ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሃይማኖትን፣ ብሔርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የሰው መግደልና የአብያተ ክርስቲያናት አስምልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በፍጹም የሚያወግዘው መሆኑን የተሰጠ መግለጫ በቅዱስነታቸው ተላልፏል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

«ተገሐሥ እምእኩይ ወግበር ሠናየ — ከክፉ ነገር ራቅ፤ ሰላምን ፈልጋት።»
(መዝ. 33፥12)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሥራቿና አምላኳ የሰላም አባትና አለቃ የሆነው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደመሆኑ በጸሎቷና በአገልግሎቷ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ሕዝቦቿና ስለ መላው ዓለም ሰላም ዘወትር ወደአምላኳ ስታማፅንና ስትማልድ የኖረች ያለችና ወደፊትም የምትኖር የሀገር ባለውለታና የሁሉም እናት መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን በተለያዩ ክልሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች የአማራና የቅማንት፣ የሱማሌና የአፋር፣ የአማራና የትግራይ የኦሮሞና የአማራ የጉምዝና የአማራ የሲዳሞና የወላይታ በሚል ብሔርና ሃይማኖትን እንዲሁም ቋንቋን መሠረት ያደረገ በኢትዮጵያ ሀገራችን እንኳንስ ሊደረጉ ይቅርና ሊታሰቡ የማይገባቸው መጠነ ሰፊ ግጭቶች በመከሠታቸው የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ በርካታ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ከቀያቸው አለአግባብ እየተፈናቀሉ ለከፋ እንግልትና ዕርዛት ተዳርገዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስ በግጭቶች እየደረሱ ካሉት የሰው ሕይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ልንማር ባለመቻላችን በያዝነው ሳምንት ችግሩ ቀጥሎ በአዲስ አበባ፣ በኦሮምያ ክልልና በሌሎችም ክልሎች እየተከሠተ ያለው ግጭት እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ ጊዜ የማይሰጥና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነትና በኅብረት ችግሩን ካልቀረፍነው መጠነ ሰፊ ጉዳትን የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ በሀገራችን ያሉ ጅምር የልማትና የእድገት ጒዞዎችን በመግታት ሀገሪቱን ለከፍተኛ ጥፋትና ድህነት የሚዳርግ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ዓመታዊ ስብሰባውን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስለ ሀገር ሰላም ቅድሚያ በመስጠትና ከሌሎች የመወያያ አጀንዳዎች በማስቀደም በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተከታዩን አስቸኳይ የአቋም መግለጫና የሰላም ጥሪ አስተላልፏል፡፡

