መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ካህናትና ምእመናን ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን እንዲጠብቁ መመሪያዎች አስተላልፏል፡-

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠር፣ በከተማና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ!
ወቅታዊ የሰው ልጅ ሥጋት በመሆን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም ዐቀፍ ሥጋት ስለተከሠተ መንግሥታት ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝብን ከሞት ለመጠበቅ አዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ እምነትና ቀኖናን ጠብቆ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ኀላፊነት አለባት፡፡ ስለዚህ ቋሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፡-

1. በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ እጅ በመንሳት ወይም በእማኄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
2. ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጒዞዎች እና ምእመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
3. ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አሰፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ እጆቻንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
4. ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅዳሴና በማሕሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
5. የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
6. በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኀይል የተስፋ ልኡክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልእኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር
7. ሥርዐተ ቅዳሴን በተመለከተ፡-
• በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልኡካን ብቻ ሥርዐተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
• በዕለቱ ለሚቆርቡ ምእመናን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቈራቢዎች ብቻ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣
• ሌሎች ምእመናን በዐጸደ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
• የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
• ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮችን ግብረ ኀይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፤
8. ከሥርዐተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግህ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማሕሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዐቱ በሚያስፈልገው ቊጥር ብቻ እና በውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈፀም፣
9. ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረትና በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ ዕጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣
10. በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በኀዘን፣ በእድር፣ በሥርዐተ ቀብር አፈጻጸምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሠራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቍጥር በጥንቃቄ እንዲፈጸም፤
11. ምእመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣
12. ለነዳያን እና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቍሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣
13. ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች በመቈጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል፡፡

በአጠቃላይ በበሽታው እስካሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን እንዲሰጥልን እንጸልያለን፤ በመላው ዓለም ዜጎቻቸውን በበሽታው ለተነጠቁ ሁሉ መጽናናቱን እንዲሰጥልን ያረፉትንም እንዲምርልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፤ በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን የራሳችሁና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠበቅ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኀላፊነታችሁን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲሆኑ በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡ ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ዓለማችንን ከጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን፡፡