• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ሚያዝያ 8 ቀን 2009 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በትንሣኤው ኀይል በመቃብር ውስጥ በስብሶ መቅረትን ሽሮ ትንሣኤ ሙታንን ያበሠረ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!!

“ወሰበረ ኆኃተ ብርት፤ ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘኀጺን
የናስ ደጆችን ሰባበረ፣ የብረት መወርወሪያዎችንም ቀጥቅጦ ቈራረጠ።»
(መዝ. 107፥16)፡፡

ይህ አምላካዊ ኀይለ ቃል ወልደ እግዚአብሔር የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥዋዕትነቱ ብቃት እንደ ናስ የጠነከሩትን የኀጢአት ደጆች እንደሚሰባብር፣ እንደ ብረት የጸኑትን የሞት ብረቶች ቀጥቅጦ በመቈራረጥ እንደሚያስወግድ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት አንደበት የተናገረው ቃለ ብሥራት ነው፤ የኀይለ ቃሉ ምሥጢራዊ ይዘት በጠንካራ ነገር የተዘጉና በጽኑ መወርወሪያዎች ክርችም ብለው የተዘጉ ደጆች መኖራቸውን ጠቁሞ፣ እነዚህን ሰባብሮና ቀጥቅጦ በሩን የሚከፍት አንድ ኀያል መሲሕ እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደምናነበው የሰው መኖሪያ የነበረው ነገተ ኤዶም በኀጢአተ ሰብእ ምክንያት በፍትሐ እግዚአብሔር ሲዘጋ፣ በሰይፈ ነበልባል እንደተከረቸመ፣ ኪሩባውያን ኀይላትም በጥበቃ እንደተመደቡበት በግልጽ ተመዝግቦአል፡፡ ይህ የጽድቅ የክብርና የሕይወት ደጅ በዚህ ሁኔታ ሲዘጋ፣ ለሰው ልጅ የቀረለት መኖሪያ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ የተዘጋጀው፣ እሳቱ የማይጠፋ፣ ትሉ የማያንቀላፋ የእቶነ እሳት ከተማ ነበረ፤ ለመለኮታዊ ሱታፌና ለዘለዓለማዊ ሕይወት ታድሎ የነበረው የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል የተጋዘው ከላይ በተጠቀሰው የዲያብሎስ ከተማ ነበር፡፡ የዚህ ከተማ ደጆችና በሮች፣ መዝጊያዎችና መወርወሪያዎች ኀጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔና ሞተ ነፍስ ወሥጋ ነበሩ፤ የሰው ልጅ ኀጢአትን ስለ ሠራ እግዚአብሔር የቅጣት ፍርድን ፈረደበት፤ ቅጣቱም የነፍስና የሥጋ ሞት ነበረ፤ እነዚህ ነገሮች እርስ በርስ እንደ ሰንሰለት ተያይዘው የዲያብሎስን ከተማ የናስና የብረት ያህል ጠንካራ ደጅ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ ይህንን በር ሰብሮና ፈልቅቆ የሰዎችን ነፍሳት ከዲያብሎስ ከተማ መዞ ማውጣት ለፍጡር ፈጽሞ የማይቻል ነበረ፤ ሦስቱም ነገሮች ከፍጡራን ዐቅም በላይ በመሆናቸው አምላካዊ ኀይል የግድ አስፈላጊ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ሥጋችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም በመገለጥ እኛ ከኀጢአት ከፍትሐ ኵነኔና ከሞተ ነፍስ የምንድንበት መንገድ እርሱ ብቻ መሆኑን በአጽንዖት አስተማረ፡፡

በመጨረሻም እንደ ትምህርቱና እንደ ቃሉ በመስቀሉ ኀይል ወይም በመሥዋዕትነቱ ብቃት ሦስቱ ነገሮች ማለትም ኀጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔና ሞተ ነፍስ ከሰው ጫንቃ ላይ እንዲወገዱ አደረገ፤ ለሰው የማይቻል የነበረ ይህ ግብረ አድኅኖ በተዋሕዶ አምላክም ሰውም ለሆነ ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚቻል ነበረና በእርሱ መሥዋዕትነት እውን ሆነ፡፡ ጥንቱም ለሰው ልጅ ሕይወትና ክብር ጠንቆች የነበሩ እነዚህ ሦስቱ ነበሩና እነሱ ተሰባብረውና ተቀጥቅጠው ሲወገዱ በሲኦል ይኖሩ የነበሩ የሰዎች ነፍሳት በአጠቃላይ ዓለም ከመፈጠሩ በፈት ወደተዘጋጀላቸው ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ተመልሰው ገቡ፡፡ ከክርስቶስ ሞት በኋላ የነፍሳተ ሰብእ ጒዞ ወደ ዲያብሎሰ ከተማ ወደ ሲኦል መሆኑ ቀርቶ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ወደ ጽዮን መንግሥተ ሰማያት ሆነ፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ከምንም በላይ በላቀ ሁኔታ የምናከብርበት ምክንያት ኀጢአት ፍትሐ ኵኔና ሞተ ነፍስ ወዲያ ተሽቀንጥረው በምትካቸው በክርስቶስ ቤዛነት ጽድቅን ይቅርታንና ሕይወተ ነፍስን የተቀዳጀንበትና ከድል ሁሉ የበለጠ የድል ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ዐቢይ ነገር የክርስቶስ ድርጊቶች በሙሉ ለሰው ድኅነት ሲባል ብቻ የተደረጉ እንጂ ለእግዚአብሔር የሚፈይዱት አንዳች ምክንያት የሌላቸው መሆኑን ነው፤ ይህም ማለት በክርስቶስ የተፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ ለእኛ ሲባል የተደረጉ መሆናቸውን መገንዘብ አለብን ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ተሰቀለ ሞተ ተቀበረ ተነሣ ሲባል እኛ ተሰቀልን ሞትን ተቀበርን ተነሣን ማለት እንደ ሆነ ልብ ብለን ልናስተውል ይገባል፤እኛ ተሰቅለን ሞተንና ተቀብረን የኀጢአታችንን ዕዳ የመክፈል ዐቅም ስላጣን ለኛ ያልተቻለውን ጌታችን ስለ እኛ ብሎ፣ በእኛ ምትክ ሆኖ ለኀጢአታቸን መከፈል የነበረበትን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ አድኖናልና ነው፡፡

