ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራን አምባሳደኖችና ኮር ዲፕሎማቶች፣ የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የተወደዳችሁ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ በአጠቃላይ በዚህ ዐቢይ በዓል የተገኛችሁና በየአካባቢው ሆናችሁ በዓሉን በማክበር ላይ የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ በማየ ጥምቀት አማካኝነት ሀብተ ጽድቅንና ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ያደለን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
‹‹ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ጽድቀ
እንግዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል።››
(ማቴ.3፡15)
ከሁሉ በፊት በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ዕለት በቃልም ሆነ በድርጊት የፈጸማቸውንና ያስተማራቸውን ነገራተ ጽድቅ ሁሉ በልዩ ተመስጦና አንክሮ በማስታወስ ልናከብር ይገባል፡፡ ጌታችን በዚህ ቀን ከተናገራቸው ዐበይት ነገሮች አንዱ ‹‹ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› የሚለው ቃል ነው፤ ይህ መለኮታዊ ቃል ሰዎች በጥምቀት ሱታፌነት የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያገኙበት ከመሆኑ አንጻር የማይታለፍ ጉዳይ እንደሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮሐንስ አስረግጦ የተናገረው ኀይለ ቃል በመሆኑ የበዓሉ ዐቢይ ርእሰ – ትምህርት ነው፡፡ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው ምግባረ ጽድቅ በሰማያውያኑም ሆነ በምድራውኑ ፍጡራን እንዲሁም በሥራዎቻቸው ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ናት፤ ነገሮች ፈራቸውን ለቀው ወደመተረማመስ፣ ወደ ዐመፅ፣ ወደ ግጭት፣ ወደ ክፋት፣ ወደጭካኔ፣ ወደ ፍርድና ቅጣት እንዲያመሩ የሚገደዱበት ዋና ምክንያት ጽድቅ ስትዘነጋ ነው ፡፡
ጽድቅ የእግዚአብሔር ባሕርይ መገለጫ፣ የሥራውና የፍርዱ መለኪያ ሚዛን ናት፤ የውሳኔውም ቀዋሚ ድንበር ናት፤ ጽድቅ ከእግዚአብሔር ባሕርይ ውጭ የሆነች ባዕድ ነገር ሳትሆን፣ የባሕርይ ገንዘቡ ሆና የኖረችና የምትኖር ናት፡፡ ፍጡራን ከጽድቅ መንገድ ሲወጡ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሁሉ ይቋረጣል ወይም ይቆማል፤ ፍጡራን ከጽድቅ መንገድ ሲወጡ ጽድቅ ራስዋ ትወቅሣቸዋለች፣ ካልተመለሱም ትፈርድባቸዋለች፣ ትቀጣቸውማለች፡፡ ጽድቅ የእግዚአብሔር ባሕርይ መገለጫና የፍርዱ መሣሪያ ስለሆነች ከእርሱ ተነጥላ አትታይምና ክፉውን ሁሉ ትጠላለች፤ እስከ መጨረሻም ትዋጋለች እንጂ፣ ከክፉ ነገር ጋር አትተባበርም፤ ፈጽማም አትስማማም፡፡
ፍጡራን ከጽድቅ ጋር ሲጣሉ ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ይጣላሉ፤ ለዚህ አስረጅ የሚሆኑ ብዙ ፍጡራን አሉ፤ በተለይም ከቀዳማውያን ፍጡራን ወገን የሆነው መልአክ እርሱም ሳጥናኤል ‹‹ወሐሰት ርእሰ ዐመፃ፤ ሐሰት የዐመፅ ሁሉ ራስ ናት›› ሲል ቅዱስ መጽሐፍ እንደተናገረ የዐመፅ ሁሉ ራስ የሆነችው ሐሰትን መርጦና ወዶ ከጽድቅ ጋራ በተጣላ ጊዜ በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶአል (መዝ. 26፥12፤ ዘፍ. 3፥1-16፤ ማቴ. 4፥10፤)፡፡ ከጽድቅ ጋር መጣላት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት እንደመሆኑ መጠን ከቅጣት ማምለጥ አይቻልምና ጽድቅ ራስዋ አጥፊን የመቅጣት ኀላፊነት ስላለባት አጥፊውን ፍጡር እርሱም ሳጥናኤልን ቀጥታለች፤ (ዘፍ. 3፡14፤ ቈላ.2፡15፤ ራእ. 12፡9፤)፡፡
