ሚያዝያ 4 ቀን የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤በሞትና በመቃብር ላይ ሥልጣን ያለው ኀያሉና አሸናፊው ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ ፡፡

‹‹ወበከመ በእንተ አዳም ኵልነ ንመውት ከማሁ በክርስቶስ ኵልነ ነሐዩ፤ ሁላችን በአዳም እንደምንሞት እንደዚሁም ሁላችን በክርስቶስ ሕያዋን እንሆናለን›› (1ቆሮ. 15÷22)፡፡

እዚህ ላይ በተገለጸው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት የሰዎች መጻኢና የመጨረሻ ዕድል ከሁለት አዳማዊ ውርስ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደተጻፈው ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ተወልዶአል፤ የእርሱ የሆነውንም ሁሉ ወርሶአል፤ ይህም ማለት በሥጋው በኩል የግብረ ኀጢአት ዝንባሌን፣ ሞተ ሥጋን፣ ወሪደ መቃብርን፣ በመቃብር ውስጥ መበስበስንና መፍረስን ሲወርስ በነፍሱ በኩል ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየትን፣ በኀጢአት ተሸንፎ የዲያብሎስ ሎሌ መሆንን፣ በኀጢአቱ ምክንያት ለኵነኔ ሲኦል ተጋላጭ መሆንን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ወርሶአል ማለት ነው፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው ቀዳማዊ አዳም በሥጋና በነፍስ ከባድ ውድቀትን ለልጆቹ አውርሶአል ማለት ነው፡፡ ከቀዳማዊ አዳም የውድቀት ዘመን ጀምሮ እስከ ስቅለተ ክርስቶስ በነበረው ረጅም ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ ከቀዳማዊ አዳም ባገኘው ውርስ ምክንያት በሥጋው ርደተ መቃብርን፣ በነፍሱ ርደተ ሲኦልን ተፈርዶበት በድርብ መከራ ሲማቅቅ ኖሮአል፡፡ ያ ዘመን ከመከራው ብዛት የተነሣ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ፣ ዓመተ መርገም ተብሎ ተሰይሞአል፡፡ ይሁን እንጂ ለምሕረቱና ለይቅርታው ወሰን የሌለው እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ውድቀት በትንሣኤ ለመቀልበስ ሲል የባሕርይ ልጁ የሆነ እግዚአብሔር ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከ፡፡

እርሱም የኛን ሥጋ ተዋሕዶ ሰው ሆነ፤ በመካከላችን ተገኝቶም ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመቃብር ወደ ትንሣኤ የሚወስደውን መንገድ በቅዱስ ወንጌሉ አስተማረን (ዮሐ. 5÷24)። የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ የአብ ልጅ ቢሆንም በሥጋው የሰው ልጅ ነውና ዳግማዊ አዳም ተብሎ ይጠራል (1ቆሮ. 15÷45-48)፡፡ በመሆኑም ዳግማዊ አዳም የተባለው ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በበኩሉ ቀዳማዊ አዳም ለልጆቹ ላወረሰው ውርስ ተቃራኒ የሆነውን ለሰው ዘር ሁሉ አውርሶአል፤ ይኸውም፡ በኀጢአት ዝንባሌ ፈንታ ጽድቀ መንፈስን፣ በሞት ፈንታ ዘለዓለማዊ ሕይወትን፣ በርደተ መቃብር ፈንታ ትንሣኤን፤ በርደተ ሲኦል ፈንታ ዕርገትን፣ በመለያየት ፈንታ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት መኖርንና የመሳሰሉትን ለልጆቹ አውርሶአል፡፡ ይህ ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ለሰው ልጅ በመሰጠቱ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ሥጋዌ፣ መዋዕለ ንስሓ፣ ዓመተ ምሕረት ተብሎ ይጠራል፡፡ ይሁንና ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ዘር በመወለዱ የእርሱ የሆነውን ሁሉ እንደወረሰ፣ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ የዳግማዊ አዳም የሆነውን ሁሉ ለመውረስ ከዳግማዊ አዳም በመንፈስ መወለድ የግድ ያስፈልገዋል፡፡ ሰው በእምነት ተፀንሶ በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ የዳግማዊ አዳም ልጅ ይሆንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይወርሳል፤ ከዚህ ዳግም ልደት በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሁሉ የቀዳማዊ አዳም ውርስ አይነካቸውም (ሮሜ 8÷1)፡፡ የዳግማዊ አዳም ውርስ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ እውን ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞለታል፤ ያን ጊዜ በመቃብር ያሉ ሙታን ሁሉ በቅፅበት ሲነሡና በሕይወት ያሉትም በአንድ ጊዜ በቅጽበት ሲለወጡ የዳግማዊ አዳም ውርስ በግልጽ ይታያል፡፡

በዚህ ጊዜ የሚሞተውና የሚበሰብሰው አካላችን የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን ሲጎናጸፍ ሞትና መቃብር ይሸነፋሉ፤ ህልውናቸውም ያከትማል (1ቆሮ. 15÷52-57)፤ በዚያን ጊዜ ከቀዳማዊ አዳም በመጣ የኀጢአት ውርስ ምክንያት የሞቱ ሁሉ ከዳግማዊ አዳም በተገኘ የጽድቅ ውርስ ምክንያት ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ (1ቆሮ. 15÷49)፤ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶና ሞትን ድል አድርጎ የተነሣበትን በዓለ ፋሲካ ዛሬ በታላቅ ድምቀትና በደስታ ማክበራችን ‹‹ሞቴንና ትንሣኤዬን አስቡ›› (1ቆሮ. 11÷26) ያለውን ቃሉን ከመፈጸም ባሻገር የኛንም ትንሣኤ በእርሱ ትንሣኤ እያየን በሃይማኖትና በማይናወጽ ተስፋ ጸንተን እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡ በእርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤዛነቱ ካቀዳጀን ጸጋ አንዱና ዋነኛው እኛን ለትንሣኤና ለዘለዓለማዊ ሕይወት ማብቃቱ ነው፡፡ ከጌታችን ትንሣኤ የምንገነዘበው ዐቢይ ነገር እርሱ በመቃብር ውስጥ ሙስና መቃብር ማለትም መበስበስና መፍረስ ሳይነካው ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ወደሰማያዊ ክብሩ እንዳረገ፣ እኛም ከእርሱ በወረስነው የጽድቅ ውርስ መሠረት እንደእርሱ ከመቃብር ተነሥተንና የዘለዓለምን ሕይወት ተቀዳጅተን ወደሰማያዊ መንግሥቱ የምናርግ መሆናችንን ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ማሳያ መስተዋትና የዘለዓለማዊው ሕይወታችን ማረጋገጫ ነውና (1ተሰ.4÷13-18)፡፡ ይሁን እንጂ የትንሣኤያችን ጒዞ የሚጀምረው ዛሬ በሕይወተ ሥጋ እያለን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ገበሬ በመኸር ወራት ጥሩ ምርትን ለማፈስ ልፋቱን በግንቦትና በሰኔ እንደሚጀምር፣ ያን ካላደረገ ደግሞ የሚያገኘው ምርት እንደማይኖር ሁሉ፣ እኛም የትንሣኤያችን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ጒዞ ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን ካልጀመርነው በዳግም ምጽአት የምናገኘው ነገር አይኖርም (ማቴ 25÷ 1-13)፡፡

