ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም 41ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በሰሜን አሜሪካ የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳስት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
የተከበራችሁ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኀላፊዎች፤
የየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችና የየክፍሉ ኀላፊዎች፤
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኀላፊዎችና የየሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፤
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣት ልጆቻችን፤
በውጭ አህጉር ከሚገኙ ልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት የመጣችሁ እንግዶች፤
በአጠቃላይ በዚህ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ ለመሳተፍ በዚህ ቅዱስ ስፍራ የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት፡-
ሁሉ የሚቻለው የሚሳነው ነገርም የሌለው አምላካችን እግዚአብሔር አርባ አንደኛውን ዓለም ዐቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ሰዓት እንድናካሂድ ስለፈቀደልን ክብርና ምስጋና አምልኮና ውዳሴ ለእሱ ይሁን፡፡ እናንተንም አቅፎ ደግፎ በሰላም ወደ ሀገራችሁና ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ መንፈሳዊ ጉባኤ ስላመጣልን በድጋሚ እሱን እያመሰገን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ደስታችንን ልንገልፅላችሁ እንወዳለን፡፡
“ገሥጽዎሙ ለሕዝብየ ወአጽንዕዎሙ ይቤ እግዚአብሔር
አጽናኑ፣ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል እግዚአብሔር”
(ኢሳ. 40፥1)
ይህ ቃል የኀያሉ አምላካችን የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ቃሉ እንደሚያመለክተው በዚህ ዓለም ያለው ሕዝብ ባለቤት ያለው መሆኑን ነው፡፡ ማንኛውም ፍጡር በራሱ ለራሱ የተፈጠረና በሕይወት የሚኖር የለም፡፡ ሁሉም በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ተፈጠረ፥ ለእግዚአብሔርም በሕይወት ይኖራል፡፡
ሰው በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ለእግዚአብሔርና የእግዚአብሔር እንደ ሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሲነግረን፡- “ወአልቦ እምውስቴትነ ዘለርእሱ የሐዩ፣ ወዘለርእሱ ይመውት፤ እመኒ ሐየውነ ለእግዚአብሔር ነሐዩ፤ ወእመኒ ሞትነ ለእግዚአብሔር ንመውት፤ እመኒ ሐየውነ ወእመኒ ሞትነ ለእግዚአብሔር ንሕነ፡- ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና ለራሱም የሚሞት የለምና፣ በሕይወት ብንኖር ለእግዚአብሔር እንኖራለን፤ ብንሞትም ለእግዚአብሔር እንሞታለን፤ በሕይወት ብንኖርም፣ ብንሞትም የእግዚአብሔር ነን ይለናል፡፡
ከዚህ ትምህርተ እግዚአብሔር እንደምንገነዘበው ሰው በዚህም ዓለም ሆነ በወዲያኛውም ዓለም፣ በሕይወት የሚኖር እንጂ የሚጠፋ አለመሆኑን፣ በዚህም ኖረ በዚያ ምን ጊዜም የእግዚአብሔር ገንዘብ መሆኑን፣ በዚህም ሆነ በዚያ ለእግዚአብሔር እንጂ ለራሱ እንዲኖር ያልተፈጠረ መሆኑን በግልጽ ያስረዳናል፡፡
ዋና ጭብጡ ሰው ፈቅዶ የፈጠረው ዛሬም ሆነ ለወደፊት የሚፈልገው ባለቤት ያለው መሆኑን፣ እሱም እግዚአብሔር እንደ ሆነ በውል ማስገንዘብ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ነው የሕዝቡ ፈጣሪና ባለቤት የሆነ እግዚአብሔር የእርሱ የሆነውን ሕዝብ እንከን እንዲነካው አልፈቀደም፤ ባለመፍቀዱም “ኢትግሥሡ መሲሓንየ፡- ማለት በልጅነት ያከበርኳቸውን ሕዝቤን አትንኩ” ብሎ ሲያስጠነቅቅ እንሰማለን፤ የሚነካም ካለ እናንተ “ሕዝቤን አጽናኑ” ብሎ አዝዞናል፡፡ የተነካውን ሕዝበ እግዚአብሔር ማጽናናት የእኛ ተቀዳሚ ተልእኮ እንደ ሆነ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በአጽንዖት ሊቀበል ያስፈልጋል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፡ የተከበራችሁ እንግዶች!!