1. ማንኛውም የተለየ ሐሳብና አመለካከት ያለው ወገን ቢኖር ሐሳቡን በሠለጠነና በሰከነ መንገድ ሀገራዊ አንድነትን ማእከል ባደረገ ሁኔታ በክብ ጠረጴዛ በመወያየት ችግሮቹ እንዲፈቱና የአሠራር ግድፈቶች ካሉም እንዲታረሙ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፣
2. የሀገር ተረካቢ የሆናችሁ መላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ከዛሬ ይልቅ ነገ በእናንተ ተተኪነትና በምታከናውኑት የማይተካ የላቀ አስተዋፅኦ ወደ ላቀ የእድገት ደረጃ ደርሳ እናንተም ሆናችሁ መላው ወገናችሁ ተጠቃሚ የሚሆንባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና እውን ለማድረግ የሀገሪቱ ሙሉ ተስፋ በእናንተ በወጣት ልጆቻችን ትከሻ ላይ የተጣለ መሆኑ ይታወቃል፤ በመሆኑም በወቅታዊና ሚዛናዊ ባልሆነ አንዳንድ ከሕግ ማዕቀፍ የወጡ አካሄዶችን በሰከነ አእምሮ እና በትኵረት በመመልከት ሀገራችን ኢትዮጵያን ከጥፋትና ካልተገባ ግጭት ትታደጓት ዘንድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከአደራ ጋር በአጽንዖት ለእናንተ ለልጆቿ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
3. በሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን የመድበለ ፓርቲ ሥርዐት ተከትሎ ለሀገራችሁ የሚሆን ልዩ ልዩ አማራጭ ሐሳቦችን በማመንጨት ሕጋዊ ዕውቅና አግኝታችሁ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኙ ሁላችሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ፖሊሲ ቀርጻችሁና ያመናችሁበትን ርእዮተ ዓለም አቅዳችሁ የምትንቀሳቀሱት ሀገራችሁ ኢትዮጵያ ወደተሻለ የእድገት ደረጃ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ ለመወጣት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከዚህ አንጻር በየጊዜው ዘር፣ ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው እየተከሠቱ ያሉ ግጭቶችን ከጅምሩ በአንድነት ማስቆም ካልተቻለ ነገ የምትረከቧትና የምታስተዳድሯት ሀገር ልትኖር ስለማትችል በቅድሚያ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይገድባችሁ ለሀገር ሰላምና አንድነት በኅብረት ዘብ በመቆም የበኩላችሁን ኀላፊነት ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
4. ለመንግሥታችሁና ለሕዝባችሁ ሙያዊ ትንታኔን መሠረት ያደረገ አማራጭ ሐሳቦችን በግብአትነት በማበርከት የሀገራችንን እድገትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዐት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ለማበርከት በማሰብ ልዩ ልዩ ጽሑፎችንና ዘገባዎችን በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ የምታቀርቡና የምታስተላልፉ የፖለቲካ ተንታኞችና አክቲቪስቶች ከስሜት፣ ከብሔር፣ ከቋንቋና ከሃይማኖት ልዩነት በጸዳ ሁኔታ እናት ሀገራችሁን ማእከል በማድረግ ለተሻለ ሰላምና አንድነት የበኩላችሁን ድርሻ ከማበርከት ባለፈ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩና አንዳንድ ያልተገቡ ትርክቶችን አላግባብ ከማሰራጨት በመቈጠብ ሀገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፤
5. የመንግሥትም ሆነ የግል የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ከተቋቋማችሁበት መሠረታዊ ተልእኮና ዓላማ አንጻር በተቻለ አቅም ዘርን፣ ቀለምን፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላቶች በመራቅና ሚዛናዊ የሆኑ መረጃዎችን ለሕዝባችን በማድረስ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የበኩላችሁን ኀላፊነት እንድትወጡ አደራ እንላለን፤
6. የማኅበራዊ ሚዲያ መሠረታዊ ዐላማው ዜጎች በእውነታ ላይ የተመሠረቱ ወቅታዊ መረጃዎችን በተሻለ ፍጥነት እንዲያገኙ ታስቦ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን በሀገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው እውነታ ከዚህ በተለየ መልኩ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር፣ ጎሳን ከጎሳ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩና ከእውነት የራቁ ግጭት ቀስቃሽ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት ሀገራችን ኢትዮጵያ የቆየ የአብሮነትና የአንድነት ባህሏን በሚያጎድፍ መልኩ ላልተገባ ዐላማ እየዋለ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፤ ከዚህ አንጻር ዛሬ በሌሎች ላይ የሚደርሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ነገ በየአንዳንዱ ቤት ሲያንኳኳ ሁሉም የጉዳቱ ሰለባ እንደሚሆን በመረዳት በተቻለ ዐቅም የማኅበራዊ ሚዲያውን ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት በመጠቀም ሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ሕዝባችን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እንጠይቃለን፤
7. ሀገር በዕውቀት እና በተሻለ ሐሳብ የምታድግና የምትመራ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገራችን ምሁራን ያላቸው ድርሻ በቀላሉ ሊገመት የማይችል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አንዳንድ ምሁራን የሚያስተላልፏቸው የኢትዮጵያን ታሪክ መሠረት ያላደረጉ ትርክቶች ለሀገራችን የግጭትና ያለመግባባት መንሥኤ ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ምሁራን በተቻለ አቅም ከልዩነትና ከግጭት ይልቅ ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
8. በየደረጃው ያላችሁ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች መላው ሕዝባችን ትመሩትና ታስተዳድሩት ዘንድ የሰጣችሁን ይሁንታና ሀገራዊ ኀላፊነት ከግምት ውስጥ ባስገባና በታላቅ ሀገራዊ ኀላፊነት ስሜት በተቻለ መጠን ግጭቶችና አለመግባባቶች ከመከሠታቸው በፊት ልዩ ልዩ የውይይት መድረኮችን ለመላው ሕዝባችሁ በማዘጋጀት እና በውይይት መድረኩ የሚገኙትን ግብአት የዕቅዳችሁ አካል አድርጋችሁ በመተግበር ኀላፊነታችሁን ከቀድሞው በተሻለና በላቀ ሁኔታ በመፈጸም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት እድገትና ብልጽግና የድርሻችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፤
9. በየደረጃው ያላችሁ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶችና አለመግባባቶች ከመከሠታቸው በፊት ቅድመ መከላከልን መሠረት ያደረገ የፀጥታ ሥራን በመተግበር እየተከሠቱ ያሉ ግጭቶችንና የሰው ሕይወት መጥፋትን እንዲሁም የንብረት ውድመትን በመከላከል የተጣለባችሁን ኀላፊነት እንድትወጡ እናሳስባለን፤
10. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያን ሰላም በማይወዱ አካላት የሚከሠቱ ልዩ ልዩ አፍራሽና ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን ወደጎን በመተውና በአርቆ አሳቢነትና በሀገር ባለቤትነት መጠነ ሰፊ ትዕግሥት የተሞላበት ሀገራዊ አንድነትና ኅብረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላበረከታችሁት የማይተካ ሚናና ታሪክ የማይረሳው ውለታ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እያመሰገነ እንደአሁን ቀደሙ ሁሉ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ዘር፣ ብሔርና ሃይማኖት ሳይለያያችሁ እጅ ለእጅ በመያያዝ የበኩላችሁን የማይተካ ድርሻ እንድትወጡ የአደራ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤
11. በሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኙ የሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ሀገራችን ኢትዮጵያ በሃይማኖት ብዝኀነትና ተቻችሎና ተከባብሮ በመኖር አስደናቂ ባህሏ ሌሎች ሀገራት የሚቀኑባትና በአርኣያነትም የሚጠቅሷት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ይህን አኲሪና አርኣያ የሆነ ታሪኳን በሚያደበዝዝ ሁኔታ ሃይማኖትና ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እየተበራከቱ በመሆናቸው ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅና ተጽዕኖ እምነታቸውን ለማምለክና ለማስመለክ የማይችሉበት የሥጋት አደጋ እየተጋረጠ ከመሆኑ አንጻር ሁሉም ቤተ እምነቶች ለሀገራዊ አንድነትና ለእምነት ነፃነት በአንድነትና በኅብረት ለመላው ሕዝባችን የሰላም ጥሪ በማስተላለፍና ዘወትር በየአስተምህሮአችን ለሕዝባችን የሰላምን ጥሪ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ኀላፊነታችንን እንወጣ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
12. በመጨረሻም ያለ ሀገር ሰላምና አንድነት እንዲሁም ፍቅርና እድገት መኖር ስለማይቻል መላው ሕዝባችን እንደየእምነቱና ሃይማኖቱ ሥርዐት ከዛሬ ጥቅምት 13 ቀን 2012ዓ.ም. ጀምሮ ለ3 ቀን ያህል በጾም፣ በጸሎትና በኀዘን ስለ ሀገር ሰላም በአንድነት ጥሪውን ለፈጣሪውና ለአምላኩ ያቀርብ ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጸሎትና ምሕላ እንዲደረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ መንፈሳዊ አዋጁንም አውጇል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የዋጀ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለዓመታዊው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

