መስከረም 16 ቀን የ2007 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
የሀገራችንን ዳር ድንበር በመጠበቅና በማስከበር በየዘርፉ ያላችሁ፥
በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ የተኛችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፤
በመስቀል ላይ በተከፈለው መሥዋዕትነት የሰውን ልጅ ከኀጢአት ፍዳ የታደገ ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ2007 ዓ.ም በዓለ መስቀል አደረሳችሁ፡፡
በመስቀል ላይ የተከናወነውና የተከፈለው ዋጋ ድንገተኛ ሳይሆን አስቀድሞ በትንቢተ ነቢያት የተነገረነው፡፡ የመስቀሉ ሥራ የማዳን ሥራ ነው፡፡ የጌታ ደስታ ከድኅነተ ምእመናን ጋር የተያያዘ ነው የሰውም ደስታ የድኅነት ባለቤት ሆኖ መገኘት ነው፡፡ መስቀል የሚለው ቃል ብዙ ትርጓሜ ቢኖረውም ሁለት ዐበይት ነገሮችን ማየት ይቻላል፡፡ ይኸውም በምሥጢራዊ ትርጒሙ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሥዋዕት በመሆን በኀጢአት የተበከለውን ዓለም ማዳኑን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ዓለም በክርስቶስ መስቀል ዳነ ሲል ሰው በክርስቶስ መሥዋዕትነት መዳኑን ያመለክታል፡፡ መስቀል ኀይላችን ነው፣ መስቀል ቤዛችን ነው፣ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ከመስቀሉ በቀር ሌላ የምንመካበት ነገር የለንም የሚሉት ኀይለ ቃላት መዳናችንና ማሸነፋችን ነው፡፡ በሌላ በኩል መስቀል የመሥዋዕትነት ትምህርት ወይም አርማ ነው፡፡ እኛም በመስቀሉ እንፈወሳለን እንባረካለንም መስቀልን ማክበር ክርስቶስን ማክበር ማለት ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት በተጀመረበት ዘመን የነበሩ ሰዎች የክርስቶስን መስቀል በመቅበርና በመሠሰወር የተነሡበት ምክንያት መስቀሉ የመፈወስ ሥልጣን በማሳየቱ ነው። የመስቀሉ መገኘት ኢአማንያንን ያሸማቀቀ ክሥተት ነበር፡፡ የመስቀሉ አዳኝነት እስከ አሁን ድረስ ቀጥሎአል የቀደሙ ቅዱሳን አባቶቻችን ካወረሱን መንፈሳዊ ውርስ አንዱ በዓለ መስቀልን እያከበሩ በሃይማኖት ጸንተው መኖርን ነው፡፡ እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማንያን በየዓመቱ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት በምናከብረው የመስቀል በዓል አማካኝነት የክርስቶስን አዳኝነት ለዓለም እንመሰክራለን በዚህም ዓለምን ወክሎ በሚገኘው የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) ሕጋዊ ዕውቅና ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ የመስቀል በዓላችን ያሬዳዊ ዜማችንና ብቸኛው ፊደላችን ልዩ የሆነው የዘመን አቈጣጠራችን የዓለም አቀፉ ተቋም ዩኒስኮ እንዲመዘግባቸው የማስተዋወቅ ሥራ ለመሥራት ጥሪአችንን እናስተላለለፋለን፡፡ ,
የዘንድሮው የመስቀልን በዓል የምናከብረው ልማታዊና ሰላማዊ ተልእኳችንን ከግብ ለማድረስ ቃል በመግባት ነው፡፡ እየተገነቡ ያሉት ሕንጻዎች የአንድነታችን መገለጫዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፤ ሁላችንም አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን በእኩልነትና በመከባበር ለአንዲት ሀገር መነሳት አለብን በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ ትምህርታዊ ማብራርያ ከሰጡ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ስጦታው በበኩላቸው የመስቀል ደመራ አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች በቅርስነት መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ ከሚገኘው ጠቀሜታ ባሻገር የሀገራችንን መልካም ገጽታ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አወንታዊ በሆነ መልኩ በመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚኖረው ይሆናል፡፡ ከቱሪስት መስሕብነት ባሻገር በዓሉ ከቀድሞ በተሻለ እንክብካቤ የሚደረግለትና ለትውልድ እንዲተላለፍ እገዛ እንደሚሰጥ ጽኑ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡የሀገራችን መንግሥት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ልዩ ልዩ የማይዳሰሱ ቅርሶች በቅርስነት እንዲመዘገቡ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡የመስቀል ደመራ በዓል የሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት በድምቀት ሲያከብሩት የኖሩት ሃይማኖታዊ በዓል ብቻ ሳይሆን ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና አግኝቶ የሀገራችንን ገጽታ በቱሪዝም ልማት ይቀይራል በኢፊድሪ ሕገ መንግሥት በተረጋገጠው የእምነት ነፃነት መሠረት የሀገራችን ሕዝቦች በዓላትን እንደ እምነታቸው ማክበር ከጀመሩ ዓመታት ተቈጥረዋል መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ሲባል አንዱ ባንዱ ላይ ጣልቃ ሳይገባ የየራሳቸውን ሥራ እንዲፈጽሙ የሚያደርግ እንጂ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚያደርጉት ተሳትፎ የሚደነቅ ነው፡፡ ይህንንም አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል፡፡ የመከባበርና የመቻቻል አኵሪ ባህላችን ማውሳት አንዱ ጉዳይ ሆኖ ዛሬ በዓለም ካሉና በሥልጣኔ ካደጉ ሀገራት እኩል የሀገራችንን ስም ለማስጠራት በመንግሥታችን የተጀመረውን ፀረ ድህነት ትግል በእልህና በወኔ እንዲሁም በታላቅ ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት ለማሳካት መረባረብ ይኖርብናል፡፡