የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ ኣሜን !!

በሀገር ውስጥና በልዩ ልዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፡-

በመዋዕለ ጾሙ ሰይጣንንና መስሓቲ ተግባሩን ድል በማድረግ ድል እንድንነሣ ያደረገን ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ጾመ ኣርብዓ በሰላም ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
‹‹ወልበሱ ወልታ እግዚአብሔር በዘትክሉ ተቃውሞቶ ለመናግንተ ሰይጣን፤
የሰይጣንን ሽንገላ መቃወም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ›› (ኤፌ.፮፥፲፩)፤

እኛ ሰዎች ቀዋሚና ምሕረት የለሽ ጠላት እንዳለን እናውቃለን፤ ይህ ጠላት ሰይጣን፣ ዲያብሎስ፣ክፉ መንፈስ፣ ርኩስ መንፈስ ተብሎ እንደሚጠራም ቅዱስ መጽሓፍ ነግሮናል፤ዲያብሎስ ከጥንት ጀምሮ በክፉ ሽንገላው ሰዎችን ሲጥል ኖሮኣል፤ ኣሁንም ከዚህ ክፉ ተግባሩ ኣልታቀበም፤ ለወደፊቱም ይታቀባል ተብሎ ኣይጠበቅም፤ ጌታችን በዚህ ዓለም በሥጋ በተገለጠ ጊዜም ይህ ክፉና ርኩስ መንፈስ በሽንገላ ቃሉ ጌታችንን ሊጥል ያልተሳካ ሙከራ ኣድርጎኣል፡፡ ርኩሱ መንፈስ ጾም መንፈሳዊ ኃይልን እንደሚያቀዳጅ ያውቃልና፣ጌታችን ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ ኣርባ ቀንና ኣርባ ሌሊት መጾሙን ተመልክቶ፣በሽንገላ ቃሉ ሊጥለው ሙከራ ኣድርጎኣል፤ይህንን ያደረገበት ዋና ምክንያትም ጾም መንፈሳዊ ኃይል መሆኑን በውል ያውቃልና በጾም ኃይል ከእጄ ያመልጣል ብሎ በማሰቡ ነው፤ ይሁን እንጂ ሰይጣን የሰውን ደካማ ጠባይ በመጠቀም ያስለመደው ሽንገላ፣በተዋሕዶ ሰውም ኣምላክም በሆነው ጌታችን ላይ ሊሳካለት ባለመቻሉ ተሸንፎና ተስፋ ቆርጦ ሊሄድ ችሎኣል፡፡

የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን!

የጌታችን ድል ኣድራጊነት ያስተማረን ብዙ ነገር ኣለ፤በዚህ ተግባራዊ ትምህርቱ እኛ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን ድል የምናደርግባቸው ሁለት መሳሪያዎችን በዋናነት ኣሳይቶናል፤ እነሱም የእግዚአብሔርን ጋሻ መልበስና በጾም መንፈሳዊ ኃይልን መቀዳጀት ናቸው፡፡ ሁሌም እንደምንማረው በውስጣችን ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ኣሉ፤ እነሱም ፍትወተ ሥጋና ፍትወተ መንፈስ ናቸው፤ እነኝህ ሁለት ነገሮች ኣንዱ ላንዱ ፍጹም ተቃራኒ መሆናቸውን ቅዱስ መጽሓፍ እንዲህ በማለት ያስረዳል፡-‹‹ እስመ ሥጋኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ መንፈስ፤ ወመንፈስኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ ሥጋ፤ ወይትኣበዩ በበይናቲሆሙ ከመ ኢትግበሩ ዘትፈቅዱ፤ ወባሕቱ እብለክሙ በመንፈስ ሑሩ ወፍትወተ ሥጋክሙ ኢትግበሩ፣ማለትም ሥጋ መንፈስ የማይወደውን ይወዳል፤ መንፈስም ሥጋ የማይወደውን ይወዳል፤እርስ በርሳቸውም ይቀዋወማሉ፤ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ ኣትችሉም፤ ነገር ግን እላለሁ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋን ምኞት ግን ከቶ ኣትፈጽሙ››(ገላ.፭÷፲፮‐፲፰)፡፡

እነኝህ የውስጣችን ጠባዮች በዚህ ደረጃ እርስ በርስ የሚቃረኑ መሆናቸው ለምናስተውላቸው በግልጽ የሚታወቁ ናቸው፤ ከዚህ ኣንጻር ሰይጣን ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ የሥጋችንን ፍላጎት እንድንከተል ይገፋፋናል፤ መሳሪያዎቹ ደግሞ ፍቅረ መባልዕት፣ ፍቅረ ንዋይና ፍቅረ ሢመት ናቸው፤ ይህም በመሆኑ ነው ሰይጣን፣ በነዚህ ጌታችንን ሊሸነግለው የሞከረ፤ይሁንና ጌታችን እነኝህን የሽንገላ መሳሪያዎች ሰባብሮ ጥሎኣቸዋል፤የጣላቸውም በጾምና በእግዚአብሔር ቃል ነው፤
ጾም መጾም ማለት ከፍቅረ መባልዕት፣ ከፍቅረ ንዋይና ከፍቅረ ሢመት ፍላጎት ጨርሶ መራቅ ማለት ነው፤ ይህንን ኣደረግን ማለት ደግሞ ሥጋችን የማይወደውን፣መንፈሳችን ግን የሚወደውን ነገር ኣደረግን ማለት ነው፤ ይህ ሲሆን ሰይጣን ከሰረ፤ ድልም ሆነ ማለት ነው፤ በዚህ መንፈሳዊ ኃይል ዲያብሎስ ተሸንፎና ተስፋ ቆርጦ ይሄዳል፡፡ ከዚህ ኣኳያ እኛም በቃለ እግዚአብሔር እየተመራን የምንጾምበት ምክንያት የሥጋችንን ፍላጎት በመግራት ለነፍሳችን ፍላጎት ለማደርና በዚህ ኃይለ መንፈስ ሰይጣንን በማሸነፍ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ ለመሆን ነው፡፡

የተከበራችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን!