ከጽድቅ ጋር የተጋጨ ሌላው ፍጡር የሰው ሁሉ አባት የሆነው አዳም ነው፤ እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና የሚሰጠው ትእዛዝ ሁሉ ከጽድቅ ጋር የሚስማማ እንጂ የሚቃረን አይደለም፡፡ በመሆኑም አዳም ያለ ዐቅሙ አምላክነትን ሽቶ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የጽድቅ ትእዛዝ ስለተላለፈ ጽድቅ ወቀሠችው፤ ፈረደችበት፤ ቀጣችውም፤ በዚህም ምክንያት አዳም ከጽድቅ ጋር በመጋጨቱ እርሱም፣ ልጆቹም በአጠቃላይ ተቀጡ፤ (ዘፍ. 3፥16-24፤ ሮሜ 5፥12-14)፡፡ ነገር ግን ጽድቅ አስተዋይ ናትና በጭፍን ሳይሆን በትክክል ትፈርዳለች፤ ጽድቅ የሳጥናኤልና የአዳም ጥፋት ልዩነት እንዳላቸው አልዘነጋችም፤ ጽድቅ የሳጥናኤል ኀጢአት ሌላ አሳሳችና ገፊ ሳይኖረው በራሱ ነፃ ምርጫና ፍላጎት በሐሰት የፈጸመው ከባድ ጥፋት እንደሆነ ታውቃለች፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሳጥናኤል ወይም በግሪክ ስሙ ዲያብሎስ የስሕተት የአመፅና የሐሰት ምንጭ መሆኑን ሲገልጽ ‹‹እውነት በእርሱ ስለሌለ በእውነት አልቆመም፤ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፤ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና›› ብሎአል፤ (ዮሐ. 8፥44)፡፡ በሌላ በኩል አዳም ጥፋትን ሊፈጽም የቻለው እንደ ዲያብሎስ ከራሱ አንቅቶ ወይም ሆን ብሎ ሳይሆን አምላክ ትሆናለህ በሚል ቅስቀሳ በዲያብሎስ ተገፋፍቶ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦአል፤ (ዘፍ.3. 1-5 ራእ.12፡9)
ስለሆነም የአዳም ጥፋት ከዲያብሎስ ጥፋት የተለየ በመሆኑ በምሕረት እንደሚታይ ጽድቅ ራስዋ ተስፋን ሰጠች፤ ተስፋውም ጽድቀ እግዚአብሔርንና ፍትሐ እግዚአብሔርን በማይቃረን መልኩ እንደሚፈጸም በረጅሙ አናገረች (ዘፍ. 3፥15፤ 22፥17፤ ኢሳ. 53፥፡11፤ ኤር. 23፥5-6)፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ጻድቅ ሳይሆኑ ጻድቅ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር መገናኘት አይቻልም፤ (2ቆሮ.6፡14-16፤ ሮሜ.3፡20-24)፡፡
በመሆኑም ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ የሚችለው ጽድቅን ሲያገኝ ብቻ ነው፤ በዚህ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄ ሆኖ ሊነሣ የሚችለው ዐቢይ ነገር ሰው እንዴት ጽድቅን አግኝቶ ጻድቅ ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ አለው፤ ይኸውም ሰው ጽድቅን ሊያገኝ የሚችለው በዋናነት ከእግዚአብሔር በሚያገኘው ወይም በሚሰጠው ጸጋ እንጂ በራሱ ጥረት ብቻ አይደለም የሚል ነው፤ (ሮሜ 3፥21-22)፡፡ የደሴተ ቆጵሮስ ኤጲስ ቆጶስ የነበረው ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው ይህንን አስመልክቶ ሲናገር “ወሶበ ርእየ ከመ ኢበቊዐ ለአድኀኖ ዓለም ደመ ኵሎሙ ነቢያት ዘተክዕወ ዲበ ምድር እምደመ አቤል ጻድቅ እስከ ደመ ዘካርያስ ወልደ በራክዩ ፈነወ ለነ ወልዶ መድኅነ ማለትም ከጻድቁ አቤል ደም ጀምሮ እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም ዓለምን ለማዳን ወይም ለማጽደቅ እንዳልበቃ ባየ ጊዜ አዳኝ የሆነው ልጁን ላከልን” ብሎአል፡፡
ከዚህ አንጻር ከጽድቀ እግዚአብሔር በስተቀር ሌላ ማጽደቂያ ያልተገኘለት የሰው ልጅ የእርሱ ጽድቅ ለእኛ ተቈጥሮልን በእርሱ የጽድቅ ስጦታ ጻድቃን እንሆን ዘንድ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሥዋዕትነት ተሰጠን፤ (2ቆሮ. 5፥21)፡፡ በእርሱ መሥዋዕትነት በተገኘው ቤዛነት የእርሱ ሕይወት ለእኛ ተሰጠ፤ የእኛ ሞት ደግሞ ለእርሱ ሆነ፤ የምሥራቃውያን ዐምደ ሃይማኖት የሆነው ሶርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ይህንን ሲገልጽ ‹‹ዘዚኣነ ሞተ ነሥአ ወእንቲኣሁ ሕይወተ ወሀበነ፤ የእኛን ሞት እርሱ ተቀበለ፤ የእርሱን ሕይወት ደግሞ ለኛ ሰጠን›› ብሏል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ወበእንተ ኀጣውኢነ ውእቱ ተሰቅለ ዲበ ዕፅ በሥጋሁ ከመ ያውጽአነ እም ኃጣውኢነ ወበጽድቁ ያሕይወነ፤ ማለትም እርሱ ስለ ኀጢአታችን በዕንጨት ላይ በሥጋው ተሰቀለ፤ ከኀጢአታችን ነፃ ያወጣን ዘንድ፣ በእርሱ ጽድቅም ያድነን ዘንድ ብሎአል›› (1ጴጥ. 2፡24)፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት፣ የሕይወትና የጽድቅ መንገድ እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚገባ ይድናል›› ብሎአል፤ (ዮሐ.14፡6) መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ጸጋሰ ወጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ኮነ፤ ጸጋና ጽድቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ›› በማለት ያረጋገጠው ይህንኑ ነው፤ (ዮሐ. 1፥17)፡፡ እንግዲህ ሰው ጽድቅን ሊያገኝ የሚችለው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንደሆነ በዚህ ሁሉ እንገነዘባለን፤
የጽድቅ መገኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆንም ለሰው ሊሰጠው የሚችል በሱታፌ ሃይማኖት ወምግባር እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፤ ጌታችን ሊጠመቅ ወደ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ ‹‹ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል›› ሲል የተናገረው ቃል በሱታፌ ጥምቀት ምክንያት የሚገኘው ጽድቀ እግዚአብሔርን ሲያመለክት ነበረ፡፡ ጽድቀ እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ ተሰጥቶ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በጥምቀት ተጀምሮ በእግዚአብሔር ጸጋና በሰው ሱታፌ እያደገ ሄዶ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ በግልጽ የሚታይና የሚፈጸም ነው፡፡ ጌታችን ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናል ማለቱ እርሱ በመምህርነትና በመሪነት፣ ሰው በተጠምቆ ሱታፌነት፣ እግዚአብሔር አብ በጽድቅ ሰጪነት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በአንጽሖና በአክብሮ፣ የሚገናኙበት የጽድቅ መንገድ ምሥጢረ ጥምቀት መሆኑን ሲያመለክት ነው ፡፡
