ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አራተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ሥነ ሥርዐት የተገኛችሁ ሁሉ፤
በማያልቅ ፍቅሩ እየጠበቀ አገልግሎታችንንም እየባረከ ሁሌ በቸርነቱ ከዘመን ወደ ዘመን የሚያሸጋግረን እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለዓመታዊው የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሁላችንንም በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!

“ብፁዓን ገባርያነ ሰላም እስመ እሙንቱ ውሉደ እግዚአብሔር ይሰመዩ
የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፤ እነሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።”
(ማቴ. 5፥9)

ይህ ትምህርተ ብፅዕና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰላም፣ ስለ አስታራቂዎችና ዋጋቸውን አስመልክቶ ያስተማረው የሕይወት ቃል ነው፤ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የሰላም ነገር በሰማይም ሆነ በምድር በፈጣሪም ሆነ በፍጡራን ዘንድ ያለው ዋጋ ተመጣጣኝም ሆነ ተወዳዳሪ አይገኝለትም፤ በሰማይና በምድር ሰላም በጠፋ ጊዜ ሰላምን ለማምጣት ሲባል አምላክ ሰው ሆኖአል፤ ዕርቅን ለማስፈን ሲባል አምላክ በሥጋ በመስቀል ተሰቅሏል፤ በዚህም ሰማይንና ምድርን ወደ ልጁ ኅብረት አምጥቶአል፤ ዕርቁንና ሰላሙንም አረጋግጦአል፡፡ እንግዲህ ይህ ከኅሊና በላይ የሆነውን የአምላክ ሥራ ስናስተውል ሰላምና ዕርቅ፣ ስምምነትና አንድነት በአምላክ ዘንድ ያላቸው ዋጋ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በሕዝብና በሕዝብ መካከል እንዲሁም በግለሰቦች መካከል የዕርቅ ተግባር እያከናወኑ ሰላምን የሚያወርዱ ሰዎችም ዋጋቸው የእግዚአብሔር ልጅ መሆንን እንደሆነ ተናግሮ የማይከዳው አምላክ ማረጋገጫ ቃሉ ሰጥቶአል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ!ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ሰላምና ዕርቅ የእግዚአብሔር ተቀዳሚ ተግባራት ናቸው፤ እነዚህ ተግባራት በየቀኑ መፈጸምና መከናወን ያለባቸው የእርሱ ሉዓላዊት መንግሥት በሆነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የመንግሥቱ ተጠሪ ደግሞ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ነው፤ ይህ ጉባኤ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሆኖ ስለዕርቅና ሰላም አበክሮ እንዲሠራ “ጠብቅ፣ አሰማራ” ተብሎ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን የተሰጠው አካል ነው፤ ምክንያቱም በሰዎች መካከል ሰላም ከሌለ ቤተ ክርስቲያንም ተጎጂ ናትና ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በሰላም ዕጦት ሕይታቸውንና ንብረታቸውን ሲያጡ ከማየት የበለጠ የቤተ ክርስቲያን ጥቃት የለምና፡፡ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ ከምንም ጊዜ በላይ በጎቹን ለመጠበቅ የሚተጋበት ጊዜ ላይ መሆኑን በውል መገንዘብ ይገባል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሁሉም በጎች እኩል ጠባቂ ነውና፤ የገለልተኝነትና የማእከላዊነት አቋሙን ጠብቆ የሁሉም ወገን አባትነቱን ሳያዛንፍ ለልጆቹ ዕርቅና ሰላም መረጋገጥ ሁሉንም በአባታዊ ፍቅር እያቀፈ ማስታረቅ በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ተግባሩ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ!
