ታኅሣሥ 29 ቀን የ2006 ዓ.ም. የልደት በዓል አስመልክቶ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየሆስቲታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፣
ወልድ ተብሎ ውሉድ እንድንባል ላበቃን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!
“ወናሁ ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ ወትሰምይዮ ስሞ ኢየሱስ ዘውእቱ ያድኅኖሙ ለሕዝቡ እምኀጢአቶሙ፤እነሆ ትፀንሻለሽ፣ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፣ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና፣ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” (ሉቃ. 1፥31፤ ማቴ. 1፥21)፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው፤ ዘለዓለማዊና ቀዳማዊ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ምክንያት የሆነው፣ የሰው ኀጢአት ነው፡፡ ሰው በኀጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ ክብሩን ካጣ በኋላ፣በነፍሱም ሆነ በሥጋው፣ለአጠቃላይ ውድቀት ተዳረገ፤ ንጹሕ የነበረ ባሕርዩ እንደ ሰኔና እንደ ሐምሌ ጎርፍ ደፈረሰ፤ የኀጢአት ድፍርሱም እየባሰና እየከፋ ከመሄድ በቀር፣ መሻሻል አላሳየም፤ ይሁንና የክብር አምላክ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ለክብር በክብር የፈጠረውን የሰው ልጅ፣እንደ ወደቀ ሊቀር አልፈለገምና፣የመዳኛ ዘዴ አበጀለት፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር፣ሰውን የማዳን ሥራው፡- መቼ? በማን? የት? እንዴት? እንደሚከናወን፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሙሉ በትንቢት፣ በምሳሌ፣ በራእይና በቀመረ ሱባዔ፣በቅዱሳን ነቢያቱ አማካኝነት፣ ለዓለም ሲገልጽ ቆየ፡፡ በእርሱ የተያዘው ቀጠሮ ሲደርስ፣በፊቱ የሚቆመውን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን፤ወደድንግል ማርያም ላከ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም፣ከእግዚአብሔር ንገር ተብሎ የተላከበትን መልእክት ይዞ፣ወደ ድንግል ማርያም መጣ፤ እንዲህም አላት “እነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና፣ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፤ እርሱ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ አላት” ከዚህ አገላለጽ በመነሣት፣ፍሬ ነገሩን ስናስተውል፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም የሚወለደው ሕፃን፡- ዕሩቅ ብእሲ (ተራሰው) ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን፣ የስሙ ትርጓሜም መድኀኒት ማለት መሆኑን፣ መድኀኒትነቱም ለሕዝቡ ሁሉ መሆኑን፣ ሕዝቡን የሚያድናቸውም ከኀጢአታቸው መሆኑን፣ በማያሻማ ሁኔታ ማወቅ ይቻላል፡፡
