• Amharic  
  • English  
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • አርዕስተ ሊቃነ ጳጳሳት
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በዓለ ደብረ ታቦርን በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

 

የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ትምህርት ነበር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

‹‹መነ ይብልዎ ሰብእ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው
ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?››
(ማቴ. 16፥13)

በሀገራችን በኢትዮጵያና በተለያዩ ክፍላተ ዓለም ሆናችሁ ይህን የቅዱስ ወንጌል ቃል በመስማት ላይ የምትገኙ ውሉደ እግዚአብሔር ሁሉ፣ እግዚአብሔር አምላካችን በረከቱን፣ ጸጋውንና መልካም ስጦታውን ሁሉ እንዲያበዛላችሁ እየጸለይን፣ እንኳን ለበዓለ ደብረ ታቦር በሰላም አደረሳችሁ እንላለን ፡፡

የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ባሕርዩንና ምሥጢረ መንግሥቱን የገለጸበት ቀን በመሆኑ፣ በክርስትናው ዓለም ዐቢይ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ነው ፡፡

የታቦር ተራራ ቀደም ሲል ከክርስቶስ ልደት በፊት ዲቦራ የተባለች ነቢይት በዚህ ተራራ ላይ ቆማ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይና የጦር አመራርን በመስጠት፣ ሕዝበ እስራኤልን ለመውጋትና ለመውረር በእብሪት ተነሣሥቶ የመጣውን ሲሣራን፣ በባርቅ አዝማችነት ድል ያደረገችበት የድል ተራራ እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎአል (መሳ. 4፥4-24)፡፡ ይህ ድል በዘመነ ሥጋዌ የሚነሡትን የኑፋቄ ትምህርቶች ሁሉ በደብረ ታቦር በሚገለጸው መለኮታዊ ትምህርት ድል የሚደረጉ መሆናቸውን የሚያመለክት ነበር፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ ስምህንም ያመሰግናሉ፤ ክንድህ ከኀይል ጋር በዚያ ይገለጻል” በማለት እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ተራራ ላይ ኀይለ መለኮቱን ሲገልጽ፣ ተራራው በብርሃነ መለኮቱ ደምቆ የደስታ ተራራ እንደሚሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንድ ሺሕ ዓመት ገደማ በትንቢት ተናግሮለታል (መዝ. 88፥12)፡፡

የክርስትና ሃይማኖት ከጥንተ ፍጥረት ጀምሮ በልዩ ልዩ ኅብረ ትንቢት፣ በልዩ ልዩ ኅብረ አምሳል፣ በልዩ ልዩ ኅብረ ቃል እንደ ሰንሰለት ተያይዞ የመጣውን ተስፋ-ድኅነት መሠረት አድርጎ የቀጠለ ሃይማኖት እንጂ፣ በሆነ ፈላስፋ ወይም የፈጠራ ክሥተት የመጣ አይደለምና፣ እንደ ሌላው ትምህርተ ክርስትና ሁሉ፣ የታቦር ተራራ መለኮታዊ ክሥተትም በድንገት የተገለጸ ሳይሆን፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት ለአንድ ሺሕ ዓመታት ያህል እየተነገረ የመጣና በተስፋ ሲጠበቅ የነበረ ድንቅ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ክሥተት እንደሆነ ከቅዱስ መጽሐፍ ትምህርት እንገነዘባለን፡፡ የትንቢትና የምሳሌ ሁሉ መዳረሻ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፣ መድኀኒታችን በሥጋ በዚህ ዓለም ተገልጾ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ሲያስተምር፣ በተነገረው ትንቢት መሠረት መለኮታዊ ባሕርዩንና ድል አድራጊው ምሥጢረ መንግሥቱን በደብረ ታቦር ላይ ገለጸ፤ የነገሩንም አፈጻጸም ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ሚከተለው ያስተምረናል፡- ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕዝቡ መካከል ተገኝቶ ከሚያስተምረው ጥልቅ ትምህርትና ከሚሠራው ድንቅ ተኣምር የተነሣ ሕዝቡ ስለማንነቱ ብዙ ያወራና ይናገር ነበር ፡፡