የጾም ዋና ዓላማ ሥጋዊ ፍላጎትን መግራት፣ በምትኩ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎትን ማጐልበት እንደሆነ ተነግሮናል፤በመሆኑም ይህንን መርሕ ጠብቀን መጾም ግዴታችን ይሆናል፤ ዛሬ ባለንበት ዓለም ሥጋዊ ፍላጎታችን ያየለበት፣መንፈሳዊ ፍላጎታችን ግን የተዳከመበት ዘመን ላይ እንገኛለን፤ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከኣንድነት ይልቅ መለያየት፣ ከመራራት ይልቅ ጭካኔ፣ ከእምነት ይልቅ ክሕደትና ኣስመሳይነት በዓለማችን ላይ የበላይነቱን ይዞ መገኘቱ ለዚህ ማሳያ ነው፤ የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን! ይሁንና ዓለም ቢሰማም ባይሰማም፣ ሓቁም ጠቃሚውም የመንፈስን ፍላጎት ማጐልበት ስለሆነ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ማለትም፣ ፍቅርን ሰላምን፣ ኣንድነትን፣ ርኅራኄንና፣ ሃይማኖትን፣ ማስፈን ምርጫችን ልናደርግ ይገባል፤ ቤተክርስቲያንም እንድንጾም የምታስተምረን እነዚህን ለመተግበር ጾም ፍቱን መሳሪያ ሆኖ ስለሚገኝ ነው፡፡

ከዚህ ኣንጻር የጾም ዓላማውና ግቡ ጽኑዕ ሃይማኖትን፣ እውነተኛ ፍቅርን፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ልባዊ ኣንድነትን፣ የማይናወጽ ፍትሕንና እኩልነትን፣ ወሰን የሌለው ርኅራኄን በውስጣችን፣ ብሎም በዓለማችን ማሥረጽ እንደሆነ በውል ተገንዝበን ጾሙን መጾም ይገባል፤ልንለብሳቸው የሚገቡ እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች የእግዚአብሔር ጋሻዎች ናቸውና፡፡ ይህንን ካደረግን እንደ ጌታችን የሰይጣንን ሽንገላ በጣጥሰን በመጣል በኣስተማማኝ ሁኔታ ድል ማድረግ እንችላለን፤ የተጠራነውም ለዚሁ ነው፡፡

በመጨረሻም፡-

የሕዝባችንና የሀገራችን የራስ ምታት ሆኖ የሚገኘውን ያለመግባባት ዝንባሌ ለመቅረፍ ከልብ በመጸለይ፣ እንደዚሁም የተራቡትን በማጒረስ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ፍትሕ ለተነፈጉትም እውነተኛ ፍትሕን በመስጠት፣ መዋዕለ ጾሙን እንድንጾመው በእግዚአብሔር ስም ኣባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሓት ለእግዚአብሔር ኣሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፰
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ታኅሣሥ 29 ቀን 2018 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመት ምሕረት፤

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ ኣምላክ አሜን!

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፣

እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም የላከ እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓስራ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!

“ወበዝንቱ ተዓውቀ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር ላዕሌነ እስመ ለወልዱ ዋሕድ ፈነዎ ውስተ ዓለም ከመ ንሕየው በእንቲኣሁ፤ ወዝንቱ ውእቱ ፍቅሩ ለእግዚአብሔር፡- የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ዘንድ ተገለጠ፤ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነው፤ (፩ዮሓ. ፬፥፱)

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው እኛ ምሥራቃውያን ክርስቲያኖች በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓል፣ የጌታችን የኣምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ነው፤ በዓለ ልደት የእግዚአብሔር ሰላምና ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ የታወጀበት ዕለት ነው፤ በዚህ ዕለት የሆነው የእግዚአብሔር ፍቅርና ሰላም ቃላዊ ወይም ተምኔታዊ ኣልነበረም፤ ወይም ደግሞ በርቀት በመልእክት የተላለፈ ኣልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ሰብእናችንን በመዋሐድ፣ በተግባር ሆኖ በመገኘት፣ እንዲሁም ለመሰጠት ዝግጁ በመሆን የተገለጠና የታየ ሰላምና ፍቅር ነው፤ እግዚአብሔር የኛን ሰላምና ፍቅር በእጅጉ የሚሻው መሆኑን ለመረዳት፣ የኛን ሰብአዊ ክዋኔ በምልአት ተዋሕዶ በመካከላችን ከመገኘት የተሻለ ሌላ ማረጋገጫ ሊኖር ኣይችልም፤ እኛ ሰዎች ለእግዚአብሔር ጠላቶቹ ተብለን በቅዱስ መጽሐፍ የተገለጽን ነን:: እግዚአብሔር ጠላቶቹን የራሱ አካል አደረጋቸው ሲባል ከመስማት የበለጠ አስደናቂ ነገር በዚህ ዓለም ምን ሊኖር ይችላል?

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

እግዚአብሔር ሰብኣዊነታችንን በምልአት ተዋሕዶ በዓለማችን እንዲገለጥ የሆነበት ዋና ምክንያት እሱ እንዳስረዳን እኛ በሕይወት እንድንኖር ነው፤ ይህንንም ያደረገው ከሁሉ በላይ የሆነ ሌላ ገፊ ኃይል ገፋፍቶት ሳይሆን ድንበር የለሽና ፍጹም ፍቅሩ አነሣሥቶት እንደሆነ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንረዳለን፤ የእግዚአብሔር ፍቅር እኛ ከምናውቀው ፍቅር ሁሉ በላይ መሆኑንም በዚህ እናስተውላለን፤ ለጠላቶቹ ሕይወት ፍቅርና ሰላም ሲል እነሱን ከመሆን አልፎ እስከ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚዘልቅ ፍቅር እጅግ በጣም ታላቅ ነው፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት !

እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፈቃድ እኛ በሕይወት በሰላምና በፍቅር እንድንኖርለት ከሆነ የእኛ ግብረ መልስም ከዚህ የተለየ ሊሆን ኣይገባም፤ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ለማዳን እንጂ ለማጥፋት አልመጣም፤ የእኛም ሕይወት የሚጠበቀው ኣንዱ ሌላውን በማዳን እንጂ በማጥፋት እንዳልሆነ ጌታችን በቃልም በተግባርም በኣጽንዖት ነግሮናል፤ በዚህ አስተሳሰብና እምነት እንድንኖርም አዞናል፡፡ ታድያ በቃሉ ለመኖርና ለእሱ ለመታዘዝ ቃል የገባን እኛ ክርስቲያኖች ይህን ሁሉ እርግፍ ኣድርገን በመተው እርስ በእርስ ለመጠፋፋት መሽቀዳደም ምን ይሉታል? ይህስ ለማን ይበጃል?  የአንድ ሀገር ሕዝቦች ይመካከራሉ፣ ይቻቻላሉ፣ ይታገሣሉ፣ ጊዜ ሰጥተው ያስቡና መፍትሔ ያበጃሉ እንጂ ማን በማን ላይ ይነሣል? ይህ ለማንኛችንም አይበጀንምና ወደ ኣእምሮኣችን እንመለስ የሚል ጥሪ የወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክት ነው፤

በመጨረሻም፤

ይህንን የተቀደሰ በዓል ስለ ሃገራችን ዘላቂ ሰላም በመጸለይና በማሰብ እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት የምግብ፣ የልብስና የመጠለያ እጥረት ያጋጠማቸው ወገኖቻችንን በመደገፍና በመርዳት ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ለሀገር ኣንድነትና ለሕዝብ ፍጹም ሰላም መስፈን ከልብ በመነሣሣት በዓሉን እንድናከብር አባታዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን!!

መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

· ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
· ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣
· ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ ቅዱስ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፤

የጎደለብንን እየሞላ አገልግሎታችንን እያቃና ከዚህ ላደረሰን፣ ይህንን ዓመታዊና ሐዋርያዊ ጉባኤያችንን ለማካሄድም ለሰበሰበን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ምስጋና እናቀርባለን፡፡
“ወእፌጽም ታሕጻጸ ሕማሙ ለክርስቶስ በሥጋየ በእንተ ሥጋሁ እንተ ይእቲ ቤተ ክርስቲያኑ፡- ስለ አካሉ ማለትም ስለ ቤተክርስቲያኑ ስል በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጎደለውን እፈጽማለሁ” (ቈላ.፩÷፳፬)

ያለንበት ዓለም በሁሉም ነገር በጉድለቱ የሚታወቅ ነው፤ ጉድለት ባይኖርና ሁሉም የሞላለት ቢሆን ኖሮ ፍጥረት እርስ በርስ የሚተረማመስበት ሁኔታ አይኖርም ነበር ወይም አሁን ባለበት ደረጃ የከፋ አይሆንም ነበር፡፡  እግዚአብሔር ሁሉንም አሟልቶ መፍጠር ወይም መስጠት የሚችል ከሃሊ አምላክ ቢሆንም፣ እሱ ባወቀ ፍጥረትን ሁሉ ጉድለት ያለበት አድርጎ ፈጥሮታል፤ በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ ጉድለቱን ለመሙላት በሚያደርገው ፍትጊያ እየተጋጨ እርስ በርስ ሲተረማመስ ማየቱ የተለመደ ነው፡፡ ምድራዊቷ ቤተ ክርስቲያንም በጐዶሎው ዓለም እስካለች ድረስ ከሚመጣው ፈተና አታመልጥም፤ ይህም በመሆኑ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች “የጎደለውን እፈጽማለሁ” በማለት ሲጽፍ እናስተውላለን፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በጐዶሎው ዓለም የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ጉድለቷን ለመሙላት ብዙ መሥዋዕትነት ከፍላለች፤ ቤተ ክርስቲያን ለቀጣዩ ትውልድ መሸጋገርና የጐደለባትን ለመሙላት ስትል ከቅዱሳን ሐዋርያት አንሥቶ እስካለንበት ዘመን ድረስ ብዙና የብዙ ብዙ አበው ካህናትን፣ ሊቃውንትንና ምእመናንን ከደም ጠብታ፣ እስከ ቁስ ስጦታ ገብራለች፡፡

አሁን በምድር ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሁሉ ውጤት ናት፤ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ዛሬም የጐደለባት ብዙ ነገር አለ፤ በተቻለ መጠን እርሱን ለሟሟላት መጣርና በተሻለ ሁኔታ ወደፊት ማሻገር ደግሞ የዚህ ጉባኤ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ጉባኤ ብቻው አይደለም፤ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ የእግዚአብሔር ልጆች ድምፁን ለመስማት ከዙሪያው ሆነው በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ እነኝህ የእግዚአብሔር ልጆች ለመስማት ብቻ ሳይሆን ድምፁን ሰምተው ለመታዘዝም የተዘጋጁ ናቸው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ “ሁለትም ሦስትም ሆናችሁ በስሜ በተሰበሰባችሁበት እኔ በመካከላችሁ እገኛለሁ” በማለት ጉባኤውን የመሠረተው አምላክ ከዚህ ጉባኤ መካከል አለ፡፡

በመሆኑም ይህ ጉባኤ የተወሰን አባቶች ብቻ ሳንሆን ብዙ ሰማውያንና ምድራውያን ባለድርሻ ያሉበት፣ መንፈስ ቅዱስም በመንፈስ የሚመራው እንደሆነ የማይታበል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ጉባኤው በምድር ያለችውን የእግዚአብሔር መንግሥት በበላይነት የሚመራ ነውና፣ ያለበት ኃላፊነት ከባድና እጅግ የላቀ ነው፡፡ ጉባኤው ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ የሚሰጠው ሽልማት ታላቅ እንደሆነ ሁሉ፣ ኃላፊነቱን በትክክል ካልተወጣ ደግሞ ተጠያቂነቱ በዚያው ልክ ከባድ ነው፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለጋል ተብሎአልና፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

እኛ በአገልግሎትና በመሪነት በምንገኝበት በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የጐደሉባት ነገሮች ብዙ ናቸው፤ ከሁሉ በላይ በውስጣችን የአንድነት ጐድለት በስፋት ይታያል፤ ለተሰየምንለት መለኮታዊ ተልእኮ አንድ ሐሳብ፣ አንድ ቃል፣ አንድ ልብ ሆነን መሰለፍ ያለመቻል ክፍተት እየተንጸባረቀ ነው፡፡ የዘመኑን ጥበብና ስልት ያልተከተለ ሐዋርያዊ ተልእኮአችንና አስተዳደራችንም ምእመናንን አላረካም፤ ክፍተቱ የሚድያ ቀለብ ከመሆንም አልፎ በጎቻችን በሌሎች እንዲዘረፉ ትልቅ በር እየከፈተ ነው፡፡ በእነዚህ ዓበይት ጉዳዮች እና በመሳሰሉት ጉድለቶቻች ላይ ፈጣን፣ ቈራጥና አዋጭ የሆነ ሥራ ካልሰራን ለወደፊት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ጥያቄ ውስጥ መክተቱ አይቀሬ ነው፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

ቤተ ክርስቲያናችን በተጠቀሱት ችግሮች ተከባ ባለችበት ሁኔታ የሀገራችን ሰላም መቀዛቀዝ ደግሞ ሌላው ተጨማሪ ጉድለትን እያስከተለብን ነው፡፡ አማንያን የመንፈስና የሥነ ልቡና ሰላም ከማጣታቸውም በላይ አካላቸው ለሞትና ለጉዳት፤ ሃብታቸው ለዝርፊያና ለውድመት እየተዳረገ ነው፡፡ ይኽም ሁሉ ሆኖ ፍትሕን እያገኙ አይደለም፤ አብያተ ክርስቲያናትም በምእመናን ፍልሰት እየተዘጉም እየተቃጠሉም ነው፡፡

ከዚህም ሌላ የሌለን ነገር እንዳለ አስመስሎ ከየአቅጣጫው የሚወረወረው የባዕዳን ስም የማጥፋት ዘመቻ፣ የቤተ ክርስቲያኗን እምነት ከመንቀፍና ከማብጠልጠል በላይ አልፎ የቅዱሳንን ቅዱስ ሥዕል በአደባባይ እስከ መቅደድ ተደርሶአል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ላይ በዓላማ የተነሡ አካላት የላኳቸው እንዳሉ በሚመስል መልኩ በስመ ተሐድሶ የሚደረገው እንቅስቃሴ የኛው መለያ የሆነውን ንዋየ ቅድሳትና ልብሰ ተክህኖ፣ መዝሙርና ሥርዓተ አምልኮ በመጠቀም ቤተ ክርስቲያናችንን በአደባባይ እየተዳፈረ ይገኛል፡፡

ይህ አላስፈላጊ ተግባር የሀገሪቱን ዜጎች በእኩልነት የሚያስተዳድረውን ሕገ መንግሥት በቀጥታ የሚፃረር ድርጊት ነው፤ ሆኖም በሕግ የሚጠይቅና የሚያስቆም አካል አልተገኘም፤ እኛም ዝምታን የመረጥን መስለናል፡፡ ነገር ግን መፍትሔው ዝምታ ሳይሆን በሕግ አግባብ ነገሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ እንደሆነ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!

