መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል የቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

“ወንስእለክሙ በክርስቶስ ከመ ታሥምርዎ ለእግዚአብሔር፤
ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን” (2ቆሮ. 5፥20)

ይህ አረፍተ ነገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር ዓለሙን በክርስቶስ እንዴት እንደታረቀው ባመሠጠረበት መልእክቱ የዕርቅን አስፈላጊነት አስመልክቶ የተናገረው ነው፤ ሁላችንም እንደምናውቀው እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር መልካም አድርጎ እንደፈጠራቸው ቅዱስ መጽሐፍ ይገልጽልናል፤ ይሁንና እግዚአብሔር ፍጥረታትን ውብ አድርጎ ቢፈጥርም ከፍጥረታት መፈጠር ብዙም ሳይቈይ መጋጨትና አለመግባባት ሊጀመር ችሎአል፤ በመሆኑም የፍጥረታት መጋጨት በሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን በሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ በአራዊቱም ሆነ በእንስሳቱ፣ በአዕዋፉም ሆነ በዓሣው፣ በጥቃቅኑም ሆነ በግዙፋኑ ሲፈጸም ማየት የዕለት ተዕለት ክሥተት ሆኖ ቀጥሎአል፡፡

ይህም ሊሆን የቻለው ቀደም ሲል ሳጥናኤል የተባለው መልአክ ቀጥሎም በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረው አዳም በፈጸሙት ጥፋት ሲረገሙና ሲቀጡ፣ ፍጥረታትም አብረው የመርገሙና የቅጣቱ ተሸካሚ ለመሆን ስለተገደዱ ነው፡፡ ምክንያቱም አምላካችን እግዚአብሔር አዳምን በመርገም በቀጣበት ቀን “ርግምተ ትኩን ምድር በእንቲኣከ፤ ምድር በአንተ ምክንያት የተረገመች ትሁን” ብሎ ምድርን ሲረግማት እንመለከታለንና ነው፡፡ ይህም ማለት አዳም ሲረገም ልጆቹ ሁሉ አብረው ተረግመዋል፣ ምድር ስትረገምም በውስጧ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ አብረው ተረግመዋል ማለት ነው፡፡

ከመርገመ አዳም አንዱ “ሦክ ወአሜከላ ይውጋእከ እሾኽና አሜከላ ይውጋህ” የሚል ይገኝበታል፤ ይህ አገላለፅ ቅኔያዊ አገላለጽ ነውና በቁሙ እሾኽና አሜከላ ሳይሆን ጠቡንና ፍጅቱን ጨምሮ በአጠቃላይ በሰው ልጆች የሚደርሰውን መንፈሳዊና ሥጋዊ መከራን ሁሉ የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ይኸውና ዛሬም ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ፍጥረታት በሙሉ እርስ በእርስ ሲጣሉና ሲተረማመሱ ማየት ቀዋሚ ትዕይንት ሆኖ ይገኛል፤ ይሁንና ምንም እንኳ ችግሩ በፍጥረታት ሁሉ ላይ ሰፍኖ ቢገኝም መፍትሔ የሌለው ችግር ግን አይደለም፡፡

