ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የፆመ ፍልሰታ መግባትን አስመልክተው የተላለፈ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ዙሪያ የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፣
እንዲሁም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሰላም አደረሳችሁ።

“ወተዘከረ ሣህሎ ዘይቤሎሙ ለአበዊነ ለአብርሃም ወለዘርዑ እስከ ለዓለም፤ ለአባቶቻችን ለአብርሃምና ለዘሩ የነገራቸውን ይቅርታውን ለዘለዓለሙ አሰበ” (ሉቃ.፩፥፶፭)፣ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነች እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እግዚአብሔርን ባመሰገነችበት ምስጋናዋ፣ ከላይ የተጠቀሰውን ይህንን አረፍተ ነገር መናገሯን በቅዱስ ወንጌል ተጽፎልናል፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምስጋናዋ የገለጸችው ዐቢይ መልእክት የክብር አምላክ እግዚአብሔር የተናገረውን የማያስቀር አምላክ መሆኑን ነው፤ ኤልሻዳይ እግዚአብሔር የተስፋ አምላክ ነውና በየጊዜው ለፍጡራኑ የተስፋ ቃል ይሰጣል፣ ቃል ኪዳንም ይገባል፣ እግዚአብሔር በክዋኔው ዘለዓለማዊ እንደሆነ ሁሉ ቃል ኪዳኑም ዘለዓለማዊ እንደሆነ “ወተዘከረ ኪዳኖ ዘለዓለም፣ ማለትም ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳኑን አሰበ” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ እግዚአብሔር መፍቀሬ ሰብእ ከሆነ አምላካዊ ጠባዩ በመነጨ ፍቅሩ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጀምሮ ለአበው ቃል ኪዳን እንደገባላቸው ተጽፎልናል፣ ይልቁኑም ለአብርሃም “በዘርእከ ይትባረኩ ኲሎሙ አሕዛበ ምድር ማለትም የምድር አሕዛብ ሁላቸው በዘርህ ይባረካሉ” ብሎ ለዓለም ሁሉ የሚሆን በረከትና ድኅነት ከእርሱ እንደሚገኝ ቃል ኪዳን ገብቶለታል፤ ቅድስት ድንግል ማርያም “ለአብርሃምና ለዘሩ የተናገረውን ቃል አሰበ” ብላ የገለጸችውም ይህንን ቃል ኪዳን ነው፤ ምክንያቱም የምድር አሕዛብ ሁሉ የሚባረኩበት ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ በወቅቱ በማሕፀኗ እንዳለ ታውቃለችና ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ከቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና የምንማረው ዐቢይ ትምህርት ሁሌም የእግዚአብሔርን ድንቅ ፍቅር በማስታወስ፣ በመናገርና በመመስከር ማመስገን፣ ማሰብና ማስታወስ እንደሚገባን ነው፡፡ እግዚአብሔርም ይህንን እንደሚወድ “ወተዘከሩ መንክሮ ዘገብረ፤ ያደረገውን ድንቅ ሥራ አስቡ” ብሎ ነግሮናል፡፡

እግዚአብሔር የተናገረውን የማያስቀር ታማኝ አምላክ ነውና ለአብርሃምና ለዘሩ የገባውን ቃል ኪዳን እነሆ ከዛሬ ሁለት ሺሕ ዐሥራ አምስት ዓመታት በፊት ቃል ኪዳኑን እንደተስፋ ቃሉ በተግባር ፈጽሞአል፤የምድር አሕዛብ ሁሉ የሚባረኩበት ወይም የሚድኑበት ዘር እርሱም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብርሃም ዘር ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ የምድር አሕዛብ የሆነውን በሙሉ በደመ መስቀሉ ባርኮ አንጽቶና ቀድሶ አድኖአል፡፡ እግዚአብሔር የምድር አሕዛብ ሁሉ በምሕረትና በይቅርታ እንድንባረክበት የሰጠን ዘር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ሁላችንም መገንዘብና ማመን ይገባናል፣ ይህንን ማወቅ፣ ማስተዋልና ማመን ብፅዕና ማግኘትን ያስከትላል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም “ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ ይሉኛል” ስትል የተናገረችው ቃለ ትንቢት የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ መሆኗን ስለተረዳች ነው፡፡