በዘመናችን እየተከሠተ ያለው ችግር ስንዘረዝር ውለን ብናድር መናገሩ በራሱ መፍትሔ ሊያመጣልን አይችልም፤ ጉባኤው ከዚህ በላይ መናገር እንደሚችልም እንገነዘባለን፤ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል መደላድል ይህ ጉባኤ በዚህ ስብሰባ ሊተልም ይገባል ብለን ከአደራ ጋር ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በሌላ በኩል በሀገራችን ያለው ያለመረጋጋት በሕዝባችን አጠቃላይ ሥነ ልቡና በሀገሪቱ አንድነትና ዕድገት የሚያስከትለውን ጫና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፤ የሕዝቡ ሥነ ልቡና ከተጐዳ የነገው ዕድል ጤናማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ችግሩ እየታየ ያለው በዋናነት በሀገራችን ፖለቲከኞች በመሆኑ ነገሩ የተወሳሰበና የተራዘመ እንዲሆን አድርጎታል፤ በመሆኑም ይህ የርስ በርስ ግጭት ቆሞ ችግሮች በውይይትና በድርድር በመፍታት የወንድማማች እልቂት የሚያስቆም የሰላምና የዕርቅ ዕድል ቅድሚያ እንዲሰጠው ጉባኤው የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ የነገው ትውልድ ልማታዊ ተስፋ እውን ሊሆን የሚችለው ሰላምና አንድነት ሲኖር ነውና መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኞችና ነፍጥ ያነሡ ወገኖች ሁሉ ለሰላም መስፈንና ለልማት ዕድገት መረጋገጥ ሲባል ወደ መግባባት እንዲመጡ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም

ዓመታዊውና ቀኖናዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ዓቢይ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት የተከፈተ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ በእግዚአብሔር ስም እናበስራለን፡፡ እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲8 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን

ብፁዕ ኣቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ ኣስኪያጅ፤
ብፁዕ ኣቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፤
ብፁዕ ኣቡነ ሕርያቆስ
የኣዲስ ኣበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡር…..
ክብርት…..
ክቡራን ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣
ክቡራን ኣምባሳደሮችና የኮር ዲፕሎማቶች፣
ክቡራን የቤተ ክርስቲያናችን የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ኣገልጋዮችና ሰራተኞች፣
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ጀግኖች ኣርበኞች፣
የተከበራችሁ የፀጥታ ኣስከባሪ ኣባላት፣
የተወደዳችሁ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ልጆቻችን፣
በኣጠቃላይ በዚህ ታላቅ ሥነ በዓል የተገኛችሁና በዓለም ዙሪያ ሆናችሁ በዓሉን በመከታተል የምትገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ፦

ስሕተት በወለደው በደልና ኃጢኣት የደከሙትን በኃይለ መስቀሉ የሚታደግ ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ መስቀሉ በሰላም ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“ወለእለ ፃመዉ በመስቀሉ ይባልሕ፡- የደከሙትን በመስቀሉ ይታደጋል፤ (መጽሓፈ ኪዳን)፤

እግዚአብሔር ኣምላካችን በሁለመናው እንከን የለሽ ፍጹም ኣምላክ ነው፤ እንደዚህም በመሆኑ ጥፋትን የማይወድ ኣምላክ ነው፤ ይሁንና የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ሕግ ላይ ድፍረትን የተሞላ ስሕተት ወይም ጥፋት በመፈጸሙ እግዚአብሔርን ኣስቈጣ፤ ከዚህ ኣንጻር ሰው በዚህ ተግባሩ ደካማ ሆኖ ተገኘ። እግዚአብሔርም ፈታሒ በጽድቅ፣ ኰናኒ በርትዕ ነውና ሰውን በጥፋቱ ቀጣ፤ የቅጣቱም ዓይነት ሞት ነበረ፤ በሰው ላይ የተላለፈው የሞት ቅጣትም በምድርም፣ በሰማይም ተፈጻሚ ሆነ፤ ይህም ማለት ሰው በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ኑሮው ከእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ከሆነው ሁሉ ተለየ ማለት ነው፤ ይህ ቅጣት ለሰው ልጅ እጅግ የመረረ ቅጣት ነበረ።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
ክቡራን የበዓሉ ተሳታፊዎች!

እግዚአብሔር በዳኝነቱ ፈራጅና ቀጪ እንደ ሆነ ሁሉ፣ በኣባትነቱ ደግሞ መሓሪና ይቅር ባይ ነው፤ በመሆኑም በኃጢኣት ደክሞ የወደቀውን የሰው ልጅ በቤዛዊ ሞቱ ከሞተ ኃጢኣት የሚያድነው መሆኑን የሚያመለክት ተስፋ ሰጠው።
ተስፋውን በነቢያቱ ኣማካኝነት ሲገልጽለት ከቈየ በኋላ፣ ሰውነታችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም ተገለጸ፤ በዚህ ዓለም ሰው የሚድንበትን መንገድ በቅዱስ ወንጌል ካስተማረና በተግባር ካሳየ በኋላ፣ ቤዛ ሰብእ የሆነው ሞቱን በመስቀል ላይ በመቀበል ቅጣታችንን እንዲነሣ ኣደረገልን፡፡  ቅዱስ መጽሓፍ ይህንን ሲገልጽ፦ “ሁሉም በኣዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ይድናሉ” ይላል። በስሕተት፣ በበደልና በኃጢኣት የደከመው የሰው ልጅ በክርስቶስ ቤዛዊ ሞት ምክንያት ነጻነትን ኣግኝቶ ወደ ቀደመ ክብሩና ርስቱ ተመለሰ፤ ቤተ ክርስቲያን “የደከሙትን በመስቀሉ ይታደጋል” በማለት የምታስተምረን ይህንን እውነት ለመግለጽ ነው፡፡ ለዚህም ዋና ማስረጃዋ ጌታችን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ “ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት በቀኙ በኩል ለተሰቀለው በደለኛ የገባውና የፈጸመው ቃል ኪዳን ነው፤ ይህም ቃል ኪዳን ለኣማንያን ሁሉ የተገባ ቃል ኪዳን መሆኑ እሙን ነው።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች!

ምንም እንኳ በመስቀል ላይ በተፈጸመው የጌታችን ቤዛዊ ሞት ምክንያት ነባሩ ቅጣታችን ወይም ጥንተ ኣብሶ ቢነሣም በገቢር ኣበሳችን ምክንያት ዛሬም ከስሕተት መጽዳት ኣልቻልንም፡፡ በመሆኑም ዛሬም ከእውነት ጋር መጋጨታችን ስለ ቀጠለ በየጊዜው በምንፈጽመው የገቢር ኣበሳ እግዚአብሔርን ማስቈጣታችን ኣልቀረም።  የድኅነታችን ምልክትና ምስክር የሆነው ዕፀ መስቀል በሰዎች እንዲቀበር መደረጉም፣ የገቢር ኣበሳችን መቀጠሉን የሚያመለክት ምስክር ነው፡፡
ሆኖም መስቀልን መደበቅም ሆነ መሰወር ከሰው ዓቅም በላይ ነበረና በእግዚአብሔር ኃይል በጢሰ ዕጣን ኣመልካችነት ከተቀበረበት ጕድጓድ ሊወጣ ችሎኣል፡፡ እነሆም መስቀሉ እስከ ዛሬ ድረስ የእውነት መስካሪና የድኅነት ምልክት ሆኖ ቀጥሎኣል፤ ለወደፊትም በዚህ ይቀጥላል።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት
ክቡራን የበዓሉ ተሳታፊዎች!

