ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም.የጥምቀት በዓልን በማስመልከት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ያስተለለፉት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
ክቡራን አምባሳደሮችና ኮር ዲፕሎማቶች፤
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤
ወጣት የሰንበት ት/ቤት ልጆቻችን፤
በአጠቃላይ በቅርብም በሩቅም ሆናችሁ በዓሉን በማክበር የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፤

ከአባታዊ ፍቅሩ የተነሣ በጥምቀተ ማይ ለዳግም ልደት ያበቃን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሰን አደረሳችሁ።
“ዘኢይትዐወቅ ተከሥተ፤ ወዘኢይትረአይ ተርእየ፣
የማይታወቅ ተገለጠ፤ የማይታይም ታየ፤”
(ቅዱስ ኤፍሬም በሮብ ውዳሴ ማርያም)

ፈጣሬ ፍጥረታት፣ አምጻኤ ዓለማት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን በትዕይንተ ዓለማት ሁሉ በውስጥም በአፍኣም ያለ፣ ምሉእ፣ ረቂቅና ስፉሕ አምላክ ነው፡፡ አምላካችን በሁሉም ዘንድ በምልአትና በስፋት ይኑር እንጂ ከረቂቅነቱ የተነሣ በክዋኔ መለኮቱ ያየው አንድ ስንኳ የለም፣ የተለያዩ ቅዱሳን ሰዎች እንዳዩት ቢጽፉም እነርሱ በሚችሉት ዐይነት በዘፈቀደ ስለተገለጸላቸው ጻፉ እንጂ በክዋኔ መለኮቱ አይተውት አልነበረም፣ ይህም ይታወቅ ዘንድ “ለእግዚአብሔርሰ አልቦ ዘርእዮ ግሙራ አላ ወልድ ዋሕድ ዘሀሎ ውስተ ሕፅነ አቡሁ ውእቱ ነገረነ፣ እግዚአብሐርንስ አንድ ስንኳ ያየው የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ ነገረን እንጂ” ተብሎ በቅዱስ ወንጌል ተጽፎአል፡፡

እግዚአብሔር በህላዌ መለኮቱ የታየበት ጊዜ ባይኖርም ሥነ ፍጥረቱን በማየት፣ በኀልዮ፣ በአእምሮ፣ በአስተንትኖ እና በአውጠንጥኖ እንደዚሁም በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ነገረ ህላዌው በግልጽ ይታወቃል፣ በዚህ ዐይነት ህላዌ የሚኖር እግዚአብሔር፣ ትዝምደ ሰብእን ለማዳን ሲል በፈጸመው ምሥጢረ ሥጋዌ በዚህ ዓለም በመገለጹ የማይታወቀው ተገለጸ፣ የማይታየውም ታየ ተብሎ ተነገረለት፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት።

