ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
‹‹ወዓዲ እብለክሙ ለእመ ኀብሩ ክልኤቱ አው ሠለስቱ እምኔክሙ በውስተ ምድር በእንተ ኵሉ ግብር ዘሰአሉ ይትገበር ሎሙ በኀበ አቡየ ዘበሰማያት እስመ ኀበ ሀለዉ ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡኣን በስምየ፣ ህየ እሄሉ አነ ማእከሎሙ፤ ዳግመኛም ከእናንተ ሁለቱ ወይም ሦስቱ በምድር ላይ ስለሚለምኑት ሥራ ሁሉ ቢተባበሩ፣ በሰማያዊ አባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፤ ሁለቱ ወይም ሦስቱ በስሜ ተሰብስበው ካሉበት፣ እኔ ከዚያ በመካከላቸው እገኛለሁና›› (ማቴ. 18፥19-20)

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ከጌታችን፣ ከአምላካችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠንን ዐቢይ ተልእኮ ወይም ሐዋርያዊ አገልግሎት በየተሰማራንበት ሀገረ ስብከት ስናከናውን ቆይተን፣ በዓለ ትንሣኤውን ካከበርን በኋላ፣ በቀኖና ሐዋርያት ድንጋጌ መሠረት፣ ስለቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች ለመነጋገር በዚህ በርክበ ካህናት ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አንድ ላይ ስለሰበሰበን፣ አምላካችን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ እንዳስተማረን፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የገባው ቃል ኪዳን አለ፤ እርሱም ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የተፈጸመ ጽኑ ቃል ኪዳን ነው፤ ቃል ኪዳኑም የሚከተለው ነው፤ ‹‹ሁለቱ ወይም ሦስቱ በስሜ በተሰበሰቡበት፣ እኔ ከዚያ በመካከላቸው እገኛለሁ›› ይላል፤ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው፣ ቃል ኪዳን በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈጸምና ለቃል ኪዳኑ መከበር የሁለቱንም የቃል ኪዳን አካላት ኀላፊነት በግልጽ የሚያስቀምጥ ነው፤ በዚህ ሁኔታ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ከቅዱሳን አበው ጋር ቃል ኪዳን መሥርቶ እንደነበረ በቅዱስ መጽሐፍ በየቦታው ተጽፎ እናገኛለን፡፡

ይሁንና በዘመነ ሐዲስ ጌታችን ቃል ከገባባቸው ዐበይት ነገሮች አንዱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ነው፤ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በስመ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰበሰብ ኀላፊነት ተሰጥቶታል፤ ጌታችንም በስሙ በሚደረግ ጉባኤ እንደሚገኝ ቃል ገብቶአል፡፡ በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርእሰ መንበርነት፣ ቅዱስ ፓትርያርክ በመሪነት፣ ሊቃነ ጳጳሳት በአባልነት የሚገኙበት ዐቢይ ጉባኤ ነው፤ ቅዱስ ወይም ልዩ ጉባኤ የሚያሰኘውም ቅሉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በርእሰ መንበርነት የሚገኝበት በመሆኑ ነው፤ ይህ ጉባኤ ጌታችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እንደማይለየው ሲገልጽ ‹‹ወናሁ አነ እሄሉ ምስሌክሙ እስከ ኅልቀተ ዓለም፤ እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እኔ ከናንተ ጋር እኖራለሁ›› ብሎ በቃሉ አረጋግጦአል፤ (ማቴ. 28፥20)፡፡

እንግዲህ በየጊዜው ስመ እግዚአብሔርን ጠርተን በስሙ፣ ስለስሙ ብለን፣ የምናካሂደው ቅዱስ ጉባኤ ወይም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ያህል ታላቅ ክብርና ጽኑ የሆነ አምላካዊ ቃል ኪዳን ያለው እንደመሆኑ መጠን፣ ለደረጃው በሚመጥን ክብርና ልዕልና መካሄድ ይኖርበታል፡፡

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በአደራነት ያስረከበ ለዚህ ጉባኤ እንደሆነ በውል የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ ጉባኤ የእግዚአብሔር መንግሥት ወኪል እንደመሆኑ መጠን ድንበር የለውም፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት ድንበር የለውምና፤ ይህ ጉባኤ ገደብ የለሽ መንፈሳዊ ሥልጣን ከሕያው አምላክ ሲሰጠው ‹‹ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ›› ከሚል ትእዛዝ ጋር መታዘዙ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ ሥልጣን ድንበር የማይገድበው መሆኑን በግልጽ ያሳያል፤ (ማር. 16፡15)፡፡

በመሆኑም የዚህ ቅዱስ ገባኤ ሥራና ኀላፊነት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መሆኑን ሊሠመርበት ይገባል፤ ይህም በመሆኑ ነው ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም ክፍላተ ዓለም አብያተ ክርስቲያናትን ከፍታ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በማካሄድ ላይ የምትገኘው፡፡ ይሁንና አሁን የምንገኝበት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ወቅት፣ የሴኩላሪዝም አስተሳሰብ ያየለበት፤ የዓለም ሉላዊነት የበረታበት፣ የጽንፈንነትና የሽብርተኝነት መንፈስ የተስፋፋበት፣ እነዚህ ሁሉ በየፊናቸው ተሰልፈው በሃይማኖት ላይ ከባድ ተጽዕኖ የፈጠሩበት ዘመን ነው፤ ዓለም በዚህ ሥጋዊ ፍልስፍና እና ቊሳዊ አምሮት ቤተ ክርስቲያንን ለመውጋት ስትዘጋጅ እኛ የክርስቶስ ወኪሎች እንዲሁ ዝም ብለን የምናይበት ኅሊና ሊኖረን አይችልም፡፡