“ወይእዜኒ ረዐዩ ዘሀለዉ ኀቤክሙ መርዔቶ ለክርስቶስ፤ አሁንም በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ (1ኛ ጴጥ. 2፥6)፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ፣ ጠባቂ፣ መጋቢ፣ አስተናባሪና አስተዳዳሪ ነው፤ በሰማይና በምድር ያለው የሚታየውና የማይታየው ፍጥረት በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ጥበቃና አስተዳደር ሥር ነው፤ ፍጡራን ከእሱ በተገኘ የአእምሮ ነፃነት በሚፈጽሙት ተግባር የራሳቸው ድርሻና ኀላፊነት እንዳላቸው ቢታወቅም ያለእርሱ ዕውቅና የሚደረግ እንደሌለ ግን ከቅዱስ መጽሐፍ እንማራለን፡፡ እንግዲህ እሱ የጠባቂዎች ጠባቂ ሆኖ ሳለ ከፍጡራን ወገን ደግሞ በልዩ ምርጫው እየሾመ መንጋውን ወይም ፍጥረቱን ያስጠብቃል፤ ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የእግዚአብሔር አሠራር እንደሆነ ቅዱስ ያሬድ ሲገልጽ “ኢኀደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አንሥቶ እስከ ዘላለሙድረስ ምድርን ያለካህናት እና ያለ ዲያቆናት አልተዋትም” በማለት ያረጋግጣል፡፡