የመስቀሉ ዓበይት መልእክቶች ሰው ሊያምንባቸው፣ ሊቀበላቸውና ሊኖርባቸው፣ በውጤቱም በሥጋውም ሆነ በነፍሱ ሊድንባቸው እንደ ተሰጡ የማንስተው ሓቅ ነው፡፡  ሆኖም ሰዎች በኣንድ ጆሮኣችን ሰምተን በሌላኛው ጆሮኣችን ከመጣል ባለፈ፣ ያመጣነው ለውጥ እንደሌለ ተግባራችን ራሱ ምስክር ነው። ዛሬም ሕገ እግዚአብሔር በድፍረት ይጣሳል፤ የጥሰቱ ውጤትም እንደምናየው ዓለማችንን በኣጠቃላይ በመኖርና ባለመኖር ስጋት ውስጥ እየከተታት ይገኛል፡፡
ታድያ እኛስ በዚህ ሁሉ ኣልደከምንምን? የሚታደገን መስቀላዊ ኃይልስ ኣያስፈልገንምን? ለሰላማችን መጠበቅና ለድኅነታችን ዋስትናስ ከመስቀሉ ቃልና ኃይል የበለጠ ሌላ ኣለን? እንደ እውነቱ ከሆነ በንጹሁ ኣእምሮኣችን በደምብ ካስተዋልነው፣ ከመስቀሉ ቃል የበለጠ ለሰው ልጆች ሰላምንና ድኅንነትን የሚሰጥ ሌላ ኃይል በዓለማችን ውስጥ ኣይገኝም። ስለሆነም ፍጹምና ዘላቂ ሰላምን የምንሻ ከሆነ፣ በመስቀሉ ቃል እንመራ፤ የመስቀሉ ቃል ማለት ይቅርታንና ዕርቅን፣ እኩልነትንና ኣንድነትን፣ ፍትሕንና ርትዕን ማረጋገጥ ማለት እንደሆነም በውል እንወቅ፤ በዚህ ሕይወት መኖር ከጀመርን ድክመታችን በመስቀሉ ተወገደ ማለት ነው።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት!
ክቡራን የበዓሉ ተሳታፊዎች!

የዘንድሮ በዓለ መስቀል ኣከባበር ልዩ የሚያደርገው፣ እግዚአብሔር የሰጠንን የውሀ ጸጋችን ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም በኣንድነት ተባብረን ባካሄድነው ጥረት፣ የሕዳሴ ግድባችንን ኣጠናቀን ባስመረቅንበት ማግሥት እየተከበረ ያለ መሆኑ ነው፡፡  ይህ ክሥተት ለሃገራችን ዳግም ልደትን ያበሰረ ስኬት ነው ብንል ማጋነን ኣይሆንም፤ በዚህም እግዚአብሔር ኣምላካችንን ማመስገን ይገባናል፤ በስራው ላይ ታሪካዊ ኣሻራቸውን ያሳረፉትንም ሁሉ መመስገን ይገባቸዋል እናመሰግናቸዋለንም። በቀጣይም ሃገራችን ልትሰራቸው በዕቅድ የያዘቻቸውን ታላላቅ የልማት ስራዎች፣ በፍጥነትና በጥራት ተሰርተው ለሕዝባችን ጥቅም እንዲውሉ ሁላችንም መረባረብ ይኖርብናል፤ ታላላቅና ዘመን ተሻጋሪ እንዲሁም ችግር ኣስወጋጅ የሆኑ ስራዎች እውን ሊሆኑ የሚችሉ፣ ሕዝቡ በኣንድነትና በኅብረት ተነሥቶ ወደ ትግበራ ሲገባ እንደሆነ ከታላቁ የሕዳሴ ግድባችን ተምረናል፤ በመሆኑም በሕዳሴ ግድባችን ያሳየነውን ትብብርና ተነሣሽነት፣ ኣሁንም ኣጠናክረን መቀጠል ይገባናል፤ መንግሥትም ከዚህም ከዚያም የሚታዩትን ኣለመግባባቶች በዕርቅና በይቅርታ በማለፍ፣ እኩልነትን፣ ፍትሕንና ርትዕን በማረጋገጥ፣ እንደዚሁም ለሰላም መስፈን ረጅም ጉዞ በመሄድ ሕዝቡን ወደ ኣንድነት የማምጣት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በዚህ ኣጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም

የመስቀሉ መልእክት የሰው ልጆችን ሁሉ በሰላም፣ በሕይወት፣ በእኩልነትና በኣንድነት ማኖር መሆኑን ከልብ ተገንዝበን፣ በያዝነው ኣዲስ ዓመት እርስ በርሳችን ከመጠፋፋት ይልቅ በጋራ ሰርተን በጋራ የምንለማበትን ምርጫችን እናድርግ በማለት በእግዚአብሔር ስም ኣባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን። በዓለ መስቀሉን የሰላም በዓል ያድርግልን፤ ለሃገራንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን ይስጥልን!

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓም
ኣዲስ ኣበባ ኢትዮጵያ።

መስከረም 1 ቀን 2018 ዓ.ም ርዕሰ ዐውደ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል መግባትን አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

ብፁዕ_ወቅዱስ_አቡነ_ማትያስ_ቀዳማዊ_ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ #የ2018 ዓ,ም #የዘመን_መለወጫ_በዓልን መግባት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል ፣ የቅዱስነታቸው ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው።

ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ርእሰ ዐውደ ዓመት ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰንመቱ ዓመተ ምሕረት፤
በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ ኣምላክ ኣሜን!

• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
• በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ፣

ኣምላክነቱን ኣውቀን እንድናመልከው ዕድሜንና ዘመናትን የሚሰጠን እግዚብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ስምንት ዓመተ ምህረት የርእሰ ዐውደ ዓመት በዓል ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!