ቀደምት አበው “እሾህን በእሾህ” ብለው እንደተናገሩት፣ የዓለምን ጥበብ በክርስቶስ ጥበብ ለመቋቋም፣ በዓለም እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ መከታተልና ማወቅ፣ ለወደፊትም ሊያስከትለው የሚችል ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሰብኣዊና ባህላዊ ቀውስ አስቀድሞ በመተንበይ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ቃል ኀይል መጠበቅና መንከባከብ ከእኛ ይጠበቃል፡፡

በሃይማኖት ዙሪያ ያንዣበቡ እነዚህ ዓለም ዐቀፍ ተጽዕኖዎች እጅግ አስጊ ቢሆኑም፣ እነርሱን ለመከላከል ብሎም ለመቀልበስ አሁንም ቢሆን ጊዜው አልመሸም፤ በተለይም በሀገራችን ያለው ሕዝብ፣ አሁንም ምርጫው እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ በተጨባጭ የምናውቀው ሐቅ ነው፤ ይህንን ሕዝብ በሚገባ ማገልገል ከተቻለ፣ ችግሩን በሚገባ መቋቋም ይቻላል፡፡

ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑን በአግባቡ ለማገልገልና ለመጠበቅ፣ ከሁሉም በፊት የሕዝቡን ጥያቄ ማወቅ ያስፈልጋል፤ ቀጥሎም ለጥያቄው ተገቢ የሆነ መልስ በመስጠት ፍጹም መግባባት መፍጠር ይገባል፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሃይማኖት መሪዎችና ከአገልጋይ ካህናት የሚጠበቀው ሁለንተናዊ አገልግሎት በሚገባ ካገኘና በሃይማኖቱ እንዲኮራ የሚያስችል ሁኔታ ከተመቻቸለት፣ ለተጠቀሱ ዓለም ዐቀፍ ተጽዕኖዎች ተንበርካኪ አይሆንም፤ ስለሆነም የኛው የጥበቃ ስልት መቀየስ ያለበት በዚሁ መንፈስና አቅጣጫ ነው፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ በአሁኑ ጊዜ የሚጠይቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤
• ሕዝቡ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ለሃይማኖት መጠበቂያ ብሎ በእምነት የሚለግሰው ገንዘብና ንብረት ከምዝበራ ተጠብቆ ለታለመለት ዐላማ ብቻ እንዲውል ይፈልጋል፤
• በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም አስተዳደር ሰፍኖ፣ አድልዎ፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ መለያየት፣ በአጠቃላይ ከሃይማኖቱ መርሕ ጋር የማይጣጣም ኋላ ቀር አሠራርና አስተሳሰብ ተወግዶ፣ የተስተካከለ ሥርዐትን ማየት ይፈልጋል፤
• ስለሃይማኖት ክብርና ህልውና ከልብ የሚቈረቈሩ፣ መልካም የሆነ ሥነ ምግባርና የተስተካከለ ሰብእና ያላቸው፣ እንደዚሁም በኑሮአቸው ሁሉ ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንደሞዴል የሚጠቀሱ ውሉደ ክህነትና ሠራተኞች እንዲመሩት ይፈልጋል፤
• ሕዝቡ ቤተ ክርስቲያን በሁሉም መስክ ጠንካራ ዐቅምን ገንብታ፣ እንደዚሁም ለሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግር ደራሽና አለሁላችሁ ባይ ሆና ማየት እንደሚፈልግ ከሚያነሣው ጥያቄ ማወቅ ይቻላል፡፡

የእኛ ተልእኮ እግዚአብሔርንና ሕዝብን ማገልገል ከሆነ፣ የሕዝቡ ጥያቄም ከሞላ ጎደል የሚታወቅ ከሆነ፣ በተሰጠን አደራና ኀላፊነት መሠረት የሕዝበ ክርስቲያኑን ጥያቄ በጽሞና አዳምጠንና ተቀብለን፣ በቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌና ባሉን የቤተ ክርስቲያን ሕጎች ማእከልነት፣ ጥያቄውን የማስተናገድ ክርስቶሳዊ ግዴታ አለብን፡፡ ከሕግ የወጣ የሥራ አፈጻጸም ሲኖርም፣ ጥብቅ ክትትልና ቊጥጥር በማድረግ በወቅቱ ማረም ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል እንደመሆኑ መጠን፣ የቤተ ክርስቲያናችን መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችሉ ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀትና በማጽደቅ፣ እንደዚሁም በአፈጻጸማቸው ጥብቅ ክትትልና ቊጥጥር በማድረግ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን እሰየው የሚያሰኝ አሠራር ማረጋገጥ አለብን፤ ይኽ ሲሆን ብቻ ነው ሕዝቡን ከቊሳዊው ዓለም ማዕበል መታደግ የምንችለው፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ የተቀደሰ ክርስቶሳዊና ሐዋርያዊ ጉባኤ፣ ከልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያናችን አመራር አካላትና ከጉባኤው የሚቀርቡትን ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት በመፈተሽና በመመርመር፣ እንደዚሁም ሕጋዊና ቀኖናዊ መፍትሔ በማስቀመጥ፣ የተሳካ ውጤት ያስመዘግብ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየጸለይንና ከልብ እየተመኘን የ2008 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዛሬ መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ፤ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!