ግንቦት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ፣ በኀይለ መለኮቱ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችንንም በልዩ አጠራሩ ጠርቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሚካሄደው በዚህ ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዐቢይ ጉባኤ ስለሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡

“ወንሩጽ በትዕግሥት ኀበ ዘጽኑሕ ለነ ተስፋነ ዘሃይማኖት ተጠብቆልን ወዳለ ተስፋ ሃይማኖት ለመድረስ በትዕግሥት እንሩጥ” (ዕብ. 12፥1)

ርክበ ካህናት ተብሎ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚታወቀው፣ ከጌታችን በዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን፣ ማለትም በመንፈቀ በዓለ ኃምሣ በየዓመቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲደረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትደነግግ ትልቅ ዐላማ አላት፤ የጉባኤው ዐላማ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመንፈስ ቅዱስ በተሰጣቸው ሐዋርያዊ ተልእኮ መሠረት በየተመደቡበት ሀገረ ስብከት ሲሠሩ በመንፈሳዊም ሆነ በአስተዳደራዊ ሥራቸው ያጋጠመ እክል ካለ በጋራ ተሰብስበው ችግሩን መፍታት የሚያስችል ጥበብ እንዲፈልጉለት ለማድረግ ነው፡፡

ከዚህም ጋር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ለሰው ሁሉ ማዳረስ የምትችልበትን ብልኀት በመንደፍ ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመጥራት ዝግጅት የምታደርግበት ዐቢይ ጉባኤ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ተልእኮ “ሑሩ ወስብኩ ወንጌለ ለኲሉ ፍጥረት፤ ሂዱ፣ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” የሚለው አምላካዊ ትእዛዝ ነው። (ማር. 16፥15)

የቤተ ክርስቲያን ሥራ በርከት ያለ ቢሆንም ተጠቃልሎ ሲታይ ለሰብከተ ወንጌል ድጋፍ ሰጪ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ከስብከተ ወንጌል ውጭ ሌላ ተግባር የላትም፡፡ እኛ የሐዋርያት ተከታዮች የሆንን ሊቃነ ጳጳሳትና ከዚያም በየደረጃው የተሰየሙ ካህናት በሙሉ እንድንሄድ የታዘዝነው ወደ አንድ ሀገረ ስብከት ብቻ ሳይሆን ወደ ዓለም ሁሉ ነው፣ የላከን አምላክ ድንበርና ወሰን የሌለው እንደሆነ ሁሉ መንግሥቱም እንደዚሁ ድንበር የለሽ ነው፤ እኛም የእርሱን ሥልጣን ስለተቀበልን ተልእኮአችን ድንበርና ወሰን የለውም፡፡

ይህም ሲባል ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው ሥልጣን በድንበር የተገደበ አይደለም ለማለት እንጂ የሥራ መደብ የለም ማለት አይደለም፤ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ ማየት ያለበት በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ በዓለም ሁሉ ወንጌልን እንዴት ማዳረስ እንዳለበት በሚቃኝ መልኩ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ወንጌልን ለዓለም የማድረስ ተልእኮ የኛ የሊቃነ ጳጳሳቱ እስከሆነ ከሁሉም ዘንድ ለመድረስ ጠንክሮ መሮጥ የኛ ግዴታ ነው፣ ሆኖም ሩጫው ዕንቅፋት አጋጥሞት ለጉዳት እንዳይዳርገን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ትዕግሥትና ማስተዋል ያልተለየው ሊሆን ይገባል፡፡ ትዕግሥትና ማስተዋልን ገንዘብ አድርጎ ሥራን መሥራት ትልቅ ጥበብ እንጂ ቸልተኝነት አይደለም፤ ሃይማኖት የሚጠበቀው፣ ድኅነትም የሚገኘው፣ በትዕግሥት እንደሆነ ራሱ ባለቤቱ “ወበትዕግሥትክሙ ታጠርይዋ ለነፍስክሙ” በማለት አስተምሮናል፡፡

ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድም አርምሞ ተዐግሦ ተዐቅብ ሃይማኖተ ማለትም ነገሮችን ታግሦ በማስተዋል ማለፍ ሃይማኖትን ትጠብቃለች ብሎ አስተምሮናል፡፡ መልእክቱ በዋናነት መሮጥንና ትዕግሥትን አጣጥሞና አገናዝቦ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል፤ ይህ ለሥራችን መቃናት በጣም ጠቃሚ ነው፣ «መዘናጋት እንዳይኖር እንሩጥ፣ ስሕተትም እንዳይበዛ በትዕግሥት ይሁን፣» የሚለውን መርሕ መከተል ለሁላችንም ይበጃል፡፡

ባለፈው ዓመት የርክበ ካህናት ጉባኤያችን በቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ብልሹ አሠራር እንዲታረም፣ ቤተ ክርስቲያናችን ልዕልናዋና ክብሯ፣ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ፣ አንድነትዋና ሥርዐቷ፣ እንደነበረው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን መወሰናችን ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸው ውሳኔዎች በጥናት ተመሥርተው ደረጃ በደረጃ በተግባር ይተረጎሙ ዘንድ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፤ ኮሚቴዎቹም የመጀመሪያ ዙር ጥናታቸውን በጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አቅርበው እንዲታይ አድርገዋል፡፡

ከዚያም በኋላ ጥናቶቹ በሊቃውንትና በባለሙያዎች እየታገዙ የቀጠሉ ቢሆኑም በሥራው ሂደት በመጠኑም ቢሆን አንዳንድ መሰናክሎች አልነበሩም ማለት አይቻልም፤ ይሁን እንጂ ቀዋሚ ሲኖዶስ በየጊዜው በሚያደርገው ክትትልና በሚሰጠው አመራር መልክ እየያዙና መሠረተ ደልደላ እየሆኑ ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተለይም በማእከል የተቋቋመው ኮሚቴና ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደንብ አጥኚ ተብሎ በድጋሚ የተሰየመው ኮሚቴ በአንድነት ሆነው ሥራውን ለመሥራት ያሳዩት ቅን ተነሳሽነት ለሥራው ጥራትና ቅልጥፍና ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ላይ የሚታየው ክፍተት የቆየና ሥር የሰደደ ከመሆኑ አንጻር በአጭር ጊዜ ይስተካከላል የሚል እምነት ብዙ ላይኖረን ይችላል፤ ይሁንና በጀመርነው መሥመር ከቀጠልን ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ ለውጦችን ማየት እንደምንችል ጥርጥር የለንም፡፡ ሆኖም መልካም አስተዳደር በፍጥነት እንዲሰፍን ወሳኝ የሆኑ መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጉን በዚህ አጋጣሚ ሳንጠቅስ አናልፍም፤ እነዚህም፤

1. በየአቅጣጫው ለሚነፍሱ የውጭ ነፋሳት የማይበገር አንድነት፤

2. ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ማእከል አድርጎ መሥራት፤

3. በእናውቅላችኋለን ባዮች ግራ ሳይጋቡ በራስ በመተማመን መወሰን፤

4. የቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን በማንም ይሁን በማን እንዳይገሠስ ጥብቅና መቆም የመሳሰሉ ባሕርያት ለዚህ ጉባኤ አስፈላጊ መሣሪያዎች ናቸው፡፡

ሌላው ከዚህ ጋር አያይዘን ማንሣት የምንፈልገው ዐቢይ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን የሰው ኀይል በአግባቡ አልምቶ ለተሻለ ውጤት የማብቃቱ ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ያለው የሰው ኀይል እንደሌላው ዓለም አጠቃቀም ብንጠቀምበት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ በአጠቃላይ ይበቃ እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡

ሁላችንም እንደምንገነዘበው በዓለም ውስጥ የሚገኘው ካህን በአጠቃላይ ቢበዛ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ ላይሆን ይችላል፣ ይሁንና የኛ ቤተ ክርስቲያን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የካህን ብዛት እያላት ለምን ብዙ የሥራ ክፍተቶች በየጊዜው ይከሠታሉ? የሚለውን ጥያቄ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በውል ሊያጤነው ይገባል፡፡

እየተፈጠረ ያለው ክፍተት ባጭሩ ለመጠቆም ያህል ያለንን የሰው ኀይል በዕውቀት አልምተን ክፍተቱን ከመሙላት ይልቅ “በምንስ የደነቈረ ምን ሲል ይኖራል” እንደሚባለው ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩት አስገዳጅ ሁኔታዎች ያመጡብንን የዘመናት ልምዶች እንደመልካም ባህል ይዘን በዚያው በመቀጠላችን ክፍተቱ ተፈጥሮአል የሚል ጽኑ እምነት አለን፤ ለቤተ ክርስቲያን አይደለም ለራሱ እንኳ በአግባቡ መቆም ያልቻለ የሰው ኀይል ይዘን የትም መድረስ አንችልም፤ ሆኖም ይህን ችግር ለማስተካከል ያለውን በማፍለስ ሌላ አዲስ ተክልን መትከል ሳይሆን ያለውን የሰው ኀይል በማልማትና በሥሩ የሠለጠነ የሰው ኀይልን በማስከተል ማስተካከል እንዳለብን ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ስለሆነም ያለንን የሰው ኀይል በዕውቀት በማልማት ክፍተቱን መሙላት ጊዜ የማይሰጥ ስለሆነ ይህ ዐቢይ ጉባኤ ሊያስብበት ይገባል እንላለን፡፡

ያለንበት ጊዜ እጅግ በጣም ከፍተኛ ውድድር የሚታይበት ጊዜ ነው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ባደረገችው ርብርቦሽ ዓለም በአድናቆት የተናገረለት የልማትና የእድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ገጠሩ ድረስ በተንቀሳቀስን ቊጥር የምናየው ነገር ሁሉ ልማትና ግንባታ ነው፣ ትምህርት ቤቱ፣ የጤና ኬላው፣ የመስኖ እርሻው፣ የትራንስፖርት ግንባታው፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታው ሁሉ ሲጣደፍ ይታያል፤ ይህ ከእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የተሰጠ ታላቅ በረከት ነው፡፡

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን የልማት በረከቱ ባለበት ብቻ እንዲቀጥል ሳይሆን ካለበት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕዝቡን በማስተማር ለልማቱና ለእድገቱ በሰፊው መንቀሳቀስ አለባት፣ የተለመደውን ሀገራዊ ኀላፊነቷም መወጣት አለባት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህች ሀገር አንድነት መጠበቅና ለህልውናዋ ቀጣይነት ለሦስት ሺሕ ዘመናት ያህል የሠራችው ጒልህና ደማቅ ሥራ አሁንም መድገም አለባት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬም እንደቀድሞው ሃይማኖታዊና ልማታዊ ሥራን በመሥራት የመሪነት ሚናዋን የምታጠናክርበት አቅጣጫ ይህ ጉባኤ መቀየስ አለበት፡፡

ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተልእኮዋን በብቃት ከመወጣት ባሻገር በትምህርት ዘርፍ፣ በጤና ዘርፍ፣ በራስ አገዝ ልማት ዘርፍ፣ ወዘተ … በመሳሰሉት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ሕዝቡን አስተባብራ በየቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ መገንባት አለባት፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰበሰብበት ዋና ዐላማ እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ዐበይት ጉዳዮችን በማጥናት፣ በመገምገምና በመወሰን የተጣለበትን ኀላፊነት ለመወጣት ነው፡፡ ስለሆነም መልካም አስተዳደር በማስፈን ለተሻለ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መሠረት የሚሆኑ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤው የተጣለበትን ኀላፊነት በተገቢው ይወጣ ዘንድ አሳስባለሁ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክ ይቀድስ አሜን