ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ቤተ ክርስቲያንን በንጹሕ ደሙ የዋጀ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምእመናንን በቅዱስ መንፈሱ መሪነት እየጠበቀ ከዚህ ጊዜ ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡ እንደዚሁም ሁላችንን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከየሀገረ ስብከታችን በረድኤት ስቦ በሀብት አቅርቦ በዚህ ሐዋርያዊና ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተገናኝተን በእግዚአብሔር ስለተሰጠን ዐቢይ ተልእኮ እንድንመካከር ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
‹‹ወመጺኦ ውእቱ መንፈሰ ጽድቅ ይመርሐክሙ ኀበ ኵሉ ፍኖተ ጽድቅ፤ ያ ሁላችንም እንደምናውቀው ይብዛም ይነስ፤ ዘመን ያለ ታሪክ አያልፍም፤ በየዘመናቱ ያለ ትውልድ በይበልጥ ደግሞ በኀላፊነት የሚቀመጡ ኀላፊዎች የታሪኩ አካል መሆናቸው አይቀርም፤ እንደሌላው ሁሉ እኛም ከዚህ እውነታ ማምለጥ አንችልም፡፡
ታሪክ አንድን ትውልድ በመልካም ወይም በመጥፎ ሊመዘግብ ይችላል፤ የእኛ ታሪክ እየተመዘገበ ያለው ከሁለቱ በየትኛው ነው? የሚለው ግን የሁላችንም መሠረታዊ ጥያቄ ሊሆን ይገባል፤ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሩቅ መጓዝና ልዩ ምሁርን መጠየቅ አያስፈልገንም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እስመ ኢኮነ ርሕ እምኔነ፤ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም›› እንዳለው የሰው ኅሊና በአካባቢውና በውስጡ ያለውን ለይቶ ማወቅ ይቅርና ከአእምሮ በላይ የሆነውን የረቂቅ አምላክ ህልውና እንኳ በመጠኑም ቢሆን ማወቅ የሚችል ነው፡፡ (ዮሐ.ሥራ 1፥27)
መንፈስ ቅዱስም ‹‹ዮም አመ ሰማዕክሙ ቃሎ ኢታጽንዑ ልበክሙ ‹ዛሬ ድምፁን በሰማችሁ ጊዜ ልባችሁን አታጽኑ›› እያለ የሚጣራበት ጊዜ እንደሆነ ማወቁ አይከብድም››:: (ዕብ. 3፥15) በመሆኑም ራስን በራስ በመጠየቅ የሚገኝ መልስና ራስን በራስ በመወሰን የሚሰጥ ዳኝነት ከሁሉም የበለጠ ፈዋሽ መድኀኒት ነውና በራሳችን ዳኝነት የቤተ ክርስቲ ያናችንን ሉዓላዊነትና አንድነት እንደዚሁም ምእመናንዋና ሀብቷ የሚጠበቁበት ሥራዎችን መሥራት የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ተግባር ነው፡፡
ታላቋና መተኪያ የማይገኝላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በውስጥም ሆነ በውጭ የተጋረጡባት ግልጽና አደገኛ ፈተናዎች እንዳሉ መገንዘብ አለብን፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ከሚታዩ ፈተናዎች አንዱና ዋነኛው በሚሊዮን የሚቈጠሩ ምእመናን ወደ ሌላ እምነት እየፈለሱ ከመሆናቸው ሌላ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት አያያዝ አስተማማኝ ሆኖ አለመገኘቱ፤ የሰው ኀይል፣ የገንዘብና የንብረት አስተዳደራችን በዘመኑ ቴክኖሎጂ የተቃኘ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያሰፈነ አለመሆኑ፤ በቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያን የማታውቀውና የማትቈጣጠረው ሀብትና ንብረት የሚሰበስቡ ማኅበራት እየተበራከቱ መምጣታቸው፤ በቤተ ክርስቲያን ስም ሀብትን የሚሰበስቡ ማኅበራት በእነርሱ የምትተዳደር ቤተ ክርስቲያን ሳትኖር የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ መብት የሆነውን ከምእመናን ገንዘብና ንብረት የመሰብሰብ ሥልጣንን ወደራሳቸው በማዞር ገንዘብና ንብረት ከምእመናን መሰብሰብ መልመዳቸው፤ በዚህም ምክንያት በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁለት የተለያዩ ዐሥራትና በኵራት ሰብሳቢዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸው፤ በቤተ ክርስቲያን እየተፈጠረ ያለው ሁለተኛ ባለሀብት ማኅበር