ከግንቦት 10 ቀን እስከ ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቊጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከተፈጸመበት ግንቦት 9 ቀን 2014ዓ.ም. ጀምሮ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1. የ2014ዓ.ም. የግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ መክፈቻ ንግግር በቤተ ክርስቲያናችንና በሀገራችን የተከሠተውን የሰላም ዕጦት ተከትሎ የደረሰው የሰው ሕይወት ኅልፈትና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል የካህናትና የምእመናንን ኅልፈተ ሕይወት ላይ ያተኰረ ሲሆን፤ በዚሁ ላይ የተነጋገረው ምልአተ ጉባኤ በሰፊው ተነጋግሮ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
2. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተከናወነው የመንፈቅ ሪፖርት፣ ምልአተ ጉባኤ ያዳመጠና የገመገመ ሲሆን በስድስት ወራት ውስጥ ተወስነው ፍጻሜ ያላገኙ ጉዳዮች አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ፍጻሜ እንዲያገኙ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
3. ሀገራዊ ሰላምን አስመልክቶ፣ በችግሩ ዙሪያ የተነጋገረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአሁኑ ደረጃ በሀገራችን ያለው የሰላም ዕጦት ላይ በሰፊው ተወያይቶ በቀጣይ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ አጠቃላይ ሰላም በሚሰፍንበት መልኩ ተነጋግሮ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዲቻል፣ ቤተ ክርስቲያናችን የአስታራቂነት ሚናዋን መጫወት እንድትችል ለማድረግ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
4. ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን በተከሠተው የሰላም ዕጦት ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችንና በካህናት አገልጋዮቻችን እንዲሁም በምእመናኖቻችን ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የበዓል ማክበሪያ ቦታዎች መነጠቅን አስመልክቶ ጉባኤው የተነጋገረ ሲሆን አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በቀጣይም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግልን በመጠየቅ፣ እስከ አሁን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ደረሰ የተባለው ችግር በዐይነትና በቊጥር ተለይቶ ለሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥት አካላት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
5. በሀገራችን በተከሠተው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ለተፈናቀሉና ለተሰደዱ ወገኖች፣ ለፈረሱና ለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋሚያ፣ ለተዳከሙ የአብነት ት/ቤቶች መደጐሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
6. በትግራይ ክልል የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያኒቱን አስመልክተው በ30/04/2014 እና በ3/06/2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ምልአተ ጉባኤው ገምግሞ በቀጣይ የክልሉ አባቶች በማእከል እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው ለሀገር አንድነትና ሰላም በጋራ እንዲሠሩ ምልአተ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
7. ቤተ ክርስቲያናችን በዘመናት በርካታ የልማት ተግባራትን ስታከናውን የቆየች ቢሆንም ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሚሰጥ የሕክምና ማዕከል ሳታቋቁም መቅረቷ ተገቢ አለመሆኑን በመገምገም፣ በቀጣይ የሕክምና ማዕከሉ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲገነባ ጉባኤው ወስኗል፡፡
8. በየሦስት ዓመቱ የሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ እና የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅን አስመልክቶ በተደረገው ምርጫ፡-
1. ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሰሜን አሜሪካ ኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣
2. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕር ዳር ከተማ ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርጎ በመምረጥ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ ሰይሟል፡፡
9. በአጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጉባኤ ላይ በቆየባቸው ቀናት ባደረገው ሰፊ ውይይት፡-
• ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት መጠናከር፣
• ለሀገራችን፣ ለሕዝባችንና ለመላው ዓለም ሰላም መገኘት፣
• ለተሰደዱና ከቀያቸው የተፈናቀሉ መረጋጋትና ወደ ቀያቸው መመለስ፣
• በሀገራችን ጦርነትና የሰላም ዕጦት በሚወገድበት ሁኔታ በሰፊው በመምከርና ለዘለቄታዊ ሰላም አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በመሆኑም መላው ሕዝባችንና የመንግሥት መሪዎች ሁሉም ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ከምንጊዜወም በላይ በአንድነት በመነሣ በትኵረት እንዲሠሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከግንቦት 9-25 ቀን 2014ዓ.ም. በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ሀገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ሲወያይ በመቆየት በዛሬው ዕለት ስብሰባውን በጸሎት ዘግቷል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን
እንዲሁም ለመላው ሕዝባችን ሰላሙንና አንድነቱን ይስጥልን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