• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም ርዕሰ ዐውደ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል መግባትን አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዐሠርቱ ወሰብዓቱ ዓመተ ምሕረት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
• በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፡፡

ሁለመናችንን በሐዲስ ምግብና እየመገበ የሚጠብቀን አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ 2016 ዓ.ም. ወደ ዘመነ ማቴዎስ 2017 ዓ.ም. በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!
‹‹ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ፤ የልባችሁን መንፈሳዊ አእምሮ አድሱ›› (ኤፌ. 4÷23)፤

በገሃዱ ዓለም በግልጽ እንደምናስተውለው ከሞላ ጎደል የማያረጅ የለም የማይታደስም የለም፤ መታደስ ባይኖር ኖሮ ሕይወታውያን ፍጡራን በሕይወት መቀጠል አይችሉም ነበር፤ የዘመን መታደስም የሥነ ፍጥረት አንዱ አካል ነው፤
እኛ ሰዎችም የሕዳሴው መሪዎች ሆነን የተሾምንባትን ምድር በየጊዜው በልማት እንድናድሳት እግዚብሔር አዞናል፤ የሃይማኖት ትልቁ ተስፋም መታደስ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ዘመንም እንደ ሌላው ያረጃል፤ ይታደሳልም፤ “ወናሁ እገብር ኵሎ ሐዲሰ እነሆ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” የሚለው የእግዚአብሔር ቃልም የዚህ አስረጅ ነው፤ በዚህ ሕገ እግዚአብሔር መሠረት እነሆ አሮጌውን ዘመን የምንሸኝበት አዲሱን ዘመን ደግሞ የምንቀበልበት ምዕራፍ ላይ ነን፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፡-
ፍጥረታትን በማደስ ሕይወትን የማስቀጠል ሥልጣን በዋናነት የእግዚአብሔር ብቻ መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ ይሁን እንጂ ሰውም ሥነ ፍጥረትን በማደስና በማጐስቈል ረገድ ያለው ሚና ቀላል አይደለም፤ ይህም ሰው በምድር ላይ እንዲሠለጥን ወይም ፍጥረትን እንዲገዛና እንዲመራ በፈጣሪ ከተሰጠው ሥልጣን የሚመነጭ ነው፤  ዛሬም ዓለማችን በመታደስ ያይደለ በማርጀት ላይ የምትገኘው ከሰዎች ድርጊት የተነሣ እንደሆነ እንገነዘባለን፤ የአየሩ መለወጥ፣ የበረዶው መቅለጥ፣ የሙቀቱ ማሻቀብ፣ የዝናሙ ማጥለቅለቅ፣ የባሕሩ መናወጥ ወዘተ. እየተፈጠረ ያለው ኃላፊነት ከጐደለው የሰው አጠቃቀም የተነሣ እንደሆነም ተደጋግሞ እየተነገረን ነው፤ እኛም በዓይናችን እያየን ነው፤  ከዚህ በተለየ ደግሞ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሰው ምድረ በዳውን ወደ ሐመልማለ ገነት ሲቀይር የሚስተዋልበት ሌላ ገጽታ አለ፤ ይህ የሚያሳየው ሰው በሥነ ፍጥረት ላይ የማደስና የማጐስቈል ብሎም የማጥፋት ሚና ያለው መሆኑን ነው፤ ሰውም እንደሌላው ሥነ ፍጥረት የሚያረጅም የሚታደስም ነው፤ ይህም በብዙ አቅጣጫ ሊከሠት ይችላል፤ ሰዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሁለቱንም ማለትም ማርጀትና መታደስን ሊያስተናግዱ ይችላሉ፤ ሰዎች በመንፈሳዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በማኅበራዊና በመልካም አስተዳደር ወዘተ. የላቀ ዕድገትን ሲያስመዘግቡ በመታደስ ላይ እንደሆኑ ይታወቃል፤ የዚህ ተቃራኒ የሆነውን ይዘው እየተጓዙ ከሆነ ደግሞ ተቃራኒውን ወይም ማርጀትን እያስተናገዱ እንደሆነ ይታወቃል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች በመንፈሳቸውም ሆነ በአእምሮአቸው፣ በነፍሳቸውም ሆነ በአካላቸው በመታደስ እንዲኖሩ እንጂ እርጅና እንዲጫጫናቸው አይፈልግምና “የልባችሁን መንፈስ አድሱ” በማለት ያስተምረናል፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!
የክርስትና ሃይማኖት የመጨረሻው ግብ የፍጥረት መታደስ ነው፤ ይህም ማለት የሃይማኖቱ አስተምህሮ መዳረሻ ከሞት በኋላ ትንሣኤ ከዚያም ፍጻሜና እንከን የሌለው ጣዕመ ሕይወት አለ ብሎ ሰውን ለዘላለማዊ ሕዳሴ ማብቃት ነው ማለት ነው፤
ከዚህ አንጻር የሰው የመጨረሻ ዕድሉ ማርጀት ሳይሆን መታደስ እንደሆነ እንገነዘባለን፤ እግዚአብሔር የሰውንና የፍጥረታትን መታደስ የሚሻው በሰማያዊው ዓለም ብቻ ሳይሆን በምድራዊው ዓለምም ጭምር ነው፤ ለዚህም ነው በየወቅቱ የሥነ ፍጥረትን ውበት እያደሰ የሚመግበን፤ አሁን ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው እኛስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመታደስ ተዘጋጅተናል ወይ? የሚለው ነው፤  ዛሬ እያንዳንዳችን ይህንን ጥያቄ አንሥተን ኅሊናችንን በጥልቀት መጠየቅ አለብን፤ በዚህም ሳናበቃ መልሱን በትክክል ማግኘት አለብን፤ በሁለንተናችን ለመታደስም ቈራጥ ውሳኔ በራሳችን ላይ ማሳለፍ አለብን፤ አዲሱ ዘመን አዲስና ብሩህ የሆነ የደስታ ሕይወት ሊያጐናጽፈን የሚችለው በዚህ መንፈስ ተቀብለን ስንጠቀምበት ነው፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!