ጌታችንም በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የተለያየ አባባል ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄድ ለማረም በፈለገ ጊዜ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?›› በማለት ደቀ መዛሙርቱን ጠየቀ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሕዝቡ የሚለውን በመጥቀስ አንዳንዶቹ ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ አንዳንዶቹም ኤርምያስ ነው ይሉሃል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ ነው ይሉሃል፣ ሌሎቹ ደግሞ ከቀደምት ነቢያት አንዱ ሳይሆን አይቀርም ይሉሃል ብለው መለሱ፡፡ ጌታችንም እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ? አላቸው፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መለሰ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ትክክለኛውንና እውነተኛውን መልስ ስለመለሰ ጌታችን ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ጴጥሮስ ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋዊና ደማዊ አእምሮ ይህንን አልገለጸልህምና ብፁዕ ነህ›› ብሎ መልሱን ከምስጋና ጋር ተቀብሎአል፤ (ማቴ. 16፡13-19)፡፡

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጌታችን ነቢይ ወይም ከነቢያት አንዱ ሳይሆን ‹‹የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ›› መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ አረጋገጠላቸው፡፡ ከዚህ ቀደምም ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠረ ጊዜ ‹‹ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ›› ሲል ስሙንና ማንነቱን በግልጽ አሳውቆ ነበር (ሉቃ. 1፡30-35)፡፡ እግዚአብሔር አብም ጌታችን በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› በማለት ገልጾ ነበር (ማቴ. 3፡17)፡፡

በጣም የሚገርመው ደግሞ አጋንንት ሳይቀሩ ‹‹አንተ ማን እንደሆንህ ዐውቀናል፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› እያሉና እየሰገዱ በተደጋጋሚ መመስከራቸው ነው (ሉቃ. 4፥31-41)፡፡ ይሁን እንጂ ጌታችን የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደሆነ በፈጣሪም ሆነ በፍጡራን ዘንድ ብዙ ጊዜ ቢነገርም ሰዎች ይህን መገንዘብና ማወቅ አቅቶአቸው ወዲያና ወዲህ ሲባዝኑ በመገኘታቸው፣ ጌታችን በስማቸው እየተጠቀሰ ያሉትን ነቢያት በተገኙበት፣ በታቦር ተራራ ላይ ማንነቱንና የመንግሥቱን ምንነት ለመግለጽ ብሎ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ በቂሳርያ ምስክርነቱን በሰጠ በስድስተኛው ቀን፣ ሦስቱ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ በዚያም ፊቱ ተለውጦ እንደ ፀሓይ ብርሃን ሆነ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፤ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩ፤ ብሩህ ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነውና እርሱን ስሙት›› የሚል ድምፅ መጣ፤ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ማለትም ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብም ከግርማ መለኮቱ የተነሣ ፈርተው በምድር ላይ ወደቁ፤ በመጨረሻም ጌታችን ዳሰሳቸውና እንዲነሡ አደረጋቸው (ማቴ. 17፥1-8)፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው ዓለም በጌታችን ማንነትና በሚያወርሳት መንግሥቱ ምንነት መንታ መንገድ ላይ ቆማ በጥርጥርና በክሕደት እንዳትጎዳ እውነተኛው ትምህርትና እምነት የትኛው እንደሆነ ለይታ እንድታውቅ ለማድረግ ነው፡፡ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ካበሠረበት ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ደብረ ታቦር ድረስ ስለጌታችን ማንነት የተነገሩ ሁሉ ፣ጌታችን ‹‹የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ መሆኑን የሚያስረግጡ ናቸው፤ ይህም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር የተወለደ እግዚአብሔር መሆኑን አረጋግጠዋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መባሉ ሰዎች ከእግዚአብሔር በባሕርይ ሳይወለዱ፣ በጸጋ ወይም በስጦታ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን መብት ተሰጥቶአቸው ውሉደ እግዚአብሔር እንደሚባሉት ዐይነት ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ብቸኛ የባሕርይ ልጅ ነው ለማለት ነው ፡፡