እኛ በክርስቶስ ቤዛነት ነፃነታችንን ተቀዳጅተን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ዳግመኛ መግባት የቻልነው ክርስቶስ የከፈለው መሥዋዕትነት ለእኛ ተብሎ ስለ እኛ የተደረገ በመሆኑ ነው፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ የእርሱ ትንሣኤ ብቻ እንደሆነ አድርገን የምንገነዘብ ከሆነ ታላቅ ስሕተትም ኀጢአትም ነው፤ ኀጢአት ኵነኔና ሞተ ነፍስ የሌለበት እርሱማ ምን ትንሣኤ ያስፈልገዋል? ትንሣኤ ለሚያስፈልገን ለእኛ ተነሣልን እንጂ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን አስመልክቶ ሲያስተምር “እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጸጋ ስለሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ አስነሣን ከእርሱ ጋርም በሰማያዊ ስፍራ አስቀመጠን” ብሎአል (ኤፌ. 2፥4-7)፡፡ ከዚህ አኳያ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በቀር የትንሣኤያችን ጉዳይ በክርስቶስ ትንሣኤ የተረጋገጠና ያለቀለት ነገር እንደሆነ ማስተዋል፣ መገንዘብ፣ መረዳትና፣ ማመን ይገባናል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ የእኛ ትንሣኤ ነው ብለን ሁሌም መውሰድና መቀበል አለብን፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ የመጨረሻ ግቡ የሰው ልጆች ትንሣኤን ማረጋገጥ ነውና፤ የትንሣኤ ዕድል በክርስቶስ ቤዛነት ለሁሉም ተሰጥቶአል፤ አዋጁም ሕጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ጸድቆአል፤ የቀረ ነገር ቢኖር የመጨረሻው ተግባራዊ ፍጻሜ ነው፤ እርሱም ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ስለሆነ ወደዚያው በእምነትና በሥነ ምግባር መገስገስ ነው፤ ሰውን ለዚህ ዐቢይ ጸጋና ዕድል ያበቃ እግዚአብሔር አምላካችን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውና ያስተማረው ሁሉ ምን ለማግኘት ነበረ ተብሎ ቢጠየቅ በአጭር አረፍተ ነገር “ሰውን ለማዳን” ነዋ ! ብሎ መመለስ ይቻላል፤ እውነቱም ሐቁም ይህና ይህ ብቻ ነው፤ ይህን ያህል ውጣ ውረድና ይህን ያህል ዋጋ ያስከፈለ የሰው መዳን በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ተፈላጊ እንደሆነ በአድናቆት መመልከትና መቀበል ታላቅ አስተዋይነት ነው፡፡ በዚህ ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ክንውን እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን በቅተናል፤ ልጆቹም ሆነናል፤ ታድያ ልጅ በጠባይም፣ በመልክም በሥራም አባቱን ቢመስል ጌጥም የክብር ክብርም ነውና በሁሉም ነገር አባታችንን መከተልና መምሰል ከእኛ ይጠበቃል፡፡ እግዚአብሔር አባታችን እንደመሆኑ፣ እኛም ልጆቹ እንደመሆናችን መጠን የአባታችንን ተቀዳሚ መደበኛና ቀዋሚ ሥራ የሆነውን ሰውን የማዳን ሥራ ሳናቋርጥ የማስቀጠል ግዴታ አለብን፡፡ ዛሬም ዓለማችን የሚያድናት፣ እስከ ሞት ድረስም ደርሶ ቤዛ የሚሆናት፣ ሰላምንና ነፃነትን የሚያቀዳጃት የእግዚአብሔርን ልጅ ትፈልጋለች፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ከመቃብር በመነሣትና ሙታንን በማስነሣት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ ጌታችን ከመሞቱና ከመነሣቱ በፊት ብዙ ሰዎችን ከረኃብ፣ ከበሽታ፣ ከሥነ-ልቡና ውድቀት አስነሥቶአል፤ ከተሳሳተ አመለካከት፣ ከጭካኔ፣ ከመለያየት አባዜም በተኣምራትም በትምህርትም አድኖአል፡፡ ጌታችን ሰውን የማዳን ሥራ በእርሱ ብቻ ተሠርቶ እንዲቀር አላደረገም፤ እኛም እንድንሠራውና እንድንፈጽመው አዘዘ እንጂ፡፡ ከዚህ አንጻር በክርስቶስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ብዙ በሽተኞች የሚያድናቸው አጥተው በየጎዳናው፣ በየሰፈሩ፣ በየመንገዱ፣ ወድቀው ይሠቃያሉ፤ እነዚህን ማን ያድናቸው? የተመጣጠነና በቂ ምግብ አጥተው ብዙ ሕፃናት፣ እናቶችና አረጋውያን በረኃብ አለንጋ ይገረፋሉ፤ ኅብስቱን አበርክቶ እነርሱን ማን ይመግባቸው? በተሳሳተ አመለካከት ለሥነ ልቡና ውድቀት፣ ለቀቢጸ ተስፋና እንደዚሁም ለስሑት ትምህርተ ሃይማኖት ተጋልጠው ሃይማኖታቸውንና ታሪካቸውን በመጻረር የሚገኙ ብዙ ናቸው፤ እነዚህን ማን አስተምሮ ወደ እውነቱ ይመልሳቸው?