በየጊዜው በተግባር የተፈተነ ጠንካራና የማያወላውል መፍትሔው ይቅርታና ዕርቅ ነው፣ ለሰው ልጅ አለመግባባትን በዕርቅ ዘግቶ ሰላምንና አንድነትን መሥርቶ በመከባበርና በመተሳሰብ በመተዛዘንና በመተጋገዝ በመረዳዳትና በመቻቻል በፍቅርና በሰላም ከመኖር የተሻለ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ይህም እውን ሊሆን የሚችለው ለኔ ለኔ የሚል የራስ ወዳድነትን አስተሳሰብ የሙጥኝ ብሎ በመያዝ ሳይሆን ለወንድሜ ለእኅቴ የሚል ቅን አስተሳሰብ አንግቦ ያም ባይሆን ለሁላችን የሚል የጋራ አስተሳሰብ በሰዎች ልቡና የበላይነት ሲያገኝ ነው፤ ከዚህ አንጻር መስቀላዊ የሆነ ንጻሬ በተላበሰ በዚህ የዕርቅ መንፈሳዊ ኀይል ጠብ ሲሸነፍ ብዙ ጊዜ አይተናል፡፡ በዕርቅ ላይ የተመሠረተ ይህ ዐይነቱ የችግር መፍትሔ በፈጣሪ ሕግም በዓለማዊ ሕግም በሞራላዊ ሕግም ፍጹም ተቀባይነት ያለው እንደሆነ የሚክድ ይኖራል ብለን አንገምትም።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ሰው በጥንተ ፍጥረት ከፈጣሪ የተሰጠው የፈለገውን የመምረጥ ሙሉ ነፃነት ያለው ታላቅ ፍጡር ከመሆኑ የተነሣ በነፃ ምርጫው እንደተሰነካከለ ሁሉ ዛሬም በነፃ ምርጫው የመስተካከል ዕድልን እግዚአብሔር አልነፈገውምና ጠብን በዕርቅ፣ በደልን በይቅርታ፣ ድህነትን በልማት፣ ክሕደትን በሃይማኖት፣ እያረመ መኖር ይችላል፤ ሰው ራሱን በራሱ ካላሰነፈ በስተቀር ይህንን ለማድረግ ዐቅሙም ችሎታውም አለው፡፡

የሰው ልጅ ችግሮችን መፍታት የሚያስችለው ብቸኛ መፍትሔ ይቅርታና ዕርቅ ብቻ እንደሆነ ካለፈውም ካለውም የሰው ልጅ ታሪክ መረዳት አያዳግትም፣ ሰው ይቅርና እግዚአብሔርም ከሰው ጋር የነበረውን ጥልና መለያየት ያስወገደው በዕርቅና በይቅርታ ነው፤ ያውም የተበደለው እሱ ሆኖ ሳለ ለበደለው ፍጡር ሲል ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ሰውን ይቅር ማለቱ የይቅርታ ዋጋ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ተቀባይነትና ተፈላጊነት እንዳለው በጒልሕ አሳይቶአል፡፡ ይህንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ መስቀልን በውል የተረዳ ፍጡር ይቅርታ ተጠይቆ ይቅርና በራሱ ተነሣሽነት ወደ በዳዩ ወገን ፈጥኖ በመሄድም ሆነ ይቅርታን በመስጠት ዕርቅን መፈጸም ተራራ አይሆንበትም፤ ችግሩ የሚከሠት ያለው የነገረ መስቀሉን ምሥጢር በጥልቀት ካለማወቅ የተነሣ ወይም ቢታወቅም በተሸናፊው የእልከኝነት መንፈስ በመሸነፍ ነው፤ ከዚህ አንጻር የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ነን የምንል ሁላችን ዕርቅንና ይቅርታን ቸል የምንል ከሆነ ከምሥጢረ መስቀሉ መራቃችንን፣ ለኀጢአትም መንበርከካችንን ልብ ብለን ልናስተውል ይገባል፡፡ ኀጢአት ደግሞ ጕዳትን እንጂ የሚያመጣልን አንዳችም ጥቅም እንደሌለ መገንዘብ ያሻል፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናችኋለን” ብሎ እነሆ በዛሬው ዕለት ሁላችንንም ይለምነናል፡፡

የሐዋርያው ጭብጥ መልእክት ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” የሚል ነው፤ ይሁንና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንዳንዶቻችን ላንገነዘበው እንችላለን፤ ይህንን በተመለከተ ቅዱስ መጽሐፍ ሲያስተምር ከወንድም ጋር መታረቅ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ማለት ነው ይለናል፡፡ ከዚህ አኳያ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ የምንችለው ከወንድማችን ጋር ስንታረቅና ስንዋደድ እንደሆነ ሐዋርያው አበክሮ ያስተምራል፤ ለዚህም ነው ቅዱስ መጽሐፍ “በአጠገቡ ያለውን ወንድሙን የማይወድ እግዚአብሔርን እወደዋለሁ የሚል ሐሰተኛ ነው፤ በአጠገቡ ያለ የሚያየውን ወንድሙን ሳይወድ የማያየውን እግዚአብሔርን እንዴት ይወደዋል? በማለት የሚያስተምረን፣ ጌታችንም ይቅር ካላችሁ ይቅር ይባልላችኋል፤ ይቅር ካላላችሁ ግን ይቅር አይባልላችሁም ብሎ አስተምሮናል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