ይህ የሚያመለክተን እግዚአብሔር ዓለምን ያለ ጠባቂ የተወበት ዘመን ካለመኖሩም ሌላ ጠባቂዎቹ ካህናትና ዲያቆናት መሆናቸውን ነው፤ ካህናት የሚለው ስያሜ የወል ስም ሆኖ ከቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ያለው ውሉደ ክህነት በሙሉ እንደሚያጠቃልል ይታወቃል፡፡ ከዚህ አኳያ ኰኵሐ ሃይማኖት ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን በተሰጠው የጥበቃ ኀላፊነት መሠረት እሱም በክህነት ለወለዳቸው ልጆቹ በፈንታው “መንጋውን ጠብቁ” እያለ ምእመናንን ሲያስጠብቅ እናያለን፡፡ ትልቁ የእግዚአብሔር ትእዛዝና የቤተ ክርስቲያን ተልእኮም ይህ የጥበቃ ተግባር ነው፡፡

እግዚአብሔር እኛ ካህናትን በኀላፊነት የሾመበት ዋና ዐላማ መንጋውን እንድንጠብቅለት ነው፤ ይህ መንጋ ተብሎ የተገለጸው ወገን የተለየ ሕዝብና ጐሳ ሳይሆን ትዝምደ ሰብእን ወይም የሰው ዘርን በሙሉ ነው፡፡ በራሱ እምቢተኝነት ከሚቀርበት በስተቀር የጌታችን ጥሪ ለትዝምደ ሰብእ በሙሉ እንደሆነ “ሑሩ ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት ሂዱ፥ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት አሳውቆናል፡፡ እንዲህም ከሆነ ጠብቁ ተብለን የታዘዝነው ያመኑትን ወይም የተጠመቁትን ብቻ ሳይሆን ያላመኑትንም ያልተጠመቁትንም በአጠቃላይ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡

ከዚህ አንጻር መንጋችንን ስንጠብቅ ያመኑትን በነፍሳቸውም በሥጋቸውም ምንም ዐይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተሟላ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ፣ ያላመኑትንም በፍቅር በማቅረብና ዘመድ ዘመድ በማለት፣ ውስጣዊና መንፈሳዊ ስሜታቸውን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በማነቃቃትና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በማምጣት እንደሆነ ለሁላችን ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ይህን የጥበቃ ሥራ በአግባቡ ለማሳካት ትልቁ ትጥቃችን ቅዱስ ወንጌል እንደሆነ ምን ጊዜም መዘንጋት የለበትም፡፡ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ የተለያዩ ዘዴዎችንና አቀራረቦችን፣ ሥልጠናዎችንና አስተምህሮዎችን መጠቀምና በዚህም የባዘነውን በግ ወደ መንጋው የምንመለስበት ታሪካዊና ወቅታዊ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ የሚባክኑና በተኵላ የሚነጠቁ በጎች እጅግ እየተበራከቱ ነው፤ ዛሬ ሁሉም ነገር መልካም ነው ብለን የምንዘናጋበት ጊዜ ሳይሆን የጐደለውን ለመሙላት ቃል የምንገባበት፣ ያንኑም በተግባር ፈጽመን በጎቻችንን የምንሰበስብበት ጊዜ ነው፤ በዚህ አኳኋን በንቃትና በትጋት በኀላፊነትና በቊጭት ከሠራን ከባዘኑት በጎች መካከል ብዙዎቹን ወደ መንጋቸው መመለስ እንደምንችል፣ ያሉትም ባሉበት ጸንተው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

