ጥር 11 ቀን 2014 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በማስመልከት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት በተወካያቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል።

ጥር 11 ቀን 2014 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በማስመልከት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት በተወካያቸው በብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የውጭ ጉዳይና የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የበላይ ኀላፊ ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የመንበረ ፓትርያርክ ዋና ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊና የአርሲና ምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሲዳማ፣ የጌድኦ የአማሮና የቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
ክቡራን ሚኒስትሮች፣
የተከበራችሁ የመንግሥት ልዩ ልዩ ባለ ሥልጣናት፣
ክቡራን አምባሳደሮችና ኮር ዲፕሎማቶች፣
ክቡራን የቤተ ክርስቲያናችን የየመምሪያውና የድርጅት ኀላፊዎች፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኀላፊዎች፣የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ወጣት የሰንበት ት/ቤት ልጆቻችን፣
የተወደዳችሁ የፓሊስና የፀጥታ አካላት፣
በአጠቃላይ በዚህ ታላቅ የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል የተገኛችሁ ምእመናንና ምእመናት በሙሉ፤

በንስሓ መንፈስ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በማየ ጥምቀት በማንጻት ከፍዳ ኀጢአት ነፃ የሚያደርግ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ አራት ዓመተ ምሕረት በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ።

“ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት
መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ፤”
(ማቴ. 3÷1)፤

ይህንን ቃለ ቅዱስ ወንጌል፣ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስና ተጠማቂው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትምህርታቸው ርእስ አድርገው ያስተማሩበት ቃለ ብሥራት ነው፡፡ ትምህርቱ የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር ንስሓ እንደሆነ በዋናነት ያመለክታል፡፡ መንግሥተ ሰማያት ማለት በሰማያትም በምድርም በአጠቃላይ በትዕይንተ ዓለማት ሁሉ በምልአት የምትገኝ የእግዚአብሔር ሥልጣን ናት፤ ጌታችንም ሆነ ቅዱስ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚለውን አረፍተ ነገር የትምህርታቸው ዋና ርእስ አድርገው ማስተማራቸው፣ የእግዚአብሔር ሥልጣን በተነሳሕያንንና በኢተነሣሕያን ላይ ለይታ ልትፈርድ መዘጋጀቷን ለማመልከት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን ግልጽ ሲያደርግ “እነሆ ምሣር በዛፎች ላይ ተቀምጦአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራው ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል” ካለ በኋላ “እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” በማለት የንስሓን አስፈላጊነት ያስገነዝባል፡፡ ይህ የንስሓ ጥሪ ለተወሰኑ ሰዎች ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የተላለፈ አምላካዊ ጥሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር በአጠቃላይ በኀጢአት አረም የተዋጠ ሆኖ ስለተገኘ፣ ከዚህ አረም ነፃ ለመሆን በእግዚአብሔር ፊት የመጀመሪያው ተግባር ንስሓ መግባት ስለሆነ ነው፡፡ የትምህርቱ ዋና ዐላማ ሰዎች አምነውና በንስሓ ተራምደው ወደ ጥምቀት ሲደርሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን ልትቀበላቸው ዝግጁ ናት የሚለውን መልእክት በዋናነት ማስተላለፍ ነው፡፡ ጌታችን ሲጠመቅ ሰማይ መከፈቱ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥልጣን በንስሓ ታድሰው ለሚቀርቡና ለሚጠመቁ ምእመናን ያዘጋጀችው ሰማያዊ ርስት ማደልን ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን መብትንም ጭምር ለመስጠት ነው፡፡ “ይህ ልጄ ነው” የሚለው አምላካዊ ድምጽም ይህንን ያመሠጥራል፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣንን ሰጣቸው” ተብሎ ተነግሮናልና፡፡

የተወደዳችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች ምእመናንና ምእመናት፤

የበዓለ ጥምቀት ዐቢይ ጥሪ፣ ሰማያዊ ርስትንና የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን መብትን ለማግኘት በእምነት ገብታችሁ፣ በንስሓ ተራምዳችሁ በጥምቀት ሀብተ ንጽሐን ተጐናጸፉ የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ እኛ ልንወስደው የሚገባን ትልቅ ኀላፊነት እንዴት ንስሓ እንግባ? የሚለውን ነው፡፡ ትምህርቱን በትክክል ተቀብለን ለተግባራዊነቱ በቈራጥነት ከተነሣን፣ ንስሓ መግባት የሚያስፈልገን መሆኑን ለማወቅ የማያወላውል ዘዴ አለን፡፡ እርሱም “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚል ነው፡፡ ይህ ትምህርት ጌታችን ያስተማረው፣ ዓለም በሙሉ “ወርቃማ ሕግ” ብሎ የተቀበለው ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ የኀጢአትና የጽድቅ መመዘኛ የሚሆን ሚዛን የለም፡፡ ይህንን ሚዛን በቀጥታ ወደ ራሳችን አእምሮ አስገብተን ከመዘን፣ በአኛ ላይ ሊደረግብን የማንፈልገውን በሌላ ወንድም ላይ እንዳደረግን፣ አእምሮአችን በዝርዝር ይነግረናል፡፡ በዚህ ጊዜ አእምሮአችን የመሰከረብንን ጥፋት ተቀብለን መጸጸትና ንስሓ መግባት ከአኛ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አንጻር አእምሮውን ጠይቆ ከኀጢአት ንጹሕ ነህ የተባለ እዚህ መካከላችን ይኖር ይሆን? የሚለውን ብንጠይቅ ፍጹም ንጹሕ ሆኖ የሚገኝ ያለ አይመስለንም፡፡ ከተገኘም ቅዱስ መጽሐፍ አይቀበለውም፡፡ ለምን ቢባል? ለአንዲት ሰዓት ስንኳ ከስሕተት የማንነፃ ድኩማን ስለሆንን ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ይህንን በተመለከተ ሲያስተምረን ”አልበደልንም የምንል ከሆነ እግዚአብሔርን ውሸተኛ እናደርገዋለን፡፡ ቃሉም በኛ ውስጥ የለም”ይላል፡፡ እንግዲያውስ ሁላችንም በድለናል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርም፣ አእምሮአችንም በዚህ ተስማምተው አዎን ነው መልሳቸው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንድ ሁላችንም ንስሓ መግባት ግዴታችን ነው።

የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች ምእመናንና ምእመናት!ንስሓ በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በሰው መካከል እውነተኛ ሰላምንና ዘላቂ ፍቅርን የሚገነባ  የሕሊና መሐንዲስ ነው፡፡ ሰላምና ፍቅር ከሰው ልጆች እየራቀ የመጣው በንስሓ የታጀበ እምነት መከተል ባለመቻላችን እንደሆነ ንጹሕ ልቡና ላለው ሁሉ የተደበቀ ምሥጢር አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ በሀገራችን ውስጥ ላለው ወቅታዊ ሁኔታም ፈውሱ በንስሓ የታጀበ፣ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር የሚያስታርቅ ሃይማኖትን ገንዘብ አድርጎ መመላለስ የግድ ሆኖ ይገኛል፡፡ ትክክለኛ ንስሓ በራስ ላይ እንጂ በሌላ ላይ መፍረድን አይፈቅድም፡፡ ሁሉም ራሱን ፈትሾ በራሱ ላይ መፍረድ ከጀመረ፣ ያኔ ያማረ ውጤት ይገኛል፡፡ ወደ ፍጹም ሰላም የሚያደርስ መንገድ ያኔ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በራሳችን ላይ እየፈረድንና በንስሓ እየታደስን ልንኖር የሃይማኖታችን መርሕ እንደሚያስገድድ ተገንዝበን ንስሓ በመግባት ወደ ሰከነ አእምሮአችን ልንመለስ ይገባል።

በመጨረሻም ከበዓለ ጥምቀት አስተምህሮ እንዳስተዋልነው፣ በአበው ብሂልም “መተው ነገሬን ከተተው” እንደሚባለው በንስሓ መንፈስ ቅራኔን፣ ጥላቻን፣ በቀልንንና ቂምን እርግፍ አድርገን በመተው ለሰላም የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ለሀገራችን አንድነትና ለሕዝባችን ደኅንነት የሚበጀውን ሥራ እንድንሠራ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

በዓሉን የደስታ፣ ዘመኑም የሰላም ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።

 

ታኅሣሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም የልደት በዓልን መግባት አስመልክተው ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፤

እኛን ለማዳን ሥጋችንን ተዋሕዶ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው በመሆን በዚህ ዓለም የተወለደው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

“ወውእቱ ቃል ሥጋ ኮነ
ያ ቃል ሥጋ ሆነ፤”
(ዮሐ. 1፥14)

ቅዱስ እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት ኖላዊው፣ ጥንት በሌለው ጥንት የነበረ፣ አሁንም ያለ፣ ወደፊትም ፍጻሜ በሌለው ህላዌ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ከሦስቱ አካላት “ቃል” ተብሎ የተገለጸው አንዱ አካል ማለትም እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ በብሥራተ ገብርኤል፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ መጋቢት ሃያ ዘጠኝ ቀን በአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመተ ዓለም በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን ተፀነሰ፡ ፡“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ቃል እግዚአብሔር ነበረ” ተብሎ ማንነቱ በቅዱስ ወንጌል የተረጋገጠለት “እግዚአብሔር ቃል” በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድሰት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍስዋ ነፍስን ነሥቶ በመዋሐድ እንደኛ ፍጹም ሰው ሆነ፡፡

“እግዚአብሔር ቃል” ሰው ከሆነበት ቅጽበት አንሥቶ መለኮትነቱ ከሰውነቱ፣ ሰውነቱም ከመለኮትነቱ ባለ መለያየት፣ ባለ መጠፋፋት፣ ባለ መለዋወጥ፣ ባለ መከፋፈልና ባለ መቀላቀል አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ፡፡ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ በመሆን የተፈጸመው የአምላካችን ምሥጢረ ተዋሕዶ ለዘለዓለሙ የጸና ነው፡፡ ይህ ምሥጢረ ተዋሕዶ እግዚአብሔር ለሰው ያለው የፍቅር ጥግ ያሳየ አምላካዊ ድርጊት ነው፡፡ ይህ አምላካዊ ፍቅር ሰውነትን ከባርነት ነፃ ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ ሰውነት በተዋሐደው መለኮት ምክንያት በመንበረ ጸባኦት ተቀምጦ የፍጥረት ሁሉ ገዢ እስከ መሆን ያበቃ ስለሆነ፣ ተመሳሳይም ሆነ ተነፃጻሪ ምሳሌ የማይገኝለት፣ ፍቅር ሁሉ የሚበልጥ የእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር ነው” ለዚህም ነው “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” እያለ ቅዱስ መጽሐፍ የሚያስተምረን። የአምላክና የሰው ተዋሕዶ በማሕፀነ ድንግል ማርያም ከተፈጸመበት ጊዜ አንሥቶ መለኮትነቱንና ሰውነቱን በሚገልጹ ስሞች አማኑኤል፣ ኢየሱስ፣ መሲሕ፣ ክርስቶስ፣ መድኀኔ ዓለም እየተባለ ይጠራል፡፡ እነኝህ ስሞች መለኮትነትን ብቻ፣ ወይም ደግሞ ሰውነትን ብቻ የሚያመለክቱ ሳይሆን የመለኮትና የሰውነት ተዋሕዶን በምሥጢር የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም በዛሬው ዕለት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን የተወለደው ሕፃን ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው እንጂ ሰው ብቻም አይደለም፣ አምላክ ብቻም አይደለም። ይህም በመሆኑ ነው በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ” ተብሎ ለእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ለፍጡር የማይቀርብ ክብርና ምስጋና ከሰማይ ሠራዊተ መላእክት የቀረበለት፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የሌለ “እግዚአብሔር ቃል” ሰው ሊሆን የቻለው ሰውን ለማዳን ነው፡፡ ሰውን ለማዳን ሲባል የተፈጸመው ይህ ተዋሕዶ፣ በአምላክ ዘንድ ሰውን ማዳን ምን ያህል ታላቅ ነገር እንደሆነ ማስተዋል ለሰው ልጆች ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ምሥጢር ይልቅ ዓለምን ያዳነበት እንደሚበልጥ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ ይህ የአምላካችን አድራጎት እኛም ሰውን ከማዳን የበለጠ ሥራ ሊኖረን እንደማይገባ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ከጌታችን ልደት ምሥጢራዊ መልእክት እንደምናስተውለው አንድነትን፣ ፍጹም ፍቅርን፣ ምሉእ ሰላምን፣ እግዚአብሔርን በመዝሙር ማመስገንን እና ማምለክን፣ ከተቸገሩት ማኅበረሰብ መካከል ተገኝቶ የሰውን ችግር ተካፋይ መሆንን ከአምላክ የተቸረን ፍጹም በረከት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምሥጢረ ተዋሕዶ፣ ዝማሬ መላእክቱ፣ በከብቶች በረት መወለዱ፣ ለእረኞች መገለጡ፣ በዕለተ ልደቱ ከተገለጡ ዐበይት ክሥተቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዚህም ቤተ ልሔም የእግዚአብሔር ክብር የበራላት፣ የመላእክትና የእረኞች መዝሙር የደመቀላት፣ እግዚአብሔር፣ መላእክትና ሰዎች በአንድነት የተገኙላት የእውነተኛዪቱ መንግሥተ እግዚአብሔር ማሳያ ሁና ተገኝታለች፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

