• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

የካቲት 9 ቀን የ2007 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በመላ ዓለም የምትገኙ፣ በሃይማኖት ጸንታችሁ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን እንዲፈጽምላችሁ በናፍቆት የምትጠባበቁ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ምእመናንና ምእመናት፤

ኀጢአትን በምግባረ ጽድቅ ለምንደመስስበት፣ ዲያብሎስን በእግዚአብሔር ቃል ድል ለምናደርግበት ለታላቁ ጾማችን ለጾመ ኢየሱስ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“እስመ አኮ ክመ በኅብስት ባሕቲቱ ዘየሐዩ ሰብእ አላ በኵሉ ቃል ዘይወጽእ እምአፉሁ ለእግዚአብሔር፤ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።” (ማቴ. 4÷4)

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፣ ሳይውል ሳያድር ወዲያውኑ ወደ ምድረ በዳ ሄዶ ጾምን መጾም ጀመረ፡፡ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሲጾም ከአራዊት በቀር ከእርሱ ጋር ማንም አልነበረም፤ መዋዕለ ጾሙን ከፈጸመ በኋላ ዲያብሎስ አዳምን ባሳተበት መብል እርሱንም ለማሳሳት ከጀለ፤ ሆኖም ጌታችን ‹‹ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም›› በማለት የማሳሳቻ ግንቡን ናደበት፤ ቀጥሎም ዲያብሎስ ‹‹መላእክቱን ስላንተ ያዝልሃል፣ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል›› ብሎ መጽሐፉን በትዕቢት መንፈስ በመጥቀስ ጌታችን ከመቅደሱ አናት ራሱን እንዲወረውር በስሑት ጥቅሱ ወተወተ፤ ይሁንና አሁንም ጌታችን ‹‹አምላክህን እግዚአብሔርን አትፈታተነው›› ተብሎ ተጽፎአል በማለት በድጋሚ የጥፋት መረቡን በጠሰበት፡፡ (መዝ. 90÷11፤ ዘዳ. 6÷16)

ዲያብሎስ ለሦስተኛ ጊዜ የዓለምን ክብርና ብልጽግና በማሳየት ጌታችንን ለእኔ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ ብሎ በፍቅረ ንዋይ አማካኝነት በአምልኮ ባዕድ ሊያጠምደው ሞከረ፤ ያን ጊዜ ጌታችን ሂድ፣ አንተ ሰይጣን ‹‹ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ›› (ዘዳ. 6÷13) ተብሎ ተጽፎአል ብሎ ዲያብሎስን ተስፋ ቈርጦና ተሸንፎ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር አንዳች ነገር ሲሹ ከእህልና ከውኃ ተከልክለው፣ በጾም ተወስነው፣ ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን ሲለምኑ ተቀባይነትን ያገኙ እንደነበረ በቅዱስ መጽሐፍ በብዙ ቦታ ተጽፎአል፤ በዚህም ነቢዩ ዳንኤልና ዕዝራ፣ እንደዚሁም ሙሴና ኤልያስ፣ አስቴርና ወንድሟ መርዶክዮስ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው ፤ ከሀገር አንጻር ደግሞ የነነዌ ከተማን ብንመለከት ስለጾም ጠቃሚነት በቂ ትምህርት እናገኛለን። (አስ. 4፥1-4፣ ዮና. 3፥1-10)

አበው ነቢያት በጾምና በጸሎት ሆነው ያቀረቡትን ተማሕፅኖና ልመና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ የሚሹትን እንዳገኙ ቅዱሳት መጻሕፍት መስክረዋል፡፡ ጌታችን፣ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የተጓደለውን ለማሟላት፣ የረቀቀውን ለማጕላትና የተዛባውን ለማስተካከል የመጣ እንደመሆኑ መጠን “ኦሪትንና ነቢያትን ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም” በማለት አስተምሮአል፤ (ማቴ 5÷17)፤ በመሆኑም ሙሴና ኤልያስ እንዳደረጉት እርሱም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመጾም ሰይጣንን ድል አድርጎአል፤ ከድርጊቱ ሂደት እንደምንገነዘበው ሰይጣን ሰውን ለመጣል የሚጠቀምባቸው ዋና ዋና መሣሪያዎች መብል፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ መሆናቸውን በዚህ እናስተውላለን ፤ ዲያብሎስ እናታችን ሔዋንን በዛፉ ፍሬ እንድትጎመጅ፤ እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ በሚለው ቅስቀሳ ሁሉን በእጇ እንድትጨብጥ በሚያስመስል የሐሰት ምክር እንድትወድቅ አድርጎአል (ዘፍ. 3÷4-8)። ዲያብሎስ ጌታችንን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጾ በአዳማዊ ቁመና ሲመለከተው በቀዳማዊ አዳም የተጠቀመውን ስልት ተጠቅሞ ዳግማዊ አዳምን ለመጣል ብዙ ተጠብቦአል፤ ይሁን እንጂ ‹‹ተልባ መስሎሽ ሰናፍጭ ትቀምሽ›› እንደሚባለው በቀዳማዊ አዳም ያስለመደው ዘዴ ዳግማዊ አዳም በተባለ በጌታችን ላይ ሊሠራለት አልቻለም ፡፡

