ነሐሴ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ በዓለ ዕርገት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በመላው ዓለምና በሀገር ውስጥ ሆናችሁ፣ በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቅድስት ድንግል ማርያም ተስባችሁ፣ የጾመ ፍልሰታ ለማርያምን በጾም ፣ በጸሎት፣ በምጽዋት፣ በአምልኮና ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል ያሳለፋችሁ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት በሙሉ፡፡

በቅዱስ አጠራሩ ወደ እርሱ ያቀረበን፣ ከቅዱሳን ጋር ሰማያዊ ርስቱን እንድንካፈል ያደረገ፣ ሰውን የሚወድ፣ መሓሪውና ይቅር ባዩ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ፍልሰታ ለቅድስት ድንግል ማርያም በሰላም አደረሳችሁ!!

“እስመ ኅሉቀ ወምቱረ ነገር ይነግር እግዚአብሔር ውስተ ዓለም ዘሀለዎ ይግበር
እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ ያደርገው ዘንድ ያለውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ይናገራል።”
(ሮሜ 9÷28)፡፡

ይህንን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትምህርተ ወንጌል መርሐ ግብር በመከታተል የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፣ በዛሬው ትምህርታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ነገረ ትንሣኤ እንማራለን፤ በዚህ መነሻነትም እግዚአብሔር ከሞት በኋላ ስላለው አጠቃላይ ዘለዓለማዊ ሕይወት የገለጸልንን እንሰማለን፡፡ በተለይም የእኛ የሰው ልጆች ትልቁና የመጨረሻው ተስፋችን ትንሣኤ ሙታን ስለሆነ በዚህ ዙሪያ እግዚአብሔር በተግባርና በትምህርት የገለጸልንን እንመለከታለን፤ ስለሆነም ቃሉን ሰምተን እንድናስተውልና ለእርሱ ታዛዥ ሆነን በቃሉ እንድንኖር እግዚአብሔር ዐይነ ልቡናችንን ያብራልን፡፡

የትምህርታችን ርእስ፦ “እስመ ኅሉቀ ወምቱረ ነገረ ይነግር እግዚአብሔር ማለትም እግዚአብሔር ያደርገው ዘንድ ያለውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ይናገራልና” የሚል ነው ፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ እንደተጻፈው የሙታን መነሣትን በተመለከተ እግዚአብሔር ያለቀና የተቈረጠ ጉዳይ እንደሆነ በብዙ ቦታ በማያሻማ መልኩ አሳውቆናል፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ሥራ ለወዳጆቹ ለነቢያት ሳይገልጽ የሠራበት ጊዜ የለም፣ ሲናገርም ግልጽና የማያሻማ አድርጎ በቊርጥ እንደሚያሳውቅ የርእሳችን ኀይለ ቃል ያሳያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በነቢዩ በአሞጽ አድሮ እንደገለጸው “እስመ አልቦ ዘይገብር እግዚአብሔር ዘኢተናገረ ወዘኢከሠተ ለአግብርቲሁ ነቢያት፤ በእውነት ጌታ እግዚአብሔር (ምሥጢሩን) ለባሪያዎቹ ለነቢያት ያልገለጸውናን ያልተናገረውን ምንም አያደርግም” ብሏል (አሞ. 3÷7)። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ለወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን ሥራ ለወዳጆቹ ሳይገልጽ እንደማይሠራ ያስገነዝባሉ።

እኛም ኅሊናችንን እና መንፈስ ቅዱስን አስተማሪ፣ መሪ አድርገን ነገሩን ስናጤነው ትክክለኛ መሆኑን ለመረዳት አስቸጋሪ ሆኖ አይታይም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሥራዎቹን ሁሉ ከመሆናቸው በፊት ለነቢያቱ እየገለጸ እንደሠራ፣ ለነቢያቱ ከገለጸውም አንዳች ስንኳ ሳያስቀር እንደፈጸመ በብዙ ቦታ ተጽፎ እናገኘዋለንና ነው፤ ይኸውም እውነት እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ፣ በታሪክ ፍጻሜ፣ በሥነ ምድር ጥናት ሳይቀር የተረጋገጠና በየጊዜው እየተረጋገጠ ያለ ሐቀ ነው፡፡ እግዚአብሔር ካሁን በፊት ተናግሮ ሳይፈጽመው የቀረ ነገር እንደሌለ፣ ለወደፊትም ከተናገረው ውስጥ የሚቀር ነገር እንደሌለ መገንዘብ ከእኛ ከፍጡራኑ ይጠበቃል፡፡

