ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጥምቀት በዓል በጃንሜዳ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ፤
ሥጋችንና ነፍሳችንን ከቃሉ ጋር በውኃ መታጠብ ያነፃን የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አንድ ዓመተ ምሕረት በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ!!
“ወውእቱ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ቅዱስ ወበእሳት
እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤”
(ሉቃ. 3፥16)
ጥምቀት ማለት የተለያየና ሰፋ ያለ ትርጒም ቢኖረውም ምሥጢራዊ ትርጒሙን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው መንጻት፣ መተባበር፣ መለወጥ፣ መሻገር፣ አዲስ ሕይወት፣ አዲስ ልደት፣ አዲስ ፍጥረት፤ የሚሉት መሠረተ ሐሳቦችን ያመሠጥራል፡፡
የጥምቀት ጥንተ ታሪክ ስንመለከት ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጀምሮ ይነሣል፤ በዘመነ ብሉይ ሰውን ጨምሮ ልዩ ልዩ ነገሮችን ለማንጻት ማጠብና ማጥመቅ የተለመደ ሃይማኖታዊ ተግባር ነበረ፤ ከዚያ ተያይዞ በወረደው ሥርዐትና ትውፊት መሠረት ነቢያትና ካህናት በየዘመናቸው ያጠምቁ ነበረ፤ በክፉ ደዌ ተይዞ ይሰቃይ የነበረ ጻድቁ ኢዮብ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ከጽኑ ደዌው ድኖአል፤ ሶርያዊው ንዕማንም በነቢዩ በኤልሳዕ ትእዛዝ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ከለምጽ በሽታው ተፈውሶአል፤ ደቂቀ እስራኤልም የኤርትራን ባሕርና የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገራቸው ጥምቀት ተብሎ ተጽፎአል፤ በተለይም ታቦተ እግዚአብሔርን ተሸክመው ይጓዙ የነበሩ ካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስ ወንዝ ውኃን ሲነኩና ውኃው ሲቆም የሆነው ክሥተት ጥምቀት ተብሎአል፤ ይህ ዐይነቱ የጥምቀት ሁኔታ በየጊዜው እየተፈጸመ እስከ ዘመነ ዮሐንስ መጥምቅ ደርሶአል፡፡ ከጥምቀተ ክርስቶስ በፊት የነበሩት ጥምቀታት በክርስቶስ ለሚሰጠው እውነተኛ ጥምቀት እንደ ምሳሌ እንደ ጥላና እንደ አመልካች ቀስት የሚያገለግሉ ማዘጋጃ ነበሩ እንጂ ስርየተ ኀጢአትን፣ ሀብተ ንጽሕን፣ ሀብተ ልደትን፣ አዲስ ሕይወትን የሚያጎናጽፉ አልነበሩም፤ የሚከናወኑትም በውኃ ብቻ ነበረ እንጂ በመንፈስ ቅዱስ ጭምር አልነበረም፤ ለዚህም ነው መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ እኔ ለንስሓ የሚሆን የማዘጋጃ ጥምቀት አጠምቃለሁ፤ ከኔ በፊት የነበረው፣ ከኔ የሚበረታው፣ ከኔ በኋላ የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በውኃ ብቻ ሳይሆን በውኃ፣ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል በማለት የመሰከረው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ የማጥመቅ ሥራን ያከናውን የነበረው እንዲሁ በድንገትና ያለአስተምህሮ አልነበረም “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ “የሚለውን የኃጥአን ዋና ተስፋ ዐቢይ ርእስ አድርጎ በመጠቀም የንስሓን ጠቃሚነትና የኀጢአትን ጎጂነት በስንዴና በገለባው እየመሰለ አጒልቶ ያስተምር ነበር፤ በሰዎች መካከል የበላይና የበታች ሳይኖር ሁሉም በእኩልነትና በኅብረት በተስተካከለ ህላዌ ይኖሩ ዘንድ “ ተራራውና ኮረብታው ዝቅ ይበል፤ ጐድጓዳው ይሙላ” እያለ ደጋግሞ አስተማረ፤ ክፋት ጠማማነት ተወግዶ በሰው አእምሮ ውስጥ የተስተካከለና ቅን አስተሳሰብ ሰፍኖ ይኖር ዘንድ ጠማማውና ጠመዝማዛው፣ ሸካራውና ጐባጣው መንገድ ሁሉ ተስተካክሎ ቀጥ ይበል ብሎ አሰምቶ ተናገረ፤ እነዚህ ድርጊቶች ንስሓን ገንዘብ ባደረገ ሰብኣዊ ሕይወት ውስጥ የሚታዩ ግዙፋን ፍሬዎች ናቸውና እነዚህ በሰው አፍአዊና ውሣጣዊ ሕይወት ጎምርተውና አፍርተው እንዲታዩ ቅዱስ ዮሐንስ ያለመታከት አስተማረ፤ ሰው በንስሓ ሕይወት ለመታደስ ሳይዘጋጅ ዘርን በመቁጠር የእገሌ ልጅ ነኝ እያለ በዘር የሚመካ ከሆነ በሁለመናው ወድቆ ሌሎች ቀድመውት ወደፊት እንደሚራመዱ “አብርሃም አባት አለን በማለት የምትድኑ አይምሰላችሁ” እያለ በማስተማር በዘር መመካትን ከንቱ እንደሆነ አሳይቶአል፤ ቅዱስ ዮሐንስ በማጠቃለያ ትምህርቱ “ እነሆ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራውን ለመቊረጥ ከዚያም በእሳት ለማቃጠል “ በማለት ሥልጣነ እግዚአብሔር ኢተነሳሕያንን ለመቅጣት፣ ተነሳሕያንን ለመሸለም መዘጋጀቱን አስረግጦ አስምሮአል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ እያለ ሕዝቡን በማስተማርና በማጥመቅ ተግባር በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምዶ በነበረበት ጊዜ ጌታ ሊጠመቅ ወደ እርሱ መጣ፤ ቅዱስ ዮሐንስ አንተን ማጥመቅ አልችልም ቢልም በተነገረው አምላካዊ ቃልና ትእዛዝ መሠረት በዮርዳኖስ ወንዝ አጥምቆታል፤ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ ሦስት ዐበይት ነገሮች ተከናውነዋል፤ ይኸውም፡ ሰማያት ተከፍተዋል፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ላይ ተቀምጦአል፣ እግዚአብሔር አብ “የምወደው ልጄ ይህ ነው “ ብሎ የእሱን የባሕርይ አባትነት፣ የጌታችንን የባሕርይ ልጅነት ገልጾአል፡፡ ይህ መለኮታዊ አስተርእዮ በአንድ በኩል ጌታችን አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን ሲያረጋግጥ፣ በሌላ በኩል ሰው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ሲጠመቅ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ከኀጢአት ነጽቶ በልጅነት ክብር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደሚገባ ያሳያል፤ ከዚህም ጋር መንግሥተ ሰማያት ለጥሙቃን ምንጊዜም ክፍት መሆኗን እናስተውላለን፤ ቅዱስ ዮሐንስ እሱ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃል ብሎ ያስተማረው ትምህርት ምን ማለት እንደሆነም በጌታችን ጥምቀት በግልጽ ታየ፤ ታወቀ፤ ከዚህም የተነሣ ዛሬ ምእመናን በውኃና በመንፈስ ቅዱስ ይጠመቃሉ፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
በዘመነ ዮሐንስ የነበረው የዘረኝነት ዐይነት፣ መለያየት፣ ጠማማነትና የተመሰቃቀለ ማኅበራዊ ሕይወት ሀገራችንን ጨምሮ መላ ዐለማችንን ዛሬም ክፉኛ እየናጠ እንደሆነ የማንክደው እውነታ ነው፡፡ አይሁዳውያን እኛ የአብርሃም ዘርና ልጆች ስለሆን ከሌላ የተሻልን ነን የሚል አመለካከት ሲጎዳቸው እንጂ ሲጠቅማቸው አላየንም፤እኛ ኢትዮጵያውያንም የሁላችን የጋራ ባሕርይ መጠሪያ በሆነው ስም ማለትም ሰው በሚለው የማንነታችን መገለጫ ስም ብቻ ተዋደን ተስማምተንና ተጋግዘን፣ በአንድነትና በእኩልነት በመኖር ፈንታ ኋላ በኀጢአት ምክንያት በተፈጠረው የነገድ፣ የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የመልክዐ ምድር ወዘተ እየተለያየን ራሳችንን በራሳችን እንዳንጐዳ መጠንቀቅ ይኖርብናል፤ ለሰው ከሰው የበለጠ ሌላ ማንነት እንደሌለው ለማሳየት እግዚአብሔር ሁላችንንም ሰው ተብለን እንድንጠራ አድርጎአል፣ በዚህ ተፈጥሮኣዊ ስማችንም አንድ አድርጎ እንደ አዳነን ቅዱስ መጽሐፍ ዋቢአችን ነው፤ እኛም ምን ዐይነት ፍጡር እንደሆን ብንጠየቅ መልሳችን ሰው የሚል እንጂ ሌላ መልስ ሊኖረን አይችልም፤ ታድያ ይህን እውነታ ጨፍልቀን በቋንቋ፣ በነገድ፣ በጎሳ፣ እየተለያየን አንተ የዚህ ነህ፣ አንተ የዚያ ነህ፣ አንተ ውጣ፣ አንተ ቆይ የምንልበት ባህል ከየት የመጣ ነው? ነባሩ ጥንታዊውና የተከበረው ኢትዮጵያዊ ባህላችንስ ይህ ነው ወይ?