• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ጥር 11 ቀን 2010 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

የመሓሪነትና የአባትነት ቃሉን በመግለጽ ልጅነታችንን እንደገና የመለሰልን እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ በሰላም አደረሳችሁ!!

“ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ
እነሆ ከሰማይ ቃል መጣ፤”
(ማቴ. 3፥17)

በዓለ አስተርእዮ ወይም በዓለ ኤጲፋንያ ከሌሎች በዓላት ለየት የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉ፤ ከነዚህም መካከል የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትና የሰው ልጆች የድኅነት አቅጣጫ ኩነቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር አንድም፣ሦስትም እንደሆነ የሚያመለክቱ የተለያዩ ጭብጦች መኖራቸው ከጥንት ጀምሮ ቢታወቅም፣ አካላዊ በሆነ ኩነት በግልጽ የታወቀው ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ዕለት ነው፤ በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በላዩ ተቀመጠ፤ ወዲያውኑ ከሰማይ የምወደው፣ በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው የሚል ቃል ወይም ድምፀ ቃል መጣ፤ ይላል (ማቴ 3፤17)፡፡ ጌታችን ከድንግል ማርያም እንደሚፀነስ ቅዱስ ገብርኤል የምሥራቹን መልእክት ለድንግል ማርያም ባደረሰ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ካንቺ የሚወለደው ቅዱስ ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ብሎ ሲናገር ፣ የእግዚአብሔር ሦስትነት በግልጽ የታወቀበት ክሥተት ነበረ ፤ ሆኖም በዚህ ጊዜ የተገለጸው ሦስትነት መንፈስ ቅዱስ፣ ወልድ፣ እግዚአብሔር ተብሎ በስምና በግብር ከመገለጽ በቀር በአካል የታየበት ሁኔታ አልነበረም፡፡

በዮርዳኖስ ወንዝ ግን እግዚአብሔር ወልድ በአካል በወንዙ መሐል ሲጠመቅ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በአካለ ርግብ አምሳል ከሰማያት ወርዶ በጌታችን ላይ ሲቀመጥ፣ እግዚአብሔር አብም በተለየ አካሉ ስለ ባሕርይ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ድምፁን ሲያሰማ የታየበትና የተሰማበት ሁኔታ ስለነበረ፣ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት በማያሻማ ሁኔታ ታወቀ፣ ተረጋገጠ፤ በመሆኑም በዓለ ጥምቀት የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት በተጨባጭ የታወቀበት ዕለት በመሆኑ በዓለ አስተርእዮ ይባላል ፤ አስተርእዮ ማለት የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት በአካልም፣ በስምም፣ በግብርም የተገለጸበት፣ የታወቀበትና የተረጋገጠበት ቀን ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዕለተ ፅንስ ጀምሮ የአምላክነቱን ኀይልና ማንነት የሚያመለክቱ ብዙ ነገሮች የተፈጸሙ ቢሆኑም፣ በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምስክርነት እሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የተመሰከረውና የታየው በዕለተ ጥምቀት በፈለገ ዮርዳኖስ ነው፣ በዚህም በዓለ ጥምቀት የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት በግልጽ የታወቀበትና የተረጋገጠበት ዕለት በመሆኑ በዓለ አስተርእዮ ወይም የመገለጥ ዕለት ተብሎ ይታወቃል፡፡

