መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን

ብፁዕ ኣቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዕ ኣቡነ ሕርያቆስ
የኣዲስ ኣበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡር…..
ክብርት…..
ክቡራን ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣
ክቡራን ኣምባሳደሮችና የኮር ዲፕሎማቶች፣
ክቡራን የቤተ ክርስቲያናችን የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ኣገልጋዮችና ሰራተኞች፣
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ጀግኖች ኣርበኞች፣
የተከበራችሁ የፀጥታ ኣስከባሪ ኣባላት፣
የተወደዳችሁ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ልጆቻችን፣
በኣጠቃላይ በዚህ ታላቅ ሥነ በዓል የተገኛችሁና በዓለም ዙሪያ ሆናችሁ በዓሉን በመከታተል የምትገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ፦

ስሕተት በወለደው በደልና ኃጢኣት የደከሙትን በኃይለ መስቀሉ የሚታደግ ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ መስቀሉ በሰላም ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“ወለእለ ፃመዉ በመስቀሉ ይባልሕ፡- የደከሙትን በመስቀሉ ይታደጋል፤ (መጽሓፈ ኪዳን)፤

እግዚአብሔር ኣምላካችን በሁለመናው እንከን የለሽ ፍጹም ኣምላክ ነው፤ እንደዚህም በመሆኑ ጥፋትን የማይወድ ኣምላክ ነው፤ ይሁንና የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ሕግ ላይ ድፍረትን የተሞላ ስሕተት ወይም ጥፋት በመፈጸሙ እግዚአብሔርን ኣስቈጣ፤ ከዚህ ኣንጻር ሰው በዚህ ተግባሩ ደካማ ሆኖ ተገኘ። እግዚአብሔርም ፈታሒ በጽድቅ፣ ኰናኒ በርትዕ ነውና ሰውን በጥፋቱ ቀጣ፤ የቅጣቱም ዓይነት ሞት ነበረ፤ በሰው ላይ የተላለፈው የሞት ቅጣትም በምድርም፣ በሰማይም ተፈጻሚ ሆነ፤ ይህም ማለት ሰው በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ኑሮው ከእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ከሆነው ሁሉ ተለየ ማለት ነው፤ ይህ ቅጣት ለሰው ልጅ እጅግ የመረረ ቅጣት ነበረ።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
ክቡራን የበዓሉ ተሳታፊዎች!

እግዚአብሔር በዳኝነቱ ፈራጅና ቀጪ እንደ ሆነ ሁሉ፣ በኣባትነቱ ደግሞ መሓሪና ይቅር ባይ ነው፤ በመሆኑም በኃጢኣት ደክሞ የወደቀውን የሰው ልጅ በቤዛዊ ሞቱ ከሞተ ኃጢኣት የሚያድነው መሆኑን የሚያመለክት ተስፋ ሰጠው።
ተስፋውን በነቢያቱ ኣማካኝነት ሲገልጽለት ከቈየ በኋላ፣ ሰውነታችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም ተገለጸ፤ በዚህ ዓለም ሰው የሚድንበትን መንገድ በቅዱስ ወንጌል ካስተማረና በተግባር ካሳየ በኋላ፣ ቤዛ ሰብእ የሆነው ሞቱን በመስቀል ላይ በመቀበል ቅጣታችንን እንዲነሣ ኣደረገልን፡፡  ቅዱስ መጽሓፍ ይህንን ሲገልጽ፦ “ሁሉም በኣዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ይድናሉ” ይላል። በስሕተት፣ በበደልና በኃጢኣት የደከመው የሰው ልጅ በክርስቶስ ቤዛዊ ሞት ምክንያት ነጻነትን ኣግኝቶ ወደ ቀደመ ክብሩና ርስቱ ተመለሰ፤ ቤተ ክርስቲያን “የደከሙትን በመስቀሉ ይታደጋል” በማለት የምታስተምረን ይህንን እውነት ለመግለጽ ነው፡፡ ለዚህም ዋና ማስረጃዋ ጌታችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ “ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት በቀኙ በኩል ለተሰቀለው በደለኛ የገባውና የፈጸመው ቃል ኪዳን ነው፤ ይህም ቃል ኪዳን ለኣማንያን ሁሉ የተገባ ቃል ኪዳን መሆኑ እሙን ነው።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!

ምንም እንኳ በመስቀል ላይ በተፈጸመው የጌታችን ቤዛዊ ሞት ምክንያት ነባሩ ቅጣታችን ወይም ጥንተ ኣብሶ ቢነሣም በገቢር ኣበሳችን ምክንያት ዛሬም ከስሕተት መጽዳት ኣልቻልንም፡፡ በመሆኑም ዛሬም ከእውነት ጋር መጋጨታችን ስለ ቀጠለ በየጊዜው በምንፈጽመው የገቢር ኣበሳ እግዚአብሔርን ማስቈጣታችን ኣልቀረም።  የድኅነታችን ምልክትና ምስክር የሆነው ዕፀ መስቀል በሰዎች እንዲቀበር መደረጉም፣ የገቢር ኣበሳችን መቀጠሉን የሚያመለክት ምስክር ነው፡፡
ሆኖም መስቀልን መደበቅም ሆነ መሰወር ከሰው ዓቅም በላይ ነበረና በእግዚአብሔር ኃይል በጢሰ ዕጣን ኣመልካችነት ከተቀበረበት ጕድጓድ ሊወጣ ችሎኣል፡፡ እነሆም መስቀሉ እስከ ዛሬ ድረስ የእውነት መስካሪና የድኅነት ምልክት ሆኖ ቀጥሎኣል፤ ለወደፊትም በዚህ ይቀጥላል።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራን የበዓሉ ተሳታፊዎች!