በሌላ አባባል በባሕርያዊ ልደት ክዋኔ ከሰው የተወለደ ሰው፣ ከእንስሳም የተወለደ እንስሳ እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር በባሕርይ የተወለደም እግዚአብሔር ከመሆን በቀር ሌላ ሊሆን አይችልምና ጌታችን የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ በመሆኑ እግዚአብሔር ነው ማለት ነው፡፡ ፍጡራን በሙሉ በባሕርይም፣ በመልክም ራሳቸውን የሚመስል ልጅ እንደሚያስገኙና ባሕርያዊ ውርስንም በዘር እንደሚያስተላልፉ ሁሉ፣ ጌታችንም የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ስለሆነ በባሕርዩም፣ በመልኩም እንደአባቱ ነው፤ እንደዚሁም ለአባቱ ያለው ሁሉ ገንዘቡ በመሆኑ እንደ አባቱ እግዚአብሔር ነው፤ በዚህ የባሕርይ ልጅነት ዐይነት ከእግዚአብሔር የተወለደ ሌላ ልጅ የለምና ቅዱስ መጽሐፍ ጌታችንን ‹‹አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ወይም ወልድ ዋሕድ›› ይለዋል ፡፡ ይህ አገላለጽ የጌታችን ወልደ እግዚአብሔርነት በጸጋ ወይም በችሮታ ከእግዚአብሔር ከተወለድነው ከክርስቲያኖች ልጅነት ጋር በእጅጉ የተለየ መሆኑን ያስረዳል፣ (ዮሐ. 1፡ 12-18፣ ዮሐ. 3፡16)፡፡

ጌታችንም ይህንን ሲያመለክት ነው ‹‹እኔና አብ አንድ ነን፤ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተም የእኔ ነው›› ያለው (ዮሐ. 10፡30፣ 14፡11፤ 16፡15፤ 17፡10)፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም ‹‹በመጀመሪያው ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ … ያ ቃል ሥጋ ሆነ›› በማለት የጌታችንን እግዚአብሔርነት በማያሻማ መልኩ በግልጽ ጽፎልናል፤ (ዮሐ. 1፡1-14)፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ዐቢይ ነገር ጌታችን የእግዚአብሔር አብ ልጅ ቢሆንም፣ በአባቱና በእርሱ መካከል መቀዳደምና መበላለጥ የሌለ መሆኑን ነው፤ ምክንያቱም ባሕርየ እግዚአብሔር አንድ ከመሆኑም ሌላ በሦስቱ አካላት መካከል የባሕርይና የህልውና ልዩነት የለምና ነው፡፡ ቃል የሚለው የጌታችን ስምም ይህንን በሚገባ ይገልጸዋል፤ ምክንያቱም፡- የቃል ህላዌ ከልብና ከእስትንፋስ እንደማይቀድም ወይም እንደማይዘገይ ሁሉ ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስም በህላዌው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ የማይቀድም ወይም የማይዘገይ መሆኑን በግልጽ ያስረዳልና ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ከጥንት ዘመን ጀምሮ ማለትም ከዘመነ ብሉይ አንሥቶ በግልጽና በማያሻማ መልኩ የተገለጸ ቢሆንም፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አባባሎችን በመፍጠር መለያየታቸው አልቀረም፡፡ ሆኖም ከሰዎች ደካማ ዕውቀትና አናሳ ግንዛቤ የተነሣ ችግሩ መከሠቱ ባይቀርም፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ግን ጌታችን ‹‹የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ›› እንደሆነ በማያሻማ መልኩ ነግረውናል፤ እግዚአብሔር አብም በፈለገ ዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ይህንን አረጋግጦልናል፤ ቅዱስ ገብርኤልም በናዝሬት ከተማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባበሠረ ጊዜ፣ ቅዱስ ጴጥሮስም በቂሳርያ እግዚአብሔር ገልጾለት በመሰከረ ጊዜ፣ አጋንንትም በቅፍርናሆም ጌታችንን ባዩ ጊዜ፣ እርሱ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክረዋል፡፡

የእግዚአብሔር ልጅ ማለትም እግዚአብሔር ማለት እንደሆነ ተቃዋሚዎቹ አይሁድ ሳይቀሩ ያወቁትና የተረዱት ሐቅ ነበረ፡፡ አይሁድ ይህን ግንዛቤ ሊይዙ የቻሉት፣ የሰው ልጅ ሰው ከመሆን በቀር ሌላ እንስሳ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጅም እግዚአብሔር ከመሆን በቀር ሌላ ሊሆን እንደማይችል በመገንዘባቸው ነው፤ አይሁድ ቁም ነገሩን አምነው ባይቀበሉትም አባባሉን ግን ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ተገንዝበውታል፡፡ ነገሩም እንዲህ ተገልጾአል፡- ‹‹ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ አይሁድ ሊገድሉት ፈለጉ›› ይላል ቅዱስ መጽሐፍ፤ ይህ የአይሁድ ቍጣ፣ እግዚአብሔር አባቴ ነው ማለቱ፣ እግዚአብሔር ነኝ ማለቱ ነው፤ ከሚል የተነሣ እንደሆነ ጥቅሱ ያመለክታል (ዮሐ. 5፡18)፡፡

ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች የነቢያትን ስም እየጠቀሱ ስለማንነቱ ይናገሩት የነበረውን አባባል ፍጹም ስሕተት መሆኑን ለማሳየት፣ በቅዱስ ጴጥሮስ የተነገረውን ምስክርነት፣ እንደገና በዓበይተ ነቢያት በሙሴና በኤልያስ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በባሕርይ አባቱ በእግዚአብሔር አብ፣ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ መሆኑን በታቦር ተራራ ላይ አረጋገጠ፤ ይህም ከሆነ ዓለም ስለጌታችን ማንነት መቀበል ያለባት እውነት ይህና ይህ ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ስሕተትም፣ ቅዠትም፣ ውሸትም ከመሆን በቀር ምንም ዐይነት እውነትነት የለውም ፡፡

እኛም ከዚህ ተነሥተን ስለጌታችን ማንነት አምነን ስንመሰክር፡- ‹‹በአንድ የእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፤ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ የሆነ፤ ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ ያለእርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የሌለ›› እያልን እናምናለን፤ እንመሰክራለንም ፡፡ ከዚህም ጋር ‹‹ጌታችን ሰውም፣ አምላክም ነውና በወልደ እግዚአብሔርነቱ እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ፣ በክርስቶስነቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጅም የሰው ልጅም መሆኑን አንዘነጋም፤ ስለሆነም ወልደ እግዚአብሔርና ወልደ ማርያም የሆነው ክርስቶስ ከሁለት አካላት አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርያት አንድ ባሕርይ ሆኖ በተዋሐደ ህላዌ በታቦር ተራራ ላይ ቆሞ ሳለ፣ አብ ‹‹ይህ የምወደው ልጄ ነው፤ እርሱ የሚላችሁን ስሙ›› በማለቱ፣ ጌታችን በተዋሕዶ ‹‹የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ›› መሆኑን ዐውቀናል፤ አምነናልም፤ ከዚህ አኳያ ስለክርስቶስ ማንነት የሚጠይቀን ካለ መልሳችንም፤ እምነታችንም ምሥጢረ ተዋሕዶ የተገለጸበት ይኸው የደብረ ታቦር ትምህርት ብቻ ነው ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ላይ የገለጸው የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅነቱን ብቻ ሳይሆን ምሥጢረ መንግሥቱንም ጭምር ነው፡፡ ነቢያትም፣ ጌታችንም፣ ሐዋርያትም፣ ብዙ የተናገሩላት፣ የእግዚአብሔር ልጆች የሆንን ምእመናንም በተስፋ የምንጠባበቃት የእግዚአብሔር መንግሥት፣ በመጨረሻ ጊዜ ተገልጻ ሁሉንም በቍጥጥሯ ሥር እንደምታደርግ ይታወቃል፤ (ራእ. 21፥1-4)፡፡ ስለሆነም የዚህ መንግሥት ገዥ ማን ነው? በዚህ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩስ እነማን ናቸው? ይህ መንግሥት ሲገለጥ የሚሆነው ክሥተትስ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ የደብረ ታቦር ክሥተት በሚገባ ገልጾታል፡፡ የታቦር ተራራ ውብና አስደሳች ከመሆኑም ሌላ በጣም ከፍ ያለ ተራራ ነው፤ ቅዱስ ያሬድ የዚህን ተራራ ውበት ሲገልጽ ‹‹ሰላም ለከ ኦ ደብረ ታቦር ዘከለሎ ብርሃን ይሤኒ ላሕዩ እምኵሉ አድባር፤ ከተራሮች ሁሉ ይልቅ ውበትህ ያማረ፣ ብርሃነ መለኮት የጋረደህ ደብረ ታቦር ሆይ ሰላምታ ላንተ ይገባል›› ብሎአል፡፡