‹‹ወገብረ ኵሎ ኅቡረ ወኵሎ ኣሕዛበ እምአሐዱ ዕጓለ እመሕያው ከመ ይንበሩ ዲበ ኵሉ ገጸ ምድር፤ ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኃሥዎ ለእግዚአብሔር፤ እመ ይረክብዎ፤ ወያደምዕዎ፤ ወኢኮነ ርሑቀ እምኵልነ፡- ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከኣንድ ፈጠረ፤ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ደረጃ መደባላቸው፤ ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም›› (የሐ. ሥራ. ፲፯÷፳፮)።

ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ትዕይንተ ዓለምንና በውስጡ የሚገኙ ፍጥረታትን የፈጠረ ኣምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት የሚታዩና የማይታዩ ተብለው በጥቅል በቅዱስ መጽሓፍ ተገልጸዋል፤ የሰው ልጅ ከፍጥረታት መካከል ሆኖ ከኣንድ ወገን የተገኘ እንደሆነ በዚህ ጥቅስ ተጽፎኣል፤  የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ክብርና ደረጃ እንዳለው በቅዱስ መጽሓፍ በተደጋጋሚ ተገልጾኣል፤ ልዩ የሚያደርገውም ከኣፈጣጠሩ ጀምሮ ነው።

ሰው ልዩ ፍጡር መሆኑን ከሚገለጽባቸው መካከል እግዚአብሔር በሦስትነቱ “ሰውን በኣርኣያችንና በኣምሳላችን እንፍጠር” በሚል ልዩ ኣገላለጽ መፈጠሩ፣ ኣፈጣጠሩም በእግዚአሔር መልክና ኣምሳል መሆኑ፣ በእግዚአብሔር እፍታ ሕያው ነፍስ እንዲኖረው መደረጉ፣ በሥልጣንም የፍጥረታት ሁሉ የበላይ ሆኖ መሾሙ ከሌሎች ፍጥረታት ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ኣንጻር ሰው በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ነው፤ የሁሉም ገዥ ነው፤ በተለይም በዚህ ዓለም ከሰው በላይ ሆኖ የፍጡራን ገዥ የሆነ ፍጡር እንደሌለ ሁላችንም የምናየውና የምናውቀው ነው። በላይኛው ዓለምም ቢሆን መላእክትን ጨምሮ ሰማይና ምድርን ከነግሣንግሡ እየገዛ ያለው ሰው የሆነ ጌታ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ገዥ ነው፤ እሱ ሰብእናችንን በፍጹም ተዋሕዶ የተዋሓደ በመሆኑ ሰብእናችን በተዋሕዶተ ቃል ኣምላክ ሆኖ የፍጥረታት ሁሉ ገዥ ሆኖኣልና ነው።

ቅዱስ መጽሓፍም “ወተኰነኑ ሎቱ መላእክት ወሥልጣናት ወኵሉ ኃይል፡- መላእክት፣ ሥልጠናትና ኃይል ሁሉ ተገዙለት” በማለት ይህንን ያረጋግጣል፤ ይህ እግዚአብሔር ለኛ ለሰዎች ያጐናጸፈን ግሩምና ኣስደናቂ ጸጋ ነው፤ ለዚህም ነው “ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፡- ሰው ከፍጥረት ሁሉ ይከብራል” ተብሎ የሚዘመረው።

 የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት!

እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሆነን እንድንኖር በእግዚአብሔር ስንፈጠር በሕይወት እንድንኖር ነው፤ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ሰውን ከኣንድ ፈጠረ የሚለው መጽሓፍ ቅዱሳዊ ኣስተምህሮም ይህንን ያመለክታል። ሰዎች በምድር ላይ በሕይወት እንዲኖሩ የተፈጠሩ ሆነው እያለ በሕይወት እንዳይኖሩ ማድረግ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር መጋጨትን ያስከትላል፤በዘመናችን ዓለማችንን እየፈተነ ያለው ተቀዳሚ ፈተና ሰዎች በሕይወት እንዳይኖሩ የማድረግ ዝንባሌ ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ በዓለም ባይኖር ኖሮ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ድሆች ባሉበት ዓለም ለሰው ልጅ ሕይወት ማጥፊያ የሚሆን መሳሪያ ለማምረት ኁልቈ መሣፍርት የሌለው ገንዘብ ኣይወጣም ነበር።
ይህ ክፉ የዓለም ዝንባሌ እንደ ክፋት ብቻ ሳይሆን እንደ ሞኝነትም የሚያሳይብን ነው፤ማንኛችንም ሰዎች ‹‹ሰው ማጥፋት ይሻላል ወይስ ማዳን›› ተብለን ብንጠየቅ መልሳችን ምን እንደሚሆን ይታወቃል። ነገር ግን ኣንፈጽመውም፣ ሞኝነት የሚያሰኘውም እዚህ ላይ ነው፤ የሚጠቅመንንና የመሰከርንለትን ትተን የሚጐዳንንና፣ ያልመሰከርንለትን እንፈጽማለንና ነው። ስለሆነም በሕይወት እንዲኖር የተፈጠረውን ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን ከመንፈግ መቆጠብ የኣዲሱ ዓመት ትልቁ ኣጀንዳ ኣድርገን ብንወስድ ለሁላችንም ይበጀናልና እንቀበለው እንላለን፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን! ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት!

ሰው በሕይወት እንዲኖር በእግዚአብሔር ሲፈጠር እግዚአብሔርን የሚፈልግበትና የሚያገኝበትን ዕድሜና ዘመንም እንደተሰጠው ከተጠቀሰው ክፍለ ንባብ እንገነዘባለን፤ መቼም እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረ በስራ ለስራ እንደሆነ የምንስተው ኣይሆንም፤ እግዚአብሔር ዕድሜና ዘመን ለሰዎች ሲሰጥ ሊሰራበት ነው፤ ስራውም መንፈሳዊና ዓለማዊ ነው፤ ተደምሮ ሲታይ ደግሞ ለሰው ጥቅም የሚውል ነው፤  እኛ ሰዎች በተሰጠን ዕድሜና ዘመን በመንፈሳዊው ስራችን እግዚአብሔርን ፈልገን እንድናገኝ ተፈጥረናል፤ እሱን ማግኘት የማይቻል የሚመስለን ካለንም እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ኣይደለም ተብለናልና በመንፈስ ከፈለግነው በመንፈስ እንደምናገኘው መጽሓፉ ያስረዳናል፤ስለሆነም በተሰጠን ዘመን ይህንን ስራ መስራት ይኖርብናል፤ በሌላ በኩል ለኑሮኣችን የሚያስፈልገንን ፍጆታ በበቂ ሁኔታ እንድናገኝ ላባችንን ኣንጠፍጥፈን መስራት ይገባናል፤ ይህም ከሰራን ያለጥርጥር የምናገኘው ነው፤ ሁለቱም የጐደሉብን በኛ ኣስተሳሰብ፣ ኣሰራርና ኣጠቃቀም እንጂ እግዚአብሔር ሳይፈቅድልን ቀርቶ ወይም ነፍጎን ኣይደለም፤ እግዚአብሔር የሰጠን ምድር በልዩ ልዩ ሀብተ ጸጋ የተሞላች እንደሆነች፣ የምንረግጠው መሬትም ወደ ሀብት መቀየር እንደሚቻል የተረጋገጠ ነው።

