ጥር 11 ቀን የ2007 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት በተመለከተ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
“ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ
የዕዳችንን መጽሐፍ ደመሰሰልን።”
(ቈላ. 214)
የሰው ልጅና የሌሎች ፍጡራን መኖሪያ የሆነው ዓለም በኀጢአተ ሰብእ ምክንያት ክፉኛ ተበክሎ እስከ ክርስቶስ ድረስ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል በፍዳና በኵነኔ ዕዳ ተይዞ መቆየቱ ይታወሳል፤ የዕዳው መነሻ ኀጢአተ አዳም ቢሆንም ከእርሱ በኋላ የተነሡ ልጆቹም በተመሳሳይ ኀጢአተኞች ሆነው ስለቀጠሉ ችግሩ እየባሰና እየሰፋ መጥቶ ከነፍሳዊ ኵነኔ በተጨማሪ ምድርን በጥፋት ውኃና በእሳተ ገሞራ ሊያስቀጣ ችሎአል፤ ያም ሆኖ በበደል ላይ በደል፣ በስሕተት ላይ ስሕተት ከመጨመር በቀር የተሻለ ነገር አልታየም፤ በመሆኑም ሰው ሁሉ በኀጢአት ዕዳ ተይዞ ነበር፤ (ዘፍ. 31-24፤ 717-23፤ 191-29)
እግዚአብሔር በሁለመናው ንጹሕና ቅዱስ በመሆኑ በኀጢአት የተዳደፈው ፍጡር በመንግሥቱ እንዲኖር አይፈቅድም፤ ይልቁኑም እውነተኛ ፈራጅ በመሆኑ በኀጢአት ላይ ፈርዶ ኀጢአተኛውን ይቀጣል፤ ጻድቁን ደግሞ በጽድቅ ሥራው ያከብራል፤ (ማቴ. 2546፣ ማቴ. 2211-14)፡፡ ከዚህ አንጻር ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ የነበረው ሰው ሁሉ ኀጢአተኛ ሆኖ ስለተገኘ በኀጢአት ዕዳው ከሚፈረድበት በቀር የሚድንበት ቀዳዳ አልነበረምና የሰው ዘር ሁሉ ለኀጢአት ፍርድ የተጋለጠ ሆነ፤ (ሮሜ.323)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ እውነተኛ ፈራጅ ቢሆንም መሓሪና ይቅር ባይም ነውና በልጁ መሥዋዕትነት የሰውን ዕዳ ኀጢአት ሠርዞ ሰውን በምሕረቱ የሚቀበልበት ዕድል እንዳመቻቸ በአፈ ነቢያቱ ገለጠ፤ (ኢሳ. 531-12) ዘመኑ ሲደርስም ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ሰብእ ተወለደ፤ ግዕዘ ሕጻናትን ጠብቆ በየጥቂቱ አደገ፤ በሠላሳ ዓመቱም በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡
በአራቱ ወንጌላውያን ትምህርትና ምስክርነት እንደተገለጸው ጌታችን ሲጠመቅ እግዚአብሔር አብ በብሩህ ደመና ሆኖ “ይህ የምወደው ልጄ ነው እርሱን ስሙት” ሲል፣ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ላይ ሲቀመጥ፣ ሰማያትም ሲከፈቱ መታየታቸው፣እግዚአብሔር በአካል ሦስት መሆኑንና ኢየሱስ ክርስቶስም ከሦስቱ አካላት አንዱ መሆኑን ከመታወቁም በላይ ሰው ከዕዳ ኀጢአት ነፃ ሆኖ በልጅነት ክብር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚችልበት ዕድል ምን እንደሆነ በግልጽ ያመላከተ ነበር፤ ይኸውም ሰው በእምነትና በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እንደሚችል ያረጋገጠ ክሥተት ነው፡፡
የክርስትና አስተምህሮ ትምህርተ ይማኖትንና ትምህርተ ድኅነትን በተመለከተ መሠረት አድርጎ የሚነሣው ከዚህ አስተርእዮተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መገለጥ) ነው፤ በጌታ ጥምቀት ከተፈጸመው አስተርእዮተ እግዚአብሔር የምንወስዳቸው ዐበይት ትምህርቶች የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤ ይኸውም፡- (1) እግዚአብሔር በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ መሆኑን፤ (2) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት አንዱ መሆኑን፤ (3) ሰው በንስሓ ተነሥቶ፣ በእምነት ተጒዞ፣ በጥምቀት ነጽቶ፣ በሥነ ምግባር ጸንቶ ሲገኝ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን እንደሚድንና መንግሥተ ሰማያት ለእርሱ ክፍት እንደሆነች ጌታ ሲጠመቅ ከተገለጡት ተኣምራዊ ትምህርቶች እናስተውላለን፤ (ማቴ. 31-17)