እንግዲህ የመስቀልን በዓል በምናከብርበት በዚህ ቀን ከመስቀሉ መገኘት ባሻገር ማስታወስና ማሰብ ያለብን መስቀሉ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የሚለውን ነው፤ ትልቁ ቁም ነገርም እሱ ነው፤ የመስቀሉ ዐቢይ መልእክት በሰው ልጆች መካከል ፍጹም ሰላምና ፍቅር አንድነትና እኩልነት ይቅርታና ዕርቅ ምሕረትና አዘኔታ በምልአት ሰፍኖ፣ የሰው መንፈሳዊ፣ ሞራላዊና አካላዊ ህላዌውና ጤንነቱ ያለምንም እንከን ተጠብቆ እንዲኖር ነው፤ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለዓለም ቤዛ እንዲሆን ሲሰጥ ፈቃዱ ይህ እንዲሆን ነው፡፡

ክርስቲያኖች ብሎም የዓለም ሕዝቦች ይልቁኑም የሃይማኖት መናኻሪያ በሆነችው በቅድስት ሀገር በኢትዮጵያ የምንኖር ክርስቲያኖችና ሃይማኖታውያን በሙሉ ይህንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ የማወቅና የማመን የመቀበልና የመተግበር ሃይማኖታዊ ግዴታ አለብን፤ እግዚአብሔርን እናመልካለን ለሱም እንታዘዛለን ኢትዮጵያንም እንወዳለን ብለን የምንመሰክር ከሆነ የምናከናውነው ተግባር በሙሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድና የመስቀሉን ምሥጢር የጠበቀ ሊሆን ይገባል፡፡

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የምንሻም ከሆነ ባለፉት ዘመናት የሆነውን ነገር ሁሉ እንደገና ከልብ በማጤንና ሰከን ብለን በማስተዋል ወደ እግዚአብሔር መለስ ብለን እሱን ማዳመጥ አለብን፤ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይናገራል፤ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሰማና ግልጽና ግልጽ የሆነ ቋንቋም አለው፤ እሱም ታረቁ፤ ይቅር ይቅር ተባባሉ፤ እናንተ ይቅር ስትሉ እኔም ይቅር እላለሁ፤ እንደዚሁም በረከቱንና ልማቱን አብዝቼ እሰጣለሁ፤ የምድሩን ብቻ ሳይሆን የሰማዩንም አትረፍርፌ እሰጣለሁ የሚል ነው፤ ይህንን የእግዚአብሔር ድምፅ ያልሰማ ሰው በዓለም ይኖራል ብለን አንገምትም፤ ድምፁን ሰምቶ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት የሚኖር ግን ብዙ ሊሆን ይችላል፤ የእኛም የዕለቱ መልእክት ሐዋርያው እንደተናገረው ከእልከኛ አስተሳሰብ እንውጣና የእግዚአብሔርን ድምፅ እንስማ እንቀበል እናክብርም በተግባርም ፈጽመን እናሳይ የሚል ነው፡፡

በመጨረሻም እግዚአብሔር ግጭቱን አስወግዶ ሰላሙን ፍቅሩን፣ አንድነቱንና ስምምነቱን እንዲያመጣልን፤ እኛም የዕርቅና የይቅርታ ሰዎች ሆነን እንገኝ ዘንድ በርትተን እንድንጸልይ አባታዊና መንፈሳዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር መልካም የመስቀል በዓል ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም ርዕሰ ዐውደ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል መግባትን አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵውያት በሙሉ፤

የዓመታትና የአዝማናት ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለአዲሱ ዓመት ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አምስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ።

“ወዓመቲከኒ ለትውልደ ትውልድ
ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው፤”
(መዝ. ፻፩፥፳፬)፡፡

ይህንን ቃለ እግዚአብሔር የተናገረው እግዚአብሔር በቅብእ ቅዱስ አማካኝነት ሀብተ ትንቢት ወመዝሙር ያሳደረበት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው፤ የቃሉ መሠረተ ሐሳብም ዓመታት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆናቸውን፣ እንደዚሁም የተሰጡት ለሰው ልጆች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በእርግጥም ዓመታት ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጡ ሀብቶች ናቸው፤ ዓመታት፣ ወራት፣ ዕለታት፣ ቀናት፣ ሰዓታት የሚያስፈልጉት ለሰው ልጅ እንጂ ለእግዚአብሔርና በመንፈሳዊ ዓለም ለሚገኙ ፍጡራን አይደለም፤ ምክንያቱም ሰው በደካማው ዓለም የሚኖር ደካማ ፍጡር ስለሆነ ለኑሮው ጊዜያት የግድ ያስፈልጉታል፤ በመንፈሳዊ ዓለም የሚገኙ ፍጡራን ግን፣ ድካም የሌለባቸው ትጉሃን ስለሆኑ፣ ዓመትም ቀንም ሰዓትም ወዘተ አያስፈልጋቸውም፤ የሰዓት መለኪያ ብርሃንም የላቸውም፤ ምክንያቱም ያሉበት ዓለም ሁሌም ብርሃን እንጂ ጨለማ ስለማይፈራረቀው፣ እንደዚሁም ተለዋዋጭ አየርም ሆነ ዕድሜ ስለሌላቸው ማለት ነው፤ ለሰው ግን የጊዜ መለኪያ የሚሆኑ ብርሃናትና አዝማናት ወዘተ የተመደቡለት ስለሆነ፣ በእነርሱ እየተመራ ጊዜያትን ይለካል፤ ዓመታትን ወራትንና ቀናትን ወዘተ ይቈጥራል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

ዓመታት ከእግዚአብሔር ለእኛ የተሰጡን ያለምክንያት አይደለም፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ሁሉ ክብርም ጥቅምም አለውና ልናከብረውና ልንጠቀምበት እንጂ፤ ሁላችንም እንደምንገነዘበው ጊዜ ትልቁና ቀዳሚው የሥራ መሣሪያ ነው፡፡ እህልን ዘርተን የዓመት ምግባችንን የምናገኘው ወርኀ ክረምት ስለተሰጠን ነው፤ ይህ ወቅት ባይኖር ኖሮ የእርሻ ሥራ ሠርተን ራሳችንን መመገብ እንደማንችል የምንስተው አይሆንም፡፡ ከዚህ አንጻር ዓመታትንና ወቅቶችን እንደ አመቺነታቸው እየተጠቀምን ልንሠራባቸው እግዚአብሔር አመቻችቶ ሰጥቶናል ማለት ነው፤ ስለዚህ በብሂለ አበው “ጊዜ ሳለ ሩጥ ….” እንደሚባለው ሁሉንም በጊዜው ጊዜ መሥራትና ተጠቃሚ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ሰውም ሆነ ጊዜ ለሥራ የተፈጠሩበት ምክንያት መክበርም መዳንም ማግኘትም ማደግም መልማትም በሥራና በሥራ ብቻ የሚገኝ ከመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ “ብላዕ በሐፈ ገጽከ፤ በፊትህ ላብ እንጀራህን ብላ” የሚለው አምላካዊ ትእዛዝም ይህንን ይገልጻል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

