መስከረም 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
ፍጥረታትን ሁሉ በጸጋው ፈጥሮ የሚመግብና የሚመራ መሐሪውና ይቅር ባዩ አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን ዓመት በሰላም አስፈጽሞ ለአዲሱ የምሕረት ዓመት ስላደረሰን ፍጹም ክብር አምልኮትና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፤ እንደዚሁም ለሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት በዓለ መስቀል እንኳን በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!
“ወይመጽእ መዋዕለ ሣህል እምቅድመ ገጹ ለእግዚአብሔር
ከእግዚአብሔር ዘንድ የይቅርታ ዘመን ይመጣል፤”
(የሐዋ.ሥራ 3፥19)
ይቅርታ ከእግዚአብሔር የሚመነጭና ለዓለም ሁሉ ባለመቋረጥ የሚፈስ፣ ቀዋሚ የምሕረት ጅረት ነው፤ ሰማይ ከነግሡ ምድር ከነልብሱ በህልውና ጸንቶ ሊኖር የቻለውና የሚችለው በእግዚአብሔር ይቅርታ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፍጥረት በበደለ ቊጥር ሳይቈጣ እግዚአብሔር በምሕረትና በይቅርታ ሁሉንም እያለፈ ፍጥረቱን ይመግባል፣ ይመራል፣ ያስተዳድራል፣ ይንከባከባል፤ የእግዚአብሔር ይቅርታ ሁሌ የማያቋርጥ ትልቅ ጸጋ ቢሆንም በመስቀል ላይ የገለጸው ይቅርታ ከሁሉም የላቀ ነው፡፡ ምክንያቱም በመስቀል ላይ የተፈጸመው ይቅርታ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘለዓለማዊ በመሆኑ፣ እንዲሁ በነፃ የተሰጠ ሳይሆን መለኮት በተዋሐደው ደሙ የተገኘ በመሆኑ፣ በከፊል ሳይሆን ሰማያውያንንና ምድራውያንን ሁሉ በአንድነት ያጥለቀለቀ በመሆኑና ለወደፊትም የኀጢአት ሁሉ ማስተስረያ አድርጎ ያቆመው የይቅርታ ሕግ በመሆኑ በመስቀሉ ላይ የሆነው ይቅርታ ከይቅርታ ሁሉ ይበልጣል፡፡
በመስቀል ላይ የተፈጸመው የዕርቅና የይቅርታ ጸጋ ፊተኞቹንና ኋለኞቹን ሁሉ ያካተተ በመሆኑ ድንበር የለሽ ይቅርታ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ይቅርታ ምድርን መላ፤ ሰማያትም በእግዚአብሔር ቃል ጸኑ፤ ኀይላቸውም ሁሉ ከአፉ እስትንፋስ የተገኘ ነው ብሎ የሚያስተምረን ይህንን ለመግለጽ ነው፡፡ (መዝ. 32፥6)
ቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ፤
ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳትና ሜትሮፖሊታኖች፤
ክቡራንና ክቡራት የበዓሉ ተሳታፊዎች፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ክፍለ ዓለም በተሻለና በደመቀ ሁኔታ በዓለ መስቀልን የምታከብርበት ምክንያት እግዚአብሔር ለፍጡራኑ ከሠራው ሥራ ሁሉ ይልቅ በመስቀሉ የሠራው እጅግ የላቀና ሰውን ከሞተ ነፍስ የታደገ በመሆኑ ነው፡፡ ነገረ መስቀሉ ሁሉንም በእኩልነት ተቀብሎ ያስማማና አንድ ያደረገ፣ ሰላምንና ፍቅርን ያሰፈነ፣ በአምልኮተ ጣዖትና በብልሹ ሥነ ምግባር፣ በተሳሳተ እምነትና አስተሳሰብ ተበላሽቶ የነበረውን ዓለም ፍጹም ሰላማዊ ርትዓዊና ትሩፋዊ በሆነ ትምህርቱ ያጣፈጠ ነው፡፡
በዓለም ውስጥ የኢትዮጵያ ምእመናንን ያህል የመስቀልን ጣዕም የተገነዘበ የለም በሚያስብል ሁኔታ፣ ትእምርተ መስቀሉ በልብሳችን፣ በአካላችን፣ በቤታችን፣ በሥራ ዕቃዎቻችን፣ በጌጦቻችን፣ በዕለት ተዕለት ሥራችንና እንቅስቃሴአችን ሁሉ ሊኖር የቻለው፣ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን አበው የመስቀሉን ጣዕም በነፍስ ወከፍ ኢትዮጵያዊ ኅሊና በሚገባ እንዲሠርጽ የሚያስችል ሥራ በመሥራታቸው እንደሆነ የማይካድ ነው፤ ለዚህም ማስረጃችን ጥዑም ለጒርዔየ ነገረ መስቀልከ የመስቀልህ ነገር ለጒረሮዬ ጣፋጭ ነው ብሎ ኢትዮጵያዊው ነባቤ መለኮት ቅዱስ ያሬድ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ትክክለኛውን መስቀል ከተቀበረበት ቦታ ከጎልጎታ በዛሬው ዕለት በተከሠተው ተኣምር ምክንያት እንዲወጣ ካደረገ በኋላ በሂደት ወደ ኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲገባ ማድረጉ የኢትዮጵያውያንን ፍቅረ መስቀል አይቶ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል፤ በመሆኑም ኢትዮጵያን ከባዕድ ወራሪ፣ ከባዕድ አምልኮና ባህል የተጠበቀ፣ የነፃነት፣ የሃይማኖት፣ የአንድነት ኀይል የሆነ፣ በሥነ ምግባር የበለጸገ፣ ኵሩና ጨዋ የሆነ ፣ ለማንም ይሁን ለማን ያልተበገረ ሕዝብ በዚህች ምድር በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲኖር ያደረገ፣ በሀገሪቱ መሐል ዙፋኑን ዘርግቶ የተቀመጠው የመስቀሉ ኀይል እንደሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ ያውቃል፤ ዛሬ በዚህች ሰዓት በዚህ አደባባይ በተግባር እየገለጽነው ያለ ዐቢይ ትዕይንትም ይኸው ሐቅ ነው፡፡