ሁላችንም እንደምንገነዘበው አምላካችን እግዚአብሔር ሠርቶ የሚያሠራ አምላክ እንጂ መክሊቱን ቀብሮ በስንፍና የሚኖረውን የሚወድ አምላክ አይደለም (ማቴ. 25÷24-30)፤ አምላካችን ከባሕርይ አምላክነት በስተቀር ሁሉን በሁሉ የሚያሳትፍ አምላክ እንደሆነ ምን ጊዜም አንርሳ፤ “ቅዱስ ተብሎ ቅዱሳን እንድንባል፣ ጻድቅ ተብሎ ጻድቃን እንድንባል፣ ክቡር ሆኖ ክቡራን እንድንሆን፣ ሕያው ሆኖ ሕያዋን እንድንሆን ፈቅዶልናል” (1ጴጥ. 1÷16)፡፡ በመሆኑም እርሱ የመልካም ሥራ ሁሉ ባለቤት እንደሆነ እኛም የመልካም ሥራ ባለቤቶች በመሆን ትንሣኤያችንን ከዚህ እንድንጀምር ተሳትፎውን ማለትም እርሱን መምሰልን ከእኛ ይፈልጋል (ማቴ. 5÷48)። ዛሬ ዓለማችን በፀጥታ ዕጦት እየታመሰች የምትገኘው ከሥነ ምግባር ጉድለት የተነሣ እንደሆነ ሁሉም ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል፡፡ በልዩ ልዩ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ የሚገኙ የትምህርት ተቅዋማት የሥነ ምግባር ትምህርትን እያስተማሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዓለማችን በመልካም ሥነ ምግባር ከመበልጸግ ይልቅ በዘቀጠና ለአእምሮ በሚዘገንን ነውረ ኀጢአት ክፉኛ እየተናጠች ትገኛለች፡፡ ይህ ሁሉ የሥነ ምግባር ውድቀት ሊመጣ የቻለው በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የሥነ ምግባር ትምህርት በፈሪሀ እግዚአብሔር ያልተቃኘ ከመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል (መዝ. 110÷10፤ 1ቆሮ. 1÷20-21)፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ተቀባይነት ያላት ሀገር እንደሆነች ቅዱስ መጽሐፍ ሊመሰክርላት የቻለው በተቀደሰው ባህሏና በመልካም ሥነ ምግባሯ፣ በጸናው ሃይማኖቷና በእውነተኛው ትውፊቷ እንጂ በሌላ በምንም እንዳልሆነ በአጽንዖት መገንዘብ ያሻል፡፡ (መዝ. 71፡9፤ 67፡31) በሀገራችን ከምናስታውሰው ነባሩና ሃይማኖታዊ ባህላችን አንዱ ለብቻ መመገብ እንደነውር የሚወሰድ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መልካም ሥነ ምግባራችንና ቅዱስ ባህላችን ዛሬም ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ የሁላችንም ኀላፊነት ነው፡፡ የትንሣኤያችንን ጒዞ ዛሬ እንጀምር ስንል የተራበውን ማጒረስ፣ የተጠማውን ማጠጣት፣ የታረዘውን ማልበስ፣ ያዘነውን ማጽናናት፣ የታመመውን መጠየቅና መርዳት፣ ስደተኛውን ማስተናገድ፣ የታሰረውን መጠየቅ፣ የሥራ ጊዜን በአልባሌ ቦታ አለማጥፋት፣ ለሰላም፣ ለሀገር ልማትና ለእድገት በአንድነት መሰለፍ፣ ሁሉንም ነገር በፍቅርና በስምምነት ብቻ መፍታት የመሳሰሉትን ሁሉ የሕይወታችን መርሆዎች አድርገን በተግባር እናውላቸው ማለታችን ነው፤ ይህንን የምናደርግ ከሆነ እውነትም የትንሣኤን ጒዞ በትክክል ጀምረናል ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም፡ ሁላችሁም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በተቀደሰው እምነት ጸንታችሁ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን መሠረት ያደረገ ሥነ ምግባር አንግባችሁ፣ የሀገራችንን ሰላም በጽኑ እንድትጠብቁ፣ ልማቷንና እድገቷን እንድታፋጥኑ፣ አንድነታችሁንና እኩልነታችሁን አጥብቃችሁ እንድትይዙ፣ በዓለ ፋሲካውንም የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስና የተጠሙትን በማጠጣት፣ በሰላምና በፍቅር እንድታከብሩ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን፡፡