በዚህ አሁን ባለንበት ዘመን የእግዚአብሔር ሕዝብ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው ብሎ መጠየቅ ከኛ ይጠበቃል፡፡ ሕዝባችን በአሁኑ ጊዜ ሕይወቱንና ንብረቱን፣ ልጁንና ሚስቱን፣ ቤተ ሰቡንና ሰላሙን እያጣ ነው፡፡ ያላጣው ነገር የለም፤ ሁለመናው ተነክቶአል፡፡ ይህ ሲሆን እኛ ማድረግ ያለብን ነገር ምን እንደሆነ ተነግሮናል፤ እርሱም ማጽናናት ነው፡፡ ከማጽናናትም አልፎ ቤዛ ሆኖ እስከ መሰጠት ድረስ መራመድ ነው፡፡
ያለንበት ጊዜ ይህንን ሁሉ እየጠየቀን ነው፡፡ ሕዝቡን ማጽናናት ከኛ ይጠበቃል፡፡ ሕዝቡን የምናጽናናው በቃላት ብቻ ሊሆን አይገባም፤ በመሐሉ ገብተን በመገሠጽና በመምከር፣ በማስተማርና በማሳመን፣ በማስታረቅና እፎይታን በማጐናጸፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ሕዝቡ ሕዝባችን ነው፤ እኛም የእርሱ ነን፡፡ ሕዝባችን እርስ በርስ ነው እየተላለቀ ያለው፤ ሌላ ተጨማሪ ቢኖርም ከኛ በተፈጠረው ክፍተት እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ ሕዝባችንን የሚያጣላና የሚያፋጅ፣ አሁን ከደረሰበት ደረጃም የሚያደርስ በቂ ምክንያት የለውም፡፡ ቢኖርም በውይይትና በምክክር፣ በፍቅርና ጊዜ ሰጥቶ በማሰላሰል መልክ ሊይዝ የሚችል ነው፡፡ መሬቱ እንደሆነ የትም አልሄደም፤ ሊሄድም አይችልም፤ እዚያው ከነበረበት ነው ያለው፡፡ ሕዝባችንን ግን ከነበረበት እያገኘነው አይደለንም፡፡ በዚህ ዓለም ድጋሚ ላናገኘው አግባብ በሌለው አኳኋን በየቀኑ እየተሰናበተን ነው፡፡ አሁን ጥያቄው ምን እናድርግ? ነው፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራን እንግዶቻችን፤
ዛሬ ተሰብስበን የምንነጋገረው ስለ ሰበካ ጉባኤ ነው? ወይስ ስለመልካም አስተዳደር? ሕዝቡ ከሌለ እኮ ሃይማኖቱም፣ ገቢውም፣ አስተዳደሩም ነገ ሊቆም ይችላል፡፡ እዚህም እዚያም በየቀኑ እንደቅጠል እየረገፈ ያለው እኮ በመስቀላችን ያጠመቅነው፣ ማዕተበ ክርስትና ያሰርንለት፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት አጭተን ያዘጋጀነው፣ ቤተ ክርስቲያንን ተረክቦ ሊያስቀጥልልን ዐይናችንን የጣልንበትና ተስፋም ያደረግንበት ልጃችንና ወገናችን ነው፡፡ ዝም ብሎ ማየቱ አያስጠይቅም ትላላችሁ?
እኛ ግን በእግዚአብሔርም፣ በሰውም፣ በታሪክም፣ በሞራልም ያስጠይቃል ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ ውስጥ እየተሳተፋ ያሉ ሁሉም ልጆቻችን ናቸው፡፡ የተጣሉበትንም ነገር በውል ማወቅ አንችልም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር እናውቃለን፤ እሱም ሁሉም የኛ ልጆች መሆናቸውን እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ነው፡፡ በመሆኑም ከነዚህ ውስጥ አንድስ እንኳ እንዲሞትብን ወይም እንዲጐድልብን አንፈልግም፡፡ ሁሉም በሕይወት፣ በሰላምና በጤና እንዲኖሩልን እንሻለን፡፡
ፍጅትና እልቂት ይጐዳናል እንጂ ማናችንንም አይጠቅምም፡፡ እስካሁን ጦርነት ይጠቅማል ብሎ ሲናገር የሰማነው አንድ ስንኳ የለም፡፡ ታድያ ለማይጠቅም ነገር ለምን እንለፋለን? ከኛ ውጭ ያለው ዓለም ግጭቱ ቆሞ ሰላማዊ ውይይት ይካሄድ ሲል፣ መንግሥትም ሲቀበል፣ በሌላ በኩል ያለው ወገናችንም ሲቀበል፣ እኛስ ይሄንን ደግፈን ድምፃችንን ለሕዝባችን፣ ለመንግሥት እና ለሰላም እየተጋ ላለው የዓለም ዐቀፍ ማበረሰብ ብናሰማ ተገቢ አይደለምን? ይህንን በተመለከተ የነገሩን አሳሳቢነት ከልብ ተገንዝቦ ይህ ጉባኤ የሚለው ነገር እንዲል እንጠብቃለን ፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራን እንግዶቻችን!!
