ጥቅምት 12 ቀን እስከ 22 ቀን 2008 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በመደበኛ ስብሰባ፤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ተራ ቍጥር 164 በተደነገገው መሠረት የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከጥቅምት 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ለዐሥራ ሁለት ቀናት ያህል ባደረገው ስብሰባ፡ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዳይፋለስ ለመጠበቅና ለመቈጣጠር፤ ካህናት በመንፈሳዊው ተልእኮአቸው እንዲፋጠኑ ለማስተባበር፤ ምእመናን በምግባር፣ በሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ለማስተማር፤ እግዚአብሔር የሚመሰገንበትን፣ ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልበትን ሥርዐት ለመወሰን፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ሥራውን በጸሎት ጀምሮአል፡፡

1. ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተደረገውን የመክፈቻ ንግግር በቤተ ክርስቲያኒቱ እየተሠሩ ያሉትን የሥራ ሂደቶች የዳሰሰና በሁሉም አቅጣጫ ቤተ ክርስቲያኗ የደረሰችበትን እድገትና ሊሠራ የሚገባውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በሚገባ የሚያስገነዝብ በመሆኑ፤ እንዲሁም በሀገራችን በአንድ አንድ አካባቢ በተፈጠረው የዝናም እጥረት ምክንያት በተከሠተው ድርቅ ለተጐዱ ወገኖች ሊደረግ ስለሚገባው ሰብኣዊ አገልግሎት ርዳታንና ትምህርትን ለመስጠት የሚያስችል አባታዊ መመሪያ በመሆኑ ተግባራዊ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
2. በተለያየ ጊዜና ምክንያት ኢትዮጵያ ሀገራችንን ድርቅ እያጠቃት ጥቂት የማይባሉ የሀገሪቱ ዜጎች ለረሀብ ሲጋለጡ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በተለመደው የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህላችንን በተግባር በማሳየት፣ ፈታኝ ችግሮችን ማሳለፋችን ይታወቃል፡፡ በአሁኑም ጊዜ በዝናም ዕጦት ምክንያት በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተከሠተው ድርቅ ምክንያት ለረኃብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመታደግ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በማድነቅ ቤተ ክርስቲያናችንም የተለመደውን አስፈላጊ እገዛና ድጋፍ ማድረግ ስላለባት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በአንድ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ድጋፍ ሰጭ በጎ አድራጊዎች ጋር በመቀናጀት የርዳታ ሥራውን እንዲያፋጥን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
3. የመልካም አስተዳደር ዕጦትንና የሙስና መስፋፋትን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ሰፊ ውይይት በማድረግ፣ እንዲህ ዐይነቱ ሀገርንና በአጠቃላይም የሰውን ልጅ ሁሉ የሚያጎድፍ ክፉ ተግባር በመሆኑ ሀገርንና ወገንን እንዳይጐዳ አጥብቆ መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ አጥብቃ እንድታስተምር፣ ይህ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሙስና መስፋፋት የችግሩ መነሻና መፍትሄ መታወቅ ስላለበት አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗን ሁለንተናዊ ችግር የሚያጠና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ያካተተ 9 አባላት ያሉበት ዐቢበይ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተቋቁሟል፡፡
4. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአገር ባለውለታ እንደመሆኗ ለዘመናት ሕዝቡን ስለ ሰላም፣ ስለ ልማት፣ ስለ አገር ፍቅርና ስለአብሮነት ጊዜው በፈቀደው መንገድ ሁሉ ስታስተምር ቆይታለች፡፡ አሁንም ዘመኑ ባፈራው መገናኛ ብዙኃን አብዛኛውን ኅብረተሰብ በትምህርት ለመድረስ እንዲያስችላት የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ስርጭት መጠቀም እንድትችል በባለሙያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት እና ብር12,000,000 (ዐሥራ ሁለት ሚሊዮን ብር) የአንድ ዓመት በጀት ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቋል፡፡
5. የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑ አረጋውያን የሚጦሩበትን፤ በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት የሚያድጉበትን የምግባረ ሠናይ ተቋማትን ያላቋቋሙ አህጉረ ስብከት እንዲያቋቁሙ፤ አቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት አህጉረ ስብከትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ መመሪያ ተሰጥቷል፤
6. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመማር ማስተማር ሥርዐትን በመዘርጋት በአገር ደረጃ የትምህርት መሠረት መሆኗ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በቤተ ክርስቲያኒቱ የተከፈቱና የመማር ማስተማር ሥራውን እያከናወኑ ያሉ ሦስቱ መንፈሳዊ ኮሌጆች ተማሪዎችን አስተምሮ ለቁም ነገር በማብቃት ቤተ ክርስቲያንና አገርን እንዲጠቅሙ፣ ለኅብረተሰቡ የምሥራች ተናጋሪና ሰላምን የሚሰብኩ ሁነው እንዲያድጉ ለማድረግና ኮሌጆቹን ለበለጠ እድገት ማብቃት በሚያስችልበት ሁኔታ የኮሌጁን የውስጥ ይዘት እንዲያጠኑ 3 ብፁዓን አባቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡
7. ቤተ ክርስቲያኒቱ በማታውቀው ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ ሳያገኙ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ትምህርታዊ ስብከት የሚያስተላልፉ ዝማሬ የሚያሰሙ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ልዩ ልዩ በራሪ ወረቀቶችን የሚያሳትሙ ሁሉ በአገሪቱ ሕግ መሠረት በሕግ እንዲጠየቁ፣ ለሚመለከታቸውም የሚዲያ አካላት ማሳሰቢያ እንዲደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