እኛም እንደ እሷ “አንትሙ ውእቱ ታቦቱ ለመንፈስ ቅዱስ ማለትም እናንተ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ናችሁ” ተብለናል፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ (መለኮት) የሆነችው በሃይማኖት በትሕትና ነው፤ ከዚህ አንጻር እኛም በሃይማኖት ጥላ ሥር ሆነን በትሕትና በፍቅር በአንድነት የምንኖር ከሆነ የእግዚአብሔር ማደሪያ ለመሆናችን ሌላ ምስክር አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም ጌታችን “ተፋቀሩ በበይናቲክሙ ወእምከመ ተፋቀርክሙ በበይናቲክሙ የአምረክሙ ዓለም በዝንቱ ከመ አርዳእየ አንትሙ፤ እርስ በርሳችሁ አብዝታችሁ ተፋቀሩ፤ እርስ በርሳችሁ ከተዋደዳችሁ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ዓለም በዚህ ያውቃል” ብሎ እንዳስተማረን ምስክሮቻችን ፍቅር አንድነትና ትሕትና ይሆናሉና ነው፡፡

የተወደዳችሁ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ከነገው ዕለት ጀምሮ የምንጾመው የጾመ ማርያም ዋና ዐላማ ጠብንና ጥላቻን ማሸነፍ የሚያስችል የይቅርታን የፍቅርንና የአንድነትን ኀይል በመለኮት ፈቃድ ለማጐልበት ነው፤ የተለየ የጾም፣ የጸሎት፣ የንስሓ ጊዜ ወስኖ እግዚአብሔርን መለመንና ከእርሱ ጋር መገናኘት ከጥንት ጀምሮ የሃይማኖት መርሕ ነው፡፡ በዚህ መርሕ ተመርተው ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን ከመከራና ከፈተና የታደጉ ቅዱሳን ብዙ ናቸው፡፡ የልቡናቸውን መልካም ምኞት ያገኙም እንደዚሁ ብዙ ናቸው፡፡

እኛም ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በደነገገችው የቀኖና ድንጋጌ መሠረት የምንጾመው ጾመ ማርያም፣ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን የልቡናቸውን መሻት እንዲፈጽምላቸው የጾሙትና የለመኑትን ያገኙበት ኩነት መነሻ አድርገን እግዚአብሔር እንደነርሱ የልቡናችንን መሻት እንዲፈጽምልን በማመንና ተስፋ በማድረግ ነው፤ ከዚህ አንጻር የቅድስት ድንግል ማርያም ነገረ ትንሣኤ ወፍልሰት በማሰብ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት በብርቱ እንጥራለን፣ እንጾማለን፣ እንጸልያለን፣ በንስሓም ወደ እርሱ እንቀርባለን፣ ቅዱስ ምሥጢረ ቊርባንንም እንቀበላለን፤ በዚህም ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛለን፡፡ ይህ ሲሆን እግዚአብሔር የልባችንን መሻት በብሩህ ገጽ ተቀብሎ ይፈጽምልናል፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ፍጹም ሰላም ያላት ሀገር እንድትኖረው ነው፤ ይህ ትክክለኛ ፍላጎት ነው፡፡ ይሁንና ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉም ነገር ስለማይሆን ፍጹም ሰላም በሀገር ሰፍኖ ሕዝባችን እግዚአብሔር በሰጠው ምድር በፍቅር፣ በአንድነት በነፃነትና በእኩልነት እንዲኖር ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ በዚህ ወቅት የቅድስት ድንግል ማርያምን ጸሎትና ስእለት ተማሕፅኖና አስተበቊዖት አጋዥ አድርገን በልዩ ሱባዔ ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በንስሓ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ ነዳያንን በመርዳትና ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል እሱን መማፀን ይኖርብናል፡፡

በመጨረሻም፤ በሀገራችን የተከሠቱት ያላስፈላጊ ግጭቶችን በድርድር ለመፍታት እየተሞከሩ ያሉ አንዳንድ የሰላምና የውይይት ድምፆች ተስፋ ሰጪ ስለሆኑ ሥር ሰደው፣ በተግባር ተተርጉመው፣ ለተጐዳው ሕዝባችን መጠገኛ ይሆኑ ዘንድ፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ በዚህ ዙርያ በሱባዔው ወቅት ወደ እግዚአብሔር አቤት በማለትና ሂደቱን በመደገፍ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ፣ መንግሥትም ሆነ የዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ በዚህ በጎ ሐሳብ እንዲገፉበትና ሕዝባችንንና ሀገራችንን ከጥፋት እንዲታደጉ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ጾሙን የሰላም የስርየት የፍቅር የአንድነት ጾም ያድርግልን፡፤
ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