በእግዚአብሔር ዘንድ እነዚህን ሥራዎች መሥራትና ማስተካከል የሕዝበ ክርስቲያኑና የመምህራነ ወንጌል ግዴታዎች ናቸው፡፡ በማኅበረ ሰቡ ሥር ሰደውና ተስፋፍተው የሚታዩት እነዚህ መሰል ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ችግሮችን በወሳኝነት ለመቋቋም ትምህርትና ልማት መተኪያ የሌለው ሚና ይጫወታሉ፤ ለሀገራችን ድህነት መወገድ ቍልፍ መፍትሔ ሃይማኖትና ልማትን አጣምሮ መያዝና በእነርሱ ጸንቶ መኖር አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ከነዚህ ውጭ የሆነ ኑሮ ምንም ቢሆን ምሉእ አይደለም፤ ጣዕምም የለውም፤ የሰውን ሁለንተናዊ ሕይወት ለማዳንሁለቱንም በተግባር መተርጐም ያስፈልጋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በእነዚህ ነገሮች የታደለች እንደነበረችና እነዚህን አጣምራ በመያዝ የት ደርሳ እንደነበረ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የሚታዩና የማይታዩ መረጃዎች ምስክርነታቸውን ከመስጠት ዛሬም አልተገቱም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን የተያያዘችውን የልማትና የሰላም ጒዞ አጠናክራ እስከ ቀጠለች ድረስ ሕሙማን የሚፈወሱባት፣ ርኁባን ጠግበው የሚኖሩባት፣ በመንፈሳዊና በዘመናዊ ዕውቀት የበለጸጉ ዜጎች የሚታዩባት ሀገር የማትሆንበት ምክንያት ምንም የለም፡፡ መላው የሀገራችን ሕዝቦች በኑሮአቸወና በሕይወታቸው መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉት በሌላ ሳይሆን እነርሱ ራሳቸው እንደቀድሞ አባቶቻቸው በራስ በመተማመንና በልበ ሙሉነት፣ በትጋትና በቅንነት፣ በፍቅርና በስምምነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት፣ በሰላምና በአንድነት በመቻቻልና በአብሮነት ሆነው በሚያስመዘግቡት የልማት ውጤት እንደሆነ መርሳት የለባቸውም፡፡ ሀገርን ለማልማትና የጠላትን ጥቃት በብቃት ለመመከት በአንድነት ሆኖ ከመታገል የተሻለ አማራጭ የለም፤ ስለዚህ ሕዝባችን እነዚህን እስከመቼውም ቢሆን በንቃት ሊከታተላቸውና ሊጠብቃቸው ይገባል፤ በአእምሮ የላቁ ሆኖ መገኘት በራሱ እውነተኛ ትንሣኤ ነውና፡፡

በመጨረሻም፡ የጌታችን ትንሣኤ “ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ዐላማን ያሳካ ፍጻሜ እንደሆነ ሁሉ የትንሣኤ ልጆች የሆን እኛ ሰውን ለማዳን በሚደረገው መንፈሳዊና ልማታዊ ርብርቦሽ ተሳትፎአችንን አጠናክረን እንድንቀጥል መንፈሳዊና አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡ መልካም በዓለ ትንሣኤ ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32017-04-16 13:22:572025-01-28 13:24:10ሚያዝያ 8 ቀን 2009 ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: መጋቢት10 ቀን 2009 ዓ.ም የደብረ ዘይት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: መጋቢት10 ቀን 2009 ዓ.ም የደብረ ዘይት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ መጋቢት10 ቀን 2009 ዓ.ም የደብረ ዘይት በዓል ቃለ ምዕዳንና... Link to: ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top