መቼም “እምነ ረኃብ ይኄይስ—-” እንደተባለው ሞትም ቢሆን እየበሉ ቢሆን ነውና የሚሻለው፣ በሰበካ ጉባኤ ሕገ ደንባችን መሠረት የቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ የሀገራችን ምጣኔ ሀብትን የማሳደግ፣ የመጠበቅና ፍትሓዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል ማረጋገጥ የኛ ሌላኛው ተልእኮ ነው፡፡
ሰበካ ጉባኤ የተቋቋመውም ለዚህ ተብሎ እንደሆነ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፤ ጠቃሚ ውጤቱም በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ ነገር ግን፡-
• የሰበካ ጉባኤ አመሠራረትና ጒዞው፣
• አሁን ያለበት ደረጃ ትክክል ነው ወይስ የሚቀረው አለ?
• የቀረው ካለስ ለምን አናስተካክለውም?
• ለወደፊትስ የሰበካ ጉባኤ ሀብተ በረከት እንደሚፈለገው በፍጥነት አድጎ ለሕዝቡ ተደራሽ እስከ መሆን ለምን አናደርሰውም? በሚል ትክክለኛና ሙያዊ ጥናት ተካሂዶ ለዚህ ጉባኤ ማቅረብ የሚቀርብን ይመስለናል፡፡
ይህ ነጥብ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ በሁለቱም ጉባኤያት እንድናየው ቢደረግ መልካም ይመስለናል፡፡ ምስጋና ይድረሳቸውና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና ከጎናቸው የነበሩ ሊቃውንት አባቶች ለሰበካ ጉባኤ መመሥረትና ሥር መስደድ እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት እንደከፈሉ ይህ ጉባኤ መርሳት የለበትም፡፡ የእነርሱ ክብርና ሕያው ታሪክ መጠበቅ ያለብን በጽሑፍና በንግግር ብቻ ሳይሆን የሰበካ ጉባኤ ዐላማ ሙሉ በሙሉ ግቡን መትቶ ቤተ ክርስቲያን ከገጠር እስከ ከተማ ራሷን ስትችል፣ ከዚያም አልፋ ተርፋ በየቤተ ክርስቲያኑ የአብነት ት/ቤቶችና የዘመናዊ ት/ቤቶች በብዛትና በጥራት ተከፍተው፣ የሕዝበ ክርስቲያኑ ልጆችንና ሌሎችንም አቅፋ ስታስተምር፣ ዕጓለ ማውታና አረጋውያን ስትጦር፣ ሕሙማንን ስትፈውስ በአጠቃላይ የሕዝበ እግዚአብሔር እናትነትዋን በሚገባ ስትወጣ በማሳየት ሊሆን ይገባል፡፡ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ በቅጡ ባይያዝም ከገቢ አንጻር በከተሞች አካባቢ የተሻለ የሰበካ ጉባኤ ሀብተ በረከት ይታያል፡፡
እሱም ቅዱሱ ሕዝበ እግዚአብሔር በሙዳየ ምጽዋት ከሚያኖረው በረከት እንጂ፣ አስተምረንና ተከታትለን፣ ቀስቅሰንና አሳምነን በቃለ ዐዋዲው መሠረት አስተዋፅኦውን እንዲከፍል አድርገን እንዳልሆነ ጥቆማ ይደርሳል፡፡ በገጠርም በተመሳሳይ ሁኔታ ኮታ እየተጣለ የሚሰበሰብ እንጂ እያንዳንዱ ምእመን አስተዋፅኦውን በትክክል እንዲከፍል እያደረግን እንዳልሆነ ይሰማል:: ከዚህም ጋር በየመንገዱ የሚንጠባጠበው በዚያው ልክ እንደ ሆነ ይደመጣል፡፡ ታድያ እንዲህ ሲሆን ዝም የምንል ከሆነ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መንፈስ አይወቅሰንም? ለምንስ እንወቀሳለን? ጉባኤው ከተቀበለን አሁን አጥብቀን የምናሳስበው የሰበካ ጉባኤ ጉዛችን ምን እንደሚመስል በባለሙያዎች በትክክል ቢጠናና ቢገመገም፣ ከዚያም አይተነው ወደ ተሻለ የእድገት ጒዞ ብንራመድ እንላለን፡፡ ምክንያቱም አንድ ሥራ በየጊዜው እየተገመገመ፣ እየታረመና እየተስተካከለ ካልተሠራ የሚቀረው ነገር አይታጣምና ነው፡፡
ከዚህ በተረፈ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ሰጭነትና መሪነት ደጋውን ወጥታችሁ፣ ቈላውን ወርዳችሁ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ አገልግሎቷን በማስቀጠል ሁላችሁም የቤተ ክርስቲያናችን ተጠሪዎች ላደረጋችሁት የላቀ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አርባ አንደኛውን ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ የከፈትን መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበሥራለን፡፡
እግዚአብሔር የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