ሰው ከመጠመቁ በፊት ጽድቅን አያገኝም፤ አይሰጠውምም፤ ምክንያቱም ኀጢአተኛ ነውና፤ ነገር ግን ከጥምቀት በኋላ በተሳትፎ – ጥምቀት የእግዚአብሔርን ጽድቅ ይሰጠዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የጽድቅ ሕይወት አንድ ብሎ ይጀምራል፤ በይቀጥላልም ሰው በሱታፌነቱ ከእግዚአብሔር ጋር ሆኖ በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በሥነ ምግባርም ጭምር ጽድቅን እያሰፋና እያሳደገ ከሠላሳ ወደ ስድሳ፣ ከስድሳ ወደ መቶ ደረጃ ያደርሳል፤ ከበዓለ ጥምቀት የምንማረው ዐቢይ ሃይማኖታዊ ትምህርት ይህ ነው (ማቴ.13፡23)፡፡ እዚህ ላይ ክርስቲያኖች ሁሉ ሊገነዘቡት የሚገባ ዐቢይ ነገር እግዚአብሔር በሁሉም ነገር አሳታፊ አምላክ መሆኑን ነው፤ እግዚአብሔር ምንም እንኳ የሚሳነው ነገር የሌለና ሁሉን የሚችል አምላክ ቢሆንም፣ በሥራው ሁሉ ፍጡራንን በአጠቀላይ፣ በተለይም ሰው የሥራው ተሳታፊ እንዲሆን በተፈጥሮ ሳይቀር ጸጋውን አብዝቶ ሰጥቶታል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ በዘር እንዲባዙ ማድረጉን እናውቃለን፤ ሆኖም መባዛት ያለተባትና እንስት ተሳትፎ እንዲሆን አላደረገውም፤ ቀጣይ የሆነ ዘር ወይም ትውልድ እንዲኖር የተባትና የእንስት ፆታዊ ተሳትፎ ወይም ውሕደት የግድ ያስፈልጋል፤ ይህ የሚያሳየው እግዚአብሔር በሥራው አሳታፊ አምላክ መሆኑን ነው፡፡ የሰው ጽድቅም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ እግዚአብሔር ጽድቅን በጸጋው ቢሰጥም ያለሰው ተሳትፎ ግን የሚገኝ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ለማግኘት ሰው የግድ ማመን አለበት፣ የግድ መጠመቅ አለበት፣ የግድ መቊረብ አለበት፣ የግድ በሥነ ምግባር አጊጦ መኖር አለበት፣ በሌላ አገላለጽ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ጸንቶ መኖር አለበት፣ ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ሰው በጽድቀ እግዚአብሔር ተሳትፎ አድርጎአል ማለት ነው፤ በመሆኑም ሰው በዚህ ብቻ ጻድቅ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይችላል፡፡ በሃይማኖት ላይ የሥነ ምግባር ተሳትፎ ከሌለ ግን ጽድቅ የለም፤ ጻድቅ መሆንም አይቻልም፤ ሥነ ምግባር ከሌለ ሃይማኖቱ ራሱ የሞተ ይሆናል ማለትም ጽድቅን አያስገኝም ተብሎ ተጽፎአልና፤ ጽድቅም ከሌለ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የለም ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነው (ያዕ.2፡18-26፤ ማቴ25፤1-46)፡፡ በዚህ ክርስቶሳዊ አስተምህሮና ሐዋርያዊ ትውፊት መሠረት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ነገረ ድኅነትን በተመለከተ ሃይማኖትና ሥነ ምግባር የማይነጣጠሉና የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች እንደሆኑ በማስረገጥ ሰው ሃይማኖትና ሥነ ምግባርን ጠብቆ በመኖር ይጸድቃል ብላ ታስተምራለች ፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ በተጠመቀበት ዕለት የተላለፈው መለኮታዊ ትምህርት ሰው ሃይማኖትንና ሥነ ምግባርን አንድ አድርጎ መያዝ እንዳለበት የሚያመለክት ነው፤ በዕለተ ጥምቀት ቃል በቃል የተላለፈው የእግዚአብሔር አስተምህሮ ‹‹ይህ ልጄ ነው፤ የሚላችሁን ስሙ›› የሚል ነው፤ (ማቴ3፡17፤ 17፡5)፤ ከዚህ መለኮታዊ ቃል እንደምንገነዘበው ‹‹ይህ ልጄ ነው›› የሚለው ኀይለ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን አምነን እንድንቀበል የሚያስገነዝብ ሲሆን ይዘቱ ሃይማኖትን ይመለከታል፤ (ዮሐ.1፡3)፤ ‹‹የሚላችሁን ስሙ›› የሚለው ቃል ደግሞ ሃይማኖትንና ሥነ ምግባርን የሚመለከት ሆኖ ጌታችን ‹‹በእኔ እመኑ፤ በአባቴም እመኑ፤ መልካም የሠሩ ወደዘለዓለም ሕይወት፣ ክፉ የሠሩ ግን ወደ ዘለዓለም ኵነኔ ይሄዳሉ›› በማለት ሃይማኖትንና ሥነ ምግባርን የጽድቅ ምሰሶ አድርጎ ያስተማረውን ሰምተን በተግባር እንድንፈጽም የሚያስገነዝብ ኀይለ ቃል ነው፤ (ዮሐ. 14፥1፤ 5፥29)፡፡
