መጋቢት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በዓለ ደብረ ዘይት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ልጆቻችን በሙሉ፤

ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለበዐለ ደብረ ዘይት በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ።

“ወባሕቱ ጸልዩ ከመ ኢይኩን ጕያክሙ በሰንበት ወበክረምት
ሽሽታችሁ በሰንበትና በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ።”
(ማቴ. 24፥20)

የችግሮች ሁሉ ቊልፍ መከላከያ የሆነው ይህ የጸሎት አስተምህሮ፣ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ በይቀጥላልም ለእኛ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ሁሉ ያስተማረው ዐቢይ ትምህርት ነው፡፡ በግዘፍ የሚታዩት የምልአተ ዓለም (ዩኒቨርስ) ክፍለ ዓለማትና በውስጣቸው የሚገኙ ሥጋውያንና ደማውያን ፍጡራን በሙሉ፣ መጨረሻ እንዳላቸው የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለባቸው የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ዓለማትን በሙሉ የፈጠረ የእግዚአብሔር አካላዊ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በምልአተ ዓለም የሚገኘው ግዙፍ ፍጥረት በሙሉ ሰማያትና ምድርም ጭምር መጨረሻ እንዳላቸውና በኅልፈት ታሪካቸውና ህልውናቸው እንደሚዘጋ አበክሮ ተናግሮአል፤ ለእኛም አሳውቆናል፤ ጌታችን የዓለምን ፍጻሜ የሚያስረዳይህንን ትምህርት ሲያስተምር ዘመኑን ቀኑንና ሰዓቱን ለይተን ልናውቅ እንደማንችል ከመግለጹ ባሻገር ያለን አማራጭ ዕድል ሁል ጊዜ ተዘጋጅቶ መኖር ብቻ እንደሆነ አጥብቆ አስተምሮናል፡፡

ጌታችን የዓለም ዕድሜ የሚጠናቀቅበት ዓመት እንዲሁም ቀንና ሰዓት ልናውቅ እንዳልተፈቀደ ቢያስተምርም የዓለም ፍጻሜ መቃረብን የሚጠቁሙ ግዙፍና ተጨባጭ ምልክቶች እንደሚከሠቱ ግን በግልጽ አሳውቆናል፡፡ በአጠቃላይ የዓለም ፍጻሜ እየተቃረበ ሲመጣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ የማያውቅ አሰቃቂና አስጨናቂ መከራ በዓለም ላይ እንደሚከሠት በሚገባ አስተምሮናል፤ ከምልክቶቹ መካከልም የሚከተሉት በዋናነት ተጠቅሰዋል፤ እነሱም፡ ቅዱስ ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ብዙ ሐሰተኞችና አስመሳይ የክርስትና መምህራን ይመጣሉ፤ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስመ ክርስቶስ የሚሰብኩ ሐሰተኞች በየአካባቢው ይነሣሉ፤ ረኃብ ቸነፈር የምድር መንቀጥቀጥና መናወጥ በተደጋጋሚ ይከሠታል፤ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ለጦርነት ይሰላለፋሉ፤ የጦርነት ድምጽ በየአቅጣጫው ይሰማል፤ ከዐመፅና ከክፋት የተነሣ ፍቅር ከሰዎች ትጠፋለች፤ ብዙ ሰዎች ሃይማኖታቸውን ይክዳሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ሃይማኖታውያን ክርስቲያኖች ስሙን በመጥራታቸው ብቻ ይጠላሉ፤ ሐሰተኞቹ መምህራን ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ነገሮችን በማሳየት ብዙ ክርስቲያንን ያስታሉ የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች በሚከሠቱበት ጊዜ የሰው ልጅ በሰላም ገብቶ በሰላም መውጣት አጥቶ፣ ዕለታዊ ኑሮው ተበጥብጦ፣ ህልውናው እንደሚቃወስ፣እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታም እንደሚፈጠር ጌታችን በደብረ ዘይት ትምህርቱ ላይ በማያሻማ ሁኔታ አስተምሮናል፤ እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ ብሎም አስጠንቅቆናል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

