመናን ሀብት እንደሚባክን መረጃዎች አሉ፤ ይህም የሚከናወነው በሀገር ውስጥና በውጭ ጭምር ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስና ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን ድርጊት አርሞና አስተካክሎ መልክ ካላስያዘ በቀር ጒዳቱ የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን አንድነትዋንና ህልውናዋንም ጭምር ከባድ አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል፤ በታሪክም ተወቃሽነትን ያስከትላል ስለዚህ እኛ የምንለው አሁንም መፍትሔ እናበጅለት ነው፡፡

በመጨረሻም፤ ይህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ የጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ የቀረቡትን ዐበይት ጒዳዮች በጥልቀትና በማስተዋል ተመልክቶ ለወሳኙ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ግብአት የሚሆን የውሳኔ ሐሳብ እንዲያስተላልፍ በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክልን፤ ይቀድስልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32020-10-13 14:52:092025-01-28 14:53:13ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. 39ኛው ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም.የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም.የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም.የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ... Link to: ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top