ከግንቦት 14 ቀን እስከ ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ከግንቦት 14-ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስመልከቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዩች ላይ ለ18 ቀናት ሲመክር ቆይቶ በርካታ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ጠቃሚ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ በዚህም መሠረት፡-

1. ለጉባኤው መክፈቻ የቀረበው ንግግር ቤተ ክርስቲያናችን ለምታከናውነው መንፈሳዊ ተግባር በእጅጉ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘው በቀጣይ ለሚደረገው የሥራ ስምሪት መመሪያ በማድረግ ጉባኤው አጽድቋል፡፡
2. ከግንቦት 2010 – ግንቦት 2011 ዓ.ም. በቋሚ ሲኖዶስና በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተወስነው የተላለፉ ጉዳዮች አፈጻጸማቸው በእጅጉ ውጤታማ መሆናቸውን ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቋል፡፡
3. የቋሚ ሲኖዶስ ሥልጣንና የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ተከሠቱ በተባሉ የሥራ አፈጻጸሞችና ታዩ በተባሉ ግድፈቶች ጉባኤው በሰፊው ተነጋግሮ በቀጣይ ማንኛውም መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን መሠረት አድርጎ እንዲሠራ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
4. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በሌሎችም መላው አህጉረ ስብከት እየታዩ ባሉ ችግሮች ላይ በመነጋገር፣ ለቀጣዩ የቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር ጠቃሚ ግብአቶችን ማግኘት እንዲቻል ችግሮቹን አጥንተውና ለይተው የሚያቀርቡ ብፁዓን አባቶችና ባለሙያዎች እንዲሰየሙ ተደርጓል፡፡
5. ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተከሥተው የነበሩ ችግሮች በአጥኚ ልኡካን ተጣርቶ በቀረበ አጀንዳ ላይ በመነጋገር ለአብያተ ክርስቲያናቱ መፍትሔ ይሆናል የተባለ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
6. የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤቶችና ሕንጻዎች ሆነው ሳለ ያለአግባብ ተወርሰው የነበሩ በመንበረ ፓትርያርኩ ኩታ ገጠም የሚገኙ ሕንጻዎች በክቡር የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ቍርጠኛ አመራር በመመለሳቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያናችን መብት መጠበቅ የሰጠውን ትኵረት በማድነቅ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል፡፡
7. በውጭ አገር የሚገኙ አህጉረ ስብከትን በማጠናከር መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎታቸውን ማስፋፋት እንዲቻል ከቃለ ዐዋዲው ጋር እና ከየአገሮቹ መንግሥታት ሕግ ጋር የተጣጣመ ደንብ እንዲዘጋጅና ለጥቅምቱ 2012 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
8. ለተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለአብነት ት/ቤቶች፣ ሰው ሠራሽ አደጋ ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ ለጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻ ማደሻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
9. መንግሥት ዜጎች እንዲቈጠሩ በያዘው መርሐ ግብር መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች በትክክል እንዲቈጠሩ፣ ቈጠራውም በሰላም እንዲከናወንና አገራዊው ተልእኮውም እንዲሳካ በየአህጉረ ስብከቱ ትምህርት እንዲሰጥ አስፈላጊውም ክትትል እንዲደረግ የኮሚቴ አባላት እንዲሰየሙ ተደርጓል፡፡
10. በጉባኤው፡- “ግጭቶችና አፈታታቸው በዓለም ዐቀፍና በአገር ዐቀፍ እይታ” በሚል ስለ ወቅታዊ የሀገራችን ሰላምና ሊደረግ ስለሚገባው ሐዋርያዊ ተልእኮ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ በስፋት በመነጋገር በአገራችን ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዐት እንዲያድግ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲጐለብትና ድህነት እንዲወገድ በሁሉም አቅጣጫ መሥራት እንደሚያስፈልግ ለሚመለከታቸው ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡
11. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ሆነው በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች በሚቆዩባቸው ዓመታት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ፣ የእምነት ነፃነታቸው ተረጋግጦ፣ እንደ እምነታቸው ሥርዐት በዓመት ውስጥ ባሉ ሰባት አጽዋማት የመጾም መብታቸው ተጠብቆ፣ አስፈላጊው አቅርቦት እንዲደረግላቸው፣ ሃይማኖታዊ በዓላትንም በሚያከብሩበት ጊዜያት የኖረና የቆየውን ትውፊታዊ አልባሳትን የመልበስ መብታቸው እንዲጠበቅ ለየኮሌጆቹና ዩንቨርሲቲዎች የቅዱስ ሲኖዶሱ ማሳሰቢያ እንዲደርሳቸው ወስኗል፡፡
12. የአገራችንን የቱሪስት መስሕብነት ምክንያት በማድረግ ዜጎች በቅድስናና በፈሪሀ እግዚአብሔር ተከብረው የሚታወቁባት የአገራችንን ታሪክ የሚቀይር የዜጎችን መልካም ሥነ ምግባር የሚለውጥ ሕገ ተፈጥሮንና የተቀደሰውን ሥርዐተ ጋብቻን የሚያበላሽ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የተወገዘ ግብረ-ሰዶምን በአገራችን ለማስፋፋት፣ በዚህም የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቅድስና የሚጐዳ ሕገ-ወጥ ተግባር ለመፈጸም፤ መቀመጫውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው የግብረ ሰዶማውያን አስጐብኚ ድርጅት በመቃወም ወደ ቅድስት አገራችን ኢትዮጵያ እንዳይገባ፣ ቅዱሳት መካናትንም እንዳይጐበኝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አውግዟል፡፡ የሀገራችን ዜጎች ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንም ከእንዲህ ዐይነት የአገራችንን መልካም ገጽታና መልካም ሥነ-ምግባርን ከሚያበላሽ፣ በሃይማኖት ትምህርት ተጠብቆ የቆየው ባህላችንን ከሚያጠፋ፣ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ጠላት ከሆኑ ወራሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ በሀገራችንም ይህንን ሕገ-ወጥ ተግባር በመደገፍ እየተባበሩ ያሉት ግለሰቦችና ድርጅቶች ሁሉ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡
13. ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ችግር አስመልክቶ በስፋት ሲነጋገር የሰነበተው ጉባኤ፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንና በምእመናን ተከታዮቿ ላይ እየደረሰ ያለው፡-

• የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣
• የክርስቲያኖችን መገደል እና ከቀያቸው መፈናቀል፣
• በሃይማኖታቸውና በሃይማኖታዊ ሥርዐታቸው ላይ ተጽዕኖ ማድረግ፣
• የአብያተ ክርስቲያናት ነባር የይዞታ ቦታዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ መቀማት፣
• ለቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራዊና ልማታዊ ተግባር በጎ ፈቃድ አለማሳየትና የመሳሰሉት፤
ሪፖርቶች ከየአህጉረ ስብከቱ ቀርበው ጉባኤው በኀዘን ተመልክቶታል፡፡ በዚሁ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አገሪቱንና ሕዝቡን ይመራሉ ተብለው አደራ ለተቀበሉ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ሁሉ ማእከላዊው መንግሥት አስፈላጊውን መመሪያ እንዲሰጣቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ጠይቋል፡፡

14. በየሦስት ዓመቱ በቅዱስ ሲኖደስ ምልአተ ጉባኤ የሚመረጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ምርጫ አስመልክቶ በሰፊው በመወያየትና አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ፡- (ሀ) ብፁዕ አባ ዮሴፍ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣ (ለ) ብፁዕ አባ ያሬድ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በማድረግ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሰይሟል፡፡ ከዚህም ጋር አዲስ የሀገረ ስብከት ደረጃ የተሰጣቸው ዞኖችና መምሪያዎች ላይ ብፁዓን አባቶችን መድቧል፡፡
15. ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ከመሠረት ጀምሮ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚለውን መርሕ ተከትላ፣ ሰላሟን፣ ፍቅርዋንና አንድነትዋን ጠብቃ፣ ከውጭ የሚመጡባትን ባዕዳን ወራሪዎች በመመከት ክብርዋንና ልዕልናዋን ለረጅም ዘመናት ጠብቃና አስጠብቃ የኖረች፣ ወደፊትም በዚሁ ጸንታ የምትኖር ታላቅ ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ሕዝቦችዋም በአሁኑ ዘመን የሚታዩትን ያልተለመዱ ባሕርያት በሰከነ መንፈስ ቆም ብለው በመምከርና በመወያየት ወደ ጥንተ ሰላምዋ እንድትመለስ የማድረግ ኀላፊነት አለባቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በማኅበራዊው ዘርፍም ለሀገር እድገትና ለሕዝቦች ኑሮ መሻሻል፣ በተለይም ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት በመቆም ድርሻዋን እንድትወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ዐበይት ጉዳዮች ላይ ለ18 ቀናት ያህል በአገር ዐቀፍ ጉዳዮች በስፋትና በጥልቀት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!