በሂደት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሁለት የመክፈል አዝማሚያ እንዳለው ግልጽ ማስረጃ መገኘቱ፤ ማኅበራቱ በመንግሥትና በቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ ሀብት የሚሰበስቡ በመሆናቸው ገንዘቡ በሚያስከትለው ሌላ ጉዳት ቤተ ክርስቲያን በአክራሪነት የምትፈረጅበት አጋጣሚ መከሠቱ፤ ማኅበራት በሌላቸው ሥልጣን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ሥራ በቀጥታ ጣልቃ እየገቡ የሰላም ጠንቅ ሆነው መገኘታቸው፤ ችግሩን በቀላሉ ለማስተካከል ቢሞከር እንኳ ማኅበራቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የሚሰ ጣቸውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኝነቱና ቅንነቱ ፈጽሞ የሌላቸው ሆነው መገኘታቸው አስቸኳይ መፍትሔ የሚሻ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር ሆኖ ተገኝቶአል፡፡
‹‹በይሉኝታ የራስ ዓሊ ቤት ተፈታ›› እንደ ተባለው ትዕግሥትና ደግነት በዚያም ላይ ይሉኝታ ተጨምሮበት ካልሆነ በቀር እነዚህን ወገኖች የምናስተናግድበት ቤትና የምንዳኝበት ሕግ ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በሃይማኖታችን ትውፊት ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ጸበልን ቀምሶ የሚኖር የጽዋ ማኅበር ካልሆነ በቀር በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ቤተ ክርስቲያንን አህሎ የተደራጀና ቤተ ክርስቲያን አከል የሆነ ገንዘብ ሰብሳቢ ማኅበር ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ስለሆነም በመልካም አስተዳደር፣ በሀብትና በንብረት አያያዝ፣ በመሪ ዕቅድ እየተመሩ ሥራ መሥራትን አስመልክቶ የተጀመሩ ሥራዎች አጠናክሮና አፋጥኖ ከዳር የማድረሱ ተግባር እንዳለሆኖ በተለይም በምእመናን ፍልሰትና በማኅበራት ጉዳይ ላይ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕጋዊና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጡ ቤተ ክርስቲያንን የመታደግ ጉዳይ መሆኑን በአጽንዖት ሳንጠቁም አናልፍም፡፡
በመጨረሻም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ግልጽ በሆነ ሁኔታ እያልን ያለነው፡-
1. የምእመናን ፍልሰት በአሁኑ ጊዜ እየተባባሰ ስለመጣ ሁላችንም ተባብረንና አስፈላጊውን ሥራ ሠርተን ፍልሰቱን እናስቁም፤
2. የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት በመጠበቅ መልካም አስተዳደርን እናስፍን፤
3. በቤተ ክርስቲያን ስም የሚሰበሰብ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የማታውቀው፣ የማትቈጣጠረውና የማታዝበት ገንዘብና ሀብት ሊኖር አይገባም፤
4. በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ያልታቀፈና ለቤተ ክርስቲያን የማይታዘዝ ማኅበር በቤተ ክርስቲያን ስም ተደራጅቶ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ የሚያስከትለው ጉዳት ከባድ ስለሆነ፣ በሕግ ማስተካከል አለብን የሚሉትን ነው፡፡
ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን በግልጽ አውቆ የቤተ ክርስቲያኒቱን ወቅታዊ ችግር በመፍታት ረገድ የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ፣ እንደዚሁም በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ያሉትን ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዐት ልትመሩ ይገባችኋል ብሎ እንዲመክራቸው፣ እነዚህ ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ተጽዕኖ በመፍጠር ታሪካዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ጉባኤያችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፤አሜን፡፡