ነገር ግን እኛ በምንራመድበት በእግራችን ሥር ያለውን ሀብት ትተን በሩቅ ያለውን ስንመለከት ሁሉን ያጣን ሆነን በችግር ወድቀን እንገኛለን፤ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን በኣሁኑ ጊዜ እየተፈታተነን ያለው ይኸው የተሳሳተ እሳቤ ነው። ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ኣድርገን በማመን በእኩልነት፣ በኣንድነትና በስምምነት ከመጠቀም ይልቅ ያ የኔ ነው ያም የኔ ነው በሚል ኣባባል ምን ያህል ዋጋ እየተከፈለ እንደሆነ እያየን ነው፤ ይህ ግለኝነት ያየለበት ኣስተሳሰብ ገታ ኣድርገን በእኩልነትና በኣብሮነት የሚያሳድገንን ኣስተሳሰብ በእጅጉ ይጠቅመናል። ይህንንም የኣዲሱን ዓመት ምርጥ እሳቤ ኣድርገን ብንወስድ የተሻለ መግባቢያ ሊሆን ይችላል፤ ኣዲሱ ዓመት በኣዲስ እሳቤ ካላጀብነው ኣዲስ ሊሆን ኣይችልምና ነው።
ስለሆነም ኣዲሱን ዓመት መልካም በሆነ ኣዲስ ኣሳብ ፣እግዚአብሔርንና ሰውን በሚያገናኝ ቅዱስ ተግባር፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በዕርቅና በስምምነት እንድንቀበለው ወቅታዊ ጥሪያችን ነው።

በመጨረሻም፣

ኣዲሱ ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፣ ለሕዝቦች ኣንድነትና ስምምነት እንደዚሁም ኣለመግባባትን በፍትሕና በዕርቅ ለመፍታት ከልብ የምንተጋበት መልካም የስኬት ዘመን እንዲሆንልን እንጸልይ፣ በዚህም መላ ሕዝባችን ጠንክሮ እንዲሰራ ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ ኣባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

እግዚአብሔር ኣምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኣሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
መስከረም 1 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የፆመ ፍልሰታ መግባትን አስመልክተው የተላለፈ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ ኣብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሓዱ ኣምላክ ኣሜን፤

በሀገራችን በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፡-

የክብር ባለቤት እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓ.ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም ኣደረሳችሁ!

‹‹ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፣ ነፍሴ እግዚአብሔርን እጅግ ታከብረዋለች›› (ሉቃ.፩÷፵፮)፤

ይህንን ዐረፍተ ነገር የተናገረችው ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በሰራው ስራ ሰውነታችንን ለመዋሓድ የመረጣት ምርጥ የፍጥረት ወገን ናት፤ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ተፈጥሮኣል፤የእግዚአብሔርም ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያም መመረጥም በእግዚአብሔር ለሰው የተደረገ ምርጫ ነው፤  የሰው መዳን ከጥንቱ ከጠዋቱ በእግዚአብሔር ልዩ ኣሰራር እንደሚከናወን በነቢያት የተገለጸ ነበረ፣‹‹ኣኮ በተንባል ወኣኮ በመልኣክ ኣላ ለሊሁ እግዚእ ይመጽእ ወያድኅነነ፤ በኣማላጅም ኣይደለም፤ በመልኣክም ኣይደለም እሱ ራሱ ጌታ መጥቶ ያድነናል እንጂ›› የሚለው የነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ትንቢትም ይህንን ያስረዳል፤ ቃለ ትንቢቱ ድኅነታችን በጌታ ቤዛነት እንደሚከናወን ያረጋግጣል፤ይህም ሊሆን የቻለው ከፍጡራን ወገን በደሙ ቤዛነት ፍጡራንን የሚያድን ስለሌለ ነው፤  ከዚህ ኣንጻር የሰው መዳን በእግዚአብሔር ኣሰራር በደም ቤዛነት ከሆነ፣ በደሙ ቤዛነትም ዓለምን ማዳን የሚችል ከፍጡር ወገን ከሌለ፣ መዳናችን በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር እጅ ብቻ የተንጠለጠለ ነበረ፤ እግዚአብሔር በደሙ ቤዛ ሆኖ ዓለምን ለማዳን ደግሞ ደም ሊኖረው ይገባ ነበር፤ በመሆኑም እግዚአብሔር በክዋኔው ደም የሌለው ስለሆነ ለቤዛ ዓለም የሚፈስ ደምን ገንዘብ ማድረግ ነበረበት፤ይህንን ደም ለመዋሓድ ቅድስት ድንግል ማርያምን መረጠ፤ ለዚህ ብቁ እንድትሆንም በእስዋ ላይ ስራውን ሰራ፤በምርጫውም መሠረት ከቅድስት ድንግል ማርያም ደማዊ ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ ለቤዛዊ መሥዋዕት መንገዱን ኣመቻቸ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት መሰላል ለመሆን በእግዚአብሔር የተመረጠች በመሆኗ ኣንቀጸ ኣድኅኖ ወይም የድኅነት በር ትባላለች፤ቅድስት ድንግል ማርያም ለዚህ ታላቅ ነገረ ድኅነት መመረጥዋ እጅግ ታላቅ ዕድል መሆኑን ስለተገነዘበች ‹‹ታላላቅ ስራዎችን ሰርቶልኛልና›› በማለት እግዚአብሔርን በመዝሙር ኣመስግናለች ኣክብራለችም፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

የቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና እና የኣምልኮ መዝሙር የኛም መዝሙር ነው፤ እግዚአብሔር ለቅድስት ድንግል ማርያም ታላላቅ ስራዎችን እንደሰራ ለኛም ብዙ ታላላቅ ስራዎችን ሰርቶልናል፤ እየሰራልንም ነው፤ ለሰራልን ኣምላክም እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ ክብርን መስጠት ይገባናል፤ ለእግዚአብሔር የምንሰጠው ክብርም በቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በተግባር የሚታይ ሊሆን ይገባል፤ የድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሕይወት በማስተዋል በትሕትና፣ በትዕግሥት በርኅራኄ በመታዘዝ በንጽህና በቅድስና በክብርና በበረከት የተሞላ እንደሆነ በቅዱስ መጽሓፍ ከተጻፈው ሥነ-ሕይወቷ መረዳት እንችላለን፤  ታድያ በእርሷ ክብርና ተማሕፅኖ የምንተማመን ልጆቿም የእሷን ያህል እንኳ ባንችል ወደእርስዋ የሚጠጋጋ መንፈሳዊ ሕይወት ሊኖረን ይገባል፤ ይህም የምናደርገው ለእግዚአብሔር ክብርና ለእኛ መዳን ሲባል ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን ስናከብር እንከብራለን እንድንማለን፤ ለእግዚአብሔር ክብር የማንሰጥ ከሆነ ግን ውጤቱ መክበር ሳይሆን ሌላ ነው የሚሆነው፤

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!

