• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ታህሣሥ 28 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ልደት መልእከት፣ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤ የርስተ መንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ በጌታችን በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ የወለደን እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ!!

“ወበዝንቱ ተዐውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም ከመ ንሕየው በእንቲአሁ፤ የእግዚአብሔር ፍቅሩ በዚህ በእኛ ላይ ታወቀ፤ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደዓለም ልኮታልና” (1ዮሐ.4፡9)፡፡

የእግዚአብሔር ባሕርይ ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይስማማውም፤ ጽድቅ እንጂ ሐሰት አይዋሐደውም፤ ብርሃን እንጂ ጨለማ አይቀርበውም፤ ሕይወት እንጂ ሞት በእርሱ ዘንድ የለምና በፍጹም ፍቅሩ እኛን ለመፈለግ ሥጋችንን ለብሶ በመካከላችን ስለተገኘ ለእርሱ የሚገባ የአምልኮ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም በሆነ ፍቅሩ ሰማያትንና ምድርን እንደዚሁም በውስጣቸው የሚገኙትን፣ የሚታዩና የማይታዩትን ፍጥረታት ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶአል፤ ወይም አስገኝቶአል፣ ፈጣሬ ፍጥረታት የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን በየዐይነቱ የፈጠራቸው ፍጥረታት በእርሱ ዘንድ ከሚታወቁ በስተቀር በፍጡራን ዐቅም ተቈጥረው የሚዘለቁ ባይሆኑም በጥቅሉ የሚታዩና የማይታዩ፣ ሕይወት ያላቸውና የሌላቸው ተብለው ሊመደቡ ይችላሉ፡፡

ከፍጡራን መካከል ሕይወት ያለውና በግዙፋኑ በኩል ሊታይ የማይችለው የቀደመ ስሙ ሳጥናኤል የኋላ ስሙ ሰይጣን፣ ወይም ዲያብሎስ የተባለ ረቂቅ መልአክ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ነፃ ፈቃድ ለክፉ ነገር በመጠቀም በፈጸመው ትልቅ በደል ለፍርድና ለቅጣት ተዳርጎአል (ኢሳ. 14፥12-15፤ ይሁዳ 1፥6)፡፡ ይህ ስሑት ፍጥረት በራሱ ስሕተት ሳያበቃ ሕያው ሆኖ በግዘፍ የሚታየውን ሰው በማሳሳት እንደእርሱ ለፍርድና ለቅጣት እንዲጋለጥ አደረገ (ዘፍ 3፥1-24፤ ራእ. 12፥7-9)፡ በዚህም ምክንያት ሰው ሕይወቱን አጣ፤ ሕይወት ማጣት ማለት እግዚአብሔርን ማጣት ወይም ከእግዚአብሔርና ከመልካም ስጦታው መለየት፣ መራቅ፣ መወገድ ማለት ነው፡፡ ዲያብሎስ በዘረጋው ወጥመድ ተሰነካክሎ የወደቀውና ሕይወቱን ያጣው ሰው ለድርብ የሞት ፍርድ ተዳረገ፤ በዚህ ፍርድ መነሻነትም አዳም ከነልጆቹ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ወይም ሥጋው በመቃብር ነፍሱ በገሃነም እንዲቀጣ ተፈረደበት (ዘፍ. 2፥17፤ 3፥16-20)፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱ ነው፤ ከእግዚአብሔር የተለየች ሕይወት ለጊዜው ያለች እንኳ ብትመስል ለዘለቄታው የለችምና በቁም ሳለች የሞተች ናት፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከግንዱ የተለየ ዛፍ ፍሬን ማፍራት እንደማይችል ሁሉ በእኔ የማይኖርም እንደ ቅርንጫፍ ወደውጭ ይጣላል፣ ይደርቅማል፣ በእሳትም ያቃጥሉታል” ሲል ያስተማረን ከእግዚአብሔር ውጭ የሆነ ሁሉ ሕይወትን ጨምሮ ምንም ምን ሊያገኝ የማይችል መሆኑን ለማስረዳት ነው (ዮሐ15፡4-6)፡፡