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ዐቢይና መሠረታዊ ነገር የጌታችን አምላክነት በዕለተ ጥምቀት የተረጋገጠው እንዴት ባለ አገላለጽ ነው? የሚለው ነው፤ ይህንን ስንመለከት የጌታችንን አምላክነት የሚገልጸው ዋና አረፍተ ነገር ‹‹እርሱ ልጄ ነው›› የሚለው ሆኖ ይገኛል፡፡ የጌታችን ወልደ እግዚአብሔርነት ቅዱስ ገብርኤል በዕለተ ብሥራት የገለጸው፣ ጌታችንም በየጊዜው ያስተማረው፣ እግዚአብሔር አብም በፈለገ ዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ያረጋገጠው ነው፡፡ በዚህ አረፍተ ነገር የጌታችን አምላክነት እንዴት መረዳት ይቻላል? የሚለው ሲታይ፣ የአምላክ ልጅ አምላክ በመሆኑ ነው የሚል መልስ እናገኛለን፤ ከሰው የተወለደ ሁሉ ሰው እንደሚባል ከአምላክ የተወለደም አምላክ ይባላል እንጂ ሌላ ሊባል አይችልምና ነው፡፡ አንድ ልጅ በጸጋ፣ በማደጎ፣ ወይም በጉዲፈቻ ካልሆነ በቀር በግብር ባሕርያዊ የተወለደ ከሆነ የባሕርይ አባቱን ባሕርይ ሁሉ ባለቤት ስለሆነ በሁሉም ነገር እንደ አባቱ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ሲባል የጸጋ፣ የማደጎ ወይም የጉዲፈቻ ዐይነት ልጅ ሳይሆን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ነው፤ የባሕርይ ልጅ ከሆነ ደግሞ ከእግዚአብሔር የተወለደ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው፤ እስራኤል ዘሥጋ፣ እስራኤል ዘነፍስ ወይም ክርስቲያኖች፣ በደብር ቅዱስ የነበሩ ደቂቀ ሴትና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ የእግዚአብሔር ልጆች፣ የአምላክ ልጆች ተብለው ቢጠቀሱም የጸጋ ልጆች እንጂ የባሕርይ ልጆች አይባሉም፣ (ዘፀ. 4፥23፤ ዮሐ. 1፥12፤ 1ዮሐ. 3፥1፣ ዘፍ. 2፥2፤ ኢዮ. 1፤6)፡፡ ጌታችን ግን ብቸኛ የባሕርይ ልጅ እርሱ ብቻ በመሆኑ አንድያ ልጅ ወይም ወልድ ዋሕድ›› ይባላል፤ (ዮሐ. 1፥18፤ 3፥16)፤ ከሌሎች የእግዚአብሔር ልጆች ተለይቶ አንድያ ልጅ ተብሎ መገለፁ በባሕርያዊ ልደት ብቸኛ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ከዚህ የተነሣ ጌታችን የባሕርይ ልጅ ስለሆነ የባሕርይ አምላክ ከሚባል በቀር ሌላ ሊባል አይችልም፤ካህናተ አይሁድም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎአል ብለው የከሰሱት የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ነኝ ብሎ ስላስተማረና ይህ ማለት እግዚአብሔር ነኝ ማለት እንደሆነ በሚገባ ስላወቁ ነው (ዮሐ. 5፥18)፡፡ ስለዚህ ይህ የባሕርይ ልጅነቱ በእግዚአብሔር ድምፀ ቃል የተረጋገጠው በፈለገ ዮርዳኖስ በዕለተ ጥምቀት ስለሆነ የጌታችን የባሕርይ አምላክነት በውል የተገለጸበትና የታወቀበት ዕለት ነውና ይህ በዓልና ወቅት አስተርእዮ ተብሏል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፡ በዓለ ጥምቀት ጌታችን በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ ሳለ በኀጢአተ አዳም የተዘጋችው ገነት መንግሥተ ሰማያት እንደገና ተከፍታ ሰዎች ሊገቡባት የሚችሉ እንዴት ባለው ሁናቴ እንደሆነ የሚያመለክት ምሥጢረ ድኅነት የተገለጸበት ዕለት በመሆኑ አስተርእዮ ማለትም የእግዚአብሔር መገለጥ ይባላል፤ ቅዱስ ወንጌል ይህንን ሲገልጽ ጌታችን ሲጠመቅ ሰማያት ተከፈቱ ይላል፤ ይህ ኀይለ ቃል ሰዎች ሁሉ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀው የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች ሲሆኑ መንግሥተ ሰማያት ክፍት ሆና ትጠብቃቸዋለች የሚል ምሥጢራዊ መልእክት እንዳስተላለፈ በመንፈስ ቅዱስ እንገነዘባለን፤ ለዚህም ነው ጌታችን ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል በማለት በአጽንዖት ያስተማረ (ዮሐ. 3፥5፤ ማር. 16፥16)፡፡ ስለዚህ በዓለ ጥምቀት የድኅነታችን ፍኖተ ምሥጢር የተገለጸበት በመሆኑ አስተርእዮ እንለዋለን፡፡ በዚህ ምክንያት በዓለ ጥምቀት የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት፣ የጌታችን ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆን፣ የሰዎች መዳኛ የሆነው ምሥጥረ ጥምቀት የተገለጸበት ታላቅ ዕለት በመሆኑ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተርእዮ ኤጲፋንያ ተብሎ እንዲከበር ወስነዋል፣ አስተምረዋልም፤ ከዚህ አንጻር ከጥር ዐሥር ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ያለው ወቅት በአጠቃላይ አስተርእዮ ይባላል፡፡ አስተርእዮ የሚለው ቃል በሃይማኖታችን ውስጥ ትልቅ ትርጒም ያለው ኀይለ ቃል ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱን ገለጸ፤ ፈቃዱንም አስታወቀ፤የሰው ፍኖተ ድኅነትንም አሳየ፤ በማለት የሃይማኖታችን መሠረት ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ያሳያልና ነው፤ (ዮሐ ፤)፡፡

እንግዲህ ከዚህ ቃለ ቅዱስ ወንጌል እንደምንረዳው የክርስትና ሃይማኖት የተመሠረተው በሌሎች ታሪክ እንደሚታየው ሰዎች በሚያውጠነጥኑት አመክንዮ፣ በፍልስፍና ወይም በሰው ልዩ የተረት ፈጠራ ሳይሆን፣ ራሱ እግዚአብሔር የገለጸው፥ ያስተማረውና ያወጀው ሃይማኖት ነው (2ጴጥ. 1፥16-18) ።

እዚህ ላይ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ሊያውቀውና ሊገነዘበው የሚገባ ነገር የክርስትና ሃይማኖት የተጠነሰሰው የተመሰረተውና የተጀመረው እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች ገልጾ በሰጠው አስተምሕሮ ብቻ እንጂ የሰው ፈጠራ እና ፍልስፍና ያስገኘው አለመሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ፍልስፍና ቀድሞም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም ቦታ የለውም፣ምክንያቱም የሰው ፍልስፍና በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት ከመሆኑም ሌላ በሰው ተጀምሮ በማቴሪያል ወይም በቊሳቊስ ተረማምዶ የመጨረሻ መዳረሻው ሰው በመሆኑ ነው፤ ከዚህ በላይ ግን ማለፍ አይችልም፤ (1ቆሮ. 1፥20)፤ አስተርእዮተ እግዚአብሔር የገለጸው የክርስትና ሃይማኖት ግን ከእግዚአብሔር መንጭቶ በሰው ኅሊናዊ ተአምኖ ተራምዶ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ ነው ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ በተግባር የፈጸመው ኋላም በትምህርት ያጸናው ትምህርተ ጥምቀት፡- ቋንቋ፣ነገድ፣ጎሳ፣ቀለም፣ፆታ፣የሥልጣን ደረጃ ወዘተ ሳይለይ ሁሉንም የሰው ዘር ለድኅነት የጋበዘ ነው፤ ቃሉም እንደሚከተለው ተቀምጧል፡- “ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ አስተምሩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” ይላል (ማር. 16፥16)፡፡

