ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
‹‹ወዓዲ እብለክሙ ለእመ ኀብሩ ክልኤቱ አው ሠለስቱ እምኔክሙ በውስተ ምድር በእንተ ኵሉ ግብር ዘሰአሉ ይትገበር ሎሙ በኀበ አቡየ ዘበሰማያት እስመ ኀበ ሀለዉ ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡኣን በስምየ፣ ህየ እሄሉ አነ ማእከሎሙ፤ ዳግመኛም ከእናንተ ሁለቱ ወይም ሦስቱ በምድር ላይ ስለሚለምኑት ሥራ ሁሉ ቢተባበሩ፣ በሰማያዊ አባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፤ ሁለቱ ወይም ሦስቱ በስሜ ተሰብስበው ካሉበት፣ እኔ ከዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና›› (ማቴ. 18፥19-20)

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ከጌታችን፣ ከአምላካችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠንን ዐቢይ ተልእኮ ወይም ሐዋርያዊ አገልግሎት በየተሰማራንበት ሀገረ ስብከት ስናከናውን ቆይተን፣ በዓለ ትንሣኤውን ካከበርን በኋላ፣ በቀኖና ሐዋርያት ድንጋጌ መሠረት፣ ስለቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ለመነጋገር በዚህ በርክበ ካህናት ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አንድ ላይ ስለሰበሰበን፣ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ እንዳስተማረን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የገባው ቃል ኪዳን አለ፤ እርሱም ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የተፈጸመ ጽኑ ቃል ኪዳን ነው፤ ቃል ኪዳኑም የሚከተለው ነው፤ ‹‹ሁለቱ ወይም ሦስቱ በስሜ በተሰበሰቡበት፣ እኔ ከዚያ በመካከላቸው እገኛለሁ›› ይላል፤ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው፣ ቃል ኪዳን በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈጸምና ለቃል ኪዳኑ መከበር የሁለቱንም የቃል ኪዳን አካላት ኀላፊነት በግልጽ የሚያስቀምጥ ነው፤ በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ከቅዱሳን አበው ጋር ቃል ኪዳን መሥርቶ እንደነበረ በቅዱስ መጽሐፍ በየቦታው ተጽፎ እናገኛለን፡፡

ይሁንና በዘመነ ሐዲስ ጌታችን ቃል ከገባባቸው ዐበይት ነገሮች አንዱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ነው፤ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በስመ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰበሰብ ኀላፊነት ተሰጥቶታል፤ ጌታችንም በስሙ በሚደረግ ጉባኤ እንደሚገኝ ቃል ገብቶአል፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርእሰ መንበርነት፣ ቅዱስ ፓትርያርክ በመሪነት፣ ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ዐቢይ ጉባኤ ነው፤ ቅዱስ ወይም ልዩ ጉባኤ የሚያሰኘውም ቅሉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርእሰ መንበርነት የሚገኝበት በመሆኑ ነው፤ ይህ ጉባኤ ጌታችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እንደማይለየው ሲገልጽ ‹‹ወናሁ አነ እሄሉ ምስሌክሙ እስከ ኅልቀተ ዓለም፤ እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እኔ ከናንተ ጋር እኖራለሁ›› ብሎ በቃሉ አረጋግጦአል፤ (ማቴ. 28፥20)፡፡

እንግዲህ በየጊዜው ስመ እግዚአብሔርን ጠርተን በስሙ፣ ስለስሙ ብለን፣ የምናካሂደው ቅዱስ ጉባኤ ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ያህል ታላቅ ክብርና ጽኑ የሆነ አምላካዊ ቃል ኪዳን ያለው እንደመሆኑ መጠን፣ ለደረጃው በሚመጥን ክብርና ልዕልና መካሄድ ይኖርበታል፡፡

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በአደራነት ያስረከበ ለዚህ ጉባኤ እንደሆነ በውል የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ ጉባኤ የእግዚአብሔር መንግሥት ወኪል እንደመሆኑ መጠን ድንበር የለውም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት ድንበር የለውምና፤ ይህ ጉባኤ ገደብ የለሽ መንፈሳዊ ሥልጣን ከሕያው አምላክ ሲሰጠው ‹‹ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ›› ከሚል ትእዛዝ ጋር መታዘዙ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ሥልጣን ድንበር የማይገድበው መሆኑን በግልጽ ያሳያል፤ (ማር. 16፡15)፡፡