እግዚአብሔር ቃል የሚታይ ሥጋን ለብሶ በዚህ ዓለም መታየት የጀመረው በቤተ ልሔም ከተወለደበት ቀን አንሥቶ ቢሆንም ባደገበት ከተማ በናዝሬት አብረውት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ተራ ሰው እንደሆነ አድርገው ያስቡት ስለነበረ አምላክነቱን አልተረዱም ነበር፣ እሱ ራሱም ቢሆን የማስተማርና መሥዋዕት ሆኖ ዓለምን የማዳን ሥራውን እስኪጀምር ድረስ እንደተራ ሰው በመካከላቸው ኖረ እንጂ አምላክነቱን አልገለጸም ወይም አልተናገረም ነበር፡፡
ነገር ግን በፈለገ ዮርዳኖስ፣ በእደ ዮሐንስ፣ ሲጠመቅ ማንነቱ ማለትም ወልደ እግዚአብሔርነቱ በግልጽ ታወቀ፤ የጌታችን ወልደ እግዚአብሔርነትና እግዚአብሔርነት በዕለተ ጥምቀት የተገለጸውና የታወቀው በሦስት ምስክሮች ነው፣ ይኸውም አንደኛው እግዚአብሔር አብ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር፣ ይህ የምወደው ልጄ ነው” ብሎ በመመስከሩ፣ሁለተኛው መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስን ዋቢ አድርጎ “ለልየ ርኢኩ ወአነ ሰማዕቱ ከመ ወልደ እግዚአብሔር ውእቱ፣ እሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እኔ ራሴ አይቻለሁ፣ ምስክሩም እኔ ነኝ” ብሎ በመመስከሩ፣ ሦስተኛው መንፈስ ቅዱስ ራሱ በርግብ አምሳል ወርዶ በላዩ ላይ በመቀመጡ ተራ ሰው ሳይሆን ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ ታውቆአል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ማለት ደግሞ እግዚአብሔር ማለት ስለሆነ በክዋኔ መለኮቱ የማይታየው እግዚአብሔር በለበሰው የሰው ሥጋ መታየት በመቻሉ የማይታወቀው ተገለጸ፣ የማይታየውም ታየ፣ ጥንትነት ያልነበረው ሰብእነት ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቈጠርለት እግዚአብሔርም ሠላሣ ዓመት ሆነው ተብሎ ዘመን ተቈጠረለት በማለት መክብበ ሊቃውንት ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ወንጌልን ዋቢ በማድረግ አመሥጥሮ ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያዊው ርእሰ ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድም “እንዘ ሥዉር እምኔነ ይእዜሰ ክሡተ ኮነ፤ ከኛ ሥዉር ሆኖ ይኖር የነበረው ዛሬ ተገለጠ” በማለት ዘምሮ ያዘምረናል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

የእግዚአብሔርን በሥጋ ሰብእ መገለጥ ለፍጥረተ ሰብእ ለማወጅ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከጥር ዐሥር ቀን ጀምሮ እስከ ቅበላ መርዓዊ ያለውን ወቅት “ዘመነ አስተርእዮ ማለትም የመገለጥ ወቅት” በማለት ሰይማዋለች፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያንም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ባለቤቶች ነንና በትምህርተ ቤተ ክርስቲያን ጸንተን በዚህ ጊዜና ወቅት እግዚአብሔር ተገለጠ፣ እግዚአብሔር ታየ፣ በመካከላችንም ተመላለሰ፣ በልብሰተ ሥጋ እኛን ተዋሐደን፤ ተዛመደን እያልን ስለፍቅሩ፣ ስለመድኅንነቱ፣ ስለ አምላክነቱ ክብርም እንዘምርለታለን፣ እንሰግድለታለን፣ እናመልከዋለን፣ ለክብሩም አዲስ የምስጋና ቅኔ እንቀኝለታለን፡፡ በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ እግዚአብሔር በሥጋ ሰብእ የተገለጸበት ብቻም አይደለም፣ የመንግሥተ እግዚአብሔር መግቢያ በርም ከውኃና ከመንፈስ መወለድ እንደሆነ፣ ድኅነታችንም በእንስሳት መሥዋዕት ሳይሆን “ የእግዚአብሔር በግ” ተብሎ በተነገረለት በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንደሆነ በዚህ ዕለት ተከፍቶ ከታየው ሰማያዊ መንግሥቱ ውስጥ በተላላፈው አምላካዊ መልእክት መረዳት ችለናል፡፡ ለእኛ ለሰዎች የተዘጋጀልን ክብርም በጸጋ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ደረጃ እንደሆነ ተገንዝበናል፣ እንግዲህ በዓለ ጥምቀት ይህንን ሁሉ ምሥጢረ አምላክ ወሰብእ የተገለጸበት እንደመሆኑ መጠን ለሰው ልጅ በአጠቃላይ በተለይም ለክርስቲያኖች ያለው ትርጒም እጅግ በጣም ከፍ ያለ በመሆኑ በታላቅ ድምቀት ማክበራችን ተገቢ ነው፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

