ጥቅምት 12 ቀን 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡ ከየሀገረ ስብከታችን አሰባስቦና በዚህ ቅዱስ ስፍራ አገናኝቶ ስለአጠቃላይ መንፈሳዊ ተልእኮአችን ለመወያየት ያገናኘን እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡

“ኦ አባ ቅዱስ ዕቀቦሙ በስምከ ለእለ ወሀብከኒ ከመይኩኑ አሐደ ብነ ከማነ፤ ቅዱስ አባት ሆይ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው” (ዮሐ17፡11)፡፡

በቃለ እግዚአብሔርም ሆነ በገሃዳዊው ዓለም ተጨባጭ አኗኗር እንደሚታየው የፍጡራን አንድነት ተፈጥሮኣዊ ጸጋ ከመሆን አልፎ አስገዳጅ የህልውና ዋስትናም እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የአንድነት አስፈላጊነት በተመሳሳይ ዘርዐ ፍጡራን ብቻ የሚወሰንም አይደለም፤ በምንኖርባት ዓለም የሚገኙ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ፍጡራን በአጠቃላይ፣ አንድነት ኖሮአቸው እርስ በርስ የማይመጋገቡ ከሆነ ህልውና ጣዕም አይኖረውም ብቻ ሳይሆን ጭራሽኑ መኖር እንደማይችሉ ግልጽ ነው፡፡

እግዚአብሔር በከሃሊነቱ እርስ በርስ አቆራኝቶ አስተሳስሮና ተመጋጋቢ አድርጎ የፈጠራቸውን ፍጡራን በሰው ሠራሽ ምክንያት ለማለያየት መጣር፣ ሙከራ ከመሆን አልፎ ዘላቂ የሆነ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፤ ምክንያቱም ፍጡራን ሁሉ ማኅበራውያንም አሐዳውያንም ሆነው ሊኖሩ በአምላክ ጸጋ ተፈጥረዋልና ነው፤ ዛሬ ዓለም በአጠቃላይ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ሕይወት እንደ አንድ መንደር እየሆነች የመጣችው በራስዋ ጥበብ ሳይሆን እግዚአብሔር ጥንቱም ማኅበራዊ ሆና እንድትኖር አድርጎ ስለፈጠራት ነው፡፡

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም የመጣው በፍጡራን መካከል ጠንካራ ኅብረትና አንድነት እንዲኖር ለማድረግ ነው፤ ጌታችን በትምህርትም በተግባርም ያረጋገጠውም ይኸው ነው፡፡ ጌታችን ለፍጡራን በአጠቃላይ፣ በተለይም ለሰው ልጅ ያስተማረው የአንድነት ትምህርት ከራሱና ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ካለው መለኮታዊና ባሕርያዊ አንድነት ጋር በማነጻጸር መሆኑንም የአንድነት አስፈላጊነት ምን ያህል ትልቅ ስፍራ እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡

የጌታችን ትልቁ ጸሎትና ትምህርት የሰዎች አንድ መሆን እንደሆነ ከቅዱስ ወንጌል ተምረናል፣ አውቀናልም፤ በመሆኑም ክርስቶሳዊ፣ ሐዋርያዊና ዐቢይ የሆነው ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ የጌታችንን ትምህርትና ትእዛዝ የመጠበቅና የማስጠበቅ የመፈጸምና የማስፈጸም ኀላፊነት እንዳለበት መዘንጋት የለብንም፡፡

እኛ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሕዝብን አንድነት ለመጠበቅ ሕዝብን የሚያስማማና የሚያግባባ ትምህርት ማስተማር ይገባናል፣ ማስተማርም ያለብን ምንም ምን ያልተቀላቀለበት ንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ሊሆን ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሁሉንም ያስማማል ሁሉንም ያግባባል በመስማማት ላይ የተመሠረተ አንድነትም ፍሬ ሰላምን ያፈራል፡፡

እኛ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሰላም ሐዋርያት ሆነን በጌታችን ተሹመናል፤ ለሕዝቡ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሰላም እንድናደርስም “ሰላማችሁ ይድረስለት” ተብለን ሰላመ እግዚአብሔር በእኛ በኩል ለሕዝቡ ተልኮአል፤ አሁን ጥያቄው የሰላም ተልእኮውን ለሕዝቡ እንድናደርስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠንን አደራ በሚገባ እያደረስን ነው ወይ? የሚለው ነው፤ መልሱ አጭርና ግልጽ፣ እየታየም ያለ ይመስለናል፡፡

እኛ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ዓለም ንጹሕ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል እንዳናስተምርና ሕዝቡን አስማምተን አንድ እንዳናደርግ የሚከለክለን እንደሌለ እናውቃለን፣ ነገር ግን ማስተማር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እያለ በሚገባ ባለማስተማራችን ሕዝቡ ግራ ከተጋባ የጎደለ ነገር አለ ማለት ነው፤ እርግጥ ነው ይህን ስንል ሥራ አልተሠራም ትምህርትም አልተሰጠም ማለታችን አይደለም፤ነገር ግን እኛ ማየት ያለብን ጌታችን “ወገቢረክሙ ኵሎ በሉ አግብርት ፅሩዓን ንሕነ” ብሎ ያስተማረውን ነው፡፡

