ሚያዝያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በንጹሓን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው አሠቃቂ ግፍ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
“ወይቤ እግዚአብሔር ንግበር ሰብአ በአርኣያከ ወበአምሳሊከ — እግዚአብሔርም አለ ሰውን በአርኣያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” (ዘፍ.1፥26)፤ ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር በሦስት ነገሮች ከሌሎች ፍጥረታት የተለየ አድርጎ ፈጥሮታል፤ ይኸውም እንደሌሎች ፍጥረታት ይሁን በማለት በቃል – ትእዛዝ ሳይሆን ከምድር አፈር አበጅቶ ፈጥሮታል፣ ይህም ማለትም፡ በእጁ አከናውኖ፣ አሳምሮና አክብሮ የፈጠረው በመሆኑ፤ ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁናቴ በአርኣያውና በአምሳሉ የፈጠረው በመሆኑ፣ ከፍጥረታት ሁሉ ለይቶ የሕይወት እስትንፋስን እፍ ያለበት ሕያው ፍጡር በመሆኑ ከሌሎች ፍጥረታት የተለየ ያደርገዋል፡፡
በኀላፊነት ደረጃም ምድርንና በምድር ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ እንዲያስተዳድር፣ እንዲያዝና እንዲገዛ ባለሙሉ ሥልጣን ሆኖ በእግዚአብሔር ተሹሞአል፡፡
ይህ ሁሉ የሚያመለክተው ሰው በፈጣሪ ዘንድ እጅግ በጣም የተከበረና የተወደደ ፍጡር ከመሆኑም በላይ አርኣያ እግዚአብሔር፣ አምሳለ እግዚአብሔር የሆነ ክቡር ፍጥረት መሆኑን ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ክብር ታላቅነት በሚያስተምርበት ጊዜ ‹‹በወንድሙ ላይ በማይገባ የሚቈጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል›› ብሎአል፤ (ማቴ.5፡21-22) ጌታችን በዚህ ትምህርቱ የሰው ልጅን መግደል ይቅርና መሳደብና መቈጣት እንደማይቻል አበክሮ አስተምሮአል፤ ሰውን መግደል አርኣያ እግዚአብሔርን፣ አምሳለ እግዚአብሔርን ማፍረስ ስለሆነ በፈጣሪ ዘንድ ትልቅ በደል ነው፡፡
ከዚህ አንጻር በእግዚአብሔር የተሰጠውን የሰው ክብር በተግባር ለመጠበቅና ለማስከበር፣ በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ያሉትን ልጆቿን በእኩልነትና በአንድነት አስተባብራ ለዘመናት ተጭኖን የቆየውን ድህነት ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም ከዳር እስከ ዳር እየተጋች ያለችና ብሩህ ተስፋ የሠነቀች ሀገር እንደሆነች ዓለም የተገነዘበበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ እየተከሠቱ ያሉት ግድያዎች የሰውን ክቡርነት በግልጽ የሚጋፉ ናቸው፤ በመሆኑም የግድያ ድርጊት፣ ለዚያም ዐቅም በሌላቸውና መከላከል በማይችሉ ሕፃናትና እናቶች የሚፈጸሙትን ግድያዎች፣ ሁሉም አምርሮ ሊያወግዛቸውና ሊመክታቸው ይገባል፤ በተለይም በዚህ ሰሙን በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በንጹሓን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ ዘረፋና የንብረት ውድመት ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ አሳዝኖአል፡፡ ይህን ግድያ ልዩ የሚያደርገው በተለይ በሕፃናትና እናቶች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ነው፣ ይህ ኅሊናን የሚያቈስልና ሕገ እግዚአብሔርን የሚጥስ የጭካኔ ተግባር በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታወግዘዋለች፡፡
ሀገራችንም ሆነች የዓለም ማኅበረ ሰብ በአጠቃላይ የሰው ልጅ በሕይወትና፣ በነፃነት የመኖር ዋስትና ኖሮት፣ በሀገሩ ሠርቶ የመሻሻል መብቱ እንዲከበር ተግተው በሚሠሩበት ወቅት እንዲህ ያለ ድርጊት መፈጸሙ ሀገራችንን ወደኋላ የሚጎትት ስለሆነ እንዲህ ያለው ድርጊት ድጋሚ እንዳይከሠት ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ ጋር አስተማሪ የሆነ ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ አሁን የተከሠተው ዐይነት ችግር፣ ይብዛም ይነስም በጋምቤላ አካባቢ በተደጋጋሚ እየታየ የቆየ ከመሆኑ አንጻር ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያከትም ለማድረግ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግሥታት በጋራ ቢሠሩ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ቤተ ክርስቲያናችን ታምናለች፤ ለዚህም ድጋፏን ትሰጣለች፡፡
በመጨረሻም፡ በጋምቤላ ክልል በሚገኙት ልጆቻችንና ወገኖቻችን በተፈጸመው የግድያ፣ የዘረፋና የንብረት ውድመት ምክንያት የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን በራሳችንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እየገለጽን የመዋች ቤተሰቦችንና የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን እግዚአብሔር እንዲያጽናናቸው እንጸልያለን። በዚህ አጋጣሚ ቤተ ክርስቲያናችን አሁንም ሆነ ወደፊት ከክልሉ ሕዝብና መንግሥት ጎን እንደማትለይ እናረጋግጣለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