እግዚአብሔር ግልጽ አድርጎና በማያወላውል ሁኔታ ከተናገረው ውሰጥ ያልተፈጸመው አንዱና ዋነኛው የትንሣኤ ሙታን ነገር ነው፤ ይህም ቢሆን ፍጻሜው ስላልደረሰ ጊዜውን እየጠበቀ ያለ ጉዳይ እንጂ የሚቀር ሆኖ አይደለም፤ ከዚህ አኳያ እግዚአብሔር ስለ ትንሣኤ ሙታንና ስለቀጣዩ ለዘለዓለማዊ ሕይወት በትምህርትም፣ በቃልም፣ በተግባርም አስተምሮአል አሳይቶአልም፡፡ በእግዚአብሔር ቊጣ አጠገብ ምሕረቱም አይለይምና ሰዎችን ከኀጢአታቸው የተነሣ ተቈጥቶ ከገነት ካስወጣ በኋላ ፍጡራን የአቤልን መሞት በተረዱበት ማግስት ሄኖክን ሳይሞት እንዳለ ከነሥጋው ወደ ሕይወታዊ ዓለም መውሰዱ ሞት ብቻ ሳይሆን ከሞት በኋላም ሕይወት እንዳለ እግዚአብሔር ለሰዎች የተናገረበት ክሥተት ነበረ፤ ሰዎች ይህንን የሄኖክን አለመሞት አይተው በተስፋ መሞላታቸውን ሲያመለክት ከአበው አንዱ “በአቤል አፍርሆሙ ወበሄኖክ አንቅሆሙ ማለትም በአቤል መሞት አስደነገጣቸው ወይም አስፈራቸው፤ በሄኖክ አለመሞት ደግሞ አነቃቃቸው ” ሲል ተናግሮአል፡፡

በይቀጥላልም እነ ኤልያስ፣ እነ ዕዝራ ሳይሞቱ እንዳሉ ወደ ሕያዋን ዓለም ሲወሰዱ፣ እንደዚሁም እግዚአብሔር ለአርእስተ አበው የገባው ዘለዓለማዊና የሕይወት ቃል ኪዳን ጥልቅና እስከ ወዲያኛው ዓለም ድረስ የሚዘልቅ መሆኑን ግልጽ እየሆነ ሲመጣ፣ ከዚህም ጋር ነቢዩ ኤልያስ አንድ ምዉትን ሲያስነሣ፣ የእርሱ ደቀ መዝሙር የነበረ ኤልሳዕም በአጥንቱ ንክኪነት ሳይቀር ሁለት ሙታንን ሲያስነሣ፣ ነቢዩ ዳንኤልም “በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎቹ ይነቃሉ” ብሎ ሲናገር የትንሣኤ ሙታን ነገር ያለቀና የደቀቀ መሆኑ ታወቀ፤ ነቢዩ ኢሳይያስም “ሙታን ይትነሥኡ ወየሐይዉ እለ ውስተ መቃብር፤ ሙታን ይነሣሉ በመቃብር ያሉትም ይድናሉ በሕይወትም ይኖራሉ” ሲል የሙታን ትንሣኤን አይቀሬነት አስረድቶአል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ወልድ ሥጋችንን ለብሶ በዚህ ዓለም በተገለጠ ጊዜ ወልደ መበለትን፣ ወለተ ኢያኢሮስን፣ አልዓዛርን፣ አምስት መቶ ቢጽን ከሞት ከማስነሣቱም ሌላ ስለ ትንሣኤ ሙታን በሰፊው ማስተማሩን፣ ከዚህም ሌላ በትንሣኤ ሙታን እምነት ያልነበራቸው ሰዱቃውያን የተባሉ የአይሁድ ክፍሎች ስለ ትንሣኤ ሙታን ጉዳይ መስቀለኛ ጥያቄን ባቀረቡለት ጊዜ የእግዚአብሔር ኀይልና የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል ባለማወቅ ስሕተት ላይ መውደቃቸውን ገልጾ ሙታን እንደሚነሡ፣ ሰማያዊ ሕይወታቸውም እንደ መላእክት እንደሚሆን አስረግጦ ነግሮአቸዋል፡፡ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ነገረ ትንሣኤ ሙታንን በማያወላውልና በማያሻማ ሁኔታ ለዓለም በቊርጥ ተናግሮአል፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቻችን ሕዝበ ክርስቲያን፤