ከዚህ አንጻር ጥምቀተ ክርስትና ብሔርን፣ ቋንቋን፣ጎሳን፣ቀለምን፣ የሥልጣን ደረጃን ፣ ፆታን ሳትለይ ሁሉንም ሰብኣዊ ፍጡር የምትቀበልና የምታከብር፣ ወደ መንግሥተ ሰማያትም በር ከፍታ የምታስገባ ስለሆነች እኛ ክርስቲያኖች በየዓመቱ በታላቅ ሥነ ሥርዐት እናከብራታለን፡፡ የጥምቀት ሥነ በዓል አከባበር ከትምህርተ መለኮት፣ ከቅዱስ ትውፊትና ባሕል ጠቀሜታው ባሻገር የኢትዮጵያን ሕዝቦች በአንድነት የሚያስተሳስር፣ ዳር እስከ ዳር ያለ ምንም ልዩነት እንደየቋንቋው፣ እንደየ ባህሉ በኅብረት ፈጣሪውን እያመሰገነና እያመለከ ሃይማኖቱን የሚገልጽበት ፣ ማኅበራዊነቱን የሚያጎለብትበት፣ አንድነቱን የሚያጸናበት፣ ልዩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ በዓል ሆኖ በሀገራችን በኢትዮጵያ ለዘመናት ሲከበር ኖሯል፤ አሁንም እየተከበረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖተ ክርስትና ከመሰል ጎረቤት ሀገሮች በተለየ ሁኔታ ፈተናዎችን እየመከተ እስከ ዛሬ ድረስ ሊቀጥል የቻለው እንደዚህ ባለ ቅዱስ በዓልና እሱን ምክንያት አድርጎ በተገነባ የአከባበር ቅዱስ ባህል መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰላምና የፍቅር፣ የአንድነትና የመከባበር፣ የእግዚአብሔር በር እና የድኅነት መንገድ የሆነች ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ በዚች ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የቀደሙ አበው እጅግ በጣም አስደናቂ የሆነ ሃይማኖታዊ ብቃትና ቅድስናን ተጎናጽፈዋል፡፡ ሀገራዊና ማኅበራዊ አንድነትንም አረጋግጠዋል፣ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ዋስትና በቀዳሚነት ያለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመቻቻል፣ የመተማመንና፣ የመከባበር፣ አስተምህሮ ውስጥ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን የሆን ሁሉ አንድነትን በመጠበቅ ረገድ ጒልሕ ሚና ያለውን የጥምቀት በዓል ስናከብር የሕዝብና የሀገር አንድነት ለእድገታችን፣ለሕዳሴያችን፤ ለልማታችን፣ ለታሪካችንና ለጥንካሬአችን ያለውን ከፍተኛ ሚና ለመላው ሕዝባችን በተለይም ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በማስተማርና በማሥረጽ ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም መላው የሀገራችን ሕዝቦች ለሀገር ሰላምና አንድነት መጠበቅ፣ ለልማትና ለእድገት መረጋገጥ በአንድነት እንዲቆሙ፣ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራንና ሰባክያነ ወንጌልም በሕዝቦች እኩልነትና በሀገር አንድነት መጠበቅ ዙሪያ ከትምህርተ ሃይማኖቱ ጋር በማጣጣም ያለ ማቋረጥ እንዲያስተምሩ፣ ሕዝቡም ከዚያም ከዚህም ብቅ ብቅ የሚሉና ከኢትዮጵያዊ ባህላችን ወጣ ያሉ፣ ለአንድነታችንም ዕንቅፋት የሆኑ የመቈራቈስ ዝንባሌዎች ጊዜ ሳይወስዱ ለማረም በየአካባቢው ጠንክሮ እንዲሠራ፣ በይቀጥላልም እንደዚህ ካለ መዘናጋት በቶሎ ወጥቶ ወደዘላቂ የሕዳሴ ጒዞ በፍጥነት እንዲሠማራ በዚህ አጋጣሚ አበክረን እናሳስባለን፡፡

በመጨረሻም፡ የዘንድሮ በዓለ ጥምቀት ልዩ የሚያደርገው፣ ሥነ በዓሉ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ከሰጠውና ከሚሰጠው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ዕሴት፣ የባህል ዕቅበትና ድምቀት አንጻር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የባህልና የቅርስ ድርጅት ለማስመዝገብ በምንረባረብበት ወቅት በመሆኑ፣ በዓሉ ለሀገራችን አንድነትና ለሕዝባችን አብሮነት ካለው የላቀ ፋይዳ አኳያ የሚመለከታችሁ ሁሉ ማለትም የመንግሥት አካላትን ጨምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራን፣ የባህልና የቅርስ ተቈርቋሪዎች፣ ጥያቄአችን ተቀባይነት አግኝቶ ልክ እንደ መስቀል በዓል በዩኒስኮ እንዲመዘገብ በሚደረገው ጥረት ትብብራችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያሳሰብን መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የጥምቀት በዓል ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ ‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር››አሜን፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32018-01-19 13:33:392025-01-28 13:34:37ጥር 11 ቀን 2010 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ታኅሣሥ 29 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም. የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ታኅሣሥ 29 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም. የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ታኅሣሥ 29 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም. የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና... Link to: የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ Link to: የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top