ዛሬ ሌሎች፣ ከእኛ ጉድለት አለ፤ እኛ አስተካክለን መሥራት የሚገባንን አልሠራንም እያሉ ለበለጠ ሥራ ሲዘጋጁ፣ የቃሉ መልእክተኞች የሆን እኛ ይህንን እውነተኛ የጌታችን ቃል ልናልፈው አይገባም፣ እየሆነ ያለው ሁኔታም ሲታይ ሕዝቡ የስምምነት፣ የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር ሕዝብ እንዲሆን ለማድረግ የሚቀረን ሥራ እንዳለ ያመለክታል፡፡ ሕዝቡ የእግዚአብሔር ማእደ ሰላም ከሆነች ቤተ ክርስቲያኑ የሰላምን ማእድ መቋደስና ማጣጣም እንዲችል ያለማቋረጥ ስለ ሰላምና ስለፍቅር ጠንክረን ማስተማርና መሥራት ይገባናል፡፡

በተለይም በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የተከሠቱ ግጭቶችና ሁከቶች ለዘላለም ተፈቃቅረውና ተዋደው ለዘመናት በአንድነት የኖሩትን የሀገራችን ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲቃቃሩ ከማድረጉም ባሻገር የሕይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት አስከትሎአል፣ የልማት አውታሮችን ጎድቶአል፤ ብዙ ዜጎችንን ያለሥራ አስቀርቷል በሕዝቦች መካከል የኅሊና ስብራት ፈጥሮአል፤ ይህ ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራችን አሳዛኝ ክሥተት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የሕዝብ ሁሉ እናት ናት፤ እናት ከሁሉ በፊት ለልጇ ደራሽ እንደመሆኗ መጠን ቤተ ክርስቲያናችንም ችግሩ ከተከሠተበት ጊዜ አንሥቶ ኀዘኗንና የሰላም ጥሪዋና በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡ ይሁንና አሁንም የተከሠተው የሰላም መደፍረስና የኅሊና ስብራት ቀላል ስላልሆነ ሰላሙ አስተማማኝ እስኪሆንና የኅሊና ስብራቱም ተጠግኖ እስኪሽር ድረስ በሰላም መጠናከር ዙርያ መጠነ ሰፊ የሆነ ሥራ መሥራት ይኖርብናል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የሁሉም እናት ነች ስንል የኢትዮጵያ ሕዝቦችም በሙሉ ልጆችዋ ናቸው ማለታችን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወደዚህም ወደዚያም ሳትል ማእከላዊና ገለልተኛ ሆና የሰላም መልእክቷን ብቻ ለሁሉም ማድረስ ይገባታል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ዘላቂና ብዙኃኑን የሚጠቅም የሰላም ህልውናን ለማረጋገጥ በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተሳትፎዋን በማሳደግ ለሕዝብና ለሀገር ደኅንነት መሥራት ይኖርባታል፡፡ በተለይም ዘርን በመለየት የሀገርን አንድነት በመፈታተንና በሃይማኖት አመክንዮ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕዝባችንን ሀገራችንንና ሃይኖታችንን በእጅጉ የሚጎዱ ስለሆኑ ሕዝቡ እንዲጠነቀቅባቸውና በአርቆ አስተዋይነት እንዲመለከታቸው በልዩ ትኵረት ማስተማር ይኖርብናል፡፡

ሕዝቦቻችን በተለይም ወጣት ልጆቻችን ለአደጋ እየተጋለጡበት ያለው ክፍተት የሥራ አጥነት ችግር እንደሆነ እየሰማን ነው፤ ሁሉም በልቶ ካደረ ችግሩ ሊቀንስ እንደሚችል ጥርጥር የለንም፡፡ ሆኖም የዚህ ቊልፍ መፍትሔ ልማትን በማስፋፋት ዕድገትን ማምጣት ነው፡፡ ዕድገቱን ሊያመጣው የሚችል ደግሞ እኛ እየመራነውና እያስተማርነው ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ ዐቅሙን ሁሉ አስተባብሮ ወደ ልማት እንዲሠማራ ያለ መታከት ማስተማር ያለብን እኛው ብፁዓን ሊቃ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ሰባክያነ ወንጌል ነን፤ ነገር ግን አስተማሪዎች ብቻ ሳንሆን ሠርተን የምናሳይም መሆን ስላለብን ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም አቅጣጫ ልማትን በማስፋፋትና ለወጣቱ ትውልድ የሥራ ዕድልን በመፍጠር እናትነትዋን በተጨባጭ ማሳየት አለባት፤

ስለሆነም በዚህ ቅዱስ ዓመታዊ ጉባኤያችን በሰላም መጠናከርና መጠበቅ ዙርያ፣ በልማት ሥራ መስፋፋትና በስብከተ ወንጌል መጠናከር ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይት በማድረግ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሕዝባችን እንደዚሁም ለሀገራችን በአጠቃላይ የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤውን እንድናጠናቅቅ በማሳሰብ፣ ለስኬቱም ያለንን ልባዊ ምኞትና ጸሎት በመግለጽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በይፋ መከፈቱን እናበስራለን፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