በየዓመቱ በጾም፣ በጸሎት፣ በአምልኮተ እግዚአብሔር፣ በቅዳሴ፣ በውዳሴና፣ ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል የምናከብረው የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ፍልሰታ ወይም በዓለ ትንሣኤ ከዚህ በላይ ከተገለጸው ነገረ ትንሣኤ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም ለስድሳ አራት ዓመታት ያህል በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጥር ሃያ አንድ ቀን ጽርሐ ጽዮን ውስጥ በሚገኘው በባለ አደራው በዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ቤት ዐርፋለች፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ነፍስ በእደ እግዚአብሔር ፣ በይባቤ መላእክት፣ ወደ ብርሃናዊውና ሰማያዊው ዓለም ስትወሰድ፣ ሥጋዋ ደግሞ ጌቴሴማኒ ውስጥ በሚገኘው በወላጆቿ መቃብር ለማሳረፍ ቅዱሳን ሐዋርያት ሥጋዋን ተሸክመው ጒዞ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን የክርስትናውን እምነትና አስተምህሮ ያልተዋጠላቸው የአይሁድ ወገኖች ሥርዐተ ቀብሯ በሰላም እንዳይፈጸም ከመዶለታቸውም ሌላ ቅዱስ የሆነው ሥጋዋን ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅና ለመውሰድ ሞከሩ፡፡

ይህንን ሙከራ ያደረገ ታውፋንያ የሚባል ሰው ነበረና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እሱን ቀጥቶ ቅዱሱን የእመቤታችን ሥጋን ከባለ አደራው ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወደ ገነት ወሰደው፤ በዚህ ሁኔታ የቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ በዚያ እንዲቀመጥ ሆነ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ግን ወደ ወንድሞቹ ወደ ሐዋርያት ተመልሶ የድንግል ማርያምን ቅዱስ ሥጋ በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር መቀመጡን ለሐዋርያት ነገረ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወኵሎ ዘሰአልክሙ በስምየ ይትገበር ለክሙ፤ በስሜ የምትለምኑት ሁሉ ይደረግላቸኋል” ብሎ የገባላቸውን ቃል ኪዳን በመከተል የቅድስት ድንግል ማርያም አስከሬን ያለበትን ቦታ ማየትና ቅዱሱ ሥጋዋን መሳለም እንዲችሉ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ዐሥራ አራት በጾምና በጸሎት ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን ደጅ ጸኑ፡፡ጌታችንም እንደ ቃሉ ጸሎታቸውንና ጾማቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ዐሥራ አራት ቀን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥጋን አምጥቶ ሰጣቸው፤ እነሱም ሥጋዋን ተቀብለው በታላቅ ክብር በጌቴሴማኒ ውስጥ በወላጆችዋ ርስት ቀበሩአት፡፡