በመሆኑም የዚህ ቅዱስ ገባኤ ሥራና ኀላፊነት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መሆኑን ሊሠመርበት ይገባል፤ ይህም በመሆኑ ነው ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም ክፍላተ ዓለም አብያተ ክርስቲያናትን ከፍታ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በማካሄድ ላይ የምትገኘው፡፡ ይሁንና አሁን የምንገኝበት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ወቅት፣ የሴኩላሪዝም አስተሳሰብ ያየለበት፤ የዓለም ሉላዊነት የበረታበት፣ የጽንፈንነትና የሽብርተኝነት መንፈስ የተስፋፋበት፣ እነዚህ ሁሉ በየፊናቸው ተሰልፈው በሃይማኖት ላይ ከባድ ተጽዕኖ የፈጠሩበት ዘመን ነው፤ ዓለም በዚህ ሥጋዊ ፍልስፍና እና ቊሳዊ አምሮት ቤተ ክርስቲያንን ለመውጋት ስትዘጋጅ እኛ የክርስቶስ ወኪሎች እንዲሁ ዝም ብለን የምናይበት ኅሊና ሊኖረን አይችልም፡፡

ቀደምት አበው “እሾህን በእሾህ” ብለው እንደተናገሩት፣ የዓለምን ጥበብ በክርስቶስ ጥበብ ለመቋቋም፣ በዓለም እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ መከታተልና ማወቅ፣ ለወደፊትም ሊያስከትለው የሚችል ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሰብኣዊና ባህላዊ ቀውስ አስቀድሞ በመተንበይ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ቃል ኀይል መጠበቅና መንከባከብ ከእኛ ይጠበቃል፡፡

በሃይማኖት ዙሪያ ያንዣበቡ እነዚህ ዓለም ዐቀፍ ተጽዕኖዎች እጅግ አስጊ ቢሆኑም፣ እነርሱን ለመከላከል ብሎም ለመቀልበስ አሁንም ቢሆን ጊዜው አልመሸም፤ በተለይም በሀገራችን ያለው ሕዝብ፣ አሁንም ምርጫው እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ በተጨባጭ የምናውቀው ሐቅ ነው፤ ይህንን ሕዝብ በሚገባ ማገልገል ከተቻለ፣ ችግሩን በሚገባ መቋቋም ይቻላል፡፡

ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑን በአግባቡ ለማገልገልና ለመጠበቅ፣ ከሁሉም በፊት የሕዝቡን ጥያቄ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ቀጥሎም ለጥያቄው ተገቢ የሆነ መልስ በመስጠት ፍጹም መግባባት መፍጠር ይገባል፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሃይማኖት መሪዎችና ከአገልጋይ ካህናት የሚጠበቀው ሁለንተናዊ አገልግሎት በሚገባ ካገኘና በሃይማኖቱ እንዲኮራ የሚያስችል ሁኔታ ከተመቻቸለት፣ ለተጠቀሱ ዓለም ዐቀፍ ተጽዕኖዎች ተንበርካኪ አይሆንም፤ ስለሆነም የኛው የጥበቃ ስልት መቀየስ ያለበት በዚሁ መንፈስና አቅጣጫ ነው፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ በአሁኑ ጊዜ የሚጠይቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤
• ሕዝቡ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ለሃይማኖት መጠበቂያ ብሎ በእምነት የሚለግሰው ገንዘብና ንብረት ከምዝበራ ተጠብቆ ለታለመለት ዐላማ ብቻ እንዲውል ይፈልጋል፤
• በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም አስተዳደር ሰፍኖ፣ አድልዎ፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ መለያየት፣ በአጠቃላይ ከሃይማኖቱ መርሕ ጋር የማይጣጣም ኋላ ቀር አሠራርና አስተሳሰብ ተወግዶ፣ የተስተካከለ ሥርዐትን ማየት ይፈልጋል፤
• ስለሃይማኖት ክብርና ህልውና ከልብ የሚቈረቈሩ፣ መልካም የሆነ ሥነ ምግባርና የተስተካከለ ሰብእና ያላቸው፣ እንደዚሁም በኑሮአቸው ሁሉ ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንደሞዴል የሚጠቀሱ ውሉደ ክህነትና ሠራተኞች እንዲመሩት ይፈልጋል፤
• ሕዝቡ ቤተ ክርስቲያን በሁሉም መስክ ጠንካራ ዐቅምን ገንብታ፣ እንደዚሁም ለሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግር ደራሽና አለሁላችሁ ባይ ሆና ማየት እንደሚፈልግ ከሚያነሣው ጥያቄ ማወቅ ይቻላል፡፡

