መጋቢት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ሙሉ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
በትንሣኤው ኀይል ማኅለቅትና ፍጻሜ የሌለው ሕይወተ ትንሣኤን ያደለን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ።
ወእመሰ ንትአመን ከመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን ከማሁ ያነሥኦሙ እግዚአብሔር ለሙታን፤ ክርስቶስ ከሙታን እንደተነሣ ካመን እንደዚሁ እግዚአብሔር ሙታንን ያነሣቸዋል፡፡ ( 1ተሰ. 4፥13)
ለሰው ልጆች በፊታችን ተጠብቆልን ያለ ትልቅ ተስፋ፣ ትንሣኤ ሙታን ነው፤ ለሰው ልጅ የመጨረሻው የክብር ዘውድና የሕይወት ጕልላት፣ ከመቃብር ታድሶ መነሣትና እሱን ተከትሎ በሚመጣው በቀዋሚው የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ መኖር ነው፤ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነውና ፍጥረቱን በፍቅር ፈጥሮ በፍቅር ያስተዳድራል፤ እግዚአብሔር የክብር አምላክ በመሆኑ ፍጥረቱን ለማክበር ሁሌም ዝግጁ ነው፤ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለውን ፍቅርና ክብር ለመረዳት በየዕለቱ በሕይወታችን ላይ የሚፈጽመውን ጥበቃና ምግብና ማየቱ በቂ ነው፡፡እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅሩና ማኅለቅት በሌለው ልግስናው በምንኖርባት ምድር ለፍጡራኑ ኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በበቂ ሁኔታ አሟልቶ መስጠቱ ሌላው የታላቅ ፍቅሩ ማስረጃ ነው፤ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለውን ታላቅ ፍቅርና አክብሮት በይበልጥ የገለጸበት ዐቢይ ክንውን አንድ ልጁ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስን ለፍጥረቱ ቤዛ እንዲሆን ለመከራና ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ነው፤ ይህ ድርጊት እግዚአብሔር ፍጥረቱን ምን ያህል እንደሚወድ ያሳየበት የፍቅሩ ጣራ ወይም ጫፍ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለማያልቅ ኀይለ ሕይወት በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረን እኛ ከተቀመጠልን የሕይወት ድንበር ወጥተን ወደ ሞት ሀገር በመቀላቀላችን ምክንያት በብቸኝነትና በአሠቃቂ መከራ ስንማቅቅ ኖረናል ፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ሆነን ስንኖር ዝም ብሎ ማየት፣ ወሰን የለሽ ርኅራኄ ላለው ለእግዚአብሔር አምላካችን የሚቻል አልሆነም፤ በመሆኑም የመከራችንን ታሪክ በመለወጥ ያድነን ዘንድ በፈቀደ ጊዜ በአካል የሚተካከለው፣ በመለኮትና በቅድምና ከእሱ ጋር አንድ ህላዌ የሆነ የባሕርይ ልጁን ወደኛ ላከ፤ ቃሉ፣ ኀይሉና ጥበቡ የሆነ ወልድ ዋሕድ ሥጋችንን እና ነፍሳችንን ተዋሕዶ በእኛ አካል በዚህ ዓለም ተገለጸ፤ እሱ በዚህ ዓለም በቆየበት ጊዜ የሕይወት መንገድን በቅዱስ ወንጌል አስተማረን፣ የሰው ልጅ ሁሉ ብቸኛ አዳኝ መሆኑን ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማንሣት፣ ኅብስትን በማበርከት አሳየን፤ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱሰ ክርስቶስ በዚህ አምላካዊ ኀይሉ ማለትም ደምሳሴ ኀጢአት በመሆኑ፣ ሙታንን በማንሣቱ፣ አጋንንትን በማውጣቱ፣ ለሕሙማን ፈውስን በመስጠቱ፤ በኀጢአት፣ በሞት፣ በዲያብሎስና በበሽታዎች ሁሉ ላይ ላዕላዊ ሥልጣን ያለው እንደሆነ፣ ሕገ ተፈጥሮም በቊጥጥሩ ሥር መሆኑን አሳየን፤ ከዚህ በኋላ ለሰው ልጅ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ መሥዋዕትነትን በመክፈል ኀጢአታችንን አስወገደ፤ በሞቱ ሞታችንን አስቀረ፣ በትንሣኤው ሕያውነታችንን አበሠረ፤ በዚህም ተግባሩ የመዳናችንን ምሥጢር ፈጸመ፣ በጨለማና በሞት ጥላ ለነበሩም ነፃነትን ሰበከላቸው፤
