ነሐሴ 1 ቀን የ2006 ዓ.ም የጾመ ፍልሰታ መግቢያ ቃለ በረከት!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የተወደዳችሁ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትኖሩ ሕዝበ ክርስቲያን በአጠቃላይ እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለ2006 ዓ.ም ጾመ ማርያም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ወዘሰ እንተ አንቀጽ ይበውእ ኖላዌ ዐባግዕ ውእቱ
በበሩ የሚገባ የበጎች እረኛ ነው።
(ዮሐ. 10፥2)

በብሉይ ኪዳን የበጎች እውነተኛ እረኛ እንደ ሆነ በብዙ ስፍራ የተነገረለት መሲሕ አንድ ቀን በዓለም እንደ ሚገለጽና በጎቹን በትክክል እንደ ሚጠብቅ በሕዝበ እግዚአብሔር ዘንድ የታወቀና የታመነ ነበረ። (ሕዝ. 34፥1-24)።

እግዚአብሔር ያስቀመጠው ቀመረ ዘመን ሲደርስ እውነተኛው እረኛ ክርስቶስ በተነገረለት በር በኩል ወደዚህ ዓለም መጣ፤ ይኸ በር የቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ማሕፀን ነበረ (ሕዝ. 44፥2-3)። በኦርቶዶክሱ ዓለምና በሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የምንገኝ ክርስቲያኖች ቅድስት ድንግል ማርያምን ከእግዚአብሔር በታች፣ ከፍጡራን በላይ፣ ከፍ አድርገን የምናከብርበት ዋና ምክንያት ድንግል ማርያም የዓለም መድኅን የክርስቶስ መግቢያ በርና ለሰው ልጅ የድኅነት ምክንያት ስለሆነች ነው፡፡

ከዚህም የተነሣ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የተነሡ ቅዱሳን ሊቃውንት ቅድስት ድንግል ማርያምን “አንቀጸ አድኅኖ ይእቲ አልባቲ ሙስና ማለትም ስሕተት ጥፋት የሌለባት የድኅነት በር ናት” ብለው በተደጋጋሚ ገልጸዋታል”፤ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በዜማ ድርሰቱ በዚህ ኀይለ ቃል ደጋግሞ አመስግኗታል፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ለመድኀኒችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በር በመሆኗ ክርስቲያን ለሆኑ ምእመናን ሁሉ እናት ናት፤ ጌታችን አምላካችንንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ እርስዋ የክርስቲያን እናት፣ እኛ ክርስቲያኖችም የእርስዋ ልጆች በማድረግ አስተሳስሮናል። (ዮሐ. 19፥26-27)

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን በነገራቸው ቃል መሠረት ድንግል ማርያምን በእናትነት ተቀብለው በክብር ይከተሏት ነበር፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይም ሥጋዋን ራሳቸው ቀብረው የበረከቷ ተካፋይ ለመሆን በነበራቸው ከፍተኛ ጒጉት ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 14 ቀን ሱባዔ ገብተው ፈጣሪን በጾምና በጸሎት ስለለመኑ ነሐሴ 14 ቀን የለመኑትን አግኝተው ሥጋዋን በጌቴሰሜኒ ቀብረዋል፤ ሆኖም በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማያት ዐርጋለች፣ ቅዱሳን ሐዋርያትም ትንሣኤዋን በዐይን አይተው የበረከቷ ተካፋይ ሆነዋል፤ ይህንን ሐዋርያዊ ትምህርትና ትውፊት መነሻ በማድረግ በዓለም ያሉ ኦርቶዶክሳውያንና ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በየዓመቱ ከነሐሴ 1 ቀን እስከ 15 ቀን በመጾም ነሐሴ 16 ቀን በዓለ ትንሣኤዋን በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊትና ጥንታዊት እንደ መሆንዋ መጠን ከጥንት ጀምሮ ይህንን ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም ጠብቃ እስካሁን አቆይታለች፤ ለወደፊትም እስከ ዕለተ ምጽአት በዚሁ ይቀጥላል።

የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ትንሣኤ ምክንያት አድርገን የምንጸመው ይህ ጾመ ማርያም ለሀገራችን፣ ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ መዳንን፣ ምሕረትንና ይቅርታን ለማስገኘት ነው፡፡ የሃይማኖት ተልእኮ ምን ጊዜም ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን ለጒዳት መዳረግ አይደለም፤ ሃይማኖት ተቀባይነትን ሊያገኝ ሊወደድና ሊከበር የሚችለው ለሰው ልጆች በሚሰጠው ክብርና የድኅነት አስተምህሮ ነው፤ ሃይማኖት ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ተልእኮ በአግባቡ ማከናወን የሚችለው ሰላምን፣ እኩልነትን፣ መከባበርን፣ መረዳዳትን፣ ማስተዋልን ትዕግሥትንና ፍቅርን ማእከል አድርጎ ሲጓዝ ነው፡፡ ይህንን በሚቃረን መልኩ የሚጓዝ ሃይማኖት ባይኖርም የሃይማኖቱን ትክክለኛ አስተምህሮ በተሳሳተ መንገድ የሚተረጐሙና የሃይማኖትን ካባ ያጠለቁ ግለ ሰቦች በየሃይማኖቱ ውስጥ አይጠፉም፡፡ በሀገራችንም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም የሰላምና የልማት ጠንቅ ሆነው ሰላማዊ ሕዝብንና እውነተኞች አማንያንን በማስቸገር የሚገኙት እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ግለ ሰዎቹ የሃይማኖት ተልእኮ ፈጽሞ እንደ ሌላቸው ከምንም በላይ ግብራቸው ይመሰክርባቸዋል፤ ወደ ሃይማኖቱ መድረክ በእውነተኛው በር ሳይሆን በሌላ በር እየገቡ ከምንም በላይ ራሱን ሃይማኖቱን እየተገዳደሩት እንደሚገኙ ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡

ስለሆነም በበሩ ሳይሆን በሌላ መንገድ የሚገባ እርሱ እውነተኛ የበጎች እረኛ አይደለም (ዮሐ. 10፥1)፤ ብሎ ጌታችን ባስተማረን መሠረት እንደዚህ ዐይነታቸውን ግለሰቦች ነቅተን ልንከላከላቸው ይገባል፤ የሃይማኖት በሮች እምነት፣ ምግባር፣ መታዘዝ፣ ትሕትና፣ በሕግና በሥርዐት መኖር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ ስምምነት፣ መተሳሰብ፣ መከባበር፣ ሥራ መውደድ፣ ከተንኮልና ከአስመሳይነት መራቅ ናቸው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረጉ የማስመሰል ተግባራት ሁሉ ማታለያ ከመሆን አልፈው የእውነተኛ ሃይማኖት መገለጫ ሊሆኑ አይችሉም፤

እግዚአብሔር ከላይ የተገለጹት የሃይማኖት መገለጫ ፍሬዎችን ይዘንና ከማናቸውም ግብረ ኀጢአት ርቀን እርሱን በመፍራትና ለእርሱ በመታዘዝ እንድንጾም ይፈልጋል፤ እንደዚሁም የተራበውን በማጒረስ፣ የታረዘውን በማልበስ፣ የተቸገረውን በመርዳት እንድንጾም ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባናል፤ እግዚአብሔር የመረጠው ጾም ይህ ነውና፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ይቀድስ አሜን