በዓለ ጥምቀት በክርስቲያኑ ዓለም እንደየባህሉና እንደየሥርዐቱ በድምቀት የሚከበር ቢሆንም በሀገራችን በኢትዮጵያ ያለው የአከባበር ሥነ ሥርዐት ግን ከሁሉም ልዩ ሆኖ እንደሚታይ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በዓለ ጥምቀታችን ባለፈው ዓመት በዩኒስኮ ለመመዝገብ እንደበቃ ይታወሳል፡፡ የቀደሙት አበው ይህንን በዓል ሲያከብሩ ከሃይማኖቱ ባሻገር የማኅበራዊ ትሥሥሩን በሚያጠናክር ሁኔታ መቀራረብን፣ መታረቅን፣ ይቅር ይቅር መባባልን፣ አብሮ መዘመርን፣ በጋራ ማመስገንን፣ አብሮ መብላትን፣ አብሮ መጠጣትን፣ በፍቅር መተያየትን፣ በአጠቃላይ አብሮነትንና አንድነትን በሚያጐላ አግባብ ስለገነቡት በዓሉ እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በዓሉ ሁሉንም አሳታፊ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ባህሎችና የምስጋና ዘይቤዎች በልዩ ልዩ ቋንቋ ሲቀርቡ ከደስታ፣ ከአድናቆት፣ ከፍቅር፣ ከሰላምና ከመከባበር ያለፈ ሌላ እንከን የማይታይበት አስደናቂ በዓል በመሆኑ የሀገራችን በዓለ ጥምቀት አከባበር ልዩ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከሃይማኖት የመነጨው ይህ ማኅበራዊ ዕሴት ኢትዮጵያውያን ሁላችን በሚገባ ልንንከባከበውና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በዓለ ጥምቀት ለአብሮነታችንና ለአንድነታችን ሥርና መሠረት ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባል፡፡ በዘመናችን ጢስ አልባ ኢንዱስትሪ እየተባለ በሚነገርለት የቱሪስት ክፍለ ኢኮኖሚም የራሱ የሆነ ሚና እንዲጫወት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከመንግሥትም፣ ከቤተ ክርስቲያንም፣ ከሕዝቡም የተቀናጀ የጋራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ሁላችንም እንደምንገነዘበው አሁን ያለንበት የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት በዓለማችን በተከሠተው የኮረና ቫይረስ ምክንያት ቦታው ለሌላ ሥራ አገልግሎት እየሰጠ ስለቈየ ሕዝበ ክርስቲያኑን አሳስቦት ነበረ፡፡ ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጽ/ቤት ለሃይማኖቱና ለሕዝበ ክርስቲያኑ የላቀ አክብሮት በመስጠት በቦታው ይካሄድ የነበረው አገልግሎት ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጠው ከማድረጉም በላይ ቦታውን አጽድቶና አስተካክሎ በዓሉ በተለመደው አኳኋን እንዲከበር በማድረጉ በራሳችንና በሕዝበ ክርስቲያኑ ስም ሳናመሰግን አናልፍም፡፡ እንደዚሁም ቦታውን በማስከበርና በማጽዳት የላቀ ሚና የነበራቸው ወጣት ልጆቻችንንም እግዚአብሔር ይባርካችሁ ብለን እንባርካቸዋለን፣ እንመርቃቸዋለን፡፡
ከዚህም ጋር ለበርካታ ዓመታት የሕዝባችን የጤና ጠንቅ ሆኖ የቈየው የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ አሁንም ሕዝባችንን በተለይም ወጣት ልጆቻችንን እያጠቃ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡በመሆኑም ይህንን በሽታ ለመከላከል አንድ ለአንድ በመተማመን መጠበቅ የሚለውን የቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ ከሁሉም አማራጮች በላይ አስተማማኝ መከላከያ ስለሆነ ሕዝቡ ይህንን በመቀበልና በማክበር ከኤች. አይ. ቪ. ኤድስ በሽታ ራሱን እንዲጠብቅ በእግዚአብሔር ስም እንመክራለን፡፡ በበሽታው ተይዘው የሚገኙ ወገኖችም በሐኪም የታዘዘላቸውን መድኀኒት በሰዓቱ እንዲወስዱ ጸበል ሲጠመቁም ሳያቋርጡ ሁለቱንም አንድ ላይ እንዲወስዱ፣ አጥብቀን እንመክራለን፡፡

