የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም የዐቢይ ፆም መግቢያ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በተለያዩ የውጭ ሀገር ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ወገኖቻችን በሙሉ፡፡ በጾምና በጸሎት፣ በሰላምና በፍቅር የሚቀርብለትን የምእመናን ተማኅፅኖ ተቀብሎ ምሕረትንና ይቅርታን ለሕዝቡ የሚያድል እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሁለት ዓመተ ምሕረት የጾመ ኢየሱስ ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፤ ወኢይትኀፈር ገጽክሙ
ወደ እርሱ ቅረቡ፤ ያበራላችሁማል፣ ፊታችሁም አያፍርም።”
(መዝ. 34፥5)

አምላካችን እግዚአብሔር የምልአተ ዓለም የበላይ ጠባቂና አስተዳዳሪ፣ መጋቢና መሪ፣ ውሳኔ ሰጭና ተቈጣጣሪ ነው፤ እግዚአብሔር በምልአተ ዓለም ውስጥና ከዚያም በላይ በምልአትና በርቀት ያለ ነውና ሁሉንም ማድረግ የሚቻለውና የሚሳነው ነገር የሌለ የኀያላን ኀያል፣ የጥበበኞች ጥበብ፣ የልዑላን ልዑል ነው፡፡ የፍጡራን ችግሮች በሙሉ ሊቀረፉ የሚችሉት በእሱ ፈቃድና ጥበብ ብቻ ነው፤ እኛ ፍጡራን የእርሱ ፈቃድ ማስፈጸሚያ እንሆን እንደሆነ እንጂ በራሳችን ዕውቀትና ጒልበት ብቻ የምናከናውነው ሥራ፣ የምናርቀው መከራ የለም፤ ይህንን ማድረግ የሚያስችል ዐቅም ቢኖረን ኖሮ ዓለማችን ሁሌ በሥጋት ተወጥራ ለመኖር አትገደድም ነበር፡፡

እግዚአብሔር በዳኝነቱ ኰናኒ በርትዕ፣ ፈታሒ በጽድቅ ነውና በበደላችን ከመፍረድ ወደኋላ ስለማይል ኰናኒ በርትዕ ይባላል፤ ንስሓ ገብተን፣ በጾምና በጸሎት ልባችንን ሰብረን፣ ወደእርሱ ከተመለስን ደግሞ፣ ምሕረቱንና ይቅርታውን ለመስጠት ጊዜ የማይወስድ ነውና ፈታሒ በጽድቅ ይባላል፡፡ ‹‹እስከ ሺሕ ትውልድ ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን፣ ኀጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ከቶ የማያነፃ ነው›› የሚለው፣ የእግዚአብሔር ቃልም ይህንን ያረጋግጣል፤ ይህም ማለት ንስሓ ገብቶ በጾምና በጸሎት ለሚቀርብ ይቅር የሚል፣ ንስሓ ሳይገባ በበደሉ ጸንቶ ለሚኖር ግን ይቅር የማይል እውነተኛ ዳኛ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ችግርንና ጭንቀትን የማስወገድ ፍጹምና ወሳኝ ኀይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ ከሆነ በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን እንደዚሁም በየግላችን ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች እንዲታደገን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ግዴታችን ይሆናል፤ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ደግሞ የተሰበረ ልብ ሊኖረን ይገባል፤ የተሰበረ ልብ ማለት በበደሉ እጅግ የተጸጸተና ዳግም ኀጢአትን ላለመፈጸም በቍርጥ የወሰነ ማለት ነው፤ ከዚህ አንጻር ጾም የኅሊና ጸጸትን ከፍ በማድረግ ለእግዚብሔር እንድንታዘዝ የሚያደርገን ፍቱን መሣሪያ ነው፤ ስለሆነም ወደ እግዚአብሔር ቀርበን ለመለመንና ለመሰማት፣ ወደ ንስሓም ለመገሥገሥ ጾምና ጸሎት አስፈላጊዎቻችን ናቸው ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

ጾም ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጀምሮ የቀደምት አበው፣ የነቢያት፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስና የሐዋርያት፣ እንደዚሁም የሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ቀዋሚ ሕግ ነው፤ ውጤቱም ምሕረትና ይቅርታ፣ ሰላምና መዳን እንደሆነ በነነዌ የሆነውን ታሪክ ማስረጃችን ነው፡፡ ጾም የኀጢአትና የበደል አበጋዝ የሆነው ዲያብሎስን ድል ለማድረግም ዐቢይ መሣሪያ ነው፤ ዲያብሎስ በአዳም ያስለመደውን በመብል አሳስቶ የመጣል ስልት፣ ጌታችን በጾም ኀይል አሳፍሮና ድል አድርጎ እንደመለሰው ከቅዱስ ወንጌል እንማራለን፤ በዚህም ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር በፈቃደ ዲያብሎስ ላይ የበላይነትን እንዲጐናጸፍ የሚያደርግ ረቂቅ ኀይል እንደሆነ እንገነዘባለን፤ እኛ ክርስቲያኖች ጾምን የምንጾመው ከዚህ በላይ በተጠቀሰው መሠረታዊ አስተምህሮ ነው፡፡

ጾም የሚያስገኘው መንፈሳዊ ኀይል ብዙ እንደሆነ ሁሉ፣ ሠራዊቱም ብዙ ነው፤ ጾም ሲባል ብዙ ጊዜ ወደ ሰዎች አእምሮ የሚመጣው የእንስሳት ውጤት ከሆኑ ምግቦች መከልከልና ሰዓታትን ጠብቆ መመገብ የሚለው ነው፤ ነገር ግን የጾም ዐላማ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነውና ከምግብ መከልከል ብቻ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብና መልስ እንድናገኝ የሚያስችለን አይደለም፤ ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ በፍጹም ሓሳባችን፣ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን ነውና በአካላችንና በመንፈሳችን ሁሉ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ ዝግጁ በመሆን ልንጾም ይገባል፡፡ በመሆኑም በጾም ወቅት ከጥላቻና ከዛቻ፣ ፍትሕን ከማጕደልና ሰውን ከመበደል፣ ከቂምና ከበቀል ርቀን፣ እጃችንም፣ እግራችንም፣ አፋችንም፣ ዓይናችንም፣ ጆሮአችንም፣ ውስጣችንም፣ ውጫችንም ሁሉ በመልካም ሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ሕይወት አሸብርቀን መጾም ይገባናል፤ በዚህ ወቅት መስማትና ማዳመጥ ያለብን እግዚአብሔርና እግዚአብሔርን ብቻ ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና ስምምነት፣ ዕርቅና ይቅርታ፣ ምሕረትና ቸርነት፣ ርኅራኄና ኀዘኔታ፣ ጸሎትና ምፅዋት፣ ፍትሕና እውነት፣ እኩልነትና ኅብረት ነው፡፡ እነዚህን በሥራ በመተርጐም እየጾምን ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን የጨለመብንን ሁሉ ያበራልናል፤ በፊቱም ሳናፍር የፈለግነውን ሁሉ አግኝተን እንመለሳለን ፡፡

በመጨረሻም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከገጠማት ሥጋትና ጭንቀት ለመገላገል በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ከመማፀን የተሻለ አማራጭ ሊኖር አይችልምና ሕዝበ ክርስቲያኑ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰቂለ ኅሊና፣ በተመሥጦ ልቡና፣ ጽሙድ እንደ በሬ፣ ቅኑት እንደ ገበሬ ሆኖ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለሕዝቦች አንድነትና እኩልነት መጠበቅ፣ ወደ እግዚአብሔር በምሕላ እንዲያመለክት በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ወርኀ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