የጌታችን መድኀኒትነት ድንበር የለሽና፣በሁሉም በሽታዎች ላይ የሚሠራ ቢሆንም፣በዋናነት ግን፣በትልቁ የኀጢአት በሽታ ላይ ያነጣጠረ መድኀኒት መሆኑን፣ በተጠቀሰው ኀይለ ቃል መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ የሚታየውን ክፉ በሽታ ሁሉ፣ሰበብ በመሆን ጎትቶ ያመጣብን ይህ ኀጢአት ነውና፣ጌታችን በዋናነት እርሱን ለመደምሰስ መምጣቱን ለማሳየት፣ ከኀጢአታቸው ያድናቸዋል ተብሎ በግልጽ ተለይቶ ተነገረ፤ በሽታው ትልቅ መሆኑን የምንረዳውም፣ትልቅ ዋጋ ያለው መድኀኒት፤ ያውም የእግዚአብሔር ልጅን ያህል፣ለመሥዋዕትነት ያስፈልገው በመሆኑ ነው፡፡ ለመሆኑ የኀጢአት በሽታ የሚያስከትለው ጒዳት ምንድን ነው? ያልን እንደሆነ፤ ሰውን ከእግዚአብሔር በማራቅና እግዚአብሔርን በማሳጣት፣ሰውን ማዋረድ፣ ማጎሳቈልና መግደል ነው፤ ሰው እግዚአብሔርን ካጣ፣ሁሉንም ያጣል፤አዳም አባታችንና ሔዋን እናታችን ያጡትም ይህንን ታላቅ ሀብት ነበር፤እግዚአብሔርን ሲያጡ፤ሁሉንም አጡ፤ ኀጢአተኞችም ሆኑ፤ኀጢአተኛ ማለት ያጣ፣የነጣ ማለት ነው፤ምንን ያጣ? እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ያጣ ማለት ነው፤ ሰው ከእግዚአብሔር ከተለየ፡ በአጠቃላይ መልካም የሆነ ነገር ሁሉ የለም፤ሊኖር የሚችለው ተቃራኒው ነው፤ እርሱም፡- ሞት ፣ በሽታ፣ ድህነት፣ ጠብ፣ መለያየት፣ ውርደት፣ የመሳሰለው ክፉ ነገር ሁሉ ነው ሊኖር የሚችለው፤ ከዚህ አንጻር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋል ሲባል፣ በዋነኛነት እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ከማጣት ያድናቸዋል ማለት ነው፤ ይህንም በራሱ መሥዋዕትነት፣ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ስላስታረቀና ስላገናኘ፣ ድኅነታችንን በዚህ አረጋግጦልናል፤ ፈጽሞልናልም፤ (1 ቆሮ 5.19)፡፡
ዛሬ፣ እግዚአብሔርንና የእርሱ የሆነውን የምናጣበት የኀጢአት በሽታ፣በጌታችን ተወግዶአል፤ አሁን በፊታችን ቆሞ እየጠበቀን ያለው ኀጢአት ሳይሆን፣በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ጽድቅ ነው፤ ጽድቁን ተከትሎ ደግሞ፣እግዚአብሔርና የእርሱ የሆነው መልካም ነገር ሁሉ፣ ማለትም፣ መንግሥተ ሰማያት፣ ዘለዓለማዊ ሕይወትና ዘለዓለማዊ ክብር፣በፊታችን ቆመው እየጠበቁን ነው፤ እነኝህም ጌታችን ዳግመኛ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ፣እውን የሚሆኑ ናቸው፤ (1ጴጥ 1.5-7)፡፡
ዛሬ፣የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት በታላቅ ድምቀት የምናከብርበት ዋናው ምክንያት፣ በኀጢአታችን ምክንያት ያጣናቸውን እግዚአብሔርና የእርሱ ሀብታት ሁሉ፣በእርሱ ፍጹም ምሕረትና ፍቅር፣ እንደገና ያገኘናቸው መሆናችን፣ በቤተ ልሔም በግልጽ የታየበት ዕለት ስለሆነ ነው፤ የጌታችን፣ ሥጋችንን ተዋሕዶ መገለጥ፣ የመላእክት የደስታ ዝማሬ፣ የእረኞችና የሰብአ ሰገል ተኣምራዊ ጒዞ፣ የኅብረታችን መመለስን ይገልጻሉ፤ የእኛ አካለ ሥጋና፣የእርሱ አካለ መለኮት፣በተዋሕዶ አንድ አካል ሆኖ በቤተ ልሔም መወለድ፣ሰው አጥቶት የነበረውን የእግዚአብሔር ኅብረት ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣በአካለ ቃል ርስትነት፣አምላክ ለመሆን በመብቃቱ የኀጢአት ግንብ መደርመሱ እርግጥ ሆነ፤ የተፈለገው ትልቅና ወሳኝ መድኀኒትም ይሄ ነው፤ እግዚአብሔር፣ይህን ያህል ከወደደን፣ማለትም፣ ከመለኮት ጋር ለመዋሐድና፣ የመለኮት የሆነውን ሁሉ ባለቤት ለመሆን ካበቃን፣ይህን ላደረገልን አምላክ ምን ውለታ መክፈል እንችላለን?
