• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ነሐሴ 1 ቀን የ2007 ዓ.ም. የጾመ ፍልሰታ ቃለ ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ፣ የእግዚአብሔርና የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች ምእመናንና ምእመናት፣ እንኳን ለሁለት ሺሕ ሰባት ዓመተ ምሕረት የቅድስት ድንግል ማርያም መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ታዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር
ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች።”
(ሉቃ. 1፥47)

ቅድስት ድንግል ማርያም በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት አካላዊ ቃለ እግዚአብሔርን ከፀነሰች በኋላ ወደ ቅድስት ኤልሳቤጥ ቤት ገብታ ሰላምታ ባቀረበች ጊዜ በኤልሳቤጥ ማሕፀን ያለው ፅንስ በድንግል ማርያም ማሕፀን ላለው ፅንስ ከመስገዱም በተጨማሪ ቅድስት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብፅዕና በሰፊው መናገሯ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎአል (ሉቃ. 1፥45)፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር በቅዱስ ገብርኤልና በቅድስት ኤልሳቤጥ በኩል ያስነገረላትን ታላቅ ክብርና ሞገስ በማድነቅ እግዚአብሔርን በከፍተኛ ደረጃ አመሰግናለች፤ ደስታዋንም ገልጻለች፡፡

ከዚህ ከቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና የምንማረው ዐቢይ ትምህርት እግዚአብሔር በየጊዜው ያደረገልንን መልካም ነገር ሁሉ በማሰብ ለእርሱ አምልኮና ምስጋና ማቅረብ ያለብን መሆኑን ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን ባመሰገነችበት በዚህ ክፍል በእርስዋና በክርስቲያኖች መካከል ያለው የዘለዓለም ግንኙነትና ትስስር ምን ዐይነት ገጽታ እንደሚኖረው በትንቢት ተናግራለች፤ እርሱም “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” የሚል ነው (ሉቃ. 1፥48)፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ቃለ እግዚአብሔርን መጠበቅና ማስጠበቅ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ እግዚአብሔር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ከተናገራቸው ኀይለ ቃላት መካከል “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፣ ባለሟልነትን አግኝተሻል፤ ጸጋን የተመላሽ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነው” የሚሉት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው፤ (ሉቃ. 1፥28-30) በተለይም “ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል” የሚለው ቃል በቅድስት ድንግል ማርያም አንደበት የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

ይህ የእግዚአብሔር ቃል ቅድስት ድንግል ማርያምንና ምእመናንን እስከ ወዲያኛው ያስተሳሰረ የቃል ኪዳን ሐብል ነው፤ በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ ዐሥራ አምስት ቀን በጾም፣ በጸሎት፣ በአምልኮ፣ በምሥጋና፣ በንስሓና በቍርባን ለእግዚአብሔር መገዛታችንና ቅድስት ድንግል ማርያምን መማፀናችን ባለሟልነትን አግኝተሻል የሚለውን ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ባለሟል ማለት በባለሥልጣን ዘንድ ተሰሚነት፣ ተደማጭነት፣ ተቀባይነት ያለው ቀራቢ ልዩ ወዳጅ ማለት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቀደምት ቅዱሳን አበውና ነቢያት በባለሟልነታቸው በሕይወት እያሉም ሆነ ከሞቱ በኋላ በዐጸደ ነፍስ ሆነው እግዚአብሔርን እየተማፀኑ እየማለዱና እየለመኑ ሰውን ያስምሩ እንደነበር ተጽፎአል፤ (ዘፀ. 32፥11-14፤ ኢዮ. 42፥7-9፤ ነገ.ቀዳ. 11፥10-13)፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ቅድስት ድንግል ማርያም በባለሟልነቷ ብቻ ሳይሆን እርሱን ፀንሳ የወለደችና ያሳደገች የጌታችን እናትና ልዩ ባለሟል በመሆኗ በጸሎትዋ፣ በልመናዋና በአማላጅነቷ አምነን ስንማፀናት እኛን ታስምራለች ብለን እናምናለን፤