ከሰው ልጅ ቀዳማዊ ታሪክ በመነሣት የተፈጸመውን እውነታ ስናስተውል ሰው የሕይወት ራስ የሆነውን እግዚአብሔርን በማጣቱ ከባድ የሆነ የሞት ቅጣት እንዳጋጠመው እናያለን፡፡ ከዚህ በኋላ የተነሣው ጥያቄ ሰው ከዚህ የሞት ቅጣት እንዴት ሊድን ይችላል? የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር በልጁ በኩል መልሱን እንደነገረን ሰው ሊድን የሚችለው በፍቅረ እግዚአብሔር ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል ‹‹እግዚአብሔር አንድ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እስከዚህ ድረስ ወዶታል›› ብሎ የድኅነት መነሻውና መድረሻው ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነ ነግሮናልና ነው (ዮሐ. 3፥16-18)።

የጌታችን ደቀ መዝሙር የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደዓለም ልኮአልና የእግዚአብሔርን ፍቅር በዚህ ዐውቀናል፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል››ሲል የሕይወታችን ማግኛ ቊልፍ ነገር ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነ ያረጋግጣል (1ዮሐ. 4፥16)። ሁሉን የፈጠረና ሁሉን የሚችል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን ስቦና ጎትቶ ወደኛ ያመጣው ሌላ ባዕድ ኀይል ሳይሆን በባሕርዩ ውስጥ ያለው ፍጹም ፍቅር ነው፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ፍቅር ምክንያት ወደእኛ መጣ፣ መጥቶም ሥጋችንን ከማይሞተው አካለ መለኮቱ ጋር በማዋሐድ መለያየትን አስወግዶ ወደእርሱ አቀረበን፡፡

የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ መጋቢት 29 ቀን በማሕፀነ ማርያም ሲፈጸም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባሕርየ መለኮት፣ ባሕርየ ሥጋን ገንዘብ አደረገ፤ ባሕርየ ሥጋም፣ ባሕርየ መለኮትን ገንዘብ አደረገ፤ በዚህም መሠረት የአምላክና የሰው ተዋሕዶ ተፈጸመ፡፡ ሰው የሆነው ቃለ እግዚአብሔር ወልድ በተፀነሰ በዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን፣ በታኅሣሥ ወር፣ በዛሬው ዕለት ከቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ልሔም ተወለደ፤ በዳዊት ከተማ በቤተ ልሔም የተወለደው ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋችንን ተዋሕዶ በፈጸመው የኀጢአት ካሳ፣ እኛ ከሞት ፍርድ ነፃ ወጥተን ወደ ሕይወት ለመሸጋገር በቅተናል፤ ይህም የሆነው በፍቅረ እግዚአብሔር ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ በማክበር ላይ የምንገኘው ዐቢይ በዓል በእግዚአብሔር ፍቅር ተመሥርቶ ሰውን ለማዳን የተፈጸመው የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ነው፤ (ሉቃ.2፡6-20)፡፡ የልደተ ክርስቶስ በዓል የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነፃነትና የእኩልነት በዓል ነው፤ በዚህ ዕለት ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን እረኞች በአንድነትና በፍቅር ‹‹በምድርም ሰላም ይሁን›› እያሉ ስለ ሰላም ዘምረዋል፤ ይህ ዕለት ምድራውያን ነገሥታትና በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ እረኞች ፈጣሪያቸውን በእኩልነት ያዩበትና የሰገዱበት፣ በሰማያውያንና በምድራውያን ማለትም በእግዚአብሔርና በሰዎች፣ በሰዎችና በመላእክት መካከል ልዩ ግንኙነት እንደተፈጠረ የተገለጸበት፣ የተበሠረበትና የተዘመረበት ቀን በመሆኑ በዓሉ የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነፃነትና የእኩልነት በዓል ተብሎ ይታወቃል፡፡

