ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል በተባለውን የሰው መግደልና መፈናቀል እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል

ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል በተባለውን የሰው መግደልና መፈናቀል እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል፣ ሲኖዶሱ በኢትዮጵያ ሶማሌ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት 4 ሚሊዮን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት 4 ሚሊዮን ብር ርዳታ እንዲሰጥ የተወሰነውን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትኖሩ፣ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሆይ!!

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅድመ ታሪክ ዘመን አንሥቶ ህልውናዋ፣ ታሪክዋ፣ ገናናነትዋ ታላቅነትዋና ሥልጣኔዋ በዓለም ዘንድ የታወቀ ታላቅና አኵሪ ሀገር ናት፤ ለታላቅነትዋ ዐቢይ አስተዋፅኦ ካበረከቱት መካከል በፈሪሀ እግዚአብሔርና በአምልኮተ እግዚአብሔር የተገነባ፣ ስለ ሃይማኖቱና ስለ አንድነቱ ፍንክች ሳይል በአንድነትና በጽናት የቆመ ሕዝብ ያላት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የሃይማኖት ሥርጸት የዜጎች የማይበጠስ አንድነትና ማኅበራዊ መስተጋብር ጸጋ ሀገሪቱ ከውጭ ወራሪዎች የሚሰነዘርባትን ማንኛውንም ጥቃት በሚገባ እየመከተች እስካሁን በኀያልነት ዘልቃለች፡፡

በዚህም የዓለም ሁሉ ጸሐፍትና ምሁራን ብቸኛ የሆነ አንጸባራቂ ታሪኳን ማንነትዋንና ነፃነትዋን በደማቅ ቀለም ጽፈውላታል፣ በቀላሉ ተዝቆና ተተንትኖ የማያልቅ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ታሪኳ በዓለምና በአፍሪካ ጎልቶ ሊወጣ የቻለው ሕዝቦቿ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቀለም፣ በመልከዐ ምድር፣ በባህልና በጥቃቅን ምክንያቶች ለሚፈጠሩ ልዩነቶች ቦታ ሳይሰጡ ዘላቂና የጋራ ጥቅማቸውን ለሚያረጋግጥ ሀገራዊ አንድነት ከማንም በፊት ቅድሚያ ሰጥተው እንደ ችቦና እንደ ነዶ አንድ ላይ በመቆማቸው እንደሆነ ታሪካችን አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡ በተለይም በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሀገራችን ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ አልፎም ለመላው አፍሪካና ለመላው የዓለም ጥቍር ሕዝቦች ተምሳሌት የሚሆን አንጻባራቂ የልማት፣ የአንድነትና የመልካም አስተዳዳር ስኬት ታረጋግጣለች ብሎ የዓለም ሕዝብ ተስፋ በጣለባት ወቅት፣ ዜጎች ለታሪካቸው፣ ለባህላቸውና ለሃይማኖታቸው የማይመጥን ሰብእና እንደዚሁም በዓለም ሕዝብ ፊት ኀፍረትና ፀፀት የሚያስከትል ተግባር እንዳይፈጽሙ በእጅጉ መጠንቀቅ አለባቸው፤

እንደሚታወቀው ሁሉ በመንፈሳዊው ዓለም ካልሆነ በቀር እኩያት ፍትወታት ባየሉበት በዚህ ዓለም እንከን የለሽ ሥራና ሠሪ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፤ በመሆኑም ስላለፈው እንከን ስናቀነቅን የወደፊቱ ዕድል እንዳያመልጠን ሁሉንም ነገር በይቅርታና በፍቅር ማለፍ አማራጭ የሌለው ጥበብ እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በውል ሊገነዘቡት ይገባል፣ሀገራችን ኢትዮጵያ በጥቍሮች ዓለም፣ በአፍሪካና ይልቁንም በምሥራቅ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና እንድትታይ ያደረጋት ምሥጢር የሃይማኖቷ ጸጋና የሕዝቦችዋ አንድነት እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ወጣት ልጆቻችን ከልብ እንድትገነዘቡት አጥብቀን እንመክራለን፤

ታላቅና ገናና የሆነች ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንደ ታፈረች፣ እንደተከበረችና ኀያል እንደሆነች እንደጥንቱ እንድትቀጥል የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ በእርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ ነገር ግን መንገዱን ስተን ወደ ገደል እንዳንገባ በማስተዋልና በአርቆ አሳቢነት መጓዝ ይገባናል፤ በዚህ ዙሪያ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና አርቲስቶች ያለመታከት ሌት ተቀን መሥራት ይኖርባችኋል፤ ወጣት ልጆቻችንም በማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ፣ በአፍራሽ የቅንብር ወሬና በስሜት ሳትሸነፉ የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ከወዲሁ በመመልከት ከሁሉም በላይ ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት በጽናት እንድትቆሙ በሚወዳችሁና በምትወዱት በእግዚአብሔር ስም አጥብቀን አደራ እንላችኋለን፡፡

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች!! ለዚህች ሀገር መነሻም መገስገሻም ሆና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት እያስተናገደች የኖረችና ያለች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንደሆነች ማንም ኢትዮጵያዊ አይስተውም፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገሪቱ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቅርስ፣ የዕውቀት፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ጒልላት የሆነች፣ በማንም ይሁን በማን ላይ እጅዋን ጭና የማታውቅ፣ ሁሉንም በሰላምና በፍቅር እንደዚሁም በእናትነት መንፈስ የምትመለከት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በእርስዋ ላይ እየተሠነዘረ ያለው አሳፋሪ፣ ዘግናኝና አሠቃቂ ድርጊት የናት ጡት ነካሽ የሚያስብል፣ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል፣ በእግዚአብሔር አምናለሁ የሚል ቀርቶ ሃይማኖት የለሽ ፍጡር የማይፈጽመው ድርጊት በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል፡፡