በመጨረሻም፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን በዓለ ጥምቀት ሲያከብር ዓለማችንንና ሀገራችንን ከባድ ሥጋት ላይ የጣለው የኮረና ቫይረስ እንዳያጠቃው ሁሉም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ እንደዚሁም ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት መጠበቅ ወደ ፈጣሪ ከመጸለይ ባሻገር እርስ በርስ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝና በአብሮነት የጋራ ቤቱ የሆነች ኢትዮጵያን እንዲጠብቅ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ ጥምቀት ያድርግልን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ታኅሣሥ 29 ቀን 2013 ዓ.ም የልደት በዓልን መግባት አስመልክተው ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት ሁሉ፤
ከጥንት ጀምሮ የነገረንን ተስፋውን ለመፈጸም በዚህ ዓለም የተወለደው የተስፋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ።

“ወናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ፣ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ማለት ነው” (ኢሳ. 7፥14፤ ማቴ. 1፥23)

የምሕረት አባት እግዚአብሔር አምላካችን በእውነተኛ ዳኝነቱ በኀጢአት ላይ መፍረዱ የማይቀር ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን ይቅርባይነቱ አይለይም፡፡ በመሆኑም ሰው በበደሉ ምክንያት ቢፈረድበትም የሚድንበትንም ተስፋ ወዲያውኑ ተነግሮታል፤ ሰውም ያንን ተስፋ እንደሚፈጸምለት በማመን ለዘመናት ሲጠባበቅ ኖሮአል፣ ከዚህ አኳያ የተሰጠው ተስፋ በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ አገላለጽ፣ በተለያዩ ቅዱሳን ነቢያት በየጊዜው ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ከነዚህም መካከል ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ይገኝበታል፣ ነቢዩ ስለዚህ ተስፋ ሲናገር “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው” በማለት ተስፋውን በትንቢቱ አጒልቶ ተናግሮአል፡፡ ወንጌላዊ ቅዱስ ማቴዎስም ይህ ተስፋ የተነገረው ለእመቤታችን እናትነት፣ ለጌታችን ልጅነት እንደዚሁም ድኅነትን ለሚሻ ለሰው ልጅ ሁሉ እንደሆነ በወንጌሉ አስረድቶናል፤ በተስፋው መሠረት የሚወለደው ልጅም አማኑኤል የሚል ስም እንዳለውና ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጦአል፣ ምሥጢሩ ከሕፃኑ መወለድ በፊት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መለያየት እንደነበረ፣ ሕፃኑ አማኑኤል ሲወለድ ግን እግዚአብሔርና ሰው መለያየታቸው ቀርቶ በከዊን አንድ እንደሆኑ ያስረዳናል፤ እንደዚህ ባለ ሁኔታ፣ በትንቢት ሲነገር የቆየው የእግዚአብሔርና የሰው ምሥጢረ ተዋሕዶ በዕለተ ፅንስ በማሕፀነ ማርያም እውን ሆነ፤ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ “አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ” ከዘጠኝ ወር በኋላም በዛሬው ዕለት ታኅሣስ ፳፱ ቀን በቤተ ልሔም ከተማ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሰውን ሥጋ ለብሶ ወይም ተዋሕዶ መታየቱ ሰውን እንደታረቀው እና እንዳቀረበው፣ የአካሉ አካል እስከ ማድረግ ድረስ ደርሶም እንደወደደው በግልጽ ታወቀ፡፡ በመሆኑም ይህንን የአምላክና የሰው በከዊን መዋሐድ ያዩ ሰማያውያን ሠራዊት በከፍተኛ አድናቆትና በሐሤት “በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር ይገባል፤ በምድርም ለሰው ልጅ ሰላም ይገባል፤ ምክንያቱም ሰውን በእጅጉ ወዶታልና” በሚል ሰማያዊ አዲስ መዝሙር ቤተ ልሔምን አሸበረቋት፡፡ በቤተ ልሔም የነበሩ እረኞችም የምስጋናውና የክብሩ ተሳታፊዎች ነበሩ፣ ስለዚህ በዓለ ልደተ ክርስቶስ የከዊን ተዋሕዶው በአምላክና በሰው መካከል፣ የአንድነቱ ጥምረት በመላእክትና በሰዎች መካከል የተከናወነበት ታላቅ ቀን በመሆኑ በሰው ልጅ የድኅነት ጒዞ ዋናው መሠረት የተጣለበት ቀን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የተባለው ትንቢትም በዚህ ቀን በትክክል መፈጸሙን እንገነዘባለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ልደተ ክርስቶስ የተለያዩት የተገናኙበት፣ የተራራቁት የተቀራረቡበት፣ ሰማያውያንና ምድራውያን ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለ ሰላም በኅብረት የዘመሩበት ታላቅ በዓል ነው፣ ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለሰላም አስፈላጊነት በተመለከተ ከልደተ ክርስቶስ የበለጠ አስተማሪና ትምህርት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፣ ስለአንድነት ጠቀሜታም ከልደተ ክርስቶስ የተሻለ አስተምህሮ ይኖራል ተብሎ አይታመንም፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ሆነ ሌላው ማኅበረሰብ ለሰማያዊም ሆነ ለምድራዊ ኑሮአችን፣ ለነፍሳችንም ሆነ ለሥጋዊ ሕይወታችን የሚበጀን ምንድን ነው? ብሎ የሚጠይቅ ካለ መልሱ ከልደተ ክርስቶስ ይገኛል፤ መልሱ ከሁሉ በፊት ከእግዚአብሔር ጋር መሆን ነው፣ መልሱ ከእግዚአብሔር ሠራዊት ጋር በአንድነት ስለ ሰላም፣ ስለዕርቅና ስለፍቅር መዘመር ነው፣ ይህ ከሆነ የተመሰቃቀለ ሕይወት አይኖርም፤ ሥጋት፣ ጭንቀት አይኖርም፤ ቢከሠትም እንኳ በፍቅርና በሰላም ይሸነፋል፤ ስለዚህ የሰው ልጅ በአጠቃላይ ለሰላምና ለአንድነት ዋጋ እንዲሰጥ ያስፈልጋል፤ ችግሮች በዓለማችን ተበራክተዋል፤ የኮሮና በሽታ በአንድ ወገን ክትባት ተገኘለት ሲባል፣ እንደገና ሌላ መሰል በሽታ በአዲስ ሁኔታ እንደተከሠተ እየሰማን ነው፤ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታም ገና ፋይሉ አልተዘጋም፣ አለመግባባቶችም እየተካረሩ መጥተው ወደ ግጭት አምርተዋል፣ ረኃብ መፈናቀል እና ሌሎች ችግሮች ዓለማችንን እየናጧት ይገኛሉ፣ ይኼ ለምን ሆነ ቢባል የልደተ ክርስቶስ መልእክት ቸል ከመባሉ የተከሠተ ችግር ከመሆን አያልፍም፡፡ ስለሆነም የዚህ ሁሉ መፍትሔ የሚገኘው ከክርስቶስ ልደት ነውና ልደቱን ስናከብር ለእግዚአብሔር ክብር በመቆም፣ ለሰው ልጅም ሰላምን ለመስጠትና ለመቀበል በመዘጋጀት ሊሆን ይገባል፤ ከዚህም ጋር የታመሙትንና፣ የታሠሩትን በመጠየቅ፣ የተራቡትንና የተጠሙትን በማብላትና በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ ለእግዚአብሔር ያለንን ክብርና፣ ለወገን ያለንን ፍቅር በመግለጽ በዓሉን ልናከብር ይገባል፡፡

በመጨረሻም በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ በየአቅጣጫው እየተከሠተ ያለው አለመግባባት ልማታችንን፣ ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተን እንዳይሆን መላው ሕዝባችን በንቃት በጥበብና በማስተዋል እንዲከታተለው፣ ሁሉም ለሀገሩና ለሃይማኖቱ ለወገኑም ተገቢ ትኲረት በመስጠት በጸሎትና በሚችለው ሁሉ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል በዚህ አጋጣሚ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ መልካም የልደት በዓል!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።