8. አንዳንድ የእምነት ተቋማት ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሆኑትን ንዋየ ቅድሳት፣ አልባሳት፣ መስቀሎች፣ መቋሚያ፣ ከበሮ፣ ጸናጽልና የመሳሰሉትን ሁሉ የራሳቸው ያልሆነውን የራሳቸው በማስመሰል እየተጠቀሙ መሆኑን ጉባኤው ተገንዝቦ በጉዳዩ ሰፊ ጥናት ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ ለማድረግ ለጥናቱ ብፁዓን አባቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡
9. በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በየአህጉረ ስብከቱ ተቋቁሞ ለበርካታ ዓመታት ለአገርና ለወገን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት በተለይ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በአንዳንድ ቦታ የተከሠተውን ድርቅ ታሳቢ በማድረግ አሳዳጊ ላጡና በድርቁ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ሕፃጻናት የተለመደውን ሰብኣዊ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
10. በየመንፈሳዊ ኮሌጆች መስፋፋትና ዕድገት ላይ የተነጋገረው ቅዱስ ሲኖዶስ ፡- በኦሮምያ፣ በጅማ ሀገረ ስብከትና በአማራ ክልል በባሕርዳር ከተማ ቤተ ክርስቲያኒቱ አዲስ የከፈተታቸው መንፈሳዊ ኮሌጆች ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የዘወትር ሥራዋ አድርጋ የያዘችውን የትምህርት ሥራ ማጠናከር እንዲያስችላት በመሆኑ የመምህራን ማሠልጠኛዎቹ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ለኅብረተሰቡ በሚጠቅም መልኩ እንዲያስቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡
11. ቤተ ክርስቲያናችን ቀጣይ ሥራዎቿን ሁሉ ካለፈው በበለጠ በመሪ ዕቅድ የተደገፈ በማድረግ ማከናወን እንዲያስችላት ለ2008 በጀት ዓመት የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድና የዕቅዱ ማስፈጸሚያ በጀት ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቋል፡፡
12. በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር አመራር ሰጭነት በልማት ዘርፍ ዙሪያ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በበለጠ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ሁሉ ሊበረታታ የሚገባ ስለሆነ ሁሎችም አህጉረ ስብከት ለመልካም አስተዳደር መስፈን ዕንቅፋት የሆኑትን እያስወገዱ፤ የልማት አገልግሎትን በመዘርጋት እንዲሠሩ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
13. ሀገራችን ኢትዮጵያ ከበሽታ፣ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ወጥታ ሌላው ዓለም ወደደረሰበት ለመድረስ የምትችለው፣ ማንኛውም ወገን ተቻችሎና ተከባብሮ ለሰላምና ለልማት ሲነሣሣ ስለሆነ፣ ይኸው ታውቆ ሁሉም ኅብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ ይወጣ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን መልእክቷን ታስተላልፋለች፡፡
14. እንደኛ እምነት ሀገራችን ኢትዮጵያ የሥራን ክቡርነት የተረዳና እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ መሆኑን የተገነዘበው ወጣቱ ትውልድ ከሚፈጽመው መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባር መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር ወጣቱ ትውልድ የሥነ አእምሮ ብቃቱን በማሳደግ፤ ሥራን የመፍጠር ክሂሎቱን ማረጋገጥ ያስችለው ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ምክርዋን ታስተላልፋለች፡፡
15. የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ተግባርና ተልእኮ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት መሆኑ ይታወቃል፤ ጉባኤው በዚሁ ጉዳይ ላይ በስፋት ተነጋግሮ ሰባኪያነ ወንጌል በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው እንዲጎለምሱ ተፈላጊው ሥልጠና እየተደረገላቸው እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡
16. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የቆየው ስምምነትና አንድነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
17. በሀገራችን ኢትዮጵያ የዜጎችን ኋላ ቀር አኗኗር ለመለወጥ ዜጎች ሁሉ በእኩልነት ተሳስበው የሚኖሩበትን እድገት ማምጣት እንዲቻል በመንግሥትና በዜጎች ሁሉ እየተደረገ ያለው ጥረት ከፍተኛ ውጤትን እያስገኘ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በይቀጥላልም በልማቱ አቅጣጫ የሕዳሴያችንንም ግድብ ከፍጻሜ ለማድረስ በሚደረገው ርብርቦሽ የሀገራችንን የተፈጥሮ ሀብትና ጸጋ በማስጠበቅ ሕዝባችንን በማትጋት ቤተ ክርስቲያናችን የበኩሏን ሁሉ እንድታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
18. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አድማስን በማስፋፋት ኢትዮጵያውያን ባሉበት በተለያዩ የውጭ አገራት ቤተ ክርስቲያን እያቋቋመች ዜጐቿን እንደምታስተምርና እንደምታጽናና የሚታወቅ ነው፡፡ አሁንም ይህንኑ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ተልእኮዋን ማስፋት እንዲቻል ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋም በሚል ጥያቄ ላቀረቡ ኢትዮጵያውያን አማንያን በጃፓንና በኮሪያ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲቋቋሙ፣ መምህራንም እንዲላኩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
19. በውጭ አገር ከሚኖሩ አባቶች ጋር ተይዞ የነበረው የሰላም ድርድር ቤተ ክርስቲያናችን ምንጊዜም ቢሆን የምትፈልገውና በዚሁም ላይ አጥብቃ ስትሠራ የቆየችበት ጉዳይ መሆኑን ጉባኤው አውስቶ በቀጣይም በውጭ አገር ከሚገኙ አባቶች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሰላሙ ሂደት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
20. ከጥቅምት 8 – 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 34ኛ መደበኛ ስብሰባ በተላለፈው የጋራ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጋግሮ የውሳኔ ሐሳቡ የ2008 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ሆኖ በሁሉም አህጉረ ስብከት ተላልፎ በየደረጃው በሥራ እንዲተረጐም ተወስኗል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ አሜን፣