የቅድስት ድንግል ማርያም ልመና ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ በቃና ዘገሊላ የሠርግ ቤት ያቀረበችው ምልጃና ልመና በሁኔታውም የተገኘው ውጤት ለኛ በቂ ማስረጃችን ነው፤ (ዮሐ. 2፡ 1-9) ከዚህም ጋር ራሱ ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ እርስዋን የኛ እናት አድርጎ፣ እኛንም የእርስዋ ልጆች አድርጎ መስጠቱ ልጅ የሚፈልገውን ነገር ከእናቱ እንደሚሻ ሁሉ እኛም የምንሻውን ነገር ታሰጠን ዘንድ እንድንማፀናት ነው፡፡ እናትም አዛኝ፣ ርኅርኅት ተቆርቋሪ አሳቢ ሆና ለልጇ እንደምትጨነቅ እርስዋም ለኛ አዛኝ ርኅርኅትና ተቆርቋሪ በመሆን ዘወትር ስለእኛ እርሱን እንድትለምንልን ነው ከዚህ ውጭ ሌላ ትርጒም ሊኖረው አይችልም፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ይህንን መሠረታዊ ትምህርት ተገንዝበውና የቅድስት ድንግል ማርያምን እናትነት ተቀብለው እርስዋን ለማግኘት ሲሉ በዚህ ወር በመጾምና እርስዋን በመማፀን ልጅነታቸውን በተግባር አሳይተዋል፤ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣውና የተላውያነ ሐዋርያት ትምህርትን በምልአት የተረዳው የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሎአል ‹‹ወይብሉ ኵሎሙ ሐዋርያቲሁ ለእግዚእነ ሰአሊ ለነ ማርያም እምነ፤ የጌታችን ሐዋርያት ሁሉ እናታችን ማርያም ሆይ ለምኝልን ይላሉ›› በማለት በድጓው በብዙ ቦታ ላይ ጽፎአል፡፡ ጥንታዊው የሐዋርያት ትምህርት፣ ትውፊትና ባህል ያልተለያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከጌታችንና ከሐዋርያት የተቀበለችውን ሁሉ ሳትሸራርፍ እንዳለ ይዛ እነሆ አስካሁን ድረስ የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና ብፅዕና እንደ ቃሉ ጠብቃ እየተጓዘች ነው፡፡ ለዚህም ዛሬ የምንጾመው የሁለት ሺሕ ሰባት ዓመተ ምሕረት የቅድስት ድንግል ማርያም ጾም ምስክር ነው፡፡

የሀገራችን ታላቅነትና ነፃነት፣ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ታሪክና ባህል፣ ቅዱስ ሥነ ምግባርና ሌላው ጸጋ ሁሉ ጠብቆ በማስጠበቅ ዛሬ በዓለም መካከል ልዩ አድናቆት ላላት ሀገር ባለቤት እንድንሆን ያስቻለን ይህ ሃይማኖታችን እንደሆነ ከቶ ሊዘነጋ አይገባም፤ አሁንም ከአባቶቻችን የወረስነው መልካም ዕሴት ለቀጣዩ ትውልድ በአስተማማኝ ለማስተላለፍ የሃይማኖታችንን እሴቶች ሁሉ በሚገባ መጠበቅ ይገባናል፤

‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም›› እንደተባለው ሁሉ ከሃይማኖታችንና ከባህላችን እንደዚሁም ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮና ከሕገ ተፈጥሮ ውጭ የሆነውን ነውረ ኀጢአት ከሌላው ሀገር ወደ ሀገራችን ለማጋባት የሚደረገው ተጽዕኖ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናንና ሁሉም ኢትዮጵያውያን አምርረው ሊታገሉትና ሊመክቱት ይገባል ፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ እኛ ‹‹እጆቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ይዘረጋሉ›› ተብሎ የተነገረልን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ነን፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ የነውረ ኀጢአት ተገዥ ሊሆን ከቶ አይችልም ብለን በጽናት መቋቋም ይኖርብናል ፡፡ ጾም የተፈጠረው ከነውረ ኀጢአት ለመራቅ፣ በንጽሕና እና በቅድስና ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ለሰው ሁሉ የርኅራኄና የፍቅር ሥራ ለመሥራት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ የጾም ወቅት ያዘኑትን በማጽናናት፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተጎሳቈሉትን በመደገፍ፣ ፍጹም ርኅራኄን ለወገኖቻችን በማሳየት አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ አለብን፣ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የዝናም እጥረት እንዳለ እየተሰማ ስለሆነ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ሱባዔ በየቤተ ክርስቲያኑ እየተገኘ የምሕላ ጸሎት በማድረስ ፈጣሪውን በኀዘንና በጸሎት እንዲለምን፣ ቅድስት ድንግል ማርያምንም እንዲማፀን መልእክታችንን ከአደራ ጭምር እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን፤እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ፤አሜን፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32015-08-07 12:52:262025-01-28 12:53:52ነሐሴ 1 ቀን የ2007 ዓ.ም. የጾመ ፍልሰታ ቃለ ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ሚያዝያ 27 ቀን እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ Link to: ሚያዝያ 27 ቀን እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡ ሚያዝያ 27 ቀን እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ... Link to: መስከረም 1 ቀን የ2008 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት Link to: መስከረም 1 ቀን የ2008 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት መስከረም 1 ቀን የ2008 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top