እኛ በየጊዜው ጾምን እንድንጾም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ፈቃደ ሥጋችንን በመግራት ለእግዚአብሔር ታዛዦች እንድንሆን ነው፤ ጾም የኃጢኣት መግቻ መሳሪያ በመሆኑ ‹‹ልጓመ ኃጢኣት›› ተብሎ ይታወቃል፤ በዚህም ሰውነታችንን ለግብረ ኃጢኣት ከሚያጋግሉ ምግቦች ኣርቀን በሰከነ መንፈስ እግዚአብሔርን እያሰብን ኃጢኣታችንንም እያስታወስን በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብና ለሱ ለመታዘዝ እንጾማለን፤  የጾም ጥቅም ከጥንት ጀምሮ የታወቀ በእግዚአብሔርና በሰውም ተቀባይነት ያለው ነው፤ እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ መታዘዝን ይወዳልና በጾምና በጸሎት ለሱ ልንታዘዝ ይገባል፤ እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ሊያድር የቻለው ‹‹እንዳልኸኝ ይሁንልኝ›› ብላ ታዛዥነትዋን በገለጸች ጊዜ ነው፤ እኛም እንዳልከን ይሁንልን እያልን እንደእስዋ ታዛዥ መሆን አለብን፤ ዛሬ በዓለማችን ያለው መተረማመስ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ያመጣው ጣጣ እንደሆነ ማንም ኣይስተውም፤ መታዘዙ ቢኖር ኖሮ የሰው ልጅ ሰውን የሚያድን ብቻ እንጂ ሰውን የሚገድል መሳሪያ ኣያመርትም ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ወንድምህን እንደራስህ ኣድርገህ ውደድ ኣለ እንጂ ግደል ብሎ ኣላዘዘምና ነው፤ኣሁንም በዚህ ባለንበት ዓለም በጣም ተባብሶ የሚገኘው የመጠፋፋት ዝንባሌ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በሰላምና በሰጥቶ መቀበል ካልተቋጨ ዳፋው ኣስከፊ መሆኑ ኣይቀርም ፤ ከዚህ አንጻር ዛሬም ለሰው ልጆች ሁሉ የምናስተላልፈው መልእክት ‹‹በፍቅር ከሆነ ትንሹም ለሁሉ ይበቃልና ያለውን በጋራ በመጠቀም በፍቅርና በሰላም እንኑር›› የሚል ነው፤ ‹‹ፍትሕና ርትዕም ለሰው ልጅ መነፈግ የበለትም፤ ሰው በምድር ላይ ሰርቶ የመኖር መብቱ ሊከበርለት ይገባል፤ይህንን ማድረግ ማለት ለእግዚአብሔር መታዘዝ ማለት ነው፤ስለሆነም ለእግዚአብሔር ክብርና ለራሳችን መዳን ስንል ለእርሱ በመታዘዝ በሕይወትና በሰላም እንኑር፡፡

በመጨረሻም፡-
በጾመ ማርያም ሱባዔ ስለሀገር ሰላምና ስለሕዝብ ደኅንነት በመጸለይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በመከራ ላይ ወድቀው የሚገኙ ወገኖቻችንን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ በመርዳት ሱባዔውን እንድናሳልፍ ኣባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን እናስተላልፋለን፤  መልካም የሱባዔ ወቅት ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሓት ለእግዚአብሔር ኣሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣
ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም
ዋሽንግተን ዲሲ

ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጰጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን ኣበው ሊቃነ ጳጰሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት!!

እንደዚሁም በዚህ ቀኖናዊና ዓመታዊ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁ በሙሉ፤ ጸጋንና ሓዋርያነትን ያጐናጸፈን ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ትንሣኤውን በሰላም ኣክብረን ይህንን ዓመታዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ለማካሄድ ስለ ሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፤ የጉባኤው ኣባላት የሆናችሁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም እንኳን ለረክበ ካህናት ጉባኤ ኣደረሳችሁ! እንኳንም በሰላም መጣችሁ!

“ረከብነ ጸጋ ወተሰየምነ ሓዋርያተ ከመ ናስምዖሙ ለኣሕዛብ ወይእመኑ በስሙ፡- ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሓዋርያነትን ተቀበልን” (ሮሜ.፩÷፭)፤ይህ ሐዋርያዊ ኣስተምህሮ የኛን ተእልኮና ተልእኮው ያስፈለገበትን ምክንያት ኣጉልቶ ያሳያል፤ የተቀበልነው ስጦታም ምን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ ምንባቡ ያስረዳል፤ ሓዋርያው በዚህ መልእክት የቅዱስ ወንጌል ኣስተምህሮ ዋና ግብ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ማድረግ ነው በማለት ያስተምረናል፤ እውነት ነው ድሮውኑም ቢሆን ለእግዚኣብሔር መታዘዝ ኣቅቶን ነው የወደቅነው፤ ዛሬም የምንነሣው ከእምነት የተነሣ መታዘዝን ገንዘብ ስናደርግ ነው፤ ከሁሉ በፊት እምነት ይቀድማል፤ ከሱ በኋላ ደግሞ ለእምነቱ በሙሉ ልብ መታዘዝ ይከተላል፤ ይህ ሲሆን መዳንና ትንሣኤ ይገኛል፤ ዓለም በእግዚአብሔር እየተደረገላት ያለ ጥሪ ይኸው የመታዘዝ ጥሪ ነው፤  ይህንን መለኮታዊ ጥሪ ለዓለም የማድረስ ኃላፊነትም ለኛ ለቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት የተሰጠ እንደሆነ ሐዋርያው አስገንዝቦኣል፤ ኃላፊነቱ ሲሰጠን ከነመሳርያው ነው፤ እሱም ጸጋና ሓዋርያነት ነው፤ እኛም እሱን ተቀብለናል፤ እንግዲያውስ የተቀበልነውን ጸጋና ሓዋርያነት በዓለም ውስጥ ላለው ሕዝበ እግዚአብሔር ኣገልግሎት ማዋል ከኛ ይጠበቃል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣበላት!!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአሁኑ ጊዜ የሌለበት ክፍለ ዓለም የለም፤ ምክንያቱም የዚህ ሲኖዶስ ወኪሎች ሊቃነ ጳጳሳት በኣፍሪካ፣ በኣውሮፓ፣ በሰሜን ኣሜሪካ፣ በላቲን ኣሜሪካ፣ በካናዳና በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያና በኣውስትራሊያ ወዘተ የሚገኙ ሕዝበ እግዚአብሔር ምእመናንን በማገልገል ላይ ይገኛሉና ነው፤ ይህ ዕድል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መለኮታዊ ተልኮውን በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ለማድረስ ምቹ መደላድል ፈጥሮለታል፡፡ከዚህም በመነሣት በየክፍለ ዓለሙ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃነ ጳጳሳት ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ባሻገር የየአካባቢውን ሕዝብ በማስተማርና በማቀፍ የተጣለባችሁን ሓዋርያዊ ተልእኮ በትጋትና በንቃት መወጣት ይኖርባችኋል፡፡

በማእከል ሆኖ እየመራ የሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚህ ተልእኮ ምቹ መደላድል የመፍጠር ኃላፊነቱን በኣግባቡ መወጣት ይገባዋል፡፡ በተለይም ትምህርተ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የተማሩና በጥልቀት የተገነዘቡ፣ ብስለትም ያላቸው፤ እንዲሁም በቋንቋና በሥነ ልቦና ዕውቀት የላቀ ሀብተ ጸጋ ያላቸውን በሐዋርያነት እያሠለጠነ በአጽናፈ ዓለም ሁሉ ሊያሰማራ ይገባል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣበላት!

በብሂለ አበው (ፀሐይ ለመስኮቷ ሳታበራ…) እንደሚባ