የመስቀሉ ዓበይት መልእክቶች ሰው ሊያምንባቸው፣ ሊቀበላቸውና ሊኖርባቸው፣ በውጤቱም በሥጋውም ሆነ በነፍሱ ሊድንባቸው እንደ ተሰጡ የማንስተው ሓቅ ነው፡፡  ሆኖም ሰዎች በኣንድ ጆሮኣችን ሰምተን በሌላኛው ጆሮኣችን ከመጣል ባለፈ፣ ያመጣነው ለውጥ እንደሌለ ተግባራችን ራሱ ምስክር ነው። ዛሬም ሕገ እግዚአብሔር በድፍረት ይጣሳል፤ የጥሰቱ ውጤትም እንደምናየው ዓለማችንን በኣጠቃላይ በመኖርና ባለመኖር ስጋት ውስጥ እየከተታት ይገኛል፡፡
ታድያ እኛስ በዚህ ሁሉ ኣልደከምንምን? የሚታደገን መስቀላዊ ኃይልስ ኣያስፈልገንምን? ለሰላማችን መጠበቅና ለድኅነታችን ዋስትናስ ከመስቀሉ ቃልና ኃይል የበለጠ ሌላ ኣለን? እንደ እውነቱ ከሆነ በንጹሁ ኣእምሮኣችን በደምብ ካስተዋልነው፣ ከመስቀሉ ቃል የበለጠ ለሰው ልጆች ሰላምንና ድኅንነትን የሚሰጥ ሌላ ኃይል በዓለማችን ውስጥ ኣይገኝም። ስለሆነም ፍጹምና ዘላቂ ሰላምን የምንሻ ከሆነ፣ በመስቀሉ ቃል እንመራ፤ የመስቀሉ ቃል ማለት ይቅርታንና ዕርቅን፣ እኩልነትንና ኣንድነትን፣ ፍትሕንና ርትዕን ማረጋገጥ ማለት እንደሆነም በውል እንወቅ፤ በዚህ ሕይወት መኖር ከጀመርን ድክመታችን በመስቀሉ ተወገደ ማለት ነው።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
ክቡራን የበዓሉ ተሳታፊዎች!

የዘንድሮ በዓለ መስቀል ኣከባበር ልዩ የሚያደርገው፣ እግዚአብሔር የሰጠንን የውሀ ጸጋችን ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም በኣንድነት ተባብረን ባካሄድነው ጥረት፣ የሕዳሴ ግድባችንን ኣጠናቀን ባስመረቅንበት ማግሥት እየተከበረ ያለ መሆኑ ነው፡፡  ይህ ክሥተት ለሃገራችን ዳግም ልደትን ያበሰረ ስኬት ነው ብንል ማጋነን ኣይሆንም፤ በዚህም እግዚአብሔር ኣምላካችንን ማመስገን ይገባናል፤ በስራው ላይ ታሪካዊ ኣሻራቸውን ያሳረፉትንም ሁሉ መመስገን ይገባቸዋል እናመሰግናቸዋለንም። በቀጣይም ሃገራችን ልትሰራቸው በዕቅድ የያዘቻቸውን ታላላቅ የልማት ስራዎች፣ በፍጥነትና በጥራት ተሰርተው ለሕዝባችን ጥቅም እንዲውሉ ሁላችንም መረባረብ ይኖርብናል፤ ታላላቅና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሁም ችግር ኣስወጋጅ የሆኑ ስራዎች እውን ሊሆኑ የሚችሉ፣ ሕዝቡ በኣንድነትና በኅብረት ተነሥቶ ወደ ትግበራ ሲገባ እንደሆነ ከታላቁ የሕዳሴ ግድባችን ተምረናል፤ በመሆኑም በሕዳሴ ግድባችን ያሳየነውን ትብብርና ተነሣሽነት፣ ኣሁንም ኣጠናክረን መቀጠል ይገባናል፤ መንግሥትም ከዚህም ከዚያም የሚታዩትን ኣለመግባባቶች በዕርቅና በይቅርታ በማለፍ፣ እኩልነትን፣ ፍትሕንና ርትዕን በማረጋገጥ፣ እንደዚሁም ለሰላም መስፈን ረጅም ጉዞ በመሄድ ሕዝቡን ወደ ኣንድነት የማምጣት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በዚህ ኣጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም

የመስቀሉ መልእክት የሰው ልጆችን ሁሉ በሰላም፣ በሕይወት፣ በእኩልነትና በኣንድነት ማኖር መሆኑን ከልብ ተገንዝበን፣ በያዝነው ኣዲስ ዓመት እርስ በርሳችን ከመጠፋፋት ይልቅ በጋራ ሰርተን በጋራ የምንለማበትን ምርጫችን እናድርግ በማለት በእግዚአብሔር ስም ኣባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። በዓለ መስቀሉን የሰላም በዓል ያድርግልን፤ ለሃገራንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን!

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓም
ኣዲስ ኣበባ ኢትዮጵያ።