ይህ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንን ያሸማቀቀ ድርጊት ነው፤ በዚህ አሳዛኝና አሠቃቂ ድርጊት ለጊዜው የታወቁት ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት ከነሙሉ ንብረታቸውና ሀብታቸው በቃጠሎና በዝርፊያ ወድመዋል፤ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና፣ ጽ/ቤቱና መኪናው፣ እንደዚሁም የቤተክርስቲያኗ ት/ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ ንብረታቸውም ተዘርፈዋል፡፡ ለጊዜው የታወቁ አምስት ካህናት በአሠቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ሰባት ካህናትም በጽኑ ተደብድበው ሞተዋል ከተባሉ በኋላ ተርፈው በሕክምና እየተረዱ ይገኛሉ፤ ገና ቊጥራቸው ያልታወቀ ምእመናንም በተመሳሳይ ሁኔታ ተገድዋል፣ ተደብድበዋልም ሀብታቸውና ንብረታቸውም ተዘርፎአል፡፡ ይህ ኢሰብኣዊ የሆነ አሠቃቂ የጭካኔ ድርጊት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን በሌሎች አብያተ ሃይማኖትም እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያንና በዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከባድ ከመሆኑ አንጻር ሁኔታውን በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በተቻለው ሁሉ የተቸገሩትን፣ የሚላስ፣ የሚቀመስ እንዲሁም የሚለበስ ያጡትን ወገኖችን ለመርዳት የበኩሉን በማድረግ እንዲረባረብ፣ የፈረሱትንና የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት እንደገና መልሶ ለመሥራት በሚደረገው ርብርብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ቤተ ክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ስም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

በመጨረሻም፡ የዜጎች ደኅንነት፣ የሀገር ሰላምና አንድነት የሚጠበቀው ገደብ የለሽ መብትና ነፃነት በመስጠት ብቻ ሳይሆን የሕግን የበላይነት በማስፈንና ሥነ ሥርዐትን በማስጠበቅ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና መንግሥት ለብሔራዊ መግባባት ሲል የሚከተለው ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት የሀገሪቷን አንድነትና የዜጎችዋን ደኅንነት በከባድ ሁኔታ እየሸረሸረ ስለሆነ ሳይውል ሳያድር የዜጎችን የመኖር ዋስትና፣ የሃይማኖትን ልዕልና በሕጉ መሠረት በመጠበቅ ፀጥታውን እንዲያስከብር፣ ኦርቶዶሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ትማፀናለች፤ እንደዚሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ኀይሎችና ሕዝቡም ከሁሉ በፊት ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ ሰጥታችሁ እንድትሠሩ፣ ወጣት ልጆቻችንም በስሜት ተገፋፍታችሁ በወገን ላይ መጨከንን ከዛሬ ጀምሮ እርም ብላችሁ እንድታቆሙ፣ መንግሥት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሚሏችሁን ብቻ እየሰማችሁ ሀገር የምታድግበትን አንድነትዋ የሚጠበቅበትንና ሰላምዋ የሚጠናከርበትን ሥራ ብቻ ለመሥራት በማስተዋል እንድትተጉ አባታዊ መልእክታችንን በድጋሚ በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የጾመ ፍልሰታ ሙሉ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት የቅድስት ድንግል ማርያም ተዝካረ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ወአፅገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን
የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው፤”
(ሉቃ. 1፥53)

ይህ ቃል፤ መንፈሰ እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ልሳን በኩል ያስተላለፈው መለኮታዊ ቃል ነው፡፡ የቃሉ መሠረታዊ መልእክት በድንግል ማርያም ማሕፀን ካደረው ከጌታችን ከመድኀኒታችንና ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ አድኅኖ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፤ ረኃብ የሚለው ቃል ሰፋ ተደርጎ ሲታይ በረኃበ ሥጋ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅም ሆነ በሌሎች ሕያዋን ፍጡራን የሚከሠት የመሠረታዊ ፍላጎት ዕጥረትን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም የዕውቀት፣ የጤና፣ የመንፈሳዊ ሕይወት፣ የሞራል፣ የሰላም አለመረጋጋትን የሚያከስትሉ የህልውና ጣዕም ዕጥረቶችን በሙሉ ሊያመለክት ይችላል ማለት ነው፡፡

በተለይም በአምሳለ እግዚአብሔርና፣ በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረውና ሕያው መንፈስ ያለው የሰው ልጅ ከመንፈሳዊ ሕይወት ርቆ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኝነት ሲያቋርጥ ከባድ የሆነ መንፈሳዊና ሞራላዊ ረኃብ ያጠቃዋል፡፡ ይህ ዐይነቱ ረኃብ ከሁሉም የባሰ ጎጂ ረኃብ ነው፤ ሰው በአምላኩ እስካመነ ድረስ በጸሎትና በሃይማኖት ፈጣሪውን ተማፅኖ በፈጣሪ በረከት ተግባሩ ሰምሮለት ረኃበ ሥጋንና ሌሎች መሰል ዕጥረቶችን ሊያስወግድ ይችላል፡፡ ከእግዚአብሔር በመለየቱ የሚያጋጥመው ረኃበ ነፍስ ግን በዚህ ዓለም ባለበት ጊዜ ጎልቶ ባይታይም በወዲያኛው ዓለም የከፋ ረኃበ ነፍስ ያገኘዋል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ ትጠግባላችሁና፤ እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ ትራባላችሁና” ሲል ያስተማረው ረኃበ ሥጋውን ከፅጋበ ነፍስ፣ ፅጋበ ሥጋን፣ ከረኃበ ነፍስ አዟዙሮ በማነፃጸር እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ከረኃበ ሥጋ ይልቅ ረኃበ ነፍስ እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ እናስተውላለን፤ በሌላ በኩል ረኃብ ማለት የእግዚአብሔርን ቃል ያለመስማት እንደሆነ ሲያመለክት እግዚአብሔር በነቢዩ አድሮ “ረኃብሰ ኢሰሚዐ ቃለ እግዚአብሔር፣ ረኃብ ማለት የእግዚአብሔርን ቃል ያለመስማት ነው ብሎአል” ከዚህ አንጻር መንፈስ ቅዱስ ባደረባት እግዚአብሔር ወልድ ማሕፀኗን መንበረ መንግሥት ባደረገላት በቅድስት ድንግል ማርያም ልሳን የተጠቀሰው ረኃብና ጽጋብ የትኛው ነው ብለን ብንጠይቅ መልሱ ከባድ አይሆንም፤ እግዚአብሔር የፍጥረቱን ረኃበ ሥጋ የማይሻ ሩኅሩኅ አባትና ፈጣሪ ቢሆንም ከሥጋዊ ይልቅ ለመንፈሳዊ፣ ከጊዜያዊ ይልቅ ለዘለዓለማዊ ሕይወት እንደሚያደላ የታወቀ ነው፤ ለሰው ልጅ ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ ወደዚህ ዓለም የመጣበት መሠረታዊ ዐላማም ይኸው ነው፤ ከዚህ አኳያ ከላይ የተጠቀሰው በረከት ከበረከተ ሥጋ በላይ የሆነ በረከተ ነፍስን የሚያመለክት ነው፡፡

ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት በዓለም ሁሉ ተንሰራፍቶ የነበረውና መድኀኒት ያልተገኘለት የምግብ ረኃብ ሳይሆን የመንፈሰ ልደትና የመንፈሰ ሕይወት ዕጦት ነው፤ ይህ ዕጦት ነው ረኃብ ተብሎ የተገለጸው፣ ቅዱስ ገብርኤል ሊያበሥር የመጣውም መንፈሳዊ በረከትን፣ እርሱም ከእግዚአብሔር ጋር በሐዲስ ልደት መገናኘትን፣ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚናኝበት ዕድል ከእግዚአብሔር የተዘጋጀ መሆኑን በቅድስት ድንግል ማርያም በረከት በኩል ሊያበሥር ነው፤ የበረከቱ መጀመሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗን ለማሳየትም እግዘአብሔር ካንቺ ጋር ነው በማለት ገልጾታል፡፡ እንግዲህ ትልቁ ረኃብ እግዚአብሔርን ማጣት፣ ትልቁ በረከት ደግሞ እግዚአብሔርን ማግኘት እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም በፊት የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ ፣ ዓመተ ኵነኔ በመሆኑ በእነዚያ ዘመናት የነበረው ትውልድ ሁሉ ከረኃበ ሥጋ ይልቅ መንፈሳዊ ረኃብ ያጠቃው ነበረ፤ በምድራዊ ሕይወቱም በአምልኮ ጣዖት፣ በክሕደት፣ በብልሹ ሥነ ምግባር፣ በቀቢጸ ተስፋ፣ በጽልመተ አእምሮ የተዋጠ፣ በሰማያዊ ሕይወቱም በኵነኔ ነፍስ በግዞት ከሰይጣን ሠራዊት ጋር በሥቃይ የሚማቅቅ ነበረ፤ ይህ ሁሉ በግዙፉ ዓለም ከሚታወቀው ረኃበ ሥጋ የባሰ ነበረ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ የተናገረችው ረኃብ እሱ ነው፤ በረከቱም በማሕፀኗ የተሸከመችው ምሉአ ጸጋ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ከበረከቱ አጠገባቸው የተባሉትም በእሱ አምነው የተጠመቁ፣ በደሙ ነጽተው ከሱ ጋር የተዋሐዱ ናቸው፤ ይህንን ያደረጉ ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር በትክክል ተገናኝተዋል፤ በረከቱም በምልአት አድሮባቸዋል፡፡ ምድራዊ ረኃብ እንኳ ቢያጋጥማቸው በሰማያዊ ተስፋ ተሞልተው ሁሌም እንደጠገቡ፤ በሰማያዊውም ዓለም ከእርሱ ጋር ነግሠው ከብረው በደስታ ይኖራሉ።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

የቅድስት ድግል ማርያም በዓለ ፍልሰታን በማሰብ፣ በይቅርታ፣ በምሕረት፣ በጸሎት፣ በአምልኮት፣ በስግደት፣ ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል፣ የምንጾመው ጾም ዋና ዐላማው ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ነው፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ግንኑነት ሲኖረን የሚጐድለን ነገር እንደሌለ እናውቃለንና፤ ቅዱሳን ሐዋርያት በዚህ ወቅት ጾመው እግዚአብሔርንም ቅድስት ድንግል ማርያምንም አግኝተዋል፤ እኛም እግዚአብሔርንም ቅድስት ድንግል ማርያምንም ለማግኘት እንጾማለን እናገኛቸውማለን ለዚህም ምስክራችን ግዙፉ ንጻሬ ዐይን ሳይሆን ረቂቁ ንጻሬ መንፈስ ነው፤ ፈጣሪዋን የምትከተል መንፈስ ምን ጊዜም ነፃና ደስተኛ ናት፤ ስለዚህ ይህንን ጾም ወጣት ሽማግሌ፣ ሕፃን ዐዋቂ ሳይባል ሁሉም እግዚአብሔርንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በመሻት ፍቅርንና መታዘዝን፣ ሰላምንና አንድነትን እንደ ሸማ በመጎናጸፍ ሁሉም ሊጾመው ይገባል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ እየታየ ያለው ተስፋ ሰጭ የሆነ የሀገራችን ሰላምና የመግባባት መንፈስ ሥር እንዲሰድ አጥብቀን ወደ ፈጣሪ የምንጮኽበት ጾም ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉና ጕዳት የደረሰባቸው ወገኖችን እንደዚሁም በሌላ ምክንያት የኑሮ እጥረት ያጠቃቸው ድሆችን ካለን ከፍለን በመመገብና በማልበስ ለእግዚአብሔር እንታዘዝ፤ ለወገኖቻችንም እንድረስ ፡፡