በመሆኑም ታላቁና ተወዳጁ የጥምቀት በዓላችን ዛሬ ስናከብር የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ዋና መገለጫ የሆነውን ‹‹ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽን (ባልእንጀራ መውደድን)›› በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በተግባር ለመፈጸም ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን መውደዳችንን የምንገልጸው ለቅዱስ ቃሉ ታዛዥ በመሆን ብቻ ነው፤ ባልጀራችንን መውደዳችን የምንገልጸው ደግሞ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ‹‹ያለውን ለሌለው ያካፍል›› ብሎ ያስተማረውን በመቀበልና በተግባር በመፈጸም ባልንጀሮቻችንን እንደራሳችን አድርገን በመውደድ ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ባልንጀሮቻችን የሚለብሱትና የሚጎርሱት፣ የሚጠጡትም ጭምር አጥተው በከባድ ችግር ላይ እንደሚገኙ እየሰማንና እያየን ነው፡፡ በመሆኑም ለነዚህ ባልንጀሮቻችን ወገናዊና ወንድማዊ የሆነ ድጋፍ ይዘን በወቅቱ በፍጥነት ልንደርስላቸው ይገባል፤ ይህም ሌላው የበዓለ ጥምቀት ዐቢይ አስተምህሮና ተቀዳሚ መልእክት ነው ፡፡
በዓለ ጥምቀት ተራራው ዝቅ ይበል፤ ጎድጓዳው ይሙላ፤ ሁሉም ትክክል ይሁን እያለ እኩልነትን፣ በደመወዛችሁ ኑሩ እንጂ ማንንም አትቀሙ እያለ ግብረ ሙስና መጸየፍን፣ ነፍስ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይመልከት እያለ በሃይማኖት መዳንን፣ ለንስሓ የሚሆን ሥራ ሥሩ እያለ የሥራና የአእምሮ ልማትን፣ ግብር ሰብሳቢውም፣ ወታደሩም፣ ፈሪሳዊውም፣ ሌዋዊውም፣ ሕዝቡም ሁሉ በአንድነት በማገናኘት አንድነትን፣ የሰላም ምልክት በሆነች በነጭ ርግብ አምሳል መንፈስ ቅዱስን በመግለጽ ፍጹም ሰላምን ያስተማረን፣ የሃይማኖት፣ የልማት፣ የእኩልነት፣ የአንድነትና የሰላም መምህራችን ነው፡፡ ስለሆነም ጽድቀ እግዚአብሔርን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ተቀብለን፣ የልማት ሥራችንን አጎልብተን፣ የአንድነት፣ የሰላም፣ የእኩልነት፣ የመከባበር፣ የመተማመንና የወንድማማችነት ነባር ዕሤቶቻችንን ጠብቀን የተራቡ ወገኖቻችንን በማገዝና በመርዳት በዓሉን ልናከብር ይገባል፤ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና፡፡
በመጨረሻም፡ ጥምቀት ማለት በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ማለት ስለሆነ በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር ሀገራችንን በልማትና በሰላም – ሕዳሴ ለመገንባት የጀመርነው ሁለተኛው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን መርሐ ግብር በተያዘለት አቅጣጫ በስኬት ለማጠናቀቅ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኙ መላ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የሥራ መስክ በትጋትና በንቃት እንዲረባረቡ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ መልካም በዓለ ጥምቀት ያድርግልን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