ጌታችን በዓለም ፍጻሜ የሚሆነውን ከባድ መከራ ብቻ ሳይሆን ልናደርገው የሚገባን ጥንቃቄንም በሚገባ ከማስተማሩም ሌላ ልናደርጋቸው ከሚገቡ ጥንቃቄዎች መካከል የሚከተሉትን ነግሮናል እነርሱም፡ (1) ሁልጊዜ ትዕግሥትን አጥብቀን በመያዝና በዚያው በመጽናት መዳን የምንችል መሆኑን እንድናውቅ፣ (2) ክርስቶስ እዚህ አለ እያሉ የሚያሳስቱ የሐሰተኞች ክርስቲያኖች ትምህርትንና የሚያደርጓቸው ታላላቅ ድንቅ ምልክቶችን ማመንና መቀበል ፈጽሞ እንደሌለብን፣ (3) የክርስቶስ ምጽአት መብረቅ ከምሥራቅ ሲወጣ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ እንደዚሁ በግልጽ ይሆናል እንጂ በእልፍኝ ወይም በሌላ ስፍራ በድብብቆሽ አለመሆኑን ዐውቀን እንድንጠነቀቅ፣ (4) የዓለም ፍጻሜና የጌታ መምጫ ቀን ለይተን ማወቅ ስለማንችል ሁልጊዜ ተዘጋጅተን እንድንኖር፣ (5) በሰንበትና በክረምት የሚሸሽ ሰው ማምለጥ እንደማይችል ሁሉ ሃይማኖትና ሥነ ምግባር የሌለው ሰውም ከመከራ አያመልጥምና በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ጸንተን በጸሎት እንድንተጋ አስተምሮናል፡፡ ጌታችን መከራው ሊሆን ግድ ነው ካለ በኋላ፣ በመከራው ከሚመጣ ጥፋት ለመዳን ምን ምን ማድረግ እንዳለብን እነሆ በግልጽ አስተምሮናል፤ በመሆኑም “ማወቅ ለመጠንቀቅ” እንደሚባለው ጌታችን መከራውንም የመከራውንም ማምለጫ አስቀድሞ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አስተምሮናልና ልናዳምጠው ልንሰማውና ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ በየቀኑ የምንሰማውና የምናየው የዓለማችን ሁኔታ ጌታችን ከነገረን ምልክት ጋር በእጅጉ የተቀራረበ ሆኖ እንደሚታይ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ በመሆኑም የጌታችን ገዢ አስተምህሮ “ሁልጊዜ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” የሚል ከመሆኑ ጋር ምልክቶቹ በዝተውና እንደቃሉ ሆነው ስናያቸው ይበልጥ መጠንቀቅ እንዳለብን ሳናሠምርበት አናልፍም፡፡

የጌታችንን ቃል ልብ ብለን አስተውለነው ከሆነ እኛ ኢትዮጵያውያንም ከዚህ የመከራ ገፈት ውጭ የሆን አይመስልም፡፡ በሀገራችን ውስጥ፣ ታላላቅ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮችን እናደርጋለን፣ ትንቢት እንናገራለን፣ ፈውስም እንሰጣለን የሚሉ ሐሳውያን በእጅጉ ተበራክተዋል፡፡ በሀገራችን ፍቅር እየቀዘቀዘ፣የግጭት ሁኔታ እየተበራከተ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ መቃቃርንና መጠራጠርን እያሳየ ነው፡፡ ብዙ ሐሰተኞች መምህራን ብዙ ክርስቲያኖችን እያሳሳቱ ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ እያደረጉ ነው፡፡ ጠብ ጥላቻ መለያየትና ረኃብ እንዳለ እየተሰማ ነው፤ እየታየም ነው፤ እነዚህ ሁሉ ለዋናው መከራ የምጥ ጣር ናቸው ብሎ ጌታችን እንደ ነገረን ሁኔታዎቹ በኅሊናችን የሚጭሩት ነገር አለና በተሰጠን የመፍትሔ አማራጭ መጠቀም ግድ ይለናል፡፡

