ጥቅምት 11 ቀን እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 በተደነገገው መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባን በማካሄድ፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለኅብረተሰባችን የሚጠቅመውን፣ ለሀገርና ለዓለም ሰላም የሚበጀውን አጀንዳ በማመቻቸት በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፡፡

“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር – ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያት እጆቻቸቸውን ወደ እግዚአብሐር ይዘረጋሉ” ይላል ነቢየ እግዚብሔር ዳዊት (መዝ. 67፣31)

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ክፍለ ዓለም፣ በአፍሪካ ቀንድ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ በዐባይ ሸለቆ ዙሪያ በቀይ-ባሕር አካባቢ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የአንድነት ዕድሜ የተቈጠረላት በዚህም ረዥም የነፃነትና የአንድነት ዕድሜዋ ብዙ አገልግሎት ያበረከተች ሰፊ ታሪክ ያስመዘገበች ሉዓላዊት ሀገር ናት፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ረዥም ዘመኗ በርካታ ደጋግ መልካም ሥራና ስም የነበራቸው ታላላቅ ሰዎች አልፈውባታል፡፡ ለታሪኳ፣ ለቅርሷ፣ ለባህሏ፣ ለዕድገቷ፣ ለድንበሯ ለአንድነቷ፣ ለነፃነቷ፣ ለክብሯ በሚገርም ወኔና ጀግንነት ደማቸውን ያፈሰሱላት፣ አጥንቶቻቸውን የከሰከሱላት ጀግኖች እንደነበሩአት አሁንም እንዳሏት በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በዘመናቸው እርስ በርሳቸው በመከባበር የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስ፣ ያለማውን በማልማት፣ ቤት የእግዚአብሔር ነው በሚል አገራዊ ትውፊት እንግዳ እየተቀበሉ እግር እያጠቡ ቤት ያፈራውን ተካፍለው በመብላት ተከባብረው በመኖር የታወቁ ደጋግ አባቶች ልጆች መሆናችን ይታወቃል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለአያሌ ዘመናት የኖሩባትና አሁንም የሚኖሩባት በአርኣያነት ልትጠቀስ የሚገባት ብቸኛ ሀገር መሆኗ ከማንም ግንዛቤ የተሠወረ አይደለም፡፡ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን፣ የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑ፣ የአገር ሀብትና ንብረት እየወደመ መታየቱ፣ ከነበሩበት እና ከኖሩበት ቦታ የሕዝቦችን ፍልሰት ማስከተሉ፣ በእነዚህም እየታዩ ባሉ ችግሮች ምክንያት በሰላማዊው ኅብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት እየሰፈነ መምጣቱና ልማታዊ ሥራዎችም ሊስተጓጐሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ተችሏል፡፡ ስለዚህ የዚሁ የጥቅምቱ 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአገሪቱ እየታየ ባለው የሰላም ችግር ላይ በሰፊው በመወያየትና በመነጋገር የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፡፡

1ኛ. በአገራችን ውስጥ ለአገራችን ዕድገት ሲባል ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች አሉን የሚሉ ወገኖች ሁሉ እንደ ጥንት አባቶቻችን ኢትዮጵያዊነትን በተላበሰ፣ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ጥያቄያቸውን ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርቡ፣
2ኛ. መንግሥት በአንድ አገር ውስጥ ለሚኖሩና ለሚያስተዳድራቸው ዜጎች እንደቤት ኀላፊና ልጆቹን እንደሚያስተዳድር መሪ እንደመሆኑ መጠን በሰከነና በተረጋጋ መልኩ ከዜጎች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በአግባቡ በመፈተሽና በማጥናት ለአገርና ለወገን የሚጠቅመውን ምላሽ እንዲሰጥባቸው ለሕዝቡ የገባውንም ቃል በተግባር አውሎ በሥራ እንዲተረጐም፣
3ኛ. የነገድ፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ለጋራ ህልውና፣ ለጋራ ልማትና ለጋራ ብልጽግና ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለጐረቤት አህጉር ብሩህ ተስፋ ሠንቆ እንደሚመጣ የተነገረለት የሕዳሴው ግንባታ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊነቱን እያስመሰከረ ስለሆነ እንዲሁም በዘመናችን የምንታወቅበት ዐቢይ ታሪካችን የዐባይ ሕዳሴ ግንባታ ግድብ የመሆኑን ያህል አሁንም ፕሮጀክቱ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በማንኛውም አቅጣጫ በሁሉም ወገን ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድነት ለግንባታው በመሰለፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣
4ኛ. ባለፈው ዓመት በነበረው የዝናም እጥረት ምክንያት በአገራችን ደርሶ የነበረው ድርቅ በመንግሥትና በመላው ኢትዮጵያዊ ሙሉ ድጋፍ ያለምንም የውጭ ርዳታ ችግሩን መወጣታችን ይታወቃል፡፡ ሆኖም በቀጣዩ ዜጎችን ለረሀብና ለስደት የሚዳርግ እንዲህ ዐይነት አስከፊ አደጋ በአገራችን እንዳይከሠት አገራችን እግዚአብሔር ባደላትና በሚያድላት የተፈጥሮ ጸጋ ምድሪቱን እየተንከባከብን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ለልማቱ በመነሣት ምርታማነትን በማሳደግ ለዕድገት እንድንበቃ ተግተን የሥራ ባህላችንን ልናዳብር ይገባል፡፡
5ኛ. ሥር ነቀል የግንባታ ሥራ እየተካሄደባት ያለች ሀገራችን ኢትዮጵያንና ጥቅሞቿን በማይጻረር በሰላማዊ መንገድ ተቀራርቦ በክብ ጠረጴዛ የጋራ ውይይት በማካሄድ ችግሮችን መፍታት አግባብነት ያለው አሠራር ስለሆነ የሀገር ጉዳይ የጋራና የውስጥ ጉዳይ እንጂ ድንበር ተሻጋሪ እንዳልሆነ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ግንዛቤን ወስደው የበኩላቸውን ድርሻ መፈጸም ይችሉ ዘንድ የራሳቸው የሆነውን አመለካከት ይዘው ሀገሪቱን ከሚመራው መንግሥት ጋር በክብ ጠረጴዛ እንዲወያዩ፣
6ኛ. ቀደምት አበው ኢትዮጵያውያን ዐረፍተ ዘመን እስከገታቸው ድረስ ሀገራቸውን ጠብቀው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ታሪክ ለቀጣዩ ታሪክ ተረካቢ ትውልድ ማቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ወጣቱ ትውልድ ከቀደምት አበው የወረሰውን ትውፊት በመከተል፡- ለሀገራችን የሚጠቅሙትን፣ ለልማትና ለሰላም የሚበጁትን፣ በሀገር ውስጥ ያሉ እና ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን አንድነትና ኅብረት የሚጠናከርበትን ሁኔታ በመሻት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡
7ኛ. አገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ራሷን ከወራሪ ጠላት በመከላከል ነፃነቷንና ክብሯን፣ ሰላሟንም ጭምር ጠብቃ ይዛ የቈየች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በየዘመናቱ የውጭ ወራሪዎችና ጣልቃ ገቦች አገጣሚዎችን እየተጠቀሙ ሕዝቧን ሰላም ለመንሳት ሙከራ ሲያደርጉ እንደቈዩና በመንግሥትና በሕዝቡ አንድነት አስፈላጊው አገራዊ ጥበቃ እየተደረገ ሳየሳካላቸው በነፃነት ኑራለች፡፡ አሁንም በአገራችን እየታየ ያለው የሰላም መታጣት አንዳንድ የውጭ ጣልቃ ገቦች እጅ እንዳለበት በርካታ አመላካች ሁኔታዎች እየታየ ሲሆን እነዚህ ከአገራችን ውጭ በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ሰላም የሚነሱ የውጭ ዜጎች ከአጥፊ ተልእኳቸው እንዲገቱ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ በማሳሰብ ድርጊቱን ትቃወማለች፡፡
8ኛ. ቤተ ክርስቲያናችን ለአገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ባለውለታ በመሆን ሕዝቡን የሰላም ወንጌል በማስተማር የተጣላ በማስታረቅ የተለያየውን አንድ የማድረግ ተልእኮዋን በመፈጸም የቈየች እንደመሆኗ አሁንም ዕለት በዕለት ከምታከናውነው መንፈሳዊ አገልግሎት ባልተናነሰ መልኩ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሕጓና በሥርዐቷ መላው ካህናትና አገልጋዮች በዕለተ ሰንበት ለሚገኘው ሕዝበ ክርስቲያን፣ በማታ ጉባኤ፣ በወርኃዊና ዓመታዊ በዓላት ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሥነ-ምግባር ታንጾ በፈረሃ እግዚአብሔር በግብረ-ገብነት ለአገሩ ሰላምና ለሕዝቡ አንድነት ተባብሮ እንዲቆም የሚያስችል ትምህርት እንዲሰጡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መመሪያን ያስተላልፋል፣
9ኛ. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እስከዛሬ ባደረገው ስብሰባ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ በቀረበው የ2009 ዓ.ም. በጀት ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡
10ኛ. ከጥቅምት 7-10 ቀን 2009 ዓ.ም.በተካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የቀረበው የጋራ መግለጫ ላይ ተወያያቶ አንዳንድ ማሻሻዎችን በማድረግ የ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ መመሪያ በማድረግ አጽድቋል፡፡
11ኛ. ለተዋሕዶ ሃይማኖታቸው ለሀገራቸው ልዕልናና ነፃነት በ1928 ዓ.ም.ከአርበኞች ጎን በመሆን ለሀገራቸው ነፃነት ጠንክረው እንዲዋጉ ሲያስተምሩ በነበረበት ወቅት በኢጣልያ ፋሽስታዊ መንግሥት በጎሬ ከተማ በ1929 ዓ.ም. በግፍ በሰማዕትነት የተገደሉት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሰማዕት ተብለው እንዲጠሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
12ኛ. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከጥቅምት 12- 16 ለአምስት ቀናት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም በቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ አሜን፡፡