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ሁላችንም እንደምናየው በቃልም ይሁን በመሠረተ ሐሳብ ዕርቅንና ሰላምን የሚቃወም ወገን ፈጽሞ የለም፤ ነገር ግን በመጓጓዣ ሐዲዱ ላይ መግባባት እየጠፋ በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን በአጠቃላይ ብዙ ጥፋት ተከሥቶአል፤ የሚያስገርመው ነገር ቢኖር ለውይይትና ለመቻቻል ሰፊ ዕድልና ጊዜ አለመስጠቱ ነው፡፡ ጉዳዩ እጅግ ግዙፍ የሆነ የሀገር ህልውና ጉዳይ ስለሆነ በጥልቀት፣ በስፋት፣ በሰከነ አእምሮና አስተሳሰብ በተረጋጋ መንፈስ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እየተካሄዱ ያሉት የግጭቶች አቅጣጫዎች የሚመስሉ ትንኰሳዎች የኋላ ኋላ ምን ያህል ፀፀት እንደሚያስከትሉ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ድብቅ ምሥጢር አይደሉም፡፡ ሳንግባባ ቀርተን ትናንትና ያጋጩን ነገሮች ብዙ አሳጥተውናል፤ ለማይመለስ ፀፀትም ዳርገውናል፤ አሁንም ተመሳሳይ ስሕተት ፈጽመን ፀፀት ላይ እንዳንወድቅ የፈለገውን ያህል ጊዜ ይውሰድ የፈለገውን ያህል ዋጋ ያስከፍል ያለአንዳች ግጭትና ደም መፍሰስ ሁሉም ነገር ወደዕርቅ፣ ወደሰላምና አንድነት ማምጣት አለብን፤ በነገሩ ላይ ሸማግሌ ከገባበት እግዚአብሔርም ከተጋበዘበት የውይይት ጊዜና ትዕግሥትም ከታከለበት ሁሉም ነገር እየዋለ እያደረ የሰላም ጎሕ እየፈነጠቀ መረጋጋት ሥር እየሰደደ፣ ጥላቻ እየተናደ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም፤ «ዕለት ለዕለት ትጐሥዕ ነቢበ፤ ወሌሊት ለሌሊት ታየድዕ ጥበበ — አንዷ ዕለት ለሌላኛዋ ዕለት መልካም ንግግርን፣ በጎ ሐሳብን ታመነጫለች፤ አንዷ ሌሊትም ለሌላኛዋ ሌሊት የበለጠ ጥበብና ማስተዋልን ትወልዳለች» የሚለው የእግዚአብሔር ቃልም ይህንን ያረጋግጣልና ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ጠንክረን ከሠራን ፍሬ እናጣለን ተብሎ አይገመትም፤ ስለሆነም ይህ ዐቢይ ጉባኤ እንደካሁን ቀደሙ ኮሚቴ አቋቁሞ መለያየት ሳይሆን የሀገር ሰላም ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተናል በሚል ቅን መንፈስ፣ በተቃርኖ ያሉ ኀይሎችን በግንባር በማግኘትና በማነጋገር የአንድ ሰው ሕይወት እንኳ እንዳይጠፋ ሁሉም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠንክሮ መማፀን አለበት፡፡ የሁሉም ምርጫ ውይይትና ውይይት ብቻ እንዲሆንም በርትቶ በመሥራት ሁሉንም ማሳመን አለበት፤ ከዐቅሙ በላይ ከሆነም ልምዱና ጥበቡ ያላቸው ሀገር ዐቀፍና ዓለም ዐቀፍ ገለልተኛ ወገኖችን በማሳተፍ የዕርቁና የሰላሙ ተልእኮ ግብ እንዲመታ ማድረግ አለበት፤ ይህ ተግባር ወቅቱ ኀላፊነት የጣለበት የቅዱስ ሲኖዶስ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ !
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችንን ለከፋ አደጋ የዳረጋት መሠረታዊ ምክንያት የአክራሪዎችና የተቃራኒዎች እንቅስቃሴ መሆኑ በውል ማወቅ አለብን፤ ይሁን እንጂ የእኛ አያያዝም በክፍተት የተሞላ በመሆኑ ከተቃራኒ አካላት ባልተናነሰ ሁኔታ እያስጠቃን ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የሚታዩ ልዩ ልዩ የአሠራር ጒድለቶች ማለትም የአስተዳደር ስልታችን የፋይናንስና የንብረት አያያዛችን ምእመናንን እያበሳጩብን እንደሆነ አንዘንጋ፤ በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች ችግሮቻችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል ዕውቀቱ፣ ልምዱና ችሎታው ባላቸው ባለሙያዎች በጊዜያዊም ቢሆን መድበን በጥናት ላይ የተመሠረተ መሪ ዕቅድ ዘመናዊ አሠራርን አዘጋጅተው እንዲያቀርቡልን ማድረግ አለብን፡፡ በሠላሳ ዘጠነኛው የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ እንደተጠቀሰው ቤተ ክርስቲያናችን በከባድ ፈተና ላይ መሆኗ ተገልጾአል፤ ስለሆነም ይህ የጥፋት ድርጊት እንዲቆም ሁነኛ መፍትሔ ማስቀመጥ ይኖርብናል፡፡
በመጨረሻም አዲሱ ዓመት ጠንካራ የዕርቅና የሰላም ሥራ ሠርተን ልጆቻችንን ከሥጋትና ከጥፋት የምንታደግበት ይሆን ዘንድ በርትተን እንድንሠራ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሁሉ ልባዊ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እያስተላለፍን፣ ዓመታዊውን የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ባርከን በጸሎት የከፈትን መሆናችንን እናበሥራለን፤ ጉባኤያችንን ጉባኤ ሐዋርያት፣ ጉባኤ አበው ቅዱሳን ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!!