እኛ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ዘመናት የታደሱ ያይደሉ በርካታ ዓመታት ተጭነውን አልፈዋል፤ ቀድሞ እንበልጣቸው ከነበሩ አህጉር በታች ሆነንም በርካታ ዓመታትን አስቈጥረናል፤ የእርስ በርስ ግጭት፣ ረኃብ፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ኋላ ቀርነት የመልካም አስተዳደር እጦት በዓለም ፊት ልዩ መለያችን ሆኖአል፤ ዛሬም ከዚህ አልተላቀቅንም ብቻ ሳይሆን እንዲያውም አጠናክረን ለማስቀጠል ውል የገባን እስክንመስል ድረስ እየቀጠልንበት እንገኛለን፤ በእውነቱ እንዲህ የመሰለ ልምድ ልናፍርበትና ንስሐ ልንገባበት እንጂ ልናስቀጥለው አይገባም፤ በተፈጥሮ የታደለች ሁሉንም አሟልታ የምትገኝ ኢትዮጵያን የመሰለች ሀገር ይዘን ከሰው በታች ሆነን ስንገኝ በስንፍናችሁ ከምንባል በቀር የሀብተ ጸጋ እጥረት አለባችሁ የሚለን አናገኝም፤
ስለዚህ አሁንም ለኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በአጽንዖት የምናስተላልፈው መልእክት ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውን አይደለም ለዓለም የሚተርፍ ሀብተ ጸጋ አላትና ለኔ ለኔ በመባባል የሕዝባችንን ሰቆቃው አናስረዝም፤ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት የሚለውን ጥሬ ሓቅ በደምብ አላምጠን መዋጥ አለብን፣ ከዚያም በእኩልነትና በአንድነት ሀገራችንን እናድስ፤ ከሌሎች በደባል የሚመጡ ነገሮችን ሳይሆን የሀገሪቱ በሆኑ ዕሤቶች እንመራ፤ ለበርካታ ዓመታት የተሸከምነው ደባል የአስተዳደር ስልት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚጣጣም ሆኖ አልተገኘም፤  የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ከማንም በላይ በፈጣሪው እንደሚመካ እሱንም አጥብቆ እንደሚያምን ልኂቃኖቻችን ተገንዘቡልን፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ባስቆጠረ ታሪካችን ከእግዚአብሔር ተለይተን አናውቅም፤ በዚህም ተጠቃሚዎች እንጂ ተጐጂዎች የሆንበት ጊዜ የለም፤ በለመደው እምነት ባህልና ዕሤት ሕዝቡን ብንመራው ሁሉም ነገር ቀላል ይሆንልናል፤ ከዚህ ውጭ እንምራህ ብንለው ግን ያጋጠመንን ችግር ማስቀጠል ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ የሁሉም መነሻ ማለትም የክፋትም ሆነ የደግነት መነሻ ውሳጣዊ አእምሮአችን ነውና እሱን በማደስ በአዲሱ ዓመት አገራችንን እንድናድስ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም
አዲሱ ዘመን በሃይማኖት መንፈስ ግጭትን በውይይት፤ መለያየትን በአንድነት፤ አለመግባባትን በዕርቅ ፈትተን በመታደስ ማማ ላይ የቆመ ማኅበረ ሰብን ለመገንባት ሁላችንም ጥረት እንድናደርግ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

አዲሱ ዓመት የሰላም የዕርቅ የእኩልነትና የአንድነት ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!አሜን::
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 1 ቀን 2017ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የብፁዕ ወቅዱስነታቸው በረከት አይለየን!

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/2017-enkusatash.jpg 850 1280 tc https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc2024-09-11 20:47:062025-02-28 20:51:23መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም ርዕሰ ዐውደ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል መግባትን አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የፆመ ፍልሰታ መግባትን አስመልክተው የተላለፈ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የፆመ ፍልሰታ መግባትን አስመልክተው የተላለፈ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የፆመ ፍልሰታ... Link to: ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top