የዘንድሮ የጾመ ማርያም ሱባዔን ልዩ የሚያደርገው ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የቆዩ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መከፋፈሉ ቀርቶ በሰላምና በአንድነት ሆነው ሃይማኖታቸውን ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን ለማገልገል በተስማሙበት ማግስት፣ እንደዚሁም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በአንድነት የነበሩትና ተለያይተው የማያውቁት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በሰላም ለሰላም ተባብረው ለመኖር ቃል በገቡበት ታሪካዊ ወቅት ላይ የሚጾም ጾም መሆኑ ነው፤ ይህ ለሕዝባችን ለሀገራችን ለሃይማኖታችን የተሰጠ ታላቅ አምላካዊ በረከት ነው፤ ይህ የሰላም የፍቅርና የአንድነት በረከት በከፍተኛ ጥንቃቄ ልንጠብቀው ይገባናል፤ ከእንግዲህ ወዲህ የሚፈናቀል ሕይወቱንም ሆነ ንብረቱን የሚያጣ ሰው እንዳይኖር፣ ያለፈው ይብቃ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተወልዶ ያደገባትና እናት ሀገሬ ናት ብሎ የሚኮራባት ኢትዮጵያ የሥጋት አገር እንዳትሆንበት አጥብቀን እንሥራ፣ እንጸልይ፣ እናስተምር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰላም፣ ከፍቅር፣ ከአንድነት፣ ይቅር ይቅር ከመባባል የተሻለ አጀንዳ እንደሌለ ዐውቆ ሰላም የየቀኑ ሳይሆን የየሰዓቱ አጀንዳ አድርጎ እንዲሠራ ከአደራ ጋር መንፈሳዊና አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም ጾም ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ፣ በጎዴ ከተማና በሌሎችም ከተሞች በደረሰው አሠቃቂ ግድያና ዘረፋ እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል

ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ፣ በጎዴ ከተማና በሌሎችም ከተሞች በደረሰው አሠቃቂ ግድያና ዘረፋ ምክንያት በየመጠለያው በረኃብ፣ በጽምና በዕርዛት ለሚሠቃዩ ካህናትና ምእመናን መንግሥት ተፋጥኖ እንዲደርስላቸውና የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ በአጽንዖት አሳሰበ፡፡ ማሳሰቢያውን ቅዱስነታቸው እንደሚከተለው አስታውቀዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረዥም የታሪክ ጒዞዋ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በእኩልነት ደረጃ ስታገለግል የኖረች እናት ቤተ ክርስቲያን ናት አሁንም አገልግሎቷን ከመፈጸም የተገታችበት ጊዜ የለም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች ሀገር ብትሆንም ሕዝቦቿ በሃይማኖት፣ በጎሣና በቋንቋ ሳይለያይዩ ሀገርን የሚወር፤ ነፃነትን የሚገፍፍ ጠላት በሀገር ላይ ሲነሣ አንድነቱን አጠናክሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የሀገሩን ነፃነት ሲያስከብር ኖሮአል፡፡ በተለይም የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች በወንድማማችነት ተሳስበው የኖሩት አንዱ የሌላውን እምነትና ሥርዐት ሳይነካ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት በመነጨ መተሳሰብና እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕግና መንግሥት ባለበት ሀገር በአንዳንድ የክልልና የዞን መስተዳድሮች በባሌ ጎባ፣ በጣና በለስ፣ በኦሮምያ ክልል፣ አሁን ሰሞኑን ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በአንዳንድ ቦታዎች በተለያየ ምክንያት በሚፈጠር የርስ በርስ ግጭት መነሻነት በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረ፣ በቅዱስ ረድኤቱ የከበረ፣ ሕያዊት፣ ነባቢት ነፍስ የተዋሐደችው፣ ፍጹም አእምሮና ዕውቀት የተሰጠው የሰው ነፍስ እየጠፋ እናያለን፤ ይልቁንም በሱማሌ ክልል ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ካህናት ተገድለዋል፤ ንብረት ተዘርፎአል፡፡ ዛሬ በመላ ሀገራችን ከመሐል ኢትዮጵያ እስከጠረፍ ዳርቻ ባሉት ክልሎችና የመስተዳድር ዞኖች ሰላም፣ ፍቅር አንድነት መከባበርና መቻቻል፤ እየተደማመጡና እየተናበቡ መሥራት በበለጠ እንዲዳብርና እንዲሰፍን የአመራር መርሕ በስፋትና በጥልቀት እየተሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ ለሚተላለፈው መመሪያና የሰላም መልእክት ትኵረት ባለመስጠት የሀገርና የወገን ፍቅር ስሜት የተለየው የጭካኔ ሥራን መሥራት ከኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚጠበቅ ተግባር ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ይህ መወገዝ ያለበት የዐመፅ ተግባር አብረው በኖሩ ወንድማማቾች መካከል የፈጠረው ግጭት፤ አለመግባባትና መቃቃር በዚህ ሳቢያ እየተካሄደ ያለው መጠፋፋት እየሰፋና እያደገ ወደሌላ ከመሸጋገሩ በፊት ከወዲሁ ታስቦበት ተፋጥኖ ይገታ ዘንድ የባለ ድርሻ አካላት ሁሉ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የተፈጠረው ችግር ተወግዶ የተሟላ ሰላምና መረጋጋት እውን እስከሚሆን ድረስ የመፍትሔው አካል በመሆን የሚቻላትን ሁሉ በመፈጸምና በማስፈጸም ያለባትን ሀገራዊ ግዴታና ኀላፊነት በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅባታል፡፡ የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰላምና መረጋጋት በሚጎዳ መንገድ የሚሄዱ ግለሰቦች ሁሉ እንዲስተካከሉ ከእግዚአብሔር ሕግ አኳያ ምክርና ትምህርት በመለገስና በማስተላለፍ ዓላማዋና ዐይነተኛው ተግባርዋ እንደሆነም ማስገንዘብ ይኖርባታል፡፡ ስለዚህ ሰላምና መረጋጋት የሚመነጨው ከቤተ ሰብና ኅብረተ ሰብ ስለሆነ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲመክሩ፣ እንዲገሥጹ እንዲያስተምሩ ያስፈልጋል፡፡