በመሆኑም ይህ ውብ፣ ብርሃናዊና ከፍ ያለ ተራራ የመንግሥተ ሰማያት አምሳያ ነው፤ ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ በግርማ መለኮት፣ በክበበ ትስብእት በዚህ ተራራ እንደተገለጸ ሁሉ፣ በመጨረሻ ጊዜ በምትገለጸዋ የእግዚአብሔር መንግሥትም ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ተገልጾ ብርሃንዋና መሪዋ፣ ገዢዋም ሆኖ በመካከልዋ እንደሚኖር ምሥጢሩ ያሳያል፡፡ በታቦር ተራራ ላይ ከነቢያት፣ ሙሴና ኤልያስ፣ ከሐዋርያት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብ፣ ከሕያዋን ኤልያስ፣ ከሙታን ሙሴ፣ ከደናግል ኤልያስ፣ ከሕጋውያን ሙሴ ተገኝተዋል።

ይህም ከክርስቶስ በፊትና በኋላ የተነሡ ቅዱሳን፣ ሙታንና ሕያዋን፣ ደናግልና ሕጋውያን በአንድነትና በእኩልነት በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ በፍጹም ደስታ እንደሚኖሩ ምሥጢሩ ያመለክታል (1ቆሮ. 15፥52፣ 1ተሰ. 4፥15፡17)፡፡ በመሆኑም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምንነት የሚጠይቀን ካለ የእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉም በላይ ከፍ ያለችና ውብ የሆነች፣ ዕጹብ ድንቅ በሆነ መለኮታዊ ብርሃን አሸብርቃ የምትኖር፤ ክርስቶስ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በቅዱሳኑ ላይ ነግሦባት የሚኖር፣ በዘመነ ብሉይም ሆነ በዘመነ ሐዲስ የተነሡ ቅዱሳን ሁሉ የሚገኙባት፣ ሙታንም ሆኑ ሕያዋን፣ ሕጋውያንም ሆኑ ደናግል፣ በአንድነትና በእኩልነት ከብረውና ደስ ተሰኝተው የሚኖሩባት፣ ዘለዓለማዊት መንግሥት እንደሆነች ከደብረ ታቦር በተማርነው ትምህርት መሠረት እንመልስለታለን፤ በዚህም አምነን እንኖራለን፡፡

የእግዚአብሔር መንግሥት ለወደፊቱ በግልጽ የምትመጣበት ጊዜ እንዳለ ብናውቅም፣ ዛሬም ቢሆን በዓለሙ ሁሉ በገዥነት አለች፤ ይልቁኑም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዛሬም የእግዚአብሔርን ሕዝብ በመምራት ትገኛለች፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ በዋናነት የሚተዳደረውና የሚመራው በእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለመሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያና እግዚአብሔር የተለያዩበት ጊዜ ፈጽሞ የለም፤ ዛሬ ለዓለም ሕዝብ ምሥጢር ሆኖ የሚገኘው የሕዝባችን አንድነትና ነፃነት የእግዚአብሔር ሕዝብ ከመሆናችን የተገኘ እንጂ ሌላ እንዳይደለ አንዘንጋ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ከደብረ ታቦር አስተምህሮ የተወረሰ ነው፤ ደብረ ታቦር የብሉዩንና የሐዲሱን፤ ሕጋዊውንና ድንግሉን፣ ፈጣሪንና ፍጡራንን፣ ሕያዉንና ምዉቱን በአንድነት በእግዚአብሔር መንግሥት ክልል ውስጥ ያገናኘ የእግዚአብሔር መንግሥት አምሳያ ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ይህንን ትምህርት ተቀብላና እንደ ደብረ ታቦር የእግዚአብሔር መንግሥት ተምሳሌት ሆና፣ የተለያየ ቋንቋና ባህል ያላቸውን ልጆቿን ሁሉ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በክብር፣ በስምምነትና በወንድማማችነት አስማምታና አቅፋ ለዝንተ ዓለም የነበረች ቅድስት ሀገር ናት፤ ይህ ለማንም ሆነ ለማን ያልተሰጠ ልዩ ጸጋና በረከት ለኢትዮጵያውያን በምልአት የተሰጠ በመሆኑ ልናከብረውና ልንጠብቀው ይገባል፤ በዚህም እጅግ ደስ ሊለንና ለዚህ የመረጠንን እግዚአብሔርን ዘወትር ልናመሰግን ይገባል፡፡