ጌታችን ዲያብሎስን ድል የነሣው በሦስት ነገሮች እንደሆነ እናያለን ይኸውም፡- አንደኛ፡ በጾም፣ በጸሎትና በእግዚአብሔር ቃል ነው (ሉቃ. 4፡1-13) ጌታችን በዲያብሎስ በኩል ይቀርቡ የነበሩ ፈተናዎች በሙሉ ያከሸፋቸው የእግዚአብሔር ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ነው፤ ዲያብሎስም በዚያው ልዋጋ ብሎ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስን ተጠቅሞአል ይሁንና ጥቅሶቹ በተቀመጠላቸው እውነተኛ ትርጒምና መንፈሳዊ ይዘት ሳይሆን ለራሱ ክፉ ዐላማ በሚያመች አኳኋን ለትዕቢትና ለፍቅረ ንዋይ ስለተጠቀመባቸው ሚዛን ሊደፉለት አልቻሉምና በመጨረሻ ሽንፈቱን ሊከናነብ ግድ ሆኖበታል ፡፡

ጾም ዲያብሎስንና አሳሳች መሣሪያዎቹን ሰባብረን የምንጥልበት መንፈሳዊና ኀያል መሣሪያችን ነው፤ በጾምና በጸሎት አጋንንት ይሸነፋሉ፣ በጾምና በጸሎት ኀጢአት ይደመሰሳል፣ በጾምና በጸሎት መልካም የሆነ የሥራ ዕቅድ ይሠምራል፤ በጾምና በጸሎት ነፍስ ከስለ ኀጢአት ትፈወሳለች፤ በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ይቻላል፤ በአጠቃላይ ጾምና ጸሎት የሥጋ ፍላጎትን በቊጥጥር ሥር በማዋል ነፍስ ኀያልና አሸናፊ ሆና የበላይነትን እንድትቀዳጅ ያደርጋሉ፡፡

እንግዲህ ጾምን እንድንጾም የምንገደድባቸው ዐበይት ምክንያቶች እነዚህ ሲሆኑ ብዙ ተከታይ ሠራዊት እንዳላቸውም መዘንጋት የለብንም በጾም ወቅት፡ እጆቻችን ለጸሎት፣ ድሆችን ለመርዳትና ለልማታዊ ሥራ የሚዘረጉ፤ አንደበታችን ሃይማኖትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን የሚሰብክ፣ ጆሮአችን ቃለ እግዚአብሔርን፣ መልካሙንና ሐቁን ነገር ብቻ የሚሰማ፣ ዐይናችንም ወደጽድቅ ሥራ ብቻ አነጣጥሮ የሚመለከት፤ እግሮቻችንም ወደ ቤተ እግዚአብሔርና ወደልማታዊ ተግባር የሚገሠግሡ መሆን አለባቸው፣ በዚህ መንፈስና ግንዛቤ ጾሙን ከጾምን ዲያብሎስን ማሸነፋችን፣ እግዚአብሔርንም መምሰላችን የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡

በመጨረሻም፡ የጾም ወራት ከምንም ጊዜ የበለጠ ሥራ የሚሠራበት እንጂ እጅና እግር አጣጥፈው የሚውሉበት ባለመሆኑ መንፈሳዊውንና ልማታዊውን ሥራችንን አቀናጅተን በመሥራት ሀገራችንን በአረንጓዴ ልማት ያጌጠች፣ ውብ፣ ለኑሮ ምቹና የተፈጥሮ ጸጋዋ የተጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ የሚደረገው የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራ፣ በወርኀ ጾሙም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምድርን ውብና ለም አድርጎ በፈጠረ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ ወርኀ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው እንዲያደርሰን የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32015-04-12 12:48:442025-01-28 12:49:56የካቲት 9 ቀን የ2007 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ጥር 11 ቀን የ2007 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት በተመለከተ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ጥር 11 ቀን የ2007 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት በተመለከተ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ጥር 11 ቀን የ2007 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት በተመለከተ... Link to: ሚያዝያ 4 ቀን የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ Link to: ሚያዝያ 4 ቀን የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሚያዝያ 4 ቀን የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top