የእኛ ተልእኮ እግዚአብሔርንና ሕዝብን ማገልገል ከሆነ፣ የሕዝቡ ጥያቄም ከሞላ ጎደል የሚታወቅ ከሆነ፣ በተሰጠን አደራና ኀላፊነት መሠረት የሕዝበ ክርስቲያኑን ጥያቄ በጽሞና አዳምጠንና ተቀብለን፣ በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌና ባሉን የቤተ ክርስቲያን ሕጎች ማእከልነት፣ ጥያቄውን የማስተናገድ ክርስቶሳዊ ግዴታ አለብን፡፡ ከሕግ የወጣ የሥራ አፈጻጸም ሲኖርም፣ ጥብቅ ክትትልና ቊጥጥር በማድረግ በወቅቱ ማረም ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል እንደመሆኑ መጠን፣ የቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችሉ ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀትና በማጽደቅ፣ እንደዚሁም በአፈጻጸማቸው ጥብቅ ክትትልና ቊጥጥር በማድረግ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን እሰየው የሚያሰኝ አሠራር ማረጋገጥ አለብን፤ ይኽ ሲሆን ብቻ ነው ሕዝቡን ከቊሳዊው ዓለም ማዕበል መታደግ የምንችለው፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ የተቀደሰ ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ ጉባኤ፣ ከልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያናችን አመራር አካላትና ከጉባኤው የሚቀርቡትን ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት በመፈተሽና በመመርመር፣ እንደዚሁም ሕጋዊና ቀኖናዊ መፍትሔ በማስቀመጥ፣ የተሳካ ውጤት ያስመዘግብ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየጸለይንና ከልብ እየተመኘን የ2008 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ፤ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ሚያዝያ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ የተነሣው፣ የሕይወት ራስና የሁሉ ፈጣሪ የሆነው፣ ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ስምንት ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!!

‹‹ዓይቴ እንከ ቀኖትከ ሞት፤ ወዓይቴ እንከ መዊዖትከ ሲኦል
ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ?››
(1ቆሮ. 15፥55)

ሞትና መቃብር የኀጢአትና የበደል ውጤቶች እንጂ የተፈጥሮ ዕድል ፈንታ ሆነው ለሰው የተሰጡ አይደሉም ፡፡ ሰው በራሱ ምርጫ ካልሆነ በቀር የሚሞት ሆኖ እንዳልተፈጠረ ቅዱስ መጽሐፍ ሲገልጽ “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” ይላል፤ (ዘፍ. 2፥16-17)፡፡ ሔዋንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መሠረት አድርጋ ስትናገር፣ ‹‹እግዚአብሔር እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም›› ብሎናል ብላ አረጋግጣለች፤ (ዘፍ. 3፥3)፡፡