ዛሬም እንደ ትናንቱ በወንድማማችነት፣ በፍቅር፣ በስምምነት፣ በእኩልነት በመዋደድ፣ በመከባበር፣ በመተማመን የተመሠረተ አንድነትን፣ ነፃነትንና ሃይማኖትን ጠብቆ መኖር ለኢትዮጵያውን ከማንኛውም በላይ የሆነ ክብርና ጸጋ ነው፤ የቀደሙት ኢትዮጵያውን አበው ለዝንተ ዓለም የገነቡት ይህ ጠንካራና ጽኑ ግንብ በተራ ምክንያት እንዳይፈርስ በሚገባ መጠበቅ አለብን ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም፤ ባሉበት ብቻ ተጠብቀው መኖር አለባቸው፤ ሕዝቡም ይህንን መጠበቅ አለበት፤ የደብረ ታቦር አስተምህሮ ይኸው ነውና ፡፡ ‹‹ጸጋ ዘአብ ሂሩት ዘወልድ ሱታፌ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀሉ ምስሌየ ወምስለ ኵልክሙ›› ‹የአብ ጸጋ፣ የወልድ ቸርነት፣ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት፤ ይህን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን ትምህርተ ወንጌል ከምትከታተሉ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ካላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁለ ጋር ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን!

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on WhatsApp
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/001-2-1000.jpg 664 1000 tc3 https://eotcp.org/a/wp-content/uploads/logo-am.svg tc32016-08-19 13:08:292025-01-28 13:10:09ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በዓለ ደብረ ታቦርን በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
Search Search

Recent Posts

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሸገር ከተማ ሀገረ ስብከት የለገጣፎ ኆኅተ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ምርቃት ሕንጻ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጡ
  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በማስመልከት ለኢትዮጵያና ለሳዑዲ መንግሥታት፣ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ
  • መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
  • ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ዘተናገረ በበዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወኣምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምእት ዓሠርቱ ወሰምንቱ ዓመተ ምሕረት

Archives

  • May 2026
  • April 2026
  • March 2026
  • February 2026
  • April 2025
  • February 2025
  • December 2024
  • October 2024
  • September 2024
  • August 2024
  • June 2024
  • May 2024
  • March 2024
  • October 2023
  • September 2023
  • November 2022
  • October 2022
  • September 2022
  • August 2022
  • June 2022
  • May 2022
  • April 2022
  • February 2022
  • January 2022
  • October 2021
  • September 2021
  • August 2021
  • May 2021
  • March 2021
  • January 2021
  • November 2020
  • October 2020
  • September 2020
  • August 2020
  • May 2020
  • April 2020
  • March 2020
  • February 2020
  • January 2020
  • November 2019
  • October 2019
  • September 2019
  • July 2019
  • June 2019
  • May 2019
  • April 2019
  • March 2019
  • January 2019
  • October 2018
  • September 2018
  • August 2018
  • July 2018
  • May 2018
  • April 2018
  • February 2018
  • January 2018
  • October 2017
  • September 2017
  • August 2017
  • July 2017
  • June 2017
  • May 2017
  • April 2017
  • March 2017
  • February 2017
  • January 2017
  • October 2016
  • September 2016
  • August 2016
  • June 2016
  • May 2016
  • April 2016
  • March 2016
  • January 2016
  • November 2015
  • October 2015
  • September 2015
  • August 2015
  • May 2015
  • April 2015
  • February 2015
  • January 2015
  • November 2014
  • October 2014
  • September 2014
  • August 2014
  • May 2014
  • April 2014
  • February 2014
  • January 2014
  • October 2013
  • September 2013
  • June 2013
  • May 2013
  • March 2013
© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Link to: ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ/ም የጾመ ፍልሰታ መግቢያ ቃለ ቡራኬና ምዕዳን Link to: ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ/ም የጾመ ፍልሰታ መግቢያ ቃለ ቡራኬና ምዕዳን ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ/ም የጾመ ፍልሰታ መግቢያ ቃለ ቡራኬና... Link to: መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት መልእክት Link to: መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት መልእክት መስከረም 1 ቀን 2009 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ...
Scroll to top Scroll to top Scroll to top