ጥምቀት ለድኅነተ ሰብእ የመጀመሪያው በር ነውና ጌታችን በጥምቀቱ ከገለጠው ተኣምራዊና ገቢራዊ ትምህርት በተጨማሪ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን በሚያስተምርበት ጊዜ “ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ብሎ የምሥጢረ ጥምቀትን ትምህርት አጠንክሮታል፤ (ዮሐ. 35)፡፡ ዓለምን የማዳን ሥራው ፈጽሞ ከተነሣ በኋላም “ሰዎችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” ብሎ አጽንቶታል (ማቴ 2819፤ ማር. 1616) በመሆኑም የምሥጢረ ጥምቀት ትምህርት ከጌታችን የጥምቀት ዋዜማ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ፣ ከዚያም በስብከተ ሐዋርያት ወቅት የትምህርተ ወንጌል ማእከል ሆኖ መነገሩና በጥብቅ መተግበሩ ጥምቀት ለሰው ልጅ ድኅነት ያለው ትርጒም ምን ያህል የላቀ እንደሆነ በትክክል ያሳየናል፤ (የሐ. ሥራ 238-42) የጥምቀትን በዓል በየዓመቱ ስናከብር በዮርዳኖስ ወንዝ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ስለ ድኅነታችን ክንዋኔ የተላለፉ አምላካዊ መልእክቶችን በሚገባ በማስታወስ፣ በማስተዋልና በተግባር በመፈጸም ሊሆን ይገባል፡፡
ከጥምቀት በዓል የምንወስደው ትምህርት ሃይማኖታዊውን ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊውንም ጭምር ነው፤ በዓለ ጥምቀት ተራራውና ኮረብታው ዝቅ ይበል፣ ጐድጓዳው ይሙላ፣ ጠማማውም መንገድ ቀጥ ይበል እያለ ሁሉም በእኩልነትና በጥሩ ሥነ ምግባር፣ በመከባበርና በመረዳዳት እንዲኖር የሚያስተምር ነው (ሉቃ. 33)፡፡ በመሆኑም በዓሉ ተወዳጅና የፍቅር በዓል በመሆኑ ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ያለው ጠቃሚነት እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ሁሉም ከሸፍጥና ከቅጥፈት ርቆ በደመወዙ ብቻ እንዲተዳደር፣ ትርፍ የሆነ ልብስና ምግብ ያለውም ለሌለው ወገኑ እንዲያካፍል፣ ጒልበተኛም በጒልበቱ ተመክቶ ደካማውን እንዳይቀማ፣ ባለሥልጣንም ሥልጣኑን መከታ አድርጎ ግፍ እንዳይፈጽም አጥብቆ የሚያስተምር በዓል በመሆኑ በዓሉ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮው ሌላ በሥነ ምግባርና በማኅበራዊ አስተምህሮም በማናቸውም መመዘኛ ተወዳዳሪ የሌለው በዓል ነው (ሉቃ. 33-14)። በበዓለ ጥምቀት አስተማሪነት ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሃይማኖታቸውን፣ አንድነታቸውን፣ ፍቅራቸውንና ባህላቸውን ጠብቀው ለዘመናት ዘልቀዋል፤ በዓለ ጥምቀት ዘር፣ ጎሳ፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ ወንዝ፣ ተራራ ሳይገድበው ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚያስተናግድና የማይበጠስ የአንድነት ገመድ ነው፡፡
ስለሆነም በዓለ ጥምቀት የሃይማኖታችን ብቻ ሳይሆን የአንድነታችንና የእኩልነታችን፣ የባህላችንና የአብሮነታችን ጠባቂ በዓል በመሆኑ ልንጠብቀው፣ ልናከብረውና ለዓለም ሁሉ ልናስተዋውቀው ይገባል፤ የበዓሉ አጠቃላይ ገጽታ ሃይማኖትና ክብር፣ ሰላምና ፍቅር፣ ነፃነትና ደስታ፣ እኩልነትና አንድነት፣ ምሕረትና ይቅርታ ነው፤ እነዚህ ዕሴቶች ለሰው ልጅ የተስተካከለ አኗኗር እጅግ አስፈላጊ ናቸውና እነዚህን ጠብቀን ከተጓዝን የማንወጣው ተራራና የማንሻገረው ወንዝ አይኖርም፤ በዘመናችን ልማቱና እድገቱ መከባበሩና ወንድማማችነቱ በሚያስደንቅ ሁኔታ እየጎለበተ የመጣው እኩልነትና ሰላም ስለተረጋገጠ ብቻ ነው፤ ስለዚህ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገ ወዲያም፣ ሰላምና እኩልነት፣ ፍትሓዊነትና ሕዝባዊነት ቦታ ሊነፈጋቸው አይገባም፤ እነዚህ መርሆዎች የሃይማኖታችን ዋና ምሰሶዎች ከመሆናቸውም ሌላ የልማታችንና የእድገታችን ዘላቂ ዋስትና ናቸውና ከማንም በላይ አብልጠን ልንጠነቀቅላቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር መልካም የጥምቀት በዓል ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ ይቀድሳችሁ፤ አሜን!