እግዚአብሔር አምላክ ያለመታከት ሠርተን ራሳችንን በራሳችን የምናስተዳድርባት በሀብትና በጊዜ የተዋበች ምድር አስረክቦናል፤ ምድሪቱንም ለእኛ በሚመች አኳኋን አበጅተን እንድንጠቀምባት የሚያስችል አእምሮና ጒልበትም ከጤና ጋር ሰጥቶናል፤ ሐቁ ይህ ከሆነ ታድያ ለምንድን ነው በምድራችን ሥጋትና ጭንቀት፤ ረኃብና ዕርዛት፣ የሀብት እጥረትና የእርስ በርስ ግጭት በስፋት የሚታየው የሚለውን ጥያቄ ሰው ሁሉ በጥልቀት ሊያጤነው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን ምድር አሁንም ለፍጡራን የሚበቃ የተትረፈረፈ ሀብት ያለጥርጥር አላት፣ የአጠቃቀም ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሀብት የሌለው የምድር አካባቢ ፈጽሞ የለም፡፡ ይህም ከሆነ ሁሉም ወደሥራና ሥራ ብቻ ተሰማርቶ ጥረቱን ከቀጠለ የሚያጣው ነገር የለም ማለት ነው፣ ሰው ጤና ዕውቀትና ሰላም ካለው ሀብታም ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ከተሟሉለት ሌላው ሁሉ እግዚአብሔር ከሰጠው ምድር ሠርቶ የሚያገኘው ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ግን ነገሩ ሁሉ ጨለማ ይሆንበታል፤ አካላዊና አእምሮአዊ ጤናውም ይደፈርስና ሳያጣ ያጣ ወደ መሆን ይቀየራል፡፡ ዛሬ በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን እየተከሠተ ያለው ሐቅ ይኸው ነው፡፡

ይህ የሰላም ዕጦት በሀገራችን በኢትዮጵያ በርከት ላሉ ዓመታት እየተደጋገመ በመከሠቱ፣ በዚህ ጠንቅ ሕዝባችን ሳያጣ ያጣ ሆኖአል፤ ኢትዮጵያን በመሰለች ለምና ምድራዊት ገነት ተቀምጠን፣ በዓለም ውስጥ የድህነት ተምሳሌት ሆነን መገኘታችን፣ የሁላችንም ኅሊና ሊኰረኲረው ይገባል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን ሁሉ በአጽንዖት የምንመክረው ዐቢይ ምክር በግጭት ችግሮቻችንን መፍታት በፍጹም አንችልም፤ በመራራቅም ማደግ አንችልም፤ በተለያየን ቊጥር ድህነታችንን ከማስቀጠልና ደካሞች ከመሆን በቀር የምናገኘው አንዳች ፋይዳ የለም፤ እውነቱ ይህ ከሆነ ከገባንበት ያላስፈላጊ ግጭት በፍጥነት ወጥተን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ወደሚያስችል ወደ ምክክርና ውይይት እንግባ፤ አዲሱ ዓመት እውነተኛ አዲስ ዓመት ሊሆን የሚችለው ይህንን ያደረግን እንደሆነ ነው፡፡ አሮጌውን አስተሳሰብ እንዳለ ተሸክመን ለመቀጠል እየዳዳን ከሆነ አዲስ ዓመት ማለቱ የአፍና የጆሮ ቀለብ ከመሆን በቀር የሚሰጠን አንዳች ትርጒም የለም፡፡ ስለሆነም አዲሱን ዓመት አዲስ የሆነ የሰላምና የዕርቅ የስምምነትና የአንድነት የይቅርታና የምሕረት የፍትሕና የእኩልነት መርሕ አንግበን ፍጹም ሰላምን ለማንገሥ በቊርጥ ማሰብና መነሣሣት አለብን፣ ይህንንም ለማሳካት በአንድ አዳራሽ፣ በአንድ ጠረጴዛ ተገናኝተን ችግሮቻችንን በውይይትና በምክክር እንድንፈታ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር የበረከት የእድገት የሃይማኖትና የልማት ዓመት እንዲሆንልን ወደ እግዚአብሔር በመጸለይና በብሩህ ተስፋ እንድንቀበለው መልእክታችንን በድጋሚ በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።