ይህ ፈጽሞ መስተካከል ያለበት አስተሳሰብ ነው፤ ተራራዎቹ ሸለቆዎቹ እንደልባችን እየተንቀሳቀስን፣ አየራቸውንም እየተጐነጨን በደስታ ልንኖርባቸው፣ ወንዞቹም ውኃ ልንጠጣባቸው፣ ልማት ልናለማባቸው፣ ቋንቋዎቹ ልንግባባባቸው፣ ክልሎቹ ልንተዳደርባቸው ተፈጠሩ እንጂ፣ እኛን ሊለያዩና ሰው መሆናችንን ሊያሳጡን አልተፈጠሩም፤ በመሆኑም የማንነት መገለጫ ሰውነት ብቻ መሆኑን ተገንዝበን ሰውን በሰውነቱ ብቻ ማክበርና መቀበል ይገባናል፤ ቅዱስ ዮሐንስም በትምህርቱ ሰውን በሰውነቱ እኩል ይሁን ያለው ለዚህ ነው፡፡
በአሁኗ ሰዓት በመላ ሀገራችን እየተከበረ የሚገኘው የጥምቀት ሥነ በዓል ሰውን ሁሉ በሰውነቱ ተቀብሎ ጸጋ እግዚአብሔርን እያደለ የሚገኝ በዓል መሆኑን ልብ ብለን እናስተውል፤ በዓሉ ደማቅና ተወዳጅ የሆነውም ለዚህ ነው፤ ተለያይቶ ውበትም፣ ጒልበትም፣ ድምቀትም የለም፣ ተጣልቶም እድገት የለም፤ ስለዚህ በዛሬው ዕለት ለመላ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን የምናስተላልፈው ዐቢይ መልእክትና አደራ ሁላችሁም በኀይለ ቃላት ውርወራ መጐናነጥን ትታችሁ፣ በወንድማዊ ፍቅር በአንድነት ተሰብስባችሁ፣ አለ የተባለውን ሁሉ በውይይትና በውይይት ብቻ ፍቱ፤ መጋጨትን፣ መንገዶች መዝጋትን፣ ሰው ማፈናቀልን፣ ማሳደድን፣ መግደልንና መዝረፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቁሙ፤ በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ያላችሁ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የማንንም ሕይወት እንዳይጠፋ አጥብቃችሁ አስተምሩ፣ምከሩ፣ አስታርቁ፤ ገሥፁ፣ የተሳሳቱትንም ወገኖች መልሱ፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆይ “የቈላ በሬ ጤፉን ሳይቀምሱ ጣፊያውን” እንደተባለው እንዳይሆን ሰላምን እኩልነትን፣ አንድነትን፣ ዲሞክራሲንና ልማትን እናመጣልሃለን ብላችሁ ለምትደክሙለት ሕዝብ ሳትሆኑና ከሕልማችሁ ሳትደርሱ ነገሩ ብልሽትሽት ብሎና የሕልም እንጀራ ሆኖ እንዳይቀር እባካችሁ በውይይት የማይፈታ ነገር የለምና አንድ ላይ ሆናችሁ በመወያየት የዚህን ሕዝብ የአንድነትና የሰላም ጥማቱን ፍቱለት፤
የተወደዳችሁ ወጣት ልጆቻችን፤
የዛሬ አርባ ዓመት የሆነውን ዐይነት አካሄድ በመድገም ታሪካዊ ስሕተትን እንዳትፈጽሙ ተጠንቀቁ!! የምትሹትንና የምትመኙትን ሁሉ ልታገኙ የምትችሉት አንድነትና ሰላም እስካለ ብቻ ነው፤ አርቆ በማየትና አስተውሎ በመራመድ በትዕግሥትና በመቻቻል ሳይሆን በኀይልና በጒልበት የምንፈልገውን እናገኛለን ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ሁሉንም ልታጡ ትችላላችሁና አስተውሉ፤ ወጣቶች ልጆቻችንና አክቲቪስቶች እስቲ እባካችሁ ሰከን በሉና ዕድሉን ለልኂቃኖቻችሁ ስጡ፤ እነርሱ የሚሏችሁን አዳምጡ፤ መደማመጥ፣ መታዘዝ፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ ርኅራኄ፣ ቸርነት ይኑር፤ ሰው ሰው ነውና ማንንም በሰውነቱ አክብሩ፤ ይህ ነው የሰላሙና የአንድነቱ መንገድ፤ በቀል ሰላምን አይወልድም፤ ይቅርታ ግን ሀገርን በሰላም ያጥለቀልቃል፤ ምሕረተ እግዚአብሔርም ከበረከት ጋር ይከተለዋል፤ ስለዚህ ከሁሉ በፊት የሀገር አንድነት፣ የሰላም መረጋገጥ፣ የሰው ልጅ መብት መከበር ይረጋገጥ፤ ሌላው ሁሉ ከዚህ በኋላ ነው፡፡
በመጨረሻም፤ እግዚአብሔር አምላካችን በጥምቀቱ ወደ እርሱ እንደሰበሰበን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ወደ አንድነት አሰባስቦ በይቅርታ፣ በሰላምና በስምምነት ያኖርልን ዘንድ ከልብ እየጸለይን መልካም በዓለ ጥምቀት ይሁንልን እንላለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