ይህ ታላቅና በእግዚአብሔር በረከት የተመላ ሕዝብ በታቦተ ሕጉና በመስቀሉ ፊት ቆሞ ፈጣሪውን ሲለምን ያልተደረገለትና የማይደረግለት ኀይለ እግዚአብሔር የለም፡፡ በመሆኑም በየዓመቱ እንዲህ ባለ ሰልፍና ትዕይንት የምናከብረው የመስቀል በዓል ታማኙና ዘለዓለማዊው፣ ሁሉን ማድረግ የሚችል፣ የኀያላን ሁሉ ኀያል የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ይህንን ቅዱስ ሀገርና ሕዝብ ከሚታየውና ከማይታየው ፈተና እንዲጠብቅልን በጸሎትና በምስጋና በአንድነት ሆነን ለመማፀን ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንፈሳዊ ኀይል በኩል የደከመችበት ጊዜ ፈጽሞ ባይኖርም በኢኮኖሚ ዐቅሟ ግን ወደኋላ የቀረችበት ጊዜ ቀላል እንዳልሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር በቊርጠኝነትና በሀገር ወዳድነት ተንቀሳቅሶ ባስመዘገበው ልማትና እድገት ስማችን እንደገና እንደጥንቱ እየገነነ እንደመጣ ሁላችንም እያየን ነው፡፡ ዛሬ የሀገራችን ልማትና እድገት በየአቅጣጫው ተፋፍሞአል፣ ዛሬ በሂደት የሚገኘው የልማትና የእድገት ግስጋሤያችን የኢትዮጵያ ከፍታ እውን ሆኖ ቀድሞ የነበረው ገናና ስማችንና ሥልጣኔአችን እስኪረጋገጥ ድረስ አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡ ከዚህ አንጻር የዘንድሮውን በዓለ መስቀል የምናከብረው ይህ የነፍስ ወከፍ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ሕልም የሆነው ራእይ እውን እንዲሆን በመጸለይ ነው ፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳትና ሜትሮፖሊታኖስ፣ክቡራን ክቡራት
የዘንድሮ የመስቀል በዓላችን ልዩ የሚያደርገው የሶስተኛ ሺሕ ወይም ሚሊኒየም ዐሥረኛ ዓመት የልማትና የእድገት ጒዞአችን በምናስብበት ወቅት፣ እንደዚሁም እጅግ በጣም ውድ እኅት የሆነችው የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊኮስ ቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ በተገኙበት እየተከበረ ያለ መሆኑ ነው፡፡ የቅዱስነታቸው ጒብኝት የመልካም ገጽታችን፣ የታላቅነታችን፣ የልማታችንና የሰላማችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሰላማችንንና አንድነታችንን ጠብቀን እስከተጓዝን ድረስ ፈላጊያችን አክባሪያችንና ወዳጃችን ብዙ ይሆናል፡፡ ሰላማችንን፣ አንድነታችንንና ወንድማማችነታችንን እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀን ወደልማትና ሥራ ስንሰለፍ ብርቱዎች ነን፤ ስለዚህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዳጅ ሰላምን መጠበቅ፣ ከበሽታ መራቅ፣ ልማትን ማፋጠን፣ እድገትን ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል፡፡
በመጨረሻም፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመሉ በአጽንዖት ለማስተላለፍ የምንፈልገው ዐቢይ መልእክት ሕዝባችን ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ድምፅ እርሱም “ ሰላም ለእናንተ ይሁን” የሚለውን ድምፅ ዘወትር እንዲሰማ ነው፤ ይህ ድምፅ የእድገቱና የድኅነቱ ዋስትና ነውና ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ድምፁን ያለማመንታት ሰምቶና ተቀብሎ፣ ከበሽታ አምጪ ተግባራትና ከሁከት ርቆ “የአትዮጵያን ከፍታ” በቀጣዮቹ ዓመታት እንዲያረጋግጥ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የመስቀል በዓል ያድርግልን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