ከዚህ አምላካዊ ቃል መረዳት እንደሚቻለው አዳም አትብላ የተባለውን ዛፍ ባይበላ ኖሮ አይሞትም ነበር ማለት ነው፤ ከዚህ አንጻር የሞትና የመቃብር ምንጩ ሕገ ተፈጥሮ ሳይሆን ግብረ ኀጢአት ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ በመሠረቱ ግብረ ኀጢአት የሚመነጨው ለእግዚአብሔር ካለመታዘዝ እንደሆነ ከዚህ መረዳት እንችላለን፤ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ሁለት ምርጫዎች ቀርበውላቸዋል፤ ማለትም በአንድ በኩል ‹‹መልካምና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብሉ፤ ከበላችሁ ግን ትሞታላችሁ›› የሚል የእግዚአብሔር ትእዛዝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ብትበሉ ሞትን አትሞቱም፤ ነገር ግን ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ ይከፈታሉ፤ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ ትሆናላችሁ›› የሚል የእባብ ወይም የሰይጣን ምክር ቀርቦላቸዋል ፡፡ በዚህ ጊዜ አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ገሸሽ በማድረግ የእባቡን ምክር ተቀብለው ዛፉን በሉ፤ በዚህም ከባድ በደልን ፈጸሙ፡፡ አዳምና ሔዋን በዚህ ድርጊታቸው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፈዋል፤ ምክንያቱም የእርሱን ትእዛዝ ትተው የእባቡን ምክር መቀበል እግዚአብሔርን ትእዛዝ ማቃለል እንደሆነ ግልጽ ነውና ፡፡ ኀጢአትን ወልዶ፣ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ከባድ የሞትና የመቃብር ቅጣትን ያስፈረደ በደል፣ ይህ ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝና የተሳሳተ ምርጫ ነው፤ የሞት ቅጣቱ ድሮውም ከዛፉ በበላህ ቀን ትሞታለህ ተብሎ በግልጽ የተነገረ ስለነበረ አዳም ዛፉን በበላ ቀን ቅጣቱ ወዲያውኑ ተግባራዊ ሆኖአል፤ ማለትም አዳም ‹‹ዛፉን እንደበላ ወዲያውኑ ራቁቱን ወጥቶአል›› በመራቆቱም ከእውነተኛው ልብስ ከእግዚአብሔርና ከጸጋዎቹ መለየቱ በዚህ ተረጋግጦአል፤ ሞት ማለት መለየት ማለት ነውና፡፡

በአዳም ላይ የተፈረደው ሞት ብቻ ሳይሆን ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ›› ተብሎም በሞት ላይ ርደተ መቃብርን ተፈርዶበታል (ዘፍ. 3፥19)፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሰው ከእግዚአብሔር በመለየቱ ሞትና መቃብር ተረክበውታል ፡፡ በይቀጥላልም ሰው ለእግዚአብሔር ያለመታዘዝ ልምዱን አጠናክሮ ሲቀጥልበት፣ ዲያብሎስም በኀጢአት ጦር ሰውን እየወጋ ሲገድል፣ መቃብርም ሙታንን እየተቀበለ ሲማግድ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት አለፉ፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመዓቱ አንጻር ምሕረቱን አያርቅምና በዲያብሎስ ምክር ድል ሆኖ የተሸነፈውን ሰው የሚታደግና ዲያብሎስን ድል የሚያደርግ ብርቱና ኀያል ዘር ከጊዜ በኋላ ከሴት እንደሚወለድ በመግለጽ ወዲያውኑ ተስፋ ድኅነትን ሰጥቶአል (ዘፍ. 3፥15)፤ ይህ ዘር የጠላት ዲያብሎስን ደጅ በድል አድራጊነት እንደሚወርስ “ዘርህ የጠላትን ደጅ ይወርሳል” ተብሎ፣ የምድር አሕዛብ ሁሉ በዚህ ዘር እንደሚባረኩና እንደሚድኑ ‹‹በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ›› ተብሎ በትንቢት እየተብራራ፣ እየተገለጸና እየተነገረ ቆይቶአል፤ (ዘፍ. 22፡17)፡፡ ይህ ድል አድራጊ ዘር እንደ ትንቢቱ ቃል ከሴት ማለትም ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በዚህ ዓለም ተገለጸ፤ ቅዱስ ወንጌልን እያስተማረ በዚህ ዓለም በተመላለሰ ጊዜም፡- ሕሙማን በመፈወስ፣ ዕዉራንን በማብራት፣ ለምጻሞችን በማንጻት፣ ሓንካሳንን በማቅናት አዳኝነቱን አስረዳ፡፡