የጥበቃ ተግባራችን ከውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነትና ከውስጥ ጥቅመኞች የተነሣ ተደጋጋሚ ዕንቅፋት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ “በእንቅርት ላይ… ” እንደሚባለው በሀገራችን በተፈጠረው ያለመረጋጋት ክሥተት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ካህናትና ምእመናን ተገድለዋል፤ አሁንም ሥጋቱ እንዳለ፣ ከቀረበልን የአህጉረ ስብከት ሪፖርት ሰምተናል፤ በዐይናችንም አይተናል፤ ነባር የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች ሥልጣንን መከታ ባደረጉ ወገኖች እየተነጠቁ ነው፤ ምእመናን በሚደርስባቸው የማያባራ ተፅዕኖና አድልዎ ከቀያቸው እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ነው፡፡

ለመሆኑ እንዲህ ዐይነቱ ኢሰብኣዊ ድርጊት እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው? ይህ ድርጊት እንዲቆም እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕት መሆን ከዚህ ጉባኤ አባላት ይጠበቃል፡፡ ይህ ጉባኤ የኀያሉ የእግዚአብሔር ጉባኤ ነው፤ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብቻ ከሰባ ሚሊዮን ያላነሰ ሠራዊት ያለው ጉባኤ እንጂ ብቻውን አይደለም፤ ይህ ጉባኤ በሙሉ ዐቅሙ ሥራውን ከሠራና ድምፁን ካነሣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ሰሚው ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በታችኛው የመንግሥት መዋቅር እየደረሰብን ያለውን የማንታገሠው ግፍ መንግሥት እንዲያስተካክልልን ደጋግመን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እኛም በጸሎት አምላካችንን ከመማፀን ጋር ሁሌም በተጎጂው ሕዝባችን መካከል እየተገኘን በልዩ ልዩ ግፍ ልባቸው የተሰበረውን የልጆቻችን ኀዘን መቅረፍ ይኖርብናል፡፡ ችግራቸውንም መጋራት ይጠበቅብናል፤ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና መገንባት አለብን፤ መንግሥትም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት ክብር ነጻነትና እኩልነትን በሚሸረሽሩ የታችኛው መዋቅር ባለሥልጣናት ላይ የማያዳግም የእርምት ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥብቅ ክትትል ማድረግ አለብን፡፡

የመንጋ ጥበቃችን ሥራ እየተሰነካከለ የሚገኘው ከውጭ ሆነው በገንዘብ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ እርስ በርሳችንን በመከፋፈል በሚተነኩሱን ኀይሎች ብቻ አይደለም፤ በውስጣችን ያለው ሕግ ያልጠበቀ አሠራርም የምእመናንን ልቡና እያቈሰለ የሚገኝ ሌላው የጥበቃችን ዕንቅፋት ነው፤በመሠረቱ ይህንን ችግር ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማፅዳት ማስተካከል ካልቻልን ችግራችን በወሳኝ መልኩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡

በመሆኑም ቀደም ሲል የተጠኑትን የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግር መፍትሔና የመሪ ዕቅድ ጥናቶች ይህ ዐቢይ ጉባኤ በወሰነው መሠረት ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአስቸኳይ ይተገብር ዘንድ ጠበቅ ያለ መመሪያ ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በብልሹ አስተዳደር አዙሪት የሚታመስ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ሊኖር አይገባም፤ በዚህ ዓመት አሠራራችንን ሁሉ አስተካክለን ወደ መንጋ ጥበቃና ወደ ልማት ሥራችን በፍጥነት መሸጋገር አለብን፡፡

በመጨረሻም፡- የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ዙሪያ መለስ ጥቃት ለመመከትና ለመከላከል ብሎም ለማስቆም አንድ የጥቃት መከላከል ግብረ ኀይል እንደዚሁም በየአካባቢው የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ ተጽዕኖዎችና አድላዊ አሠራሮችን እየተከታተለ ትክክለኛ ኢንፎርሜሽንን የሚያቀርብ የኮሙኒኬሽን ግብረ ኀይል በአሁኑ ጉባኤያችን አቋቁመን ቤተ ክርስቲያናችንንና መንጋችንን ከመከራ እንድንታደግ የሀገራችንን ሰላምና የሕዝባችንን አንድነትም በጽኑ እንድናስጠብቅ አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

 38ኛው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት 5-8 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ከልዩ ልዩ አህጉረ ዓለም የመጣችሁ፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ የሰበካ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመሳተፍ በክብር የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት፣ እግዚአብሔር አምላክ በማይሰፈር ሀብተ ጸጋው ያለፈውን የሐዋርያዊ ተልእኮ ሥራችንን ባርኮና ቀድሶ ለአዲሱ ዓመት ስላደረሰንና ለዚህ ዓመታዊ ጉባኤ ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡

“አድኅነነ እግዚኦ አምላክነ፤ ወአስተጋብአነ እምአሕዛብ፣ ከመ ንግነይ ለስምከ ቅዱስ፣ ወከመ ንትመካሕ በስብሐቲከ” አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፣ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን።›› (መዝ. 105፥47)

የእስራኤል ንጉሥና ነቢይ የነበረው ቅዱስ ዳዊት ይህ ከዚህ በላይ የተገለጸውን ቃለ መዝሙር ለእግዚአብሔር ሲያቀርብ ዋና ግቡ እግዚአብሔርን ማመስገን እንደሆነ እንገነዘባለን፤ በገጸ ንባቡ እንደሚታየው የንጉሡ ጸሎት ሕዝቡን ከአሕዛብ መካከል እንዲሰበስባቸውና እንዲያድናቸው አምላኩ እግዚአብሔርን ይማጸናል፡፡ ይህንን ጸሎት ለማቅረብ የፈለገበትም ምክንያት ሲገልጽ ሕዝቡ በአንድነት ሆነው እሱን እንዲያመሰግኑ፣ በምስጋናውም እንዲመኩ ሽቶ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ሁኔታው ይህን የመሰለ ለሕዝብ የመቈርቈርና የማስተንተን መንፈስ ከአንድ የሕዝብ መሪና አስተናባሪ እንደሚጠበቅ ፍሬ ነገሩ ያሳያል፡፡

ከሁሉ በፊት ግን ለማመስገንም ሆነ ለማምለክ የሕዝቡ ደኅንነት እንደሚያስፈልግ፣ ደኅንነት ብቻም ሳይሆን አንድ ላይ መሰባሰብም ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ልበ አምላክ ዳዊት ሳይገልጽ አላለፈም፡፡ በእርግጥም የሕዝቡ ደኅንነት ካልተጠበቀ፣ አንድ ላይ ተሰባስቦም በፍቅርና በኅብረት ካልተገኘ፣ ምስጋናም አምልኮም በአግባቡ ሊከናወን አይችልም፤ ቅዱስ ዳዊት የዚህን አስፈላጊነት በመንፈስ ቅዱስ ተገንዝቦ ነው ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን፣ አድነንም፣ ከዚያም ስምህን እናመሰግናለን፤ በስምህም እንመካለን ብሎ የጸለየው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ለሚመራቸውና ለሚያስተዳድራቸው ሕዝበ እስራኤል መጸለይ ብቻ ሳይሆን፣ የእነሱ ቤዛ ሆኖ እስከሞት ድረስ መሥዋዕት ለመሆን ‹‹ምንተ ገብሩ እሉ አባግዕ ዘአነ ኖላዊሆሙ ዳእሙ ለትረድ እዴከ ላዕሌየ ወላዕለ ቤተ አቡየ›› ‹እረኛቸው ጠባቂያቸው የሆንኩላቸው እነኝህ በጎች ምን አደረጉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ትሁን እንጂ› ብሎ አምላኩን የተማፀነ ንጉሥና ነቢይ እንደሆነም ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

የቅዱስ ዳዊት መንፈሳዊ ተሐውኮና እስከ ቤዛነት የሚዘልቅ የመሪነት ብቃት ለሰው ልጆች በአጠቃላይ፣ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ዳዊት ይመራቸው የነበሩ ሕዝቦች መዳንና መሰባሰብ ያስፈልጋቸው እንደነበረ ሁሉ፣ ዛሬም መዳን፣ መሰባሰብ፣ አንድ መሆን የሚስፈልጋቸው ሕዝቦች አሉን፤ እነዚህ የምንመራቸው ሕዝቦች ቅዱስ ስሙን እንዲያመሰግኑና በስሙ አምነው እንዲኖሩ እኛ ስለእነሱ መዳን አዘውትረን መጸለይ አለብን፤ በአንድነት እንዲሰባሰቡም ማስተማርና መምከር፣ ማስታረቅና ማግባባት አለብን ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሕዝቦች ሁለንተናዊ ደኅንነት መጸለይ፣ ማስተማርና መምከር ከእግዚአብሔር የተቀበለችው ዐቢይ ተልእኮ ከመሆኑ የተነሣ ዘወትር የምታከናውነው ተቀዳሚ ተግባርዋ ቢሆንም፣ በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ በጸሎትና በማስተማር፣ በመምከርና በማስታረቅ ተግታ የምትሠራበት ጊዜ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ዛሬ ሀገራችን በተስፋና በሥጋት መካከል ተወጥራ ያለችበት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ማእከላዊ መዋቅርም በልዩ ልዩ ቡድኖች እየተፈተነ የሚገኝበት አሳሳቢ ወቅት ላይ ነን፡፡ በዚህ ፈታኝ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ትዕግሥት ያልተለየው ጥበብና ብልኀት ተጠቅማ ልጆችዋን ወደ አንድነት ማሰባሰብ ከምንም በላይ ተቀዳሚ ተግባር አድርጋ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ከእግዚአብሔር የተሰጣት የማስታረቅና የማስተማር፣ የመምከርና የማሰባሰብ ኀላፊነት የምታከናውነው አንዱን በማራቅ፣ ሌላውን በማቅረብ አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ ሳይሆን ሁሉም ልጆችዋ ናቸውና በእኩልነት፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በገለልተኝነት መሆን እንዳለበት መዘንጋት የለብንም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከፖለቲካ ንክኪ ፍጹም ነጻ ሆና ሥራዋን እንድትቀጥል ማድረግ የሁላችንም የቤተ ክርስቲያን አመራሮች፣ አገልጋዮችና ሠራተኞች የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ሆኖም ስለሰው ልጆች ደኅንነትና እኩልነት፣ ሰላምና አንድነት የእግዚአብሔር ቃልን መሠረት አድርጋ በሰፊው የማስተማር ኀላፊነት እንዳለባት መርሳት የለብንም፡፡ በሀገራችን እየታየ ያለው ያለመግባባት መንፈስ በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ይታያል፤ ይኸውም በአንዱ ወገን የመለያየት ሥጋትን የሚከላከል ሲሆን በሌላ ወገን ደግሞ የእኩልነት ዕጦት ሥጋትን የሚከላከል ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የግራና ቀኙ ሥጋት ለምን ይታሰባል ባይባልም መድኀኒት የሌለው ሥጋት ይመስል ይህን ያህል መጠራጠሩና መራራቁ ግን ተገቢ ሆኖ አይታይም፤ ምክንያቱም ሁሉም እንደሚያምንበት የዚህ ፍቱን መድኀኒት እኩልነትን ከአንድነት፣ አንድነትን ከእኩልነት ጋር አጣምሮ መያዝ እንደሆነ አያከራክርምና ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይህንን ሊዘነጉት አይገባም፤ ሕዝቡም በዚህ ላይ በሰፊው እንዲያስብበት ያስፈልጋል፡፡

የሰበካ ጉባኤ ዐላማ ካህናትን ምእመናንና ወጣቶችን በአንድ ሕጋዊ መዋቅር አደራጅቶ ሃይማኖትን ማስተማር ማስፋፋትና ማስጠበቅ እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረትን በቅዱስ ሲኖዶስ ማእከላዊ አስተዳደር በሕግና በሥርዐት እየተቈጣጠሩ ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ማዋል ነው፤ ከዚህ ውጭ መቼም፣ የትም ቢሆን የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ተጠብቆ በስሟ የሚሰበሰብ ሀብትና ንብረት ሁሉ በእሷ ዕውቅናና ጥበቃ ሥር ሆኖ የማይከናወን አሠራረር ሥር እየሰደደ ከሄደ፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ፈተና ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ በቤተ ክርስቲያናችን እያቈጠቈጠ የመጣው የሀብት ሽሚያ ክፉ መንፈስ አንዱ ሌላውን እየወለደ ሄዶ ዛሬ የራሳችን ቤተ ክህነት እናቋቁማለን እስከማለት ተደርሶአል፡፡

ይህ ጥያቄ ሊመጣ የቻለው እውነት ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያላቋቋመችበት አካባቢ በኢትዮጵያ ኖሮ ነውን? ክርስቲያን ልጆችዋ በሚሰሙት ቋንቋ እንዳይማሩስ እውነት ከልክላ ነውን? መከልከል ቀርቶ መጽሐፉን አስተርጒማና አሳትማ ሳታሠራጭ ቀርታ ነውን? ይህ ሁሉ ፍጹም ሐሰት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በስተጀርባ ያለው ሐቅ ሌላ ነው፤ ከቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ የፋይናንስ እይታ ውጭ በቤተ ክርስቲያን ስም የደለቡ ቡድኖች መኖራቸው ስለሚታወቅ፣ እኛም በተመሳሳይ የተለየ ቤተ ክህነት አቋቁመን ሀብት እናድልብ ነው ጥያቄው፤ ይህ አዝማሚያ የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት የሚያሽመደምድ፣ አንድነትዋንም የሚፈታተን ስለሆነ ሁሉም ወገኖች ለኛ ማለትን ያቁሙና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚለውን ቅን መርሕ ይከተሉ፤ ሁሉም በአንዲት የቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ መዋቅር ሥር ሆነው ጥያቄአቸውን በተገቢውና በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ ይችላሉ፤ ከቅን አመለካከትና ከተቈርቋሪነት የሚመነጭ፣ ለቤተ ክርስያን ጠቃሚ የሆነ፣ ሕግና ሥርዐትን የተከተለ፣ መዋቅሩን የጠበቀ ጥያቄ ከምእመናን ካለ አባቶች ለማስተናገድ ዝግጁ የማንሆንበት ምክንያት የለም፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ከሚያስተዛዝበን በስተቀር የጊዜ ጉዳይ እንጂ አያዛልቅም፣ ቅዱስ ሲኖዶስም እግዚአብሔር በዳዊት አድሮ እንደተናገረው ሕዝቡን ለመሰብሰብ እንጂ በተለያዩ አደናጋሪ አባባሎች ሕዝቡን በቡድን ሊከፋፍል አልተፈጠረምና ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስሕተት እንዳይፈጸም እንጠንቀቅ፣
የሰበካ ጉባኤ ዐላማና ተልእኮም ሊሳካ የሚችለው በቤተ ክርስቲያን ስም የሚሰበሰበው ማናቸውም ሀብትና ንብረት ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታውቀውና በምታጸድቀው፣ እንደዚሁም ማእከላዊ አሠራሩን ጠብቆ በሚፈጸም መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ አሠራር እንጂ፤ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለመሻማት ጓጉተው በየጊዜውና በየአካባቢው በሚፈጠሩ የልዩ ልዩ ቡድኖች አስመሳይ የእናውቅላችኋለን ስብከት አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህ ዐቢይ ጉባኤ ጉዳዩን በአጽንዖት እንዲያጤነው ወቅታዊና አባታዊ መልእክታችን ነው፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ ዐቢይ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት የሚያስጠብቅ፣ የሀብትዋና የንብረትዋ ማእከላዊ አስተዳደርን የሚያስከብር ነውና የሀገራችን ሰላምና ልማት፣ የሕዝባችን እኩልነትና አንድነት እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነትና የሀብቷና የንብረቷ ተጠቃሚነት እውን የሚያደርግ ዐቢይና ላዕላዊ ጉባኤ እንደመሆኑ መጠን፣ እነዚህን ተግባራት በማረምና ሥርዐት በማስያዝ ረገድ በበጀት ዓመቱ ጠንክሮ እንዲሠራ በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤ ዓመታዊውንና ዓለም አቀፉን የሰበካ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ መከፈቱንም በዚሁ እናበሥራለን፡፡ መልካም የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