የዚህ በዓል ዐቢይ መልእክት ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› የሚል መሆኑን በውል መገንዘብ አለብን (ሉቃ. 2፥14)። እግዚአብሔር ጥላቻን፣ መነቃቀፍን፣ መለያየትን፣ ራስ ወዳድነትን አይወድም ባሕርዩ ፍቅር የሆነ እግዚአብሔር እነዚህን የማይወድ መሆኑን በማወቃቸው ነው ሰማያውያኑና ምድራውያኑ በአንድነት ሆነው ሰላም በምድር ይሁን ብለው የዘመሩ፤ ማንም ይሁን ማን፣ በየትኛውም ደረጃ ወይም አካባቢ ይኑር፣ ከሰላም ውጭ ጥቅሙን ማረጋገጥ የሚችል የለም፣ ሊኖርም አይችልም፤ በሰላም ውስጥ ሆኖ ግን ሁሉንም ማግኘት እንደሚቻል ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ የታየው ውጤት ምስክር ነው፡፡ ዛሬም ዓለማችንም ሆነ ሀገራችን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች በቀላሉ ማምለጥ የሚችሉት ከሁሉ በፊት ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ይዘው ሲጓዙ ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተመላልሶ ሰውን ከሞት ያዳነው ማንንም ሳይጎዳ በሰላም ጎዳና ብቻ ተጒዞ ነው፡፡ ጥላቻና ራስ ወዳድነት ሲያፈርሱና ሲያጠፉ እንጂ ሲያለሙና ሲገነቡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ታይተውም፣ ተሰምተውም፣ በታሪክ ሲደገፉም አይተን አናውቅም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በልማትና በእድገት እየገሠገሠች ያለች፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የነገ ብሩህ ተስፋ ትሆናለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሀገር ነች፤ ይህ ተስፋ እግዚአብሔር ባርኮልን በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም ወዘተ ሳንለያይ መላ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ያስገኘነው የልማት ፍሬ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡

የተገኘው ፍሬ ልማት እየበረከተና እየደለበ ወደፊት እንዲቀጥልና እንዲያድግ እንጂ በማናቸውም ምክንያት ወደኋላ እንዲመለስ ሕዝባችን መፍቀድ የለበትም፡፡ መላው ሕዝባችን በሚገባ ማጤን ያለበት ነገር ቢኖር ምንጊዜም የችግር መፍትሔ ሰላምና ልማት እንጂ ሌላ አማራጭ መፍትሔ የሌለ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም የሀገራችን ሕዝቦች የገናን የሰላም መዝሙር እየዘመሩ ለጋራ እድገትና ለእኩልነት፣ ለሕዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ልማት በጽናት መቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ሰላም ትልቁ የገና ስጦታ ነው፤ ልማትም የህልውና ማረጋገጫ ጸጋ ነው፤ ሁሉንም በእኩል እንጠብቃቸው፡፡

በመጨረሻም፡ በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት ለምግብ ዕጦት የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችን የወገንን እጅ በተስፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፤ እነዚህ ወገኖች ግማሽ አካላችን መሆናቸውን ተገንዝበንና ጌታችን እኛን ለመፈለግ ወዳለንበት የመጣበትን ፍቅር አብነት አድርገን፣ እኛም እነርሱ ወዳሉበት በፍቅር በመሄድ በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና አለን ከጎናችሁ ልንላቸው ይገባል፤ አነሰ ሳንል በወቅቱ ፈጥነን እጃችንን ልንዘረጋላቸውና በአጠገባቸው ሆነን ልናበረታታቸው ይገባል፤ እግዚአብሔር ሁላችንን እንደወደደን እኛም ወንድሞቻችንን በመመገብ፣ በማልበስና ችግራቸውን ሁሉ በመጋራት ለእግዚአብሔርና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ዛሬውኑ በተግባር እንድናሳይ መልእክታችንን በእግዚአብር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ! መልካም የልደት በዓል ያድርግልን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32016-01-07 12:57:192025-01-28 12:58:36ታህሣሥ 28 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ልደት መልእከት፣ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ጥቅምት 12 ቀን እስከ 22 ቀን 2008 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ Link to: ጥቅምት 12 ቀን እስከ 22 ቀን 2008 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ ጥቅምት 12 ቀን እስከ 22 ቀን 2008 ዓ.ም የተካሄደው... Link to: ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም የበዓለ ጥምቀት ቃለ ምዕዳንና...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top