በቤተ ልሔም የታየው አምላካዊ መገለጥ ተኣምረ አምላክ ብቻ ሳይሆን፣ በዕለቱ ከታየው ጣዕመ ሕይወት ትምህርት ወስደን እሱን እንድንለማመድ ብሎም እንድንከተል የሚያስገነዝብ አምላካዊ መልእክት የተላለፈበት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በመካከላችን የተገኘበት ዐቢይ ምሥጢር በአንድነት፣ በሰላምና በፍቅር የተወደደ እንደ ዕለተ ልደት ያለ ጣዕመ ሕይወት እንዲኖረን ብሎ እንደሆነ ልናውቅ ይገባል፡፡ ይኸውም እሱ እንደ ተዋሐደን እኛም እርስ በርሳችን ተዋሕደንና አንድ ሆነን በፍቅርና በሰላም እንድንኖር ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ በዚህ ከእርሱ ጋር እንዋሃዳለን፤ ለወደፊቱም እግዚአብሔር ሁሉን አዋሕዶ በሚመጣው ዓለመ መንግሥቱ እውን የሚያደርገው ጣዕመ ሕይወት ይኸው እንደሆነ መገንዘብ አለብን፣ መላእክት በቤተ ልሔም ለተወለደው ሕፃን ምስጋናና አምልኮ እንዳቀረቡ እኛም ለምስጋናና ለአምልኮ ተጠርተናል። እሱ ዓለመ ፍጥረትን በእጁ ጨብጦ የያዘ አምላክ ሲሆን፣ በከብቶች በረት ከእረኞች ጋር ውሎውና አዳሩ እንዳደረገ፣ እኛም ሁሌም ውሎአችንና አዳራችን ከምስኪኑ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር በማድረግ የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስ፣ የታመመውንና የታሠረውን በመጠየቅ የጣፈጠ ጣዕመ ሕይወትን መምራት ይኖርብናል፡፡ ዛሬ ሀገራችን በመከራ እየተፈተነች ያለችበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ የተፈናቀሉ፣ የተጐዱና ኑሮ የተመሰቃቀለባቸው ወገኖች በየአካባቢው በብዛት መኖራቸው ይታወቃል፣ በቤተ ልሔም የተወለደው ሕፃን ክርስቶስም ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆኖ በመካከላቸው እንደሚገኝ እሱ ራሱ ነግሮናል፣ ታድያ እኛም እዚያው ተገኝተን እንድናስተናግደው የወቅቱ ዐቢይ ጥሪያችንና መልእክታችን ነው፡፡

በመጨረሻም፤ በቤተ ልሔም ዙሪያ የጐረፈው የእግዚአብሔር ክብርና ብርሃን፣ ሰላምና ዕርቅ፣ ተዋሕዶና ምስጋና በሀገራችንም ሰፍኖ ወደ ፍጹም ሰላምና አንድነት እንደርስ ዘንድ፣ እግዚአብሔርን በጸሎት ከመለመን ጋር ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሰላም ለፍቅርና ለአንድነት ያላሰለሰ ጥረት እናደርግ ዘንድ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን