33ኛው ዓመታዊ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት 5-8 ቀን 2007 ዓ/ም አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

እንኳን ወደዚህ ታላቅ ጉባኤ መጣችሁ፣ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ” በማለት ቅዱስነታቸው ስብከተ ወንጌልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት “ይህ ዓመት ስብከተ ወንጌል ይበልጥ የምናስፋፋበት፣ የምእመናን ብዛት የምንጨምርበት፣ ሰላምን ፍቅርን የምናጠናክርበት መሆን አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ መልካም አስተዳደር ማስፈንና የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት በትክክል ሥራ ላይ ማዋል ስንችል በመሆኑ ሁላችንም ለተግባራዊነቱ መትጋት አለብን ብለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በዚህ የጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት በሚደረገው ሀገር ዐቀፍ ጥረት ቤተ ክርስቲያን ምእመናኖቿን በማስተማር ድርሻዋን መወጣት እንዳለባትና በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሥጋት በተለይ ደግሞ የአፍሪቃውያን ችግር እየሆነ ያለው የኢቦላ በሽታ ወደ ሀገራችን እንዳይገባ በመላ ሀገራችን የምሕላ ጸሎት እንዲደረግና መንግሥት እያደረገ ባለው የመከላከል ሥራ ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ ምእምናን ማስተማር እንደሚገባ አባታዊ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

ቅዱስነታቸው በዚህ አባታዊ መመሪያቸው ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት “ለቤተ ክርስቲያን ያላችኋት ሀብቶች እናንተ ናችሁ፣ በዚህ ዓመት ወጥታችሁ ወርዳችሁ በሠራችሁት ሥራ ባስመዘገባችሁት የገቢ እድገት ልትመሰገኑ ይገባል፣ ለወደፊቱም ጥረታችሁን አጠናክራችሁ መቀጠል አለባችሁ፡፡ ከዚህ ጋር የምእምናን እንደ ጥንቱ ቤተ ክርስቲያናቸውን እና እምነታቸውን አጠንክረው እንዲይዙ በስብከተ ወንጌል መጠናከርና መስፋፋት ላይ የበለጠ ልንሠራ ይገባል” ብለዋል፡፡ ‹‹መልካም አስተዳደር ምን ጊዜም ከኅሊናችን መጥፋት የለበትም ያሉት ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል ሥራችን በኀላፊነት፣ በተጠያቂነት፣ በንጽሕናና በቅድስና መሥራት አለብን›› በማለት መልእክታቸውን ቋጭተዋል፡፡