በተለይም በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ጸንቶ፣ ለትዕግሥት ተገዝቶ ነገሮችን በፍቅር ማሸነፍ፣ በጸሎትም መትጋት አሁን በሀገራችን እየተከሠተ ላለው ችግር ቁልፍ መፍትሔዎች ናቸው፤ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኀይል እግዚአብሔር እንጂ ሌላ ሰው ሠራሽና ተገለባባጭ የውጭፖለቲካዊ ፍልስፍና አልነበረም፤ሰው ሠራሽ የፍልስፍና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወደ ሀገራችን ባልገባበት ወቅት ኢትዮጵያ ከሁሉ በላይ በሆነ በእግዚአብሔር ኀይል ብቻ ትጠበቅ ስለነበረች አሁን ላጋጠመን የሃይማኖትና የሥነ ኅሊና ውድቀት ሳትንበረከክ ረጅም ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ ይህንም ስንል ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ፈጽሞ መቀበል የለብንም ማለታችን አይደለም፤ የነበረንን የኛው ታላቅ ነገርን ትተን የሌላውን ብቻ ተቀብለን ለመሮጥ የምናደርገው አካሄድ ማረም አለብን ማለታችን ነው፤ በነበረን መልካም እሤት ላይ ጠቃሚ የሆነውን ዕውቀት ከእኛው ነባር ጥበብ ጋር አጣጥመንና እንደጋቢ ደርበን መጠቀም አለብን እንጂ፣ የነበረንን የሚያሳጣ ነገር ብቻ መከተሉ አያዋጣም ነው እያልን ያለነው።

ሀገራችን የነበሯት ድንቅ ዕሴቶች በሃይማኖት እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የአንድነት፣ የመቻቻልና እየተረዳዱ እየተጋገዙ በፍቅር መኖር፣ በኢትዮጵያዊ ቅዱስ ባህልና ውርስ ተሳስሮ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ መኖር፣ ሁሉንም በይቅርታ እየተዉ መሄድ፣ ለባዕድና ለመጤ ባህል፣እንደዚሁም ለሃይማኖት ተጋፊ አለመንበርከክ፣ ችግሮችን ሁሉ በሃይማኖት መሪዎችና በሀገር ሽማግሌዎች ምክር እየፈቱ በፍቅር መርሕ ይቅር ይቅር መባባል፣ ታጋሽና አርቆ ተመልካች መሆን፣ ቂም በቀልን መጸየፍ መተኪያ የሌላቸው ውድ የሀገራችን ድንቅ ዕሤቶች ናቸው፤ አሁን የመጣብን ጣጣ እነዚህን ዕሴቶች ንቀንና ትተን ጆሮዎቻችንና ኅሊናችንን ለባሕር ማዶ ባህሎችና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች ብቻ ከፍተን ስለተገኘን፣ በተገኝው ቀዳዳ ሁሉ ባዕዳን ለራሳቸው ድብቅ ዐላማ በሚያመች ሁኔታ እኛን እየከፋፈሉ፣ በውስጥ ጉዳያችንም ጣልቃ እየገቡ እርስ በርሳችን ሊያናቁሩን እየተጉ እንደሆነ ልንዘነጋው አይገባም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን የሚበጀን ነገር ቢኖር የሚያኮሩንና አንድ የሚያደርጉን ብዙ ዕሴቶች ስላሉን እነሱን ተከትለን ችግራችንን ሁሉ በትዕግሥት፣ በይቅርታና ቂም በቀልን ፈጽሞ በመተው አንድነታችንን ማጠናከር ላይ ማተኮር ነው፤እኛ አንድ ከሆን በኋላ የሚጠቅመን የውጭ የአስተዳደር ብሂል ካለ ማስተዋል ባልተለየው የጋራ ውይይት ባለን ላይ ደርበን መጠቀም እንችላለን፡፡ የመለያየት ጎጂነቱ በማያሻማ ሁኔታ ታውቆ፣ ለብዙ ዘመናት ተለያይው የነበሩ ሀገራት በአህጉር ደረጃ ተሳስረው፣ ፓለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን በጋራ ለማሳደግና በጋራ ለመጠቀም በሚተባበሩበት በአሁኑ ዘመን፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አብረን የነበርን እኛ ኢትዮጵያውያን ቂም በቀልን መተው አንለምድ ብለን፣ የውጭ ጣልቃ ገቦችን ቅስቀሳ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት አቅቶን ችግራችንን ራሳችን በራሳችን በይቅርታና በውይይት ማስወገድ ተስኖን ታሪካችንን ጥላሸት እንዳንቀባውና ታላቋ የእግዚአብሔር ሀገር ኢትዮጵያን ፈተና ላይ እንዳንጥላት በእጅጉ መጠንቀቅ አለብን፡፡

በአሁኑ ጊዜ የተሻለችና አንድነቷ አስተማማኝ የሆነች ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሲባል ሁሉንም ነገር መተው ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፤ ቂም በቀልን፣ የጥላቻና ጽንፈኛ አስተሳሰብን፣ ያለፉትን ግድፈቶች እየተረኩ ቅራኔ ማባባስን ጭራሽ ማቆም አለብን፤ ያለፈውን ትተን ወደፊት በአንድነት ለመቀጠል ምርጫችን ካላደረግን የሚገጥመን ነገር ጥሩ አይሆንም፤ በመሆኑም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የነበረንን ፈሪሀ እግዚአብሔር ተላብሰን፣ ቂም በቀልን በመተው፣ ይቅር ባይነት ከሁሉም የላቀ ጠቃሚያችን መሆኑን ተገንዝበን ወደዚሁ አስተሳሰብና እምነት መምጣት አለብን፡፡

በመጨረሻ፤ በበዐለ ደብረ ዘይት ዕለት ለመላ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን የምናስተላልፈው ዐቢይ መልእክት የኢትዮጵያ አንድነትና እድገት የሚረጋገጠው ከሁሉ በፊት ቂምን፣ በቀልንና ጭፍን ጥላቻን ትታችሁ፣ ሁሉንም በይቅርታና በመተው ተቀብላችሁ ለወደፊቱ የተሻለችና አንድነትዋ የጠነከረ ኢትዮጵያን ለማየት አብዝታችሁ ስትሠሩ ብቻ እንደሆነ አትዘንጉ፤ ይህም ለዘለቄታው የተሳካ እንዲሆን የኢትዮጵያ ፍጹምና ዘላቂ ጥበብ ለሆነ ፈሪሀ እግዚአብሔር ፣ለትዕግሥትና ለወንድማዊ ፍቅር ዝግጁ በመሆን፣ በጸሎትም በመትጋት አንድነታችሁን እውን ታደርጉ ዘንድ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዐለ ደብረ ዘይት ያድርግልን! እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

የካቲት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉ፣ የምሕረት ጌታ የብርሃን አባት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“እስመ ኅሊናሁ ለነፍስትነ ፀሩ ለእግዚአብሔር ውእቱ
የሥጋችን አስተሳሰብ የእግዚአብሔር ጠላት ነው።”
(ሮሜ 8፥7)

እኛ ሰዎች ከሁለት ነገሮች የተገኘን ውሕድ ፍጥረቶች መሆናችን ከእግዚአብሔር ቃል በተጨማሪ በየዕለቱ የምናሳየው እርስ በርሱ የተቃረነ ድርጊት ተጨባጭ ማስረጃ ነው፤ ከዚህ አኳያ ሰው ሁሉ ከአንድ ምንጭ የተገኘ በመሆኑ ከመንፈስና ከሥጋ የተገነባ ድንቅ ፍጡር ነው፤ ሥጋና መንፈስ በሰው ዘንድ በተዋሕዶ ይኑሩ እንጂ ፍጹም ስምምነት ያላቸው ነገሮች ግን አይደሉም፤ ይልቁንም በመካከላቸው ከባድ ተቃርኖ እንዳለ “እስመ መንፈስኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ ሥጋ ወሥጋኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ መንፈስ; መንፈስ ሥጋ የማይወደውን፣ ሥጋም መንፈስ የማይወደውን ይወዳል” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡

የሁለቱ ነገሮች ተቃርኖ በዚህ ብቻ የሚያበቃም አይደለም፤ ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ አበጋዝና የሚያስገኙት ውርስም አላቸው፤ የሥጋዊ ምኞት ምንጭ ዲያብሎስ ሲሆን በባሕርዩ ለእግዚአብሔር የማይገዛ ስለሆነ የእግዚአብሔር ጠላት ነው፤ ለተከታዮቹም ሞትን ያወርሳል፤ የመንፈሳዊ ምኞት ምንጭ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ነውና በባሕርዩ ለእግዚአብሔር ታዛዥ; ተገዥና የዘለዓለም ሕይወትን የሚያወርስ ነው፤ ከዚህ አንጻር ሰው ለሥጋዊ ምኞቱ ተገዢና በሥጋዊ ፈቃድ ተሸናፊ በሆነ ጊዜ ለሥጋውና ለነፍሱ የሚተርፍ ጒዳትን እንደሚያከማች፣ በአንጻሩ ደግሞ ለመንፈሳዊ ምኞቱ ተገዢና ተባባሪ በሆነ ጊዜ ለሥጋውና ለነፍሱ የሚተርፍ ሀብተ ሕይወትን እንደሚያፈራ ዛሬም ግልጽ ሆኖ ይታወቃል፤ ለዚህም የቀዳማዊ አዳም ሥጋዊ ዝንባሌና መንበርከክ፣ የዳግማዊ አዳም (ክርስቶስ) መንፈሳዊ ምከታና ድል ማድረግ ተጨባጭ ማረጋገጫዎቻችን ናቸው፡፡

ቀዳማይ አዳም የዲያብሎስን ምክር ሰምቶ፤ ጣዕመ መብልዕን ሽቶ፣ ለፈቃደ ሥጋው አድልቶ፤ በራሱና በልጆቹ ነፍስና ሥጋ ላይ የሞት ውርስን አውርሶአል፤ ዳግማይ አዳም የተባለ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በተቃራኒው ጣዕመ መብልዕን ትቶ፣ በኀይለ መንፈስ ተዋግቶ ፣ የዲያብሎስን ፈተና በእግዚአብሔር ቃል መክቶ የአሸናፊነትና የዘለዓለማዊ ሕይወት ርስትን ለእኛ ለልጆቹ አውርሶአል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ የዚህ ዓለም ወዳጅ የእግዚአብሔር ጠላት ነው ሲል ሜዳው ሸንተረሩ፣ ሣሩ ደንጊያው ወይም ከተማው ገጠሩ ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም በዚህ ዐውደ ሐሳብ ዓለም ተብሎ የተገለጸው ፍሬ ሐሳብ እግዚአብሔርን የሚቃወም ማንኛውም ፈቃደ ሥጋ ነው፤ ይህ ዐይነቱ ፈቃደ ሥጋ ለእግዚአብሔር የማይገዛ ብቻ ሳይሆን ጠላትም ነው፤ በሰው ላይም ሞትን የሚያመጣ ነውና “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ” ተብሎ ተጻፈ።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

በነገው ዕለት የምንጀምረው የጾም ሱባዔ ሁለት ዐላማ ያለው ነው፤ ይኸውም አንደኛው ጌታችን በመዋዕለ ጾሙ ፈቃደ ሥጋንና የእርሱ አበጋዝ የሆነው ዲያብሎስን በፈቃደ መንፈስ ድል ማድረጉን ለማሰብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በሥራው ሁሉ እንድንመስለው ባስተማረን መሠረት እኛም በኀይለ ጾም መሣሪያነት እየታገዝን እንደሱ ፈቃደ ሥጋንና ዲያብሎስን በመዋጋት የፈቃደ ነፍስ ልዕልናን ለማረጋገጥ ነው፤ ይህንም ውጊያ በድል ለማጠናቀቅ የሥጋ መሣሪዎችን ጠንቅቆ ማወቅ አስፈላጊ ነው፤ ሥጋ ነፍስን የሚወጋባቸው የታወቁ መሣሪያዎች አሉት፤ ቅዱስ መጽሐፍ እነሱን እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጦአቸዋል።

ይኸውም­ ዝሙት፣ ቊጣ፣ ርኵሰት፣ አድመኛነት፣ መዳራት፣ መለያየት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ መናፍቅነት፣ ምዋርት፣ ምቀኝነት፣ ጥል፣ መግደል፣ ክርክር፣ ስካር፣ ቅንዐት፣ ዘፋኝነትና ይህንን የሚመስል ሁሉ ይላል፤ በማያያዝም እንደነዚህ ያሉትን የሚያደርጉ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ብሎ ይደመድማል፡፡ ዲያብሎስ እነዚህ የጥፋት መሣሪያዎቹን ተጠቅሞ አዳምንና ሔዋንን ባሳተበት ስልት ሥጋችንን በማስጐምጀትና ጠቃሚ ነገሮች እንደሆኑ አስመስሎ እነሱን በኅሊናችን ውስጥ በማቀጣጠል ወደ መሥገርተ ሞት ወጥመዱ ይከተናል፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በየጊዜው የምንጾመው እነዚህ የሥጋና የዲያብሎስ የሆኑ መሣሪያዎችን የመንፈስ መሣሪያዎች በሆኑ፡- በፍቅር፣ በቸርነት፣ በመንፈሳዊ ደስታ፣ በእምነት፣ በሰላም፣ በበጎነት፣ በትዕግሥት፣ በየዋህነትና ራስን በመግዛት ለመሰባበርና ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ነው፡፡

ከላይ እንደ ተመለከትነው የመንፈስ ቅዱስና የዲያብሎስ መሣሪያዎች ምን ምን እንደሆኑ ተገንዝበናል፤ በአሁኑ ጊዜ በአጠቃላይ በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በሀገራችን ያለውን የሁለቱ አሰላለፍ ምን እንደሚመስል ማስተዋሉ የሚከብድ አይሆንም፤ ሰው ሁሉ መንፈሳዊ ዕውቀቱን ተጠቅሞ፣ የዲያብሎስ መሣሪያ የሆኑትን ጥሎ፣ የመንፈስ ፍሬዎች ወይም መሣሪዎች የሆኑትን አንግቦ፣ ፈቃደ ሥጋንና ዲያብሎስን ቢመክት ኖሮ አሁን እየሆነ ያለው ሁሉ አይከሠትም ነበር፤ ነገር ግን “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ፤ ሰው በተፈጥሮ አዋቂና ክቡር ሆኖ ሳለ በተሰጠው ዕድል መጠቀም አላወቀበትም” ተብሎ በእግዚአብሔር ቃል እንደተገለጸው ያለመታደል ጉዳይ ሆኖ ሊሆን አልቻለም፤ ይሁንና ተወደደም ተጠላ በመጨረሻው ቀን ማለትም በጌታ ቀን ዲያብሎስና መሣሪያዎቹ በኀይለ መንፈስ መሸነፋቸው ብቻ ሳይሆን ከገጸ ምድር ሙሉ በሙሉ መጥፋታቸው አይቀሬ መሆኑ ቅዱስ መጽሐፍ ስለሚነግረን እስከዚያውም ቢሆን በሚጠፋ ነገር ከምንጠፋፋ የማይጠፉትን የመንፈስ መሣሪያዎችን ጨብጠን በሕይወት መኖርን ምርጫችን ብናደርግ ከጥበበኞች ሁሉ የምንበልጥ ጥበበኞች እንሆናለን፡፡

ለመጪው ሕይወት ብቻ ሳይሆን አሁን ላለንበት ጊዜያዊ ሕይወትም ቢሆን፡ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥል ይልቅ ፍቅርን፣ ከቊጣ ይልቅ ትዕግሥትን፣ ከመናፍቅነት ይልቅ እምነትን፣ ከርኵሰት ይልቅ ቅድስናን፣ ከመግደል ይልቅ ማዳንን፣ ከአድመኝት ይልቅ ሰላምን፣ ከስካር ይልቅ ራስ መግዛትን፣ ከዘፋኝነት ይልቅ ዘምሮን እጅግ እንደሚበልጥ ሁላችንም እንስማማበታለን፤ ነገሩ እውነትና ዘላቂ ሐቅ ስለመሆኑ ከስምምነታችን የበለጠ ማስረጃ ሊገኝ አይችልም፤ ስለሆነም በዚህ የጾም ወቅት እነዚህን ለመተግበር ክርስቲያኖች በቀንም፣ በሌሊትም ሊተጉ ይገባል፡፡

በመጨረሻም፡ መዋዕለ ጾም ማለት ፈቃደ ሥጋን ጆሮ ዳባ ልበስ ብለን ለፈቃደ ነፍሳችን ብቻ የምንታዘዝበት፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ ብቻ እየሰማን ለእርሱ የምንገዛበት ጊዜ ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅም ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት መሆኑን ተገንዝበን ከሁሉ በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ነዳያን ወንድሞቻችንን በመመገብና በማልበስ ሁሌ ከጎናቸው ሳንለይ ወርኀ ጾሙን እንድናሳልፍ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ወርኀ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን፡

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