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የእኛ ትንሣኤ ማሳያና አስረጅ በመሆኑ በእኛ መጻኢ ዕድል ላይ ያለው ትርጒም ከሁሉም የላቀ ነው፤ የእኛ ሕይወት እንደ ቅጽበተ ዐይን ግልጥ ብላ ጥፍት በምትል በዚህች ምድራዊ ዕድሜአችን የተገደበች አይደለችም፤ ሕይወታችን ማኅለቅትና ፍጻሜ፣ ማርጀትና ኅልፈት የሌለው ህላዌ ገና ይጠብቃታል፤ ይህ ጸጋ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ያዘጋጀልን፣ በትንሣኤው ያበሠረን የወዲያኛው ሕይወት ሀልዎትና ወሰን የለሽ ዕድሜ ነው፤ እሱ እኛን ከኀጢአትና ከሞት ለመገላገል እንደሞተ፣ እኛም ማሕየዊ ሞቱ ያስገኘልንን ድኅነት ለመቀዳጀት በመጠመቃችን የሞቱ ተባባሪዎች ሆነናል፤ እሱ ዳግም የማይሞትና ለዘለዓለም ሕያው መሆኑን ለማብሠር ሞትንና መቃብርን ድል ነሥቶ በአሸናፊነት እንደተነሣ፣ እኛም ዳግም ላንሞት ይልቁኑም የማያልቅ የኀይለ ሕይወት ባለቤቶች እንሆን ዘንድ በመጠመቃችን የትንሣኤው ተባባሪዎች ሆነናል፤ በሌላ አገላለጽ በእሱ ስም በመጠመቅ የሞቱም የትንሣኤውም ተባባሪዎች ሆነናል፤ እሱ ሞትንና መቃብርን ድል ነሥቶ እንደተነሣ፣ እኛም በጥምቀት ከእሱ ጋር በመተባበራችን ምክንያት እሱ በከፈተልን መንገድ ሞትንና መቃብርን ድል ነሥተን ከእርሱ ጋር ወደ ሰማያዊው መንግሥት እንነጠቃለን፤ በዚያም በማያልቅ ኀይለ ሕይወት ከእርሱ ጋር ፍጻሜና ማኅለቅት፣ ማርጀትና ኅልፈት በሌለበት ህላዌ እንኖራለን፤ ሰው ወዳጅ የሆነ፤ ፍቅሩና ክብሩ ማለቂያ የሌለው እግዚአብሔር አምላካችን ለእኛ ያዘጋጀው መጻኢ ዕድል ይኸው ነው፤ ስለሆነም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ የተነሣው ለራሱ ሳይሆን ለእኛ ሲል ነውና ክርስቶስ ሞቶ ተነሣ ማለት ምሥጢራዊ ትርጉሙ ሰዎችን ከፍዳ ኀጢአትና ከመርገም አላቀቀ፤ ሞትንና ሙስና መቃብርን ከሰው አራቀ፤ ሰውን በዘለዓለማዊ ሕይወት ለማኖር እንደገና አበቃ ማለት ነውና የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሰጠን ጥቅም አኳያ ሙሉ በሙሉ የእኛ ትንሣኤ እንደሆነ መረዳት ይገባናል፤ በሞቱ ድኅነታችንን፣ በትንሣኤው ሕይወታችንን መመለሱን በትንሣኤው ተግባራዊ አዋጅ ተነግሮናል፤ የመጨረሻ አፈጻጸሙ ግን ጌታችን እንደገና ተመልሶ ሲመጣ ይከናወናል፤ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሣ በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር ሙታንን ያነሣቸዋል ሲል ያስተማረን ይህንን ሲገልጽ ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸን፡ ትልቁና ዋናው የትንሣኤያችን ሕይወት በጌታችን ዳግም ምጽአት ይረጋገጣል ቢባልም ውጥኑ አሐዱ ተብሎ የሚጀመረው አሁን ነው፤ እያንዳንዷ የዕድሜያችን ሰዓት የትንሣኤ ሥራን የምናከናውንባት ዕለተ ትንሣኤ ናት፤ እግዚአብሔርን የምናመልክባትና የምናመሰግንባት ቀን ዕለተ ትንሣኤ ናት፤ ወንድም ከወንድሙ ጋር በፍቅርና በሰላም፣ በመቻቻልና በመከባበር የሚያሳልፋት ቀን ዕለተ ትንሣኤ ናት፤ ስለ ሀገርና ስለ ሕዝብ አንድነት፣ ስለ ሕዝብ አእምሮኣዊና ምጣኔ ሀብታዊ ልማት በመሥራት የምናሳልፋት ቀን ዕለተ ትንሣኤ ናት፣ በአጠቃላይ ለትልቁና ለዋናው ትንሣኤ ተሸላሚዎች አድርጎ የሚያቀርበን በዚህ ዓለም በቆየንበት የዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በበጎ ኅሊና ተነሣሥተን የምንፈጽመው የሃይማኖትና የማኅበራዊ ኑሮ የተግባር ትንሣኤ ድምር ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም በዓለ ትንሣኤ የአዲስ ሕይወት ማብሠሪያ በዓል እንደመሆኑ መጠን የሀገራችን ሕዝቦች በዓሉን ሲያከብሩ ለአዲስ ወንድማዊ ፍቅር፣ ለጠንካራ ሀገራዊ አንድነት፣ ለፍጹም ሀገራዊ መግባባትና ለተሻለ የልማት ሥራ በአንድነት ለመነሣት ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል፡፡
በመጨረሻም፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ባስተናገደችው ያላስፈላጊ ንትርክ ብዙ ነገርን እንዳጣች ኢትዮጵያውያን ሁላችን የምንስተው አይሆንም፤ ይህ ክሥተት ተስፋ ከተጣለበት የሀገሪቱ የሕዳሴ ፍኖተ ካርታ ጋር ፈጽሞ የማይሄድ ነው፤ ስለሆነም ያለፈውን ትተን ከዛሬ ጀምሮ በሠለጠነ የውይይት ዘዴና ከሁሉም በላይ ለሀገር እድገትና ለሕዝብ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ችግራችንን እየፈታን በልማትና፣ በእድገት ከበለጸጉት የዓለማችን ሀገራት ጋር እኩል ወደሚያደርገን ልማታዊ ሥራችን ፊታችንን እንድናዞር ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም በዓለ ትንሣኤ ያድርግልን እግዚአብሔር አምላክ ሀገራቸንን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