እርግጥ ነው፣ለአምላክ የሚሆን ውለታ ላይገኝ ይችላል፤ ነገር ግን፣ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ የሚያስችለን ተጨባጭ የሆነ ግብረ መልስ መስጠት፣ ከሁላችን ይጠበቃል፤ይህ ለሰው ሁሉ የሚቻል ነው፡፡ እርሱ፣ ሥጋችንን ከአፈር አንሥቶ፣ በተዋሕዶ የራሱ አካል እንዳደረገው፣እኛም በድህነትና፣ በስደት ምክንያት በሰው ሀገር አሠቃቂ የሆነ እንግልት እየደረሰባቸው የሚገኙ ወጣት ልጆቻችን፣አካላችን ናቸውና፣ ደግፈን በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ ከዚህ አኳያ መንግሥት ከፍ ያለ ገንዘብ በመመደብና አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት፣በሰው ሀገር ለከፍተኛ ጒዳት ተጋልጠው የነበሩትን ዜጎች፣ በፍጥነት ወደ ሀገር እንዲመለሱ ያደረገው ተግባር፣ቤተ ክርስቲያናችን በከፍተኛ አድናቆት ትመለከተዋለች፡፡
ለወደፊትም እንደዚህ የመሰለውን ወገንን የመታደግ ሥራ ለማከናወን መንግሥት በሚንቀሳቀሰበት ሁሉ፣ቤተ ክርስቲያናችን የበኩሏን ከማድረግ ወደኋላ እንደማትል በዚህ አጋጣሚ ታረጋግጣለች፡፡ ወጣት ልጆቻችንም፣ተሰዳችሁ ዋስትና የሌለውን የባዕድ ሀገር ሀብት ከመቋመጥ ይልቅ፣በሃይማኖታችሁና በሀገራችሁ ሆናችሁ፣ሥራን ሳትንቁና ሳታማርጡ ሌት ከቀን ጠንክራችሁ ሥሩ፤ጊዜያችሁን በሥራ ብቻ በማዋል አስተማማኝ ሀብት ማምጣት እንደምትችሉ አምናችሁ፣ ሀገራችሁን አልሙ፤ በሀገራችሁ ከብራችሁና ተደላድላችሁ፣ በክብር የምትኖሩበትን አስተሳሰብ መከተል፣ ቀዳሚ ምርጫችሁ ይሁን፤ እንደዚህ ያለውን ችግር ሁሉ በማስወገድ፣ዘላቂና መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ በሀገራችን ላይ ለማምጣት፡- በመንፈስ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ አገልግሎት ያደገችና የበለጸገች ሀገር፣ እውን ለማድረግ በሚደረገው ርብርቦሽ፣ሁላችንም በመተባበርና በቀጥታ በመሳተፍ፣ የድህነት ቅነሳ መርሐ ግብሩን፣በተፋጠነ ሁኔታ ማሳካት ይኖርብናል፡፡ በተለይም፣ በዚህ የደስታና የኅብረት በዓል፣ የእግዚአብሔር ልጆችና ፍጡራን የሆኑ ወገኖቻችን፣ ምግበ ሥጋ እየሸተታቸው፣ በምግብ ዕጦት ምክንያት ጾም እንዳይውሉና፣ እግዚአብሔር እንዳያዝንብን፣ ከእኛ ጋር በማእዳችን እንዲካፈሉ ማድረግ አለብን፤ ለእግዚአብሔር ፍቅር የምንሰጠው ግብረ መልስ ይኸው ነው፤ እግዚአብሔርና ሕዝብ፣ሕዝብና ሕዝብ፣ አንድ ላይ አገናኝቶ ለሰመረ ሀገራዊ ውጤት የሚያበቃንም እንደዚህ ያለ መተዛዘንና መረዳዳት፣ መተጋገዝና መደጋገፍ፣ መቻቻልና መስማማት ፣ መተሳሰብና መከባበር ሲኖር እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ከተቸገሩ ወገኖቹ ጋር በአንድ ማእድ እንዲያከብር፣ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የልደት በዓል ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ሁላችንንም ይባርከን ይቀድሰን፤ አሜን።