በፈጣሪ ሥልጣን ካልሆነ በቀር በፍጡር ሊደረጉ የማይችሉና ከአእምሮ በላይ የሆኑትን ዐበይት ተኣምራት በማድረግ ሁሉን የሚችል አምላክ መሆኑን አሳየ፡፡ ዲያብሎስ በጾሙ ወቅት ያቀረበበትን ፈተና በመበጣጠስ፣ እንደዚሁም አንተ ሰይጣን፣ ከእርሱ ውጣ!! እያለ ከሰዎች በማስወጣት፣ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል እያለ ኀጢአትን በማስወገድ ሥልጣነ መለኮቱን ገሐድ አደረገ፤ ‹‹አልዓዛር አልዓዛር ና ውጣ ከመቃብር›› እያለ ሙታንን በማስነሣት በሞትና በመቃብር ላይ ሥልጣን ያለው መንሥኤ ሙታን መሆኑንም በተግባር አረጋገጠ፤ በአጠቃላይ በኀጢአት፣ በዲያብሎስ፣ በሞትና በመቃብር ላይ ሙሉ ሥልጣን ያለው ድል አድራጊ ዘር መሆኑን በተጨባጭ አሳየ፡፡ የማስተማር ጊዜውን ካጠናቀቀ በኋላ፣ በሰው ፈንታ ተሰቅሎ፣ ሞቶና ተቀብሮ ስለ ሰው ኀጢአት መሥዋዕት በመክፈል አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን ሙሉ በሲኦል የነበሩትን ነፍሳት ወደጥንተ ቦታቸው ወደ ገነት መልሶ አስገባ (1ኛ ጴጥ. 3፥18-19፣ ሉቃ. 23፡43)፡፡ እርሱም በተቀበረ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በራሱ መለኮታዊ ሥልጣን ተነሣ፤ በዚህ ጊዜ የሰው መውጊያ የሆነው ሞት ተሻረ፤ ተሸነፈ፤ ኀጢአት ጠፋ፣ መቃብርም ድል ሆኖ ባዶውን ቀረ፡፡ በጌታችን ትንሣኤ የተበሠረው የሞት መሸነፍና የመቃብር ድል መሆን፣ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ ለሰው ዘር ሁሉ እውን ይሆናል፤ ያን ጊዜ ሞትና መቃብር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ህልውናቸውን አጥተው ያከትማሉ፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ሁሉ ትንሣኤ በኵር ሆኖ ተፈጽሞአል፤ በመሆኑም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ‹‹ክርስቶስ ተነሣ›› ብለን የምሥራች በመናገር ብቻ ሳይሆን እኛም እርሱ በተነሣው አኳኋን እንነሣለን እያልን ተስፋ ትንሣኤያችንን በማብሠርና በማስተጋባት ጭምር ሊሆን ይገባል፤ የእኛ ትንሣኤ በክርስቶስ ተጀምሮ አሁን በሂደት ላይ ያለ ሲሆን፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ተመልሶ ሲመጣ የሁላችን ትንሣኤ እውን ይሆናል፤ የሰው የመጨረሻ ዕድሉ ሞት ሳይሆን ትንሣኤ መሆኑንም በዚያን ጊዜ ይረጋገጣል ፡፡ በዚህም ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር እንደመሆኑ መጠን ለዘለቄታው ተሸናፊ ሳይሆን በአምላኩ ቸርነት በመጨረሻ አሸናፊ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡

ዛሬም ቢሆን የሰው አሸናፊነት በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ሕይወቱ በግልጽ የሚታይ ነው ይኸውም፡-
በሥጋዊ ሕይወቱ በኩል ከጥንት ጀምሮ በተፈጥሮ ሀብት ላይ በሚያደርገው የምርምርና የተግባር ጥረት ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና ድል በድል እየተጓዘ ዛሬ ለደረሰበት የቴክኖሎጂ ብልጽግና በቅቶአል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወቱ በኩልም ከአምልኮ ጣዖት ተላቆ በአንድ እውነተኛ አምላክ በማመንና ከእርሱ ጋር ግንኙነት በማድረግ በሞራል፣ በሥነ ምግባርና በሃይማኖት የበለጸገ ማኅበረ ሰብ በዓለም እንዲኖር አስችሎአል፡፡
ስለሆነም ዲያብሎስን፣ ኀጢአትን፣ ሞትንና መቃብርን የሚያሸንፉ መስተጋድላንና መዋእያን ቅዱሳን በብዛት እንዲገኙ አድርጎአል፤ አሁንም በዓለም ዙሪያ ሁሉ ስፍር ቊጥር የሌላቸው መንፈሳውያን አርበኞችና ድል አድራጊዎች አሉ፤ ባለፈው ዓመት በሊቢያ የተሠዉ ልጆቻችን በዚህ መንፈሳዊ አርበኝነት የቅድስና ድልን የተጎናጸፉ ተጠቃሽ ሰማዕታት ናቸው፡፡ የምንኖርባት ዓለም የትግል ሜዳ ናት፤ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን ሁሉ በትግል የተሞላ በመሆኑ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ኑሮአችን ከትግሉ ማምለጥ አንችልም፤ እውነቱ ይህ ከሆነ የሚያዋጣው ከትግሉ መሸሽ ሳይሆን ታግሎ ማሸነፍ ነው፡፡ የጌታችን ነገረ መስቀልም የሚያስተምረን “ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ያጥብዕ ወይንሣእ መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ፤ ወዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይፀመደኒ ወኢይደሉ ሊተ፤ ሊከተለኝ የሚወድ መስቀለ ሞቱን ይዞ በቈራጥነት ይከተለኝ፤ መስቀለ ሞቴን ተሸክሞ የማይከተለኝ ሊያገለግለኝም የኔ ሊሆንም አይችልም” እያለ ነው (ማቴ. 10፥38)፡፡ በዚህ ክርስቶሳዊ የተጋድሎ ጥሪ ቅዱሳን ሐዋርያትና ቅዱሳን ሰማዕታት በአጠቃላይም ክርስቲያኖች ሁሉ ወደትግሉ ሜዳ ተቀላቅለውና በድል አድራጊነት ግዳጃቸውን ተወጥተው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠች ሃይማኖትን አስረክበውናል፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ፣ ዲያብሎስንና ኀጢአትን፣ በትንሣኤው ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ እንደተነሣ፣ የእርሱ ተከታዮች የሆኑ ቅዱሳን ክርስቲያኖችም በዚያው ፍኖተ መስቀል እየተጓዙና ድልን እየተቀዳጁ ከኛ ዘንድ ያደረሱትን ሃይማኖታዊ ተልእኮ በተለመደው መንፈሳዊ ትግል በመጠበቅ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የእኛ ፈንታ ነው፡፡ የሃይማኖት ትግል በየወቅቱ የሚለዋወጥ ከሚሆን በቀር የሚቆም አይደለም፤ የዘመናችን ትልቁ የሃይማኖት ተግዳሮት ቴረሪዝም፣ ሴኩላሪዝምና ግሎባላይዜሽን በማንነትና በሃይማኖት ህልውና ላይ እየፈጠሩት ያለ ከባድ ጫና ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ በአጠቃላይም በሀልዎተ እግዚአብሔር የሚያምኑ ሁሉ ሃይማኖትና ዕሴቶቹ የፈጠሯቸው የማንነት ጸጋዎችን አጽንተው በመያዝ ካልመከቱ በቀር የሴኩላሪዝምና የግሎባላይዜሽን ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ረገድ ማለትም ሃይማኖቱንና ከሃይማኖት የተወረሱ ዕሴቶቹን፣ እንደዚሁም የተቀደሰ ባህሉን እየጠበቀ ለሃይማኖቱና ለማንነቱ እንዲቆም ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ ትመክራለች፣ ታስተምራለችም፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በሱባዔው ወቅት በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት፣ በንስሓ፣ በቅዱስ ቊርባን ፍቅርንና ሰላምን ገንዘብ በማድረግ ዲያብሎስንና ኀጢአትን ስንታገላቸው እንደቆየን ሁሉ፣ አሁንም በበዓለ ፋሲካው ቀን ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸውን ሕፃናት፣ በድርቅ የተጎዱትን ወገኖች በተለይም በአሁኑ ወቅት የግድያና የአፈና ሰቆቃ ደርሶባቸው በኀዘንና በችግር ላይ የሚገኙት የጋምቤላ ብሔረ ሰብ ልጆቻችንና ወገኖቻችን በሁሉም ነገር ከጎናቸው ሆነን በማገዝ፣ በመመገብ፣ በማጠጣትና በማልበስ፣ በሽተኞችን በመጠየቅና በመርዳት ፍጹም የደስታና የድል ቀን አድርገን ማክበር ይገባናል፤ በዚህ መልካም ሥራችንም የትንሣኤ ልጆች መሆናችንን ማስመስከር ይኖርብናል ፡፡

በመጨረሻም፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓለ ትንሣኤን ሲያከብር ማስታወስ ያለበት የክርስቶስን አሸናፊነት ነው፤ በአንጻሩ ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑ ሁሉ አሸናፊዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል፤ አሸናፊነታቸውም በሃይማኖትና በልማት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ሕዝቦች በአጠቃላይ በድህነት ላይ የጀመሩትን ትግል በድል ማጠናቀቅ ይችሉ ዘንድ ሰላማቸውንና አንድነታቸውን በመጠበቅ የሀገራችንን ሕዳሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፣ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡አሜን!