• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ጥር 11 ቀን የ2006 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

“ወለደነ ዳግመ በጥምቀቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባላት፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች እንሆን ዘንድ በጥምቀቱ ዳግመኛ ወለደን” (1 ጴጥ. 5፤ ዮሐ. 3፥5-7)፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን በአርኣያውና በመልኩ መፍጠሩ ሰው በክብር ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነ ክብር ያለው መሆኑን ለመግለጽ እንደሆነ መገንዘቡ አያስቸግርም። ሰው በተፈጥሮው በሰማይም ሆነ በምድር ካሉ ፍጥረታት ሁሉ በተለየ ሁኔታ እንደተፈጠረ በቅዱስ መጽሐፍ ግልጽ ሆኖ ተጽፎአል፤ ይኸውም በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠሩ፣ከምድር አፈር ከተፈጠረ በኋላ በአፍንጫው የሕይወት መንፈስ ከእግዚአብሔር መቀበሉ፣ በፍጥረታት ላይ ገዥ ሆኖ መሾሙና መባረኩ፣ ከሌሎች ፍጥረታት የተለየና የከበረ መሆኑን ያስረዳል፤ (ዘፍ. 1፥26-28 ዘፍ. 2፥7)፡፡

ሰው በተፈጠረበት አኳኋን የተፈጠረ ሌላ ፍጥረት ስለመኖሩ፣ ቅዱስ መጽሐፍ አይገልጽም፤ በመሆኑም ሰው የፍጥረታት ጌታ፣ የፍጡራን ሁሉ ጌጥ፣ የእግዚአብሔር ባሕርይ መገለጫ በመሆኑ፣ ክብሩ ከሁሉም ፍጥረታት በላይ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ፍጹም ፍቅር፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የገዥነቱ ተሳታፊ፣ የመንግሥቱ ክቡር ዜጋ ነው፤ ይሁን እንጂ አንድ በመንግሥት ሥራ ላይ የተሾመ፣ የተከበረና የታመነ ዜጋ ሊያከብረው የሚገባ ሕገ መንግሥት እንዳለ ሁሉ አዳም ሊያከብረው በተሰጠው የእግዚአብሔር ፍጹም ሕግ የተከለከለውን የዛፍ ፍሬ፣ ሕጉን በመጣስ በመብላቱ ከላይ የተገለጹትን በሙሉ አጣ ፡፡

ሰው በፈጸመው የሕግ መተላለፍ ጥፋት፣ ጥፋተኛ ሆኖ ስለተገኘ፣ የሞት ቅጣት ፍርድ ተፈረደበት፤ ቅጣቱም ወዲያውኑ ተፈጸመ፤ ወዲያውኑ የተፈጸመው የአዳምና የሔዋን የሞት ቅጣት የነፍስና የሥጋ መለያየት አልነበረም፤ ቅጣቱ ከእግዚአብሔር አንድነትና ክብር መለየት ነበረ እንጂ፤ ዋነኛውና ትልቁ፣ ሰውንም እጅግ በጣም የሚጎዳው ይህ ሞት ነው፤ ይህ ዓይነቱ የሞት ቅጣት በአዳም ላይ የተፈረደውና የተፈጸመው ወዲያውኑ ነበረ፤ አዳምና ሔዋን ከልብሰ ብርሃን መራቈታቸው፣ በኪሩቤል የነበልባለ እሳት ሰይፍ እየተነዱ ከገነት መባረራቸው፣ ከእግዚአብሔር አንድነት መለየታቸውን የሚያስገነዝብ ነበረ፤ (ዘፍ. 3፡1-24)፡፡

ከእረኛው ተለይቶ የጠፋ ከብት፣ ለአራዊት፣ ለሌቦችና ለሌሎች አደጋዎች የተጋለጠ እንደሚሆን ሁሉ፣ አዳምና ልጆቹም፣ ከእግዚአብሔር አንድነት ከተለዩ በኋላ፣ ለጨካኙ አውሬ ለዲያብሎስ የኀጢአት ግዛትና ለልዩ ልዩ ግብረ ኃጣውእ የተጋለጡ ሆኑ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘመነ ክርስቶስ ድረስ፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር አንድነት እንደተለየ ወይም በነፍሱ እንደሞተ ቆየ፤ (ሮሜ. 5፡14)፡፡ ይሁን እንጂ የእግዚብሔር ምሕረት ከቊጣው ጎን ስለማይለይ፣ በምሕረቱ ሰውን አሰበው፤ ቀድሞ ወዳጣው ልጅነቱና ክብሩ ሊመልሰው፣ አንድነቱን የሚመሠርትበት መንገድ አዘጋጀ፤ ይህንንም ተስፋ በነቢያት አማካኝነት ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲያናግር ከቆየ በኋላ፣ ዘመኑ ሲደርስ የባሕርይ ልጁ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደዚህ ዓለም ላከ፤ እርሱም ከሰው ዘር ከተገኘች ከቅድስት ድንግል ማርያም ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ፣ ሰውን ወደ እግዚአብሔር አንድነት የመመለስ ሥራውን አንድ ብሎ ጀመረ፤ ይህ የእግዚአብሔር ድንቅ ምሕረት፣ በሰው ልጅ መንፈሳዊ ታሪክ፣ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ በኀጢአትና በበደል ምክንያት ከእግዚአክሔር አንድነት ተለይቶና ከልጅነቱ ተራቊቶ የነበረው የሰው ሥጋ በተዋሕዶተ መለኮት ጭራሽ የአምላክ አካል ሆነ፣ በዚህም ጥንት ሲፈጠር እንደነበረው የጸጋ ገዢነት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በላይ የአምላክነት ሥልጣን ተቀዳጀ፤ እግዚአብሔር ሰውን ያከበረበት ትልቁ ምሥጢር ይህ የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ ነው “ኀበ ሀለወት ብዝሕት ኀጢአት በህየ ትበዝኅ ጸጋ እግዚአብሔር — ኀጢአት በበዛችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች” ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ የገለጸው ይህንን ነው፤ (ሮሜ. 5፥18-21)፤ ጌታም በቅዱስ ወንጌል በምሳሌ አመሥጥሮ ያስተማረው ይህንን ነው፤ (ሉቃ. 15፥1-32)፡፡

“አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” (ዘፍ. 33) ተብሎ በእግዚአብሔር ቃል የተነገረው የሰው ልጅ መጻኢ ተስፋ ድኅነትና ሉዓላዊ ክብር በምሥጢረ ተዋሕዶ እውን ሆነ፤ ምክንያቱም አካለ መለኮትን በመዋሐድ፣ በመለኮት ርስትነት የባሕርይ አምላክ ሆኖ በክብር የተገለጸው፤ በኀጢአት ብዛት ተዋርዶ የነበረው የሰው ሥጋ እንጂ፣ ንጹሓን የተባሉ ቅዱሳን መላእክት አይደሉምና፤ (ዕብ. 2፡2፡16)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በማሕፀነ ማርያም ሥጋችንን ተዋሕዶ ከተፀነሰ በኋላ፣ ሕገ ተሰብኦን ጠብቆ ተወለደ፤ በተወለደበት ቀንም ልዩና ፍጹም በሆነ ፍቅሩ፣ ሰውን በመውደዱ፣ በምድርም ላይ ሰላምንና ዕርቅን በመመሥረቱ፣ እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ ምስጋና ይገባዋል ብለው፣ የሰማይ ሠራዊት የአንድነቱን መመለስ በመዝሙራቸው አበሠሩ፤ (ሉቃ. 2፥14)፡፡ ከልደቱም በኋላ፣ ከኀጢአት በቀር ሕገ ተሰብኦን ወይም የሰው ሕገ ተፈጥሮን እየፈጸመ እስከ ሠላሳ ዓመት በሕዝቡ መካከል ለእግዚአብሔርነቱ በሚገባ ሞገስ ጸጋና ጥበብ አደገ፤ (ሉቃ. 2፥52)፤ ከዚያም የሰው ዘር በሙሉ፣ ቀድሞ ያጣውን ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት መኖር፣ በልጅነት መከበርና፣ በእግዚአብሔር መንግሥት በዘለዓለማዊ ሕይወት መኖር፣ እንደገና ማግኘት የሚቻልበትን ምሥጢር፣ ለሰዎች ለመግለጽ፣ ለማሳየትና ለማስተማር፣ ከዚህም ጋር የአንድነቱንና የሦስትነቱን ምሥጢር ለዓለም ሁሉ በግልጽ ለማሳየትና ለማስገንዘብ፣ በተወለደ በሠላሳ ዓመተ ምሕረት፣ ጥር ዐሥራ አንድ ቀን፣ በዮሐንስ እጅ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ፣ ለሰው ልጅ ፍጹም ክብርንና ድኅነትን የሚያጎናጽፉ ሁለት ዐበይት ነገሮች ተፈጽመዋል፤ እነርሱም፡- የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት፣ እግዚአብሔር በምሕረቱ ለሰው ልጅ ያዘጋጀውን ትልቅ የድኅነት ምሥጢርን የሚያመለክቱ ነበሩ፡፡

በዕለተ ጥምቀት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መሐል ቆሞ ሲጠመቅ፣ እግዚአብሔር አብ “ይህ የምወደው ልጄ ነውና እርሱ የሚላችሁን ስሙ” ብሎ ሲመሰክር፣ መንፈስ ቅዱስም የሰላም የፍቅርና የደግነት ተምሳሌት በሆነች ነጭ ርግብ አምሳል፣ በጌታችን ላይ ሲወርድ፣ የእግዚአብሔር ሦስትነት በግልጽ ታወቀ፤ ከዚያ በፊት ብዙ የዓለም ፈላስፎችና የአይሁድ ሊቃውንት፣ ግራ ተጋብተውባቸው የነበሩት፣ መንፈሰ እግዚአብሔር (ዘፍ1፡2) እና ጥበበ እግዚአብሔር ወይም ቃለ እግዚአብሔር (መዝ. 32፥61፣ ምሳ 8፥1-36፣ 9፥1-6) የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሥጢራዊ ቃላት፣ የተለየ ሦስትነት ያላቸው የእግዚአብሔር አካላትን የሚገልጹ መሆናቸው በዚህ ቀን ታወቀ፣ ተገለጸ፡፡ ጌታችንም ታላቅ ነቢይ ወይም ዕሩቅ ብእሲ (ተራ ሰው) ሳይሆን ለአባቱ አንድ የባሕርይ ልጅ የሆነ፣ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑ ቀደም ሲል በዮሐንስ ቀጥሎም በእግዚአብሔር አብ ምስክርነትና በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ርደት ተገለጸ፤ ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን የሚገልጽ ክሥተት ነበረ ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ጌታችን ሲጠመቅ ሰማያት መከፈታቸው፣ እግዚአብሔር በሦስትነት መገለጹ፣ በመጠመቅ ላይ የነበረው እግዚአብሔር ወልድ የእግዚአብሔር አብ ልጅ መሆኑ መረጋገጡ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ መውረዱ፣ በምሥጢራዊ ይዘታቸው ሲታዩ፣ የሰው ልጅ በሥሳሌ ስም በተጠመቀ ጊዜ የሚያገኘውን ጸጋ እግዚአብሔርና ሰማያዊ ክብር ምን ያህል ታላቅ መሆኑን የሚያስረዱ ነበሩ፡፡ ይኸውም ሰማያት መከፈታቸው፡- አዳም ከገነት ሲባረር የተዘጋው የእግዚአብሔር መንግሥት ለተጠመቁ ሰዎች ክፍት መሆኑን፣ ብሩህ ደመና መታየቱ፣ አዳም በበደለ ጊዜ ያጣውን የልጅነት ልብሰ ክብር ለተጠመቁ ሰዎች እንደገና የሚሰጥ መሆኑን፣ እግዚአብሔር አብ ይህ ልጄ ነው ማለቱ፡- የተጠመቁ ሰዎች እግዚአብሔር ልጆቼ ናችሁ ብሎ በልጅነት ክብር የሚቀበላቸው መሆኑን፣ መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል በጌታችን ላይ መውረዱ፣ በተጠመቁ ሰዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ አድሮባቸው እንደሚኖርና፣ ቀድሞ በአዳም ጊዜ ያጡትን ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት የመኖር ጸጋ የተመለሰ መሆኑን፣ የሚገልጽ አምላካዊ ምሥጢር ነበረ፤ (ማቴ. 3፥16-17፤ ማር. 1፥9-11፤ ሉቃ. 3፥21-22)

በመሆኑም ቀደምት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ይህን ሁሉ ምሥጢር የተገለጸበትን ሁናቴ በትክክል ለመግለጽ፣ የጥምቀትን በዓል ‹‹አስተርእዮ (Epiphany)›› ማለትም የመገለጥ፣ የመታወቅ፣ የመታየት በዓል ብለው ሰይመውታል፤ በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን ከጥር ዐሥር ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ያለውን ጊዜ፣ ‹‹አስተርእዮ›› ብላ በመሰየም የልደቱን፣ የግዝረቱን፣ የእድገቱን፣ የጥምቀቱንና የቃና ዘገሊላ ተኣምሩን በማስታወስ ትዘምራለች፣ ትጸልያለች፤ ፈጣሪዋን ታመልካለች፤ (ሉቃ. 2፥21፤ ዮሐ. 2፥1-11)፡፡ ከዚህ አኳያ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የነበረውንና ያለውን ግንኙነት ስንመረምር፣ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ሰውን በምሕረቱ ሲፈልገውና ይቅር ሲለው፣ ጸጋውንም አብዝቶ ሲሰጠው እናያለን፤ በተቃራኒው ደግሞ ሰው በተደጋጋሚ ሁል ጊዜ በኀጢአትና በስሕተት እየተሰነካከለ ሲወድቅ፣ ወገኑንና ፈጣሪውን ሲያሳዝን እናያለን፡፡ ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ይህንን የስሕተት ታሪክ በማረምና በመለወጥ፤ ሁልጊዜ በምሕረትና በፍቅር ዐይን የሚንከባከበውን ፈጣሪ በፍቅር ሊከተለው ይገባል ፡፡

እግዚአብሔር ከእርሱ አንድነት ከተለየንና ከጠፋን የጠላት መረገጫም ሆነን ለብዙ ሺሕ ዘመናት ከቆየን በኋላ የበደልነውን እኛን በፍጹም ፍቅሩ፣ በምሕረቱና በይቅርታው በጥምቀትና በቅዱስ ቍርባን አማካኝነት፣ እንደገና አንድነታችንን መልሶ ወደእርሱ አቀረበን፤ ወደ መንግሥቱም ሰተት ብለን እንድንገባ በዛሬው ዕለት ምሥጢሩን ገለጸልን፤ ሞት እርሱም ከእግዚአብሔር መለየት ቀረ፡፡ ስለዚህ የተደረገልንን ምሕረትና ይቅርታ እያሰብን እርሱን በማምለክና በመከተል፣ እርስ በርሳችን በመዋደድና በመከባበር፣ ካለን ሀብት ለተቸገረ ወገን በመለገስ፣ የኛ ያልሆነውን ባለመንካት፣ እግዚአብሔር በበረከት የሰጠንን ሀገር ለማልማት ጠንክረን በመሥራት፣ ሰላምንና ፍቅርን ሁል ጊዜ በመጠበቅ፣ ለእርሱ ያለንን ውግንና ለመግለጽ የቻልነውን ያህል መልካም ሥራ በመሥራት፣ ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጽ፡፡

ከዚህም ጋር ዛሬ የሀገራችን አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ የሚገኘው የዜጎቻችን ሕገ ወጥ ዝውውርና በስደት አገር እየደረሰባቸው ያለውን ዘግናኝ መከራ በዘላቂነት ማስቆም ይኖርብናል፡፡ ይህን መሰል ማኅበራዊ ችግር መግታት የምንችለው ያለንን ሀገራዊ ሀብት ከሙስና፣ ከምዝበራና ከብክነት በጸዳ መልኩ ጠብቀን በሀገር ልማት ላይ ማዋል ስንችል ነው፡፡ የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቊልፍ በሁሉም አቅጣጫ መጠነ ሰፊ የሆነ ልማትን በማስፋፋት፣ ወጣቱ ትውልድ በሥራ እንዲጠመድ ማድረግ ነው፡፡ ልማት ካለ ብልጽግና አለ፣ ብልጽግና ካለ ሰው በሀገሩ ሠርቶ መኖር ይችላል፣ ሰው በሀገሩ ከኖረ ክብሩና ደኅንነቱ የተጠበቀ ይሆናል፡፡ ልማት የመልካም አስተዳደር ውጤት ነው፤ ስለሆነም “ደመወዛችሁ ይብቃችሁ” የሚለውን የጥምቀት ሃይማኖታዊ ትምህርት፣ መንግሥታዊም ሆኑ ሕዝባዊ ድርጅቶች እንደዚሁም ሁሉም የሃይማኖት ተቅዋማት ሊቀበሉት፣ ሊጠብቁትና ሊያከብሩት ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ ያላትን ሀብት በትክክል በመጠበቅ በሃይማኖታዊና በሀገራዊ ልማት ላይ ለማዋል፣ እንደዚሁም በሁሉም መስክ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች ፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ስም በተለያየ አደረጃጀት ተደራጅተው በሥርዋ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሁሉ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን፣ ሕጋዊነትንና ኀላፊነትን ባረጋገጠ መልኩ ብቻ እንዲሠሩ፣ ብቻ ሳይሆን የሕዝበ ክርስቲያኑን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ፍላጎትን እንደዚሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄን መመለስ በሚያስችል ሁኔታ እንዲሠሩ የማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ በዚህም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከቤተ ክርስቲያናችን ጎን እንደሚሆን እናምናለን፤ የጥምቀትን በዓል በትክክል አክብረናል ማለት የምንችለው “ያላችሁ ይብቃችሁ፤ ማንንም አትቀሙ፤ የሥነ-ምግባር ፍሬ ይኑራችሁ፤ ሀብት ያለው ለሌለው ያካፍል” የሚለውን ሕያው ቃል በሚገባ ስንተገብር ነው፡፡ ስለሆነም በዓላችንን ስናከብር ምንም ጊዜም ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን ማእከል በማድረግ፣ ለችግሮቻችን መፍትሔ በመሻት፣ በየዓመቱ የተሻለ የእድገት ለውጥ ለማስመዝገብ ቃል በመግባት፣ ብሩህ ራእይና ተስፋ ሠንቀን በዓሉን ልናከብር ይገባል፡፡

መልካም የጥምቀት በዓል ያድርግልን!

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ! አሜን ፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc2014-01-19 10:26:312024-12-05 10:28:22ጥር 11 ቀን የ2006 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ታኅሣሥ 29 ቀን የ2006 ዓ.ም. የልደት በዓል አስመልክቶ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ታኅሣሥ 29 ቀን የ2006 ዓ.ም. የልደት በዓል አስመልክቶ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ታኅሣሥ 29 ቀን የ2006 ዓ.ም. የልደት በዓል አስመልክቶ... Link to: የካቲት 16 ቀን የ2006 ዓ.ም ዐቢይ ጾምን አስመልክቶ ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: የካቲት 16 ቀን የ2006 ዓ.ም ዐቢይ ጾምን አስመልክቶ ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የካቲት 16 ቀን የ2006 ዓ.ም ዐቢይ ጾምን አስመልክቶ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top