ከዚህ በኋላ የእመቤታችን ሥጋን በተቀበረ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ነፍሷን ከሥጋዋ ጋር አዋሕዶ በማስነሣት ወደ ብርሃናዊው ዓለም ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርጎአታል፡፡ በዕርገቷ ጊዜ በሕንድ ሀገር ቅዱስ ወንጌልን እያስተማረ የነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በደመና ሰማይ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ፣ እመቤታችን በሰማያውያን ሠራዊት ታጅባ በመላእክት ዝማሬና በቅዱሳን ይባቤ ስታርግ አገኛት፡፡ቅዱስ ቶማስ ከነበረው የድንግል ማርያም ጽኑ ፍቅር የተነሣ በቁጭት በትንሣኤሽ ቀን ሳልገኝ ቀረሁን! ብሎ ሲያዝን፣ አይዞህ ወዳጄ ቶማስ ወንድሞችህ ሐዋርያትም በክብር ገንዘው ቀበሩኝ እንጂ ትንሣኤዬን አላዩም፤ አንተ ብቻ ነህ ትንሣኤዬን ያየህ፤ ስለዚህ እኔን የገነዙበት ሰበን (መጐናጸፊያ) ለሁላችሁም ለበረከት እንዲሆናችሁ ይኸው ሰጥቻችኋለሁ ብላ በመስጠትና በማጽናናት ትንሣኤዋን ለሐዋርያት እንዲያበሥር ነግራው ዐረገች፡፡ ቅዱስ ቶማስም የተሰጠውን ሰበን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ከሐዋርያት ጋር ተገናኘ፤ ሐዋርያትም በበኩላቸው ጌታ የእመቤታችንን ሥጋዋን እንደሰጣቸውና በክብር ገንዘው እንደቀበሯት ነገሩት፤ ቅዱስ ቶማስ ግን በያዘው ሰበን ትንሣኤዋን ለመግለጽ ስለፈለገ “ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” ብሎ ተከራከራቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ነገሩ እውነት እንደሆነ ለመግለጽና እርሱን ለማሳመን ሲል መቃብሯን ቈፈረ፤ ሆኖም ሥጋዋን አላገኘም፤ ቅዱስ ጴጥሮስና ሐዋርያት በሁኔታው ደነገጡ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ እኔ ብቻ ከምነግራችሁ እናንተም ራሳችሁ አይታችሁ እንድታምኑ ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንማ ተነሥታ አርጋለች፤ እርሷን የገነዛችሁበት ሰበንም ለወንድሞቼ ለሐዋርያት ለበረከት እንዲሆናቸው ስጣቸው ብላኝ ይኸው ይዤ መጥቻለሁ ብሎ አሳያቸው፤ እነሱም ነገረ ትንሣኤዋን በመስማታቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የተገነዘችበትን ሰበን ተካፈሉት፡፡

ዛሬ በምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናትና በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ከመስቀል ጋር የሚያዘው ሰበን የእመቤታችን ትንሣኤ መታሰቢያ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ለቶማስ የተገለጸውን ነገረ ትንሣኤዋ ለእነርሱም እንዲገለጸላቸው በመሻት በድጋሚ በዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ጾምና ጸሎት ያዙ ሱባዔም ገቡ፤ አሁንም ጌታችን ጸሎታቸውንና ጾማቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ዐሥራ አምስት ቀን ሐዋርያትን ከያሉበት ሀገረ ሰብከት በደመና ሰማይ ሰበሰባቸው፤ በበነጋው ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ጌታችን እመቤታችንን፣ ቅዱሳን መላእክትን፣ ከአዳም ጀምሮ እስከዚያው ያሉትን ቅዱሳን ሁሉ አስከትሎ ተገለጠላቸው፣ ጸሎተ ቅዳሴን አድርሶ ቅዱስ ቊርባንን አቀበላቸው፤ በዚህ ሁኔታ ትንሣኤዋን ከገለጸላቸው በኋላ ይህንን ትንሣኤዋን እንዲያስተምሩ አዘዛቸው፤ ለእርሷም ሐዋርያት ለፍቅሯ ሲሉ በጾሙት በጾመ ፍልሰታ ጾምን የጾመ፣ ቅዱስ ቊርባንን የተቀበለ፣ የተራበውን ያበላ፣ የተጠማውን ያጠጣ፣ የታረዘውን ያለበሰ እምርልሻለሁ ብሎ ቃል ኪዳን በመግባት በመጣበት አኳኋን ወደ ሰማያት አርጓል፡፡

