የካቲት 16 ቀን የ2006 ዓ.ም ዐቢይ ጾምን አስመልክቶ ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ፤

እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለሁለት ሺሕ ስድስት ዓመተ ምሕረት የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

‹‹ወእመሰ በምግባረ መንፈስ ቀተልክምዎ ለምግባረ ነፍስትክሙ ተሐይዉ ለዓለም፤ በመንፈሳዊ ሥራ ሥጋዊ ሥራችሁን ብትገድሉ ለዘለዓለሙ ትድናላችሁ›› (ሮሜ 8÷13)፡፡

ጾም ከጥንት ጀምሮ በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ የተወደደ፣ የፈቃደ ሥጋ መቈጣጠሪያ፣ የፈቃደ ነፍስ ማበልጸጊያ መሣሪያ ነው፤ እነ ሙሴ፣ እነ ኤልያስና እነ ዳንኤል ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ ይገናኙ የነበረ ራሳቸውን በጾም ለእግዚአብሔር በማስገዛት ነው፤ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ፣ በሰይጣን የቀረበለትን ፈተና አሸንፎ፣ የጾምን ድል አድራጊነት በተግባርና በትምህርት አሳይቶናል፤(ማቴ.4÷1-11)

ቅዱሳን ሐዋርያትም እግዚአብሔር ሥራቸውን እንዲያቃናላቸው፣ ኀይለ መዊእ (የአሸናፊነት ኀይል) እንዲሰጣቸው በየጊዜው ይጾሙ ነበረ፤(የሐ.ሥ.10÷23) ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ህልውት በኵሉ የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ከነቢያት፣ ከጌታችንና ከሐዋርያት በተማረችው ትምህርትና በተቀበለችው ትውፊት መሠረት ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ኀይለ አጋንንትን ድል ለማድረግ፣ ከእግዚአብሔር በረከትንና ረድኤትን ለማግኘት ጾምን ትጾማለች፡፡

ሰው በተፈጥሮው እርስ በእርስ የሚጋጩ ሁለት ፍላጎቶች በውስጡ እንዳሉ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤ እነዚህ ፍላጎቶች ሥጋዊና መንፈሳዊ ተብለው የሚታወቁ ሲሆን፣ የሥጋ ፍላጎት ለነፍስ ፍላጎት፣ የነፍስ ፍላጎትም ለሥጋ ፍላጎት ተቃራኒ እንደሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት ተብራርቶና ተገልጾ ተቀምጦአል፡፡ (ገላ.5÷16-18) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በተመለከተ ሲያስተምር ‹‹የሥጋ ፍላጎት ሞትን ያመጣል፤ የነፍስ ፍላጎት ግን ሰላምንና ሕይወትን ይሰጠናል››፤ ብሎአል፤ (ሮሜ.8÷6-8)፤ የጾም አስፈላጊነት የሚመነጨውም ከዚህ መሠረታዊ ትምህርት ነው፤ ሥጋ ኀይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን አብዝቶ በተመገበ ቊጥር ኀይል ይሰማዋል፤በዚህ ጊዜ ለእግዚአብሔር መታዘዝን ይዘነጋል፣ ወንድሙን ለመበደል ይፈጥናል፣ ማመዛዘን አይችልም፤ ብዙ ስሕተትንም ይፈጽማል፤ በመጨረሻም ይሞታል ማለትም ከእግዚአብሔር ጋር አንድነትን ያጣል፤ ከመንፈሳዊ እይታ አንጻር ከእግዚአብሔር አንድነት መለየት እጅግ በጣም የከፋ ሞት ነው፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ሰው ከምግብ በታቀበ ጊዜ ረጋ ብሎ ማሰብን፣ ማስተዋልን፣ ማመዛዘንን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝን፣ ራስን መግዛትን፣ ርኅራኄንና ቸርነትን፣ ለወንድም አዛኝነትን ገንዘብ ያደርጋል፤ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋር አንድነቱን ያጠናክራል፤ በዚህም የሞት አሸናፊ ሆኖ በእግዚአብሔር መንግሥት በዘለዓለማዊ ሕይወትና ክብር ተደስቶ ይኖራል፤ ከዚህ አኳያ ጾም ለመንፈሳዊ ሕይወት መጎልበት፣ ራስን በመግዛት ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነትና አንድነት ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል፤ ጾማችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አግኝቶ ሙሉ ዋጋ ሊያሰጠን የሚችለው ከፍቅር፣ ከምጽዋት፣ ከሰላም፣ ከጸሎትና ራስን ለእግዚአብሔር ከማስገዛት ጋር ሲሆን ነው።

በፍጹም ሐሳባችን፣ በሙሉ ኀይላችንና በፍጹም ልቡናችን ለእግዚአብሔር በምንገዛበት በዚህ ወቅት ካለን ሀብት ከፍለን፤ በየሰፈሩ የሚገኙ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትን፣ ሠርተው ራሳቸውን መርዳት ያልቻሉ የአካል ጒዳተኞችን በመርዳት ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡ ወርኀ ጾም በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ሆነ በሥጋዊ ኑሮአችን ከምንም ጊዜ በበለጠ ግዙፍና ትላልቅ ሥራዎችን ሠርተን የምናጠናቅቅበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፤ በተለይም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለእግዚአብሔር ያለንን ተገዢነት ለማረጋገጥ፤ በመንፈስና በጽድቅ ሆነን በየቀኑ አብዝተን የምንጾምበትና የምንሰግድበት መሆን አለበት፤ በሥጋዊ ኑሮአችንም ሥራ ከሚያስፈቱን ነገሮች ሁሉ ርቀን ቀኑን በሙሉ በሥራ ላይ የምንውልበት ሊሆን፤ ይገባል፤ በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ በሀገራችን የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ለማሳካት አፈርን የመገደብና መስኖን የማስፋፋት ሥራ አጠናክሮ እንዲሠራና ወርኀ ጾሙን በላቀ የሥራ ርብርብ እንዲያሳልፍ መልእክታችንን አደራ ጭምር እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፡ እግዚአብሔር አምላካችን ወርኀ ጾሙን መልካም የንስሐ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የሥራ ጊዜ አድርጎ በማስፈጸም ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላምና በጤና እንዲያደርሰን በጾምና በጸሎት እንትጋ በማለት መልእክታችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ አሜን !!