ኅብረተሰቡም በዘር በሃይማኖትና በጎሣ ሳይለያይ በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢ እየተሰማና እየታየ ካለው መጥፎ እንቅስቃሴ ራሱን እንዲገታ እንዲቈጣጠር፤ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም የመልካም ሥነ ምግባር መሠረት በሆነችው ሀገራችን ላይ ችግሩ በተከሠተበት አካባቢ እየተገኙ ትምህርተ ወንጌል እየሰጡ የማረጋጋት፣ የማጽናናትና የማስታረቅ ሥራን እንዲሠሩ፡፡ ይህን አላስፈላጊ ግጭት ከሕዝባችንና ከሀገራችን እግዚአብሔር እንዲያርቅልን ጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ምክንያት በማድግ ሙሉ ሱባኤውን በሁሉም ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ፣ በጎዴ ከተማና በሌሎችም ከተሞች በደረሰው አሠቃቂ ግድያና ዘረፋ ምክንያት በየመጠለያው በረኃብ፣ በጽምና በዕርዛት ለሚሠቃዩ ካህናትና ምእመናን መንግሥት ተፋጥኖ እንዲደርስላቸውና የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡

ለሞቱት ወገኖቻችንም በመላ ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፤ በችግሩ ዙሪያ የሚገኙ የክልልና የዞን መስተዳድር አካላትም የገላጋይ ያለህ የሚል ሮሮ እስከሚሰማ ድረስ ሳይጠብቁ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ድንጋጌ በማክበርና በማስከበር ከመንግሥትና ከሕዝብ የተረከቡትን ኀላፊነት በብቃት እንዲወጡ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አደራ እያለን ይህን መልእክት እናስተላልፋለን፡፡ ኅልፈተ ሕይወት ያጋጠማቸው ወገኖቻችንን እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበልልን ያዘኑትን እንዲያረጋጋልን፤ የተጎዱትን በምሕረቱ እንዲጎበኝልን፤ ዘላቂ ሰላምም እንዲሰጠን እንጸልያለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሲኖዶሳዊ ዕርቅ፣ በሰላምና በአንድነት ወደ ሀገራቸው መግባታቸውን አስመልክቶ መንግሥት በሚሊኒየም አዳራሽ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሲኖዶሳዊ ዕርቅ፣ በሰላምና በአንድነት ወደ ሀገራቸው መግባታቸውን አስመልክቶ መንግሥት በሚሊኒየም አዳራሽ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ መርሐ ግብሩን አስምልከተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃ ይማኖት የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

“እምይእዜሰ ይኩን ሰላም — ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ይሁን፤» ሰላም ይስፈን በመላዪቱ ሀገራችን፤ ሰላምና ፍቅር አንድነት ይስፋፋ”

ክቡር የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ፣
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡራን ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች፣
ክቡራን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ካህናት፥
ክቡራን የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፣ በአጠቃላይ በዚህ የአንድነትና የዕርቅ ማብሠሪያ መርሐ ግብር ላይ የተገኛችሁ ሁላችሁ፤

«እምይእዜሰ ይኩን ሰላም — ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ይሁን፤» ሰላም ይስፈን ተብሎ የተነገረው ቃል ለሁለት ተከፍለን በነበርነው አባቶች መካከል ዕርቅ ወርዶ እውን ሆኖ፥ ሥምረት አግኝቶ ለዚህ የአንድነታችንና የደስታችን ዕለት ማብሠሪያ ቀን በመድረሳችን ከሁሉም በላይ የሰላም የአንድነት እና የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

እንዲሁም ያለፈው የመለያየት ጊዜ አብቅቶ ሰላም ተገኝቶ ብፁዕ ወቅዱስነትዎ እና ብፁዓን አባቶች ወደምትወዷትና ስትናፍቋት ወደነበረችው ቅድስት ሀገራችሁ በመምጣት በዚህ ሁኔታ አንድ ሁነን በመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ፊት ለመቆም ያስቻለንን እግዚአብሔርን ደግመን እናመሰግነዋለን፡፡

በዚሁ ሳምንት ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ረቡዕ ዕለት ቅዱስነታቸውን ከቦሌ ኤርፖርት ተቀብለን በቀጥታ ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሄደን ሰፊ የሆነ የአቀባበል ሥነ ሥርዐት እንደተፈጸመ የሚታወስ ነው፡፡

ዛሬ ደግሞ በክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋባዥነት ተመሳሳይ የአቀባበል በዓል ለማክበር በዚህ በሚሊንየም አዳራሽ ተሰብስበናልና አምላካችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡

በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የምትገኙና እንዲሁ በዚህ ዐቢይ ጉባኤ የተገኛችሁ ሁላችሁ ሐዋርያዊት ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ጒዞዋ በሃይማኖት መሪዎቿ መንፈሳዊ ብርታት፣ በሊቃውንቶቿ ትምህርት፣ በካህናቶቿ አገልግሎትና በምእመናን ተከታዮቿ ጽንዐ-ሃይማኖት ህልውናዋና አንድነቷ ተጠብቆ መኖሩ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ታሪኳንና ባህሏን ጠብቃ ለረዥም ዘመን ልትዘልቅ የቻለችበት ዐቢይ ምሥጢር፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በነበራቸው የማይበገር የአንድነት ጽናት አንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ይሁንና ላለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች አለመግባባት በመፈጠሩ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አመራር ለሁለት ተከፍሎ ቆይቶ ነበር፡፡

እንደሚታወቀው የሰላምና የአንድነት መሪና አስተማሪ ሆና ለዘመናት ሕዝቧን ስትመራ የኖረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዘመናችን ሰላምንና አንድነትን ማጣቷ መላውን የቤተ ክርስቲያን ልጆች በእጅጉ ያሳዘነና ያሳሰብ ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ እንደቆየ እንገነዘባለን፡፡

የተወደዳችሁ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ምእመናንና ምእመናት የቤተ ክርስቲያን አባቶችን አንድነት ለማየት ዘወትር ትናፍቁ እንደነበር ቅዱስ ሲኖዶስ ይገነዘባል፡፡ ሆኖም “ጊዜ ገቢር ለእግዚብሔር” እንደተባለው ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በላይ የአገር ቤትና የውጭ ሲኖዶስ በሚል በመካከላችን የጥል ግርግዳ ሆኖ ቆይቶ የነበረው ግንብ በመፍረሱና በዚህ እናንተ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ፊት በአንድነት ስንቆም የሚሰማን ልባዊ ደስታ ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡

በእኛ በአባቶቻችሁ መለያየት ምክንያት እናንተ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ግራ ገብቷችሁ በኀዘን ለኖራችሁባቸው ዓመታት ካሳ እግዚአብሔር አምላካችን ፊቱን መልሶልን፣ በዐይነ ምሕረቱም ተመልክቶን ዕርቀ ሰላም ወርዶ በአንድነት ስንጸልይ አይታችሁ ኀዘናችሁ ወደ ደስታ እንደተለወጠ እርግጠኞች ነን፡፡

እንደሚታወቀው “ሰላም” የሚለው ቃል መልካም ነገር ሁሉ ተሟልቶና ተስተካክሎ መገኘቱን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የሰላምና የይቅርታ አምላክ መሆኑን ከዚህ ተጨባጭ ሁኔታ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ተሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ጒዞዋ በሃይማኖት መሪዎቿ ብርታት፣ በሊቃውቶቿ ትምህርት፣ በካህናቶቿ አገልግሎትና በምእመናን ተከታዮቿ ጽንዐ -ሃይማኖት ህልውናዋና አንድነቷ ተጠብቆ መኖሩን ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡

በቀጣይም ከእኛ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ከእናንተ ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን የሚጠበቀው ይኸው የትናንት አባቶቻችንን ፈለግ በመከተል ለአገርና ለወገን የሚጠቅመውን ሥራ መሥራት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም እንደምንረዳውና እንደምንገነዘበው አገራችን ኢትዮጵያን ወደ ጥንተ ታሪኳ ለመመለስ እና ዜጐች ሁሉ ከአላዋቂነት መንፈስ ተላቅቀው ለሰው ልጆች ሁሉ የሚያስፈልገው መሠረታዊ ጉዳይ ተሟልቶላቸው በአገራቸው ሠርተው ፍሬ በረከት በዝቶላቸው፣ አገር ለቅቆ ከመሰደድ፣ ከርስ በርስ አላስፈላጊ ግጭት ራሳቸውን ጠብቀው በአገራቸው አምረው ደምቀው በሰላም በአንድነት እንዲኖሩ ለማድረግ በሕዝባችንም ሆነ በመንግሥታችን በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ግቡን እንዲመታ ቤተ ክርስቲያናችን በብርቱ ትጸልያለች፤ የበኩሏን የሚጠበቅባትንም ሆነ የሚፈለግባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ናት፡፡

በተለይም በአሁኑ ጊዜ በሁላችንም የዘወትር ጸሎትና ጥረት በፈቃደ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናችን የተገኘው አንድነትና ሰላም ቤተ ክርስቲያናችን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ለምታበረክተው መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ምቹ ሁኔታ የፈጠረላት መሆኑ ተስፋችንና ራእያችንን ሰፊ ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ለዚህ የዕርቀ ሰላም ድርድር አሁን ላለንበት የሠመረ ውጤት እንድንበቃ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መላው ካህናትና ምእመናን ልጆቻችን እንዲሁም ችግራችሁ የእኛም ችግር ነው በማለት ከጐናችን በመቆም በጸሎት ስትረዱን ለነበራችሁ፣ ከዚህ እስከ ሰሜን አሜሪካ በመጓዝ ለሰላሙ ጥረት ላደረጋችሁ የሰላምና አንድነት ጉባኤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን፡፡

እንዲሁም ዕርቀ ሰላሙን በአጭር ጊዜ ውስጥ አከናውነው ለመጡት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚኖሩት ሊቃነ ጳጳሳትን በእጅጉ እናመሰግናቸዋለን፡፡ በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ቅድስት አገራችንን ለመምራት ከተሰየሙበት ጊዜ አንሥቶ በአገራችን እያሳዩት ያለው የሰላምና የአንድነት ጥሪና ተልእኮ ውጤት ጋር የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ አንዱ አገራዊ ችግር አድርገው በመመልከት መለያየቱ ተወግዶ አንድነት እንዲመጣ በምክር በማግባባትና በዕርቀ ሰላሙ ጉባኤ ላይ በመገኘት እንዲሁም ይህን የዕርቅና የአንድነት ማብሠሪያ መርሐ ግብር እንዲዘጋጅ በመፍቀድና መመሪያ በመስጠት ጭምር ያደረጉት አስተዋጽኦ ምንጊዜም ታሪክ የማይረሳው ሆኖ የሚኖር ተግባር በመሆኑ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በእናንተ በመላው ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ስም ከልብ በመነጨ ስሜት እናመሰግናቸዋለን፡፡

በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያናችንን ለዚህ የዕርቀ ሰላምና አንድነት ማብሠሪያ ቀን አድርሶ በእንዲህ ዐይነቱ ታላቅ ጉባኤ እንድንገናኝ ያደረገ ሁሉን ቻይ የቤተ ክርስቲያናችን መሠረትና ራስ የሆነውን እግዚአብሔርን እናመሰግናቸዋለን፡፡

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፣ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሃያ ሰባት ዓመታት በስደት ይኖሩ የነበሩት የኢትዮጵያ አራተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በዕርቀ ሰላም እና በአንድነት ወደ ሀገራቸው ገብተዋል፡፡

ስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ቅዱስነታቸውን የተቀበሏቸው ሲሆን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት ለአቀባበሉ ለተሰበሰቡት ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን የሚከተለውን ታሪካዊና ሐዋርያዊ የአንድነትና የሰላም ቃለ በረከት አስተላልፈዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ፡፡ (መዝ. 132፥1)

• ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 4ኛ ፓትርያርክ፣
• ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉር የመጣችሁ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣
• የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዚህ ልዩ የሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብረ በዓል ለማክበር በዚህ ዐውደ ምሕረት የተገኛችሁ እንግዶች በሙሉ።

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም፤ ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ — ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ፣ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው›› ሲል ጸልዮዋል፡፡ እኛም የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታችንን የምናስተላልፈው በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ኅብረት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከብዙ ሺህ ዘመናት ጀምራ በፈጣሪዋ ታምና ነቅዕ በሌለው ሁናቴ በሃይማኖቷ ጸንታ፤ በነፃነቷ ኮርታና ታፍራ ለሥራዋም የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት መሆኑን አስተምራ፤ ጸሎቷንና ልመናዋን ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር›› ሲል ንጉሥ ዳዊት በመሰከረላት መሠረት ዕለት በዕለት እያስታኮተችና ወደ እግዚአብሔር እየጸለየች የምትኖር ስብሐተ እግዚአብሔር በየጊዜው የማይለይባት ሀገረ እግዚአብሔር ናት፡፡

ከላይ ከፍ ብሎ በመግቢያችን “ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ — ወንድሞች በጋራ ቢኖሩ ቢተዳደሩ መልካም ነው” ሲል ነቢዩ በተነበየው ትንቢትና ባቀረበው ልመና መሠረት ታማኞቹ ለመሆን ለመረጠን ፈጣሪያችን የምንመልሰው ወሮታ ቢኖር የተቀበልነውን አምላካዊ አደራ እኛም ሠርተን ጠብቀን ተከታዮቻችንንም በፍትሕ መንፈሳዊ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ በሥርዐታችን፣ በባህላችንና በወጋችን መሠረት እንዲጸኑና እንዲሠሩ በመንፈሳዊ አገልግሎታቸውም በኩል ለቤተ ክርስቲያናችንና ለቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህን የመረዳዳትንና በአንድነት የመኖርን ሐሳብ እናስተምራቸዋለን ብለን በፍጹም ልባችን ተነሣሥተናል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛው የቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ!
ሁሉም እንደሚረዳው እኛም አሜሪካን አገር በነበርንበት ወቅት የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊና ሲኖዶሳዊው አንድነታችንን ወደቀደመው መሥመሩ ለመመለስ ብዙ ተጒዘን እንደነበር ቅዱስነትዎ ያውቀዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጠረውን ልዩነትና የአንድነት መታጣት ችግሩ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ በየቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤያት በጸሎት ያልታሰበበትና ያልተወሰነበት ጊዜ የለም፡፡ ሆኖም የሀገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን የአንድነት ህልውና በሚፈልጉ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ካህናት ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግ መቆየቱ የሂደቱ ዋነኛ ታሪክ ነው፡፡

አሁንም ደግሞ ከሁሉ በበለጠ የኤ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉት የማቀራረብና የማግባባት ሥራ ከ45 ዓመታት ወዲህ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ባልታየ ሁናቴ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት መንግሥታዊ ድጋፍ ታክሎበት ችግሩ በሚፈታበት ሥፍራ በአካል ጭምር ተገኝተው በሠሩት ሥራ የቤተ ክርስቲያናችን የአንድነት ታሪክ ዋና ባለሟል ያደረጋቸው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በሠሩት መልካም ሥራ ስታመሰግናቸውና በጸሎትም ስታስባቸው ትኖራለች፡፡

ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ አለው ተብሎ በመጻሕፍት እንደተጻፈው፤ ቅዱስነትዎና እኔ ዕድሜ ከጤና እግዚአብሔር አምላካችን ሰጥቶን ይህን ቀን ለማየት ስላበቃን ለእግዚአብሔር ልዩ ምስጋና ዘወትር እያቀረብን ወንድማማችነታችንንና መንፈሳዊ አባትነታችንን አጽንተን ከመኖር በስተቀር ሌላ ምን እንከፍለዋለን፡፡

በተለይም ቅዱስነትዎና እኔ የደረስንበት ይህ ዘመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ሰላምና ፍቅር፣ የቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መሆኑን ልጆቻችን የሀገራችን መሪዎች በአጽንዖት በአደባባይ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ለሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ሲመሰክሩና ሲናገሩ ከማየትና ከመስማት በላይ ምንስ የሚያስደስት የተቀደሰ ነገር ይኖራል፡፡

ሕዝበ እግዚአብሔር የሆነው ሕዝባችን ካልተረዳዳና ካልተመካከረ፣ በአንድ ሐሳብ ካልተጓዘ ጽኑ ፈተና ያገኘዋልና ለቤተ ክርሰቲያናችንና ለሕዝባችን እውነተኛ ጥቅም በዝግታ እየተመካከርንና፤ ሥራውን የበለጠ እያሻሻልን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንመራዋለን የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡

ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አንድነትና ፍቅር መሠረት የሆኑና በወንድማማቾች መካከል ያለውን የሐሳብና የአስተዳደር ልዩነት ታላቅ ፍቅር በተሞላበት የልጅነት መንፈስ አማካሪዎቻችን ሆነው ባላሰለሰ ጥረት ለዚህ ዕድል በማብቃታቸውና በመብቃታችን ኢትዮጵያ ዛሬም ለታሪክ የሚሠሩና የሚኖሩ የጀግኖች እናት መሆኗን ቀጣዩ ትውልድ በታሪክነት የሚጠቅሰውና የሚጽፈው ተግባር ይሆናል፡፡

ይህን የምንለው የቀደሙ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያናችን ክብርና ልዕልና የለፉበትንና የደከሙበትን ጉዳይ የሚያሰናክል ሁናቴ ከ2 ዐሥርተ ዓመታት በላይ በአንዲቷ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በአስተዳደርና በሲኖዶሳዊው አመራራችን ውስጥ የቆየውን የልዩነት ታሪክ ‹‹ወንድሞች በአንድነት ሊኖሩ፣ በአንድነት ሊመሩና ሊሠሩ በመስማማት የካህናትን፣ የምእመናንንና የወጣቶችን ዕንባ የሚያብስ ውሳኔ መወሰናችን፤

በእኛ ዘመነ ክህነትና ፓትርያርክነት መታወጁ እኛን እግዚአብሔር አምላክ የበለጠ እድለኞች ያደረገን ሲሆን ለሰማዕያኑ ካህናት፣ ምእመናንና ወራዙት እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን ይህ መልካም ብሥራት ሲነገር በሕይወታቸው ያሉት በክብር ጐልምሰው ሲታዩ፤ በሞት የተለዩት አፅማቸው በወርቅ ቀለም ተጽፎ አብቦና አፍርቶ ትተዋቸው ለሄዱት ትውልዶች የታሪክ ውርስ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡

በዚህ በዛሬው ቀን የቸርነት ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን በመገኘት የአንድ አባት የእግዚአብሔርና የአንዲት እናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ልጆች ዳግመኛ በፍቅር ማሰሪያነት ታስረንና ተጣምረን እግዚአብሔርን ማመስገንና ቤተ ክርስቲያናችንን ማገልገል መጀመራችን በምድር ሠራዊትና በሰማይ መላእክት ጭምር ታላቅ ደስታ እንደሆነ እምነታችን የጸና ነው፤ እግዚአብሔርንም ዕጹብ ድንቅ ብለን ከማመስገን በላይ ምን እንላለን፡፡

አሁንም ደጋግመን የምንለው ለዚህ ዋና ዓላማ የእርስ በእርስ መመካከርን፣ መግባባትን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታንና አንድነትን፣ የሚጠይቅ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ለምንመራቸውና ለምናገለግላቸው ሕዝበ ክርስቲያን ጉዳትና ጥቅሙን እያመዛዘን የምንመክርበት፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ላለችው ለቤተ ክርስቲያናችን የሰላምና የአንድነት አስተዳደር የምንናስቀጥልበት ቀን ላይ መሆናችን የቅዱስ ሲኖዶስ የወል የሰላምና የፍቅር ድል የተበሠረበት ዕለት ነው፡፡ የፍቅርና የሰላም የአንድነት ጠላት የሆነው ዲያቢሎስ በአደባባይ የተረታበት ዕለት መሆኑንም የምንናገረው በዚሁ ዕለት ነው፡፡

ከዚሁ ጋር የማይዘነጋው ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ቅዱስነትዎና እኔ በተለይ በእግዚአብሔር ተመርጠንና ተጠርተን በ3ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ በአንድ ዕለት ተቀብተን በኤጴስ ቆጶስነት መሰየማችን ነባሩ የመነሻ ታሪካችን ነው፡፡ በተቀበልነውም የመስቀል መሸከም አደራ ቤተ ክርስቲያናችንን ስናገለግል ቆይተን ለዚሁ ለታላቁ ክብር ላበቃን አምላክ በአንደበታችን ብቻ ማመስገን አይበቃንም፡፡ ለዘለቄታ ቀዋሚ፣ ለትወልድ ተሻጋሪ፣ ለሰው ሁሉ በፍቅር የሚደርስ እኛ ጀምረን መጨረሱን ለእግዚአብሔር የምንሰጥበት ታላቅ የአደራ መቀበያና መስጫ፤ እንዲሁም ፍቅረ እግዚአብሔር ከፍቅረ ቢጽ ጋር ተዋሕዶ የተከበረበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደራዊ ሥራ በማሻሻል፡፡ በካህናት፣ በምእመናንና በወጣቶቻችን መካከል የሠለጠነ አሠራር በመትከል ስለ ሀገራችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የምንደክም የሥራ ተከፋዮች እንሆናለን፡፡

ቅዱስ አባታችን!
በጤናና በሕይወት ጠብቆ ለዚህ ዕለት አድርሶ ወደ ቅድስት ሀገርዎ ኢትዮጵያ ለመግባት እንኳን አበቃዎ እያልኩ ንግግሬን “ኅሱ ሰላማ ለሀገር — ለሀገራችሁ ሰላምን እሹ” የሚለውን ለመፈጸም “ናሁ ሠናይ ወናሁ አዳም ሶበ ይሄልዉ አኀው ኅቡረ” ለሚለው ዘይቤ ተገዥዎች ሆነን ቤተ ክርስቲያናችንንና ተከታዮቻችንን እየመራን ሐዋርያዊ ተልእኮአችንን እንደምንፈጽም ያለንን እምነት እንገልጻለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።