ጌታችንም ሆነ ሐዋርያት የሠሩትን ተኣምራትና ምግባር ትሩፋት እንደዚሁም ያስተማሩትን ትምህርት ሙሉ በሙሉ በጽሑፍ እንዳልሰፈረ በቅዱስ መጽሐፍ የተረጋገጠና በዮሐ ፳፩÷፳5 ተጽፎ የምናገኘው ሐቅ ነው፡፡ በመሆኑም ቅዱሳን ሐዋርያት በመልእክታቸው ውስጥ በጽሑፍ የሰፈረውን ብቻ ሳይሆን በትውፊትና በቃላቸው ያስተላለፉትንም ጭምር አጥብቀን እንድንይዝ “ወንድሞች ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ሁሉ ወግ (ትምህርት) ያዙ” ብለው አስተምረውናል፤( ፪ ተሰ ፪.፲5) ቅዱሳን ሐዋርያት በቃል ካስተማሩት ውስጥ አንዱ ፍልሰታ እያልን የምንጠራው የቅድስት ድንግል ማርያም ነገረ ትንሣኤ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዕርገተ ክርስቶስ በኋላ በአንደኛው ዓመት፣ ከልደተ ክርስቶስ ደግሞ በሠላሳ አራተኛው ዓመት ማለትም ሁሉም ሐዋርያት በሕይወተ ሥጋ እያሉ የክርስትና ሃይማኖትን የተቀበለች በመሆኗ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ትባላለች፤ ይህም ማለት በትውፊትም ሆነ በቃላዊ ትምህርት ከተላለፈው ከሐዋርያት አስተምህሮ ያመለጣት ምንም ነገር እንደሌለ ያመለክታል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የቅድስት ድንግል ማርያምን ሱባዔና በዓለ ትንሣኤ በከፍተኛ ሁኔታ እያከበረች ትምህርቱንም እምነቱንም ሥርዐቱንም በምልአት ይዛ መገኘቷ የዚሁ እውነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ለነገሩ እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናትም ማለትም ከደኃራውያኑ በቀር ጥንታውያኑ ሁሉ የምዕራቡም ሆኑ የምሥራቁ ክፍለ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት የድንግል ማርያምን ትንሣኤ እንደኛ ያምናሉ ያስተምራሉ ጾሙንም ይጾማሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከሁሉም ይልቅ የሐዋርያት ትውፊትና ትምህርት፣ የቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅር በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ እንደሚያይል ለማንም ግልጽ ነው፤ ይህም የቤተ ክርስቲያናችንና የምእመናኖቻችን ሃይማኖት ምን ያህል በጸጋ እግዚአብሔር የተሞላ መሆኑን ያሳያል፡፡

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን፤

የሙታን ትንሣኤ በቅድስት ድንግል ማርያም ብቻ የሚያቆም ሳይሆን በፊታችን ቆሞ ሁላችንንም እየጠበቀ የሚገኝ ድንቅ የእግዚአብሔር ግብዣ ነውና በእርስዋ ትንሣኤ ልክ እንድንነሣ ከሐዋርያት የወረስነውን ትምህርትና ትውፊት እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አጥብቀን በመያዝ እርሱን በማመንና በመጠባበቅ ለተጠራንለት የትንሣኤ ዘጉባኤ አምላካዊ ግብዣ በሚገባ ልንዘጋጅ ይገባል፤ ለዚህም እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፤ ቅድስት ድንግል ማርያምም በጸሎቷና በአማላጅነቷ አትለየን፡፡ በድጋሚ እንኳን